>

ወልቃይት ጠገዴና የወያኔ የልጅ ልጆች (ዩሐንስ ደሳለኝ - ከጀርመን)

ቀድሞ በምሰራበት የአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ አሉ የሚባሉ ቱባ ቱባ የውያኔ ባለስልጣኖች ለመዝናናት ይመጡ ነበር። እናም ባለፈው አስራምስት ቀናት በተለያዩ ድህረ ገጾች ላይ የተለቀቀውን የክንፉ አሠፋን በአቶ ሰብሃት ነጋ የሙስና ቅሌት ዙሪያ ያጥነጥነውን ዘገባ ሳነብ ወደኋላ በትዝታ ወደ አንድ አጋጥሞኝ ወደነበረ ሁነት መለሰኝ። አንዳንዴ የወያኔዎችን ሴራና አካሄዳቸውን መለስ ብየ ሳስበው በብዙ ነገር ላይ አይናችንን ከፍተን ማየትና ማስተዋል እንዴት እንዳቃተን እገነዝባለሁ።

ነገሩ እንዲህ ነው አቶ ስብሃትና ሌሎች የወያኔ ባለስልጣናት ለመዝናናትና የተለመደውን የአልኮል ሱሳቸውን ለመወጣት በዚሁ ከላይ በጠቀስኩት ክለብ ጎራ ይሉ ነበር። በተለይ ዕሁድ ዕሁድ ብዙ ግዜ ልጆቻቸውን ለማዝናናት ሲሉ ለክለቡ ቤተኛ ነበሩ። ያኔም ከሚመጡት ልጆች ውስጥ ያኔ አስራ ሁለት ዓመት ዕድሜ ላይ ይገኝ የነበረውን የአሁኑ (ክንፉ የነገረን) የጎተራ አደባባይን ኮንትራት የወሰደው፣ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ባለቤት የሆነውን ሚሊየነሩን ተከስተን የማግኘት አጋጣሚ ነበረኝ እናም አንድ ቀን ከኢትዩጵያ ውጭ ብዙ አገሮችን እንደጎበኘና ከሃገራቱም ማን ማንን እንደሚወድ?፤ ደግሞ ብዙ ግዜ የሚናፍቀውን ጠይቄው የሰጠኝ መልስና የክንፉ አሰፋን ጽሁፍ ሳነብ አሁን ባለሁበት የስደት አገር ሆኘ ነገሮች ፍንትው ብለው ታዩኝ፣ ከሞኝ ጉዋሮ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ፤ ታዲያ የያኔው ታዳጊ የዛሬው ባለሃብት ተከስተንና የእኔ ጭውውት እንዲህ ነበር የተጀመረው ፦
“ ከኢትዮጵያ ውጭ የት የት አገር ሄደሃል?”
“ ት/ቤት ሲዘጋ ለእረፍት ለንደንና አሜሪካ ሄጃለሁ “ አለኝ እነዚህን ሁለቱን ለግዜው በቅጡ አስታውሸ ጠቀስኩኝ እንጅ ሌሎች አገሮቸንም ዘረዝሮልኝ ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ የዘርዘርልኝ አገሮች ስሰማ ቅናት ቢጤ አስተናግጃለሁ ምክኒያቱም እነኝህን አገራት አብዛኛው ኢትዩጵያዊ በሰደትም ሆነ በተለያየ መንገድ መሄድ የምንመኛቸው አገራት ናቸውና፡፡ ለባለግዜውቹ ልጆች ግን የዉሃ መንገድ ነበሩ።

ጥያቄየን ለጠኩና “ ግን ከሁለቱ ሃገሮች የትኛውን ትወዳለህ ማለቴ ሁሌ የሚናፍቅህ ?” አልኩት፤ እሱም በመቀጠል “እኔ የምወደው ለንደንን ነው፤ ሁሌ እዛ ብሄድ ደስ ይለኛል “ አለኝ (በነገራችሁ ላይ የአዜብ መስፍን ልጆችም ብዙ ግዜ ረፍታችውን ለንደን እንደሚያሳልፉ ያኔም ሰምቼ ነበር)ጥያቄውን መልሶልኝ እኔም ለንደንን ለምን እንደሚወደው እያስገረመኝ ገና መገረሜን ሳልጨርስ እንዲህ ብሎ ይባስ መገረሜን ጨመረው “እኔ ግን የምወደው ሁሌ የምናፍቀው ማንን እንደሆነ ታውቃለህ ?” አለኝ… እኔም በጉጉት “ማነው አላውቅም “ አልኩት በውስጤ ማንን ልትል ይሆን እኛ ደብረዘይት ለመሄድ ጭንቅ ሆኖብናል እናንተ… እያልኩ… ሃሳቤን ሳልቋጭ ዱብዳ አውረደብኝ “ “እኔ በጣም የምወደው የተወለድኩበትን ወልቃይት ጠገዴን ነው ሁልግዜ ይናፍቀኛል“ እኔም ሳላስበው ጮክ ብየ “ እርፍ!!!!” አልኩኝ እሱም ወዲያው “ምነው ?” በሎ ቢጠይቀኝ “ምንም “ ብየ ከፊቱ ዘወር አልኩኝ በዛው ቅጽበት ተረት ተረትኩኝ ‘ላህያ ማር አይጥማትም’ ብየ… ለጥቄም እንደአዲሳቤዎችም “ፋራ “አልኩት፡፡ ነገር ግን ለካ እሱ አባቱ የተወለድክበትን አትርሳ ከለንደንና ከአሜሪካ ይልቅ እንደያኔዋ የእስራኤሎቹ ማርና ወተት እንድምታፈልቀው እንደ ከንአናን ወልቃይትን አስባት እያሉ አስጠንተው አሳድገው ዛሬ ላለበት ደረጃ አደረሱት፤ ተመልከቱልኝ አካሄዳቸውን… እኛ ቀድመን ስላልነቃን ዛሬ አገሪቷ ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች ተፈጠሩ የወልቃይት ተወላጆች በገዛ ቀያቸው የበይ ተመልካቾች ሆኑ ገሚሶቹ ተገደሉ ገሚሶቹ ተሰደዱ ወያኔና ጉጅሌዎቹ ግን ይባስ ብለው ጡረታ የወጡ የሰራዊት አባላትን ወልቃይት ላይ አስፍረው ክልሉን የትግራይ ነው ማለቱን ስራየ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ይህን ደግሞሁላችንም የምናውቀው የአደባባይ ምስጢርና በክልሉ ዙሪያ የሚደረገው ውዝግብ መፍትሄ አጥቶ እስካሁን ደም እያፋሰሰ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የአቶ ስብሃት ነጋና የሌሎቹ ወያኔ ባለስልጣን ልጆች ሰውን እያሰደዱ በሁመራ ሰሊጥና በወልቃይት ጠገዴ እርሻ አውሮፓና አሜሪካ ለመዝናናት ይመጣሉ እናም እኛን ደግሞ ዕድሜ ልካችሁን እንደተረታችሁ ኑሩ አሉን ።

እኮ እንግዲህ ይች አገር የማን ናት ?!!!
አዎ!!! አገሪቷ የተወሰኑ ሰዎች መቀለጃ ሆናለች፤ እንግዲህ ያኔ የ12 ዓመት ታዳጊ የነበረው ህጻን ልጅ ዛሬ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ መሆኑን መገመት አያዳግትም እናም የተዘራው ዘር አብቦ ፍሬ አፍርቶ ጎምርቶ ይኄው ለዛሬ ማንነት በቃ፤ እናም ተከስተ ደግሞ በተራው ለልጆቹ ተመሳስይ ሁኔታ ያስተላልፋል ፣ይች ናት እንግዲህ ደደቢት ላይ የተዘራች የአንድ ብሄር የበላይነት፟፡-
የበላይነት– በጦር ሰራዊት አመራር ፣ የበላይነት– በኢኮኖሚ ፣ የበላይነት– በትምህርትና ምርምር ዙሪያ እናም በመሳሰሉት ፣ ከዚያ ሌላውን እንደባሪያ ፍንገላ ግዜ እያሰቃዩ መግዛት አልገዛ ያለውን ማሰር መግደል፣ ቀንቶት የተሳካለት በባሌም በቦሌም ብሎ የስደት ኑሮውን እንዲጀምርና የሌላ ሰው አገር ቋንቋና ባህል ለመልመድ እየታገለ ባለበት ሆኖ የወያኔ ባለስልጣኖችና ልጆቻችው ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ መጮህ ከዚያም ሲብስ ባለበት የስደት ምድር እየተማረረ መኖርና ያችን ወደኃላ ጥሏት የወጣውን አገር መቼ ይሆን የእኩል ሃገር የምትሆነው እያለ በቁዘማ ዕድሜውን ይፈጃል ።
እነሆ እንግዲህ ኢትዩጵያ የብዙኃን መኖሪያ ፣የሰው ዘር መገኛ ፣የራሰዋ ፊደል ያላት ፣ባህሏንና ታሪኳን ለ3000 ዘመናት ጠብቃ የቆየች ፣ኩሩና የማይደፈር ህዝብ ያላት የተባልሽው ዛሬ በእዚህ ግዜ ህልማችውና ቅዝታችው ደደቢት ተወልዶ ደደቢት ያበቃው መሪ ተብየዎችን ተያዝሽ ታሪክሽ እንደገና በተንጋደደና በተንሽዋረረ ሁኔታ እየተዘወረ ያለው፣ ስለዚህ ጎበዝ እረ እንነሳ ግዜው አሁን ነው!!!!!
ሌሎች ተዛማጅ ፅሁፎችን
ዩሐንስ ደሳለኝ  ከጀርመን
Filed in: Amharic