>
5:13 pm - Wednesday April 18, 6192

ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ)

ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ፡- ባንኪ ሙን
በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ አምባሳደር ፡-

ananiya-sory-and-elias-gebiruበአንድ ሉአላዊ ሀገር ውስጥ፣ ሕዝብና መንግሥት የሚግባቡበት ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው የህግ እና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መኖሩ ቀዳሚው መሠረት መሆኑ ይታመናል፡፡ በህግ አግባብ ሥርዓትን ተከትላ የምትተዳደር ሀገርም ወደ እድገትና ብልፅግና በሂደት መሸጋገሯ አይቀርም፡፡ ከእዚህ በተቃራኒው የሚጓዙ ሀገራት ደግሞ ችግርና መከራዎቻቸው ተዘርዝረው አያልቁም፡፡

መስከረም 28 ቀን 2009ዓ.ም በሀገራችን ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ‹‹እንደ አስፈላጊነቱ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡›› በሚል ‹‹በአፌድሪ መንግሥት መውጣቱ ይታወቃል›› የአዋጁ መውጣትም የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ተናግቶ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያሳይ መንግሥት በወቅቱ ገልፆ ነበር፡፡ ነገር ግን አዋጁ ከመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችና ከህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ጋር ይጋጫል፡፡ በተለይም የመረጃ ልውውጥን ፣ በነጻነት የማሰብ ተፈጥሮአዊ እና ህገ-መንግሥታዊ መብቶችንና የመረጃ ምንጮችን የመከታል መብቶችን ሙሉ በሙሉ ይጨፈልቃል፡፡ ከሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችም ጋር በግልፅ ይጻረራል፡፡

በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29 ላይ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተደንግጓል፡፡ ይህንን ህግ በአግባቡ እና ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ በመጠቀም እኛ ስማችን ከታች የተገለፀው ኢትዮጵያዊያን የነፃ ሀሳብ አራማጅ ጋዜጠኞች፤ ላለፉት ከ6-8 ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በነፃው የህትመት ሚዲያው ዘርፍ፣ ለበርካታ ጋዜጠኞችና መጽሔቶች ላይ በምናከብረው ሙያችን ሥንሰራ ነበር፡፡ ዘርፉ በበርካታ ችግሮችና ተግዳሮቶች የታጠረ መሆኑ ሳይዘነጋ!

ከጥቅምት ወር 2008ዓ.ም ጀምሮ ‹‹ በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ልዩ ዞኖች በአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ሥር ይካተቱ›› የሚለው የመንግሥት ዕቅድ በኦሮሚያ ክልል ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞን ማስነሳቱ የሚታወስ ነው›› እኛም ይህን ህዝባዊ ተቃውሞ በወቅቱ ተጋግዘን እናዘጋጅበት በነበረው ‹‹አዲስ ገጽ›› መጽሔት www.addisgetsh.com ላይ በተለያየ የአቀራረብ ሙያዊ ዘዴ፤ በተከታታይ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ለንባብ ስናበቃ ነበር፡፡ ከኦሮሚያ ተቃውሞ ጋር በማያያዝ በአሁኑ ወቅት በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኃላ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ሂደታቸው በመከታተል ላይ የሚገኙት ታዋቂው እና የተከበሩ ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ የመጨረሻውን ሰፊ ቃለ ምልልስ አደርገው የነበረው በአዲስ ገጽ መጽሔት ላይ ነው፡፡

እኚህ ፖለቲከኛ በተቃውሞውና በማስተር ፕላኑ ዙሪያ የሰጡት የመጀመሪያ ክፍል በመጽሔቷ ላይ ታትሞ ከወጣ ከ10 ቀናት በኃላ በፖሊስ ቆጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ያሉትም ታዋቂው የኦሮሞ ህዝብ መብት ተሟጋች የሆኑት በአዲስ ገጽ መጽሔት ታትሞ ወጥቷል፡፡

በእዚህና በተያያዥ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያም በወቅቱ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መ/ቤት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ሞጋች ቃለ-ምልልስ አድርገን በመጽሔቱ ላይ በሁለት ክፍል ያለገደብ ተስተናግዷል፡፡ ይህ በተግባር የሚያሳየው መጽሔቱ ሚዛናዊና ሁሉን አሳታፊ የጋዜጠኝነት ሙያ መርህ እንደምንከተል ነው፡፡ በተጨማሪም ለረዥም ዓመታት ሲጠየቅ የነበረና እስካሁን ድረስ ምላሽ ማግኘት ያልቻለውን የወልቃይት-ጠገዴ የማንነት ጥያቄ በተመለከተም በመጽሔቷ ሽፋን ስንሰጥ ነበር፡፡ ጥያቄዎቻቸውንም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕጋዊ መንገድ ያቀርቡ የነበሩ የወልቃይት-ጠገዴ የማንነት ጉዳይን በዋነኝነት ተወክለው ይከታተሉ የነበሩትን የኮሚቴ አባላት ቃለ-ምልልስም አድርገንላቸው ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራቶች በኃላም በመጽሔቷ ላይ በደረሰው ግልጽና ስውር ደባ የተነሳ ከህትመት ውጪ ሆኗለች፡፡ ሆኖም ይህ እውነትና ሀቅን መዘገብ የጋዜጠኝነት መርህ ከገዢው ኃይል ጋር እንድንላተም አድርገናል፡፡ በሂደትም መንግሥት መንግሥት በእኛ ላይ ጥርስ እንዲነክስብን ሆኗል ብለን እናምናለን፡፡

በመፅሔቷ ላይ የተለያዩ አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮችን አንስተን ገዢውን መንግሥት ሞግተናል። ይሄ ቀውስ ከመምጣቱ በፊትም በጠረንጴዛ ዙርያ ነፃ የሃሳብ ውይይት እንዲደረግና ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጠር እኛም ለአመታት ለለመድነው ለግሉ ፕሬስ አፈና ተግዳሮት እጅ ሳንሰጥ የኢንተርኔት ሚዲያን በመጠቀም የሃገራችንን፡- የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፍትህ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ዘገባዎችን፣ ትንትታኔዎችን፣ ሂሶችን እና ሃሳቦችን እንዲሁም አጀንዳዎችን ያለማቋረጥ ስናቀርብ ነበር። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ከታወጀም በኃላም በሀገር ውስጥ ያሉ ጥቂት የግል ህትመት ሚዲያዎች እንኳን ነባራዊ እውነታን ለመዘገብና ለህዝብ ይፋ ለማድረግ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሲያዙ፤ እኛ ግን በቻልነው መጠን የየግል ማህበራዊ ሚዲያዎችን (Facebook) በመጠቀም በድፍረት የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል በማለት ዜናዎችንና የግል ሃሳቦቻችንን ስናቀርብ ቆይተናል።

ህዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም ሁለታችንንም (አብሮን የታሰረውን ፖለቲከኛውን አቶ ዳንኤል ሽበሺን ጨምሮ) በደኅንነት ኃይሎች ታፍነን ስንያዝ፤ አያያዛችን ሰብዓዊ መብታችንን የጠበቀ አልነበረም። እስካሁንም በታሰርንባቸው ሁለት የፖሊስ ጣቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶቻችን በአግባቡ አልተጠበቁልንም። ለሶስት ቀናት ያህል ለየብቻ ( በባዶ ቤት ጭምር) ታስረን ነበር። በእነዚህ ቀናት በቤተሰብ እንኳን እንድንጎበኝ አልተፈቀደም። አሁን ወደምንገኝበት እስር ቤት ከተዘዋወርን በኃላ ደግሞ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ደርሰውብናል። ለምሳሌ ያህል ተገቢውን ህክምና በወቅቱና በአግባቡ አለማግኘት፣ መፅሃፍና ጋዜጦችን ማንበብ መከልከል፣ በጠባብ ክፍል ውስጥ ከ50 በላይ እስረኞች ጋር፣ ከአእምሮ ህሙማን ጋር ፣ ያለ ፍትህ በፍርድ ቤት ሳንቀርብ መታሰር ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ተጠርጥረን የተያዝንበትም ምክንያት ከግንቦት ሰባት እና ኦነግ ጋር መረጃዎችን በኢንተርኔትና በስልክ በመለዋወጥ ህገ-መንግሥዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚል መሆኑን መርማሪ ፖሊሳችን ገልፆልን፤ ድርጊቱን አለመፈፀማችንን ቃል ሰጥተናል።

ከእዚህ ውጭ እስካሁን እንዲሁ በግፍ ታስሮ ከመቀመጥ ውጪ ምንም የተባልነው ነገር የለም። ከታሰርን ሁለት ወራት ቢያልፍም እስከአሁን ፍርድ ቤት አልቀረብንም። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ቀድሞም በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ክፉኛ ያሽመደመደው ሲሆን ገዥ ሃይሉንም ወደ ጠቅላይ አምባገነናዊ ስርአት የከተተ ነው ብለን እናምናለን። የፖለቲካ ንግግርና ተግባቦት ከመቼውም በላይ አስፈላጊ በሆነበት በዚህ ወቅት ሰዎችን ማፈንና ማሰር የባሰ ሀገሪቷን ወደ ውድቀት ይመራታል። ሚዲያም በዚህ ወሳኝ ወቅት ወሳኝ ሚና ሊኖረው በተገባ ነበር። ያም ባለመሆኑ ሀገራችን ይበልጥ ወደከፋ አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኑ ይሰማናል። እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋም ያሳስበናል። እኛም ብንሆን የዚህ አደገኛ ኹነት ሰለባ ነን። እንዲህም ሆኖ ባገኘነው እጅግ የጠበበ መንገድ ተጠቅመንም ቢሆን ነፃ ሃሳቦቻችንን በድፍረት ከመግለፅ አልተገታንም።

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለገባችበት ቀውስ መውጫ መንገዱ የነፃ ሃሳብ ክርክር መሆኑን በፅኑ እናምናለን። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የጣሰው የሀገሪቷን ህገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀፅ 19ን ጭምር ነው። አዋጁ በተግባር ተፈፃሚ መሆን ከጀመረ አንስቶ የቂም በቀል መወጣጫ መሆኑን በተግባር ማየት ችለናል:: እኛ በታሰርንበት የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምርያም ይህንን ለመረዳት ችለናል::

ዜጐች ነፃ መረጃዎችን በማግኘት በነፃ የሃሳብ ሙግት መድረክ ሀሳባቸውን አንሸራሽረው አሸናፊ ሆኖ የወጣ ሀሳብ ገዥ እንዲሆን ማድረግ ይገባል:: የሀገሪቷ ኢኮኖሚም ቢሆን በአዋጁ ሳቢያ እየተሽመደመደ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አዋጁና አፈፃፀሙ በሀገሪቷ፡- ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ቀድሞም ስር የሰደደው ሙስናም ይበልጥ ጨምሮ እየተስፋፋ ነው:: የሰውን ሥነ ልቦና በማሸማቀቅ ፍርሃትን እያነገሰ የሚገኘው ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ከሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ ሠዎች ወደ ሚስጢራዊና የታጠቀ የፖለቲካ ትግል ይበልጥ እንዲገቡ በር ይከፍትላቸዋል::

በተጨማሪም በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ያለመረጋጋት ሁኔታን በመፍጠር ለኢንቨስትመንቶች እንዳትሆን እና ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንድትገለል ያደርጋል::

‹‹በመሆኑም አዋጁ ይነሳ! እኛም በግፍ ያለወንጀላችን ታስረናል፣እንፈታ!›› እንላለን::

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ
ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ

Filed in: Amharic