>

ግራ አጋቢዎቹ የቂሊንጦ ቃጠሎን የተከተሉ ክሶች [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

qilinto-fireበነሐሴ 2008 የቂሊንጦ እስር ቤት ባልታወቀ ምክንያት በእሳት ከተቃጠለ በኋላ መንግሥት 23 ሰዊች ሞተዋል ሲል፣ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ፕሮጀክት ደግሞ ከ70 ሰዎች በላይ ሞተዋል ብሏል። መንግሥት ለቃጠሎው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ሰዎች በሦስት መዝገብ ከሷል።

ሀ) 38 ሰዎች በሽብር ወንጀል (ቀደም ብለው ከእስርቤት የማምለጥ ዕቅድ ሲያወጡ ነበር፣ ቃጠሎው የዛ ዕቅድ ቀጣይ እርምጃ ነው በሚል)

ለ) 121 ሰዎች በከባድ ነፍስ ማጥፋት (“የዱርዬው ቡድን” በሚል ተደራጅተው በቃጠሎው ሟቾችን እሳት ውስጥ ጨምረዋል በሚል)

ሐ) 5 የጥበቃ አባላት በሙስና (ለተጠቀሱት እስረኞች ገንዘብ በማስገባት ተባብረዋል በሚል)

የሚገርመው ለምሳሌ የመጀመሪያውን ብናይ አንደኛ ተከሳሹ (የአየር ኃይል መቶ አለቃው ማስረሻ ሰጤ) በቃጠሎው ወቅት ከተቃጠሉት ዞኖች ገለል ብሎ የሚገኝ ቅጣት ክፍል ውስጥ ከውጭ ተቆልፎበት ነበር። እዚያው መዝገብ ላይ ፍቅረማርያም አስማማው ተፈርዶበት ዝዋይ ወኅኒ ቤት ነበር። እንግዲህ እኔ የማላውቃቸው ሌሎቹም በተመሳሳይ በቦታው ያልነበሩ ይኖራሉ።

እዚያው መዝገብ ውስጥ አዛውንቱ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩንም (እኔ እዚያ ግቢ ውስጥ ለዓመት ያህል እስከማውቃቸው) በእንዲህ ዓይነት ነገር መጠርጠር በጣም ከባድ ነው። ሚስባህ ከድር የሚባለው ተከሳሽም እኔ ቂሊንጦ በነበርኩበት ጊዜ ውስጥ መቅዱሴ (ገበታ ተቋዳሼ ነበር)። በእንዲህ ዓይነት ወንጀል መጠርጠሩ በራሱ እሱን ለሚያውቅ ፈፅሞ አሳማኝ አይደለም። ሌሎቹስ?

ከትላንት ወዲያ 121ዱ ቀጠሮ ነበራቸው። ከችሎቱ ፈቃድ ውጪ “ገድላችኋል” ለተባሉት ሰዎች ነፍስ የኅሊና ፀሎት አድርገዋል። አብዛኞቹ ጠበቃ ሲጠየቁ የመላዕክትና ፃድቃን ሥም ሲጠሩ ነበር። ሰው ምድራዊ ፍትሕ እንደማያገኝ ተስፋ ሲቆርጥ ከሰማይ እንዲወርድለት መመኘቱ አይገርምም። ዛሬ ደግሞ 38ቱ ቀርበው ነበር። ለደረሰባቸው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ያቀረቡት አቤቱታ መልስ ሳይሰጣቸው፣ ዛሬም አቤት እያሉ ችሎቱ በአጭር ቃል ለየካቲት 22 ቀጥሮ (ለጫጫታው እንደቅጣት) አሰናብቷቸዋል። ተከሳሾቹ ከመቼውም የበለጠ ልዩ የፌዴራል ፖሊስ እጀባ ተደርጎላቸው ነበር።

Filed in: Amharic