>

"የታሪክ ሂሳብ ማወራረዱን አቁሙ!" ፕ/ር መረራ ጉዲና

በክንፉ አሰፋ

amsterdam-dr-merara-gudina “በውይይት የማይፈታ ችግር የለም። ስትወያዩ ግን የታሪክ ሂሳብ ማወራረዱ ላይ አታተኩሩ። ትኩረታችሁን አሁን የተጋፈጥናቸው ችግሮች ላይ አድርጉ።” ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አስታወቁ።

ፕሮፌሰሩ ይህንን የገለጹት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በኔዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያ ጋር በትላንትናው እለት 20 November 2016 በአምስተርዳም ባደረጉት ውይይት ላይ ነው። በውይይቱ የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ተገኝተው ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ስለ ሃገሪቱ ፈታኝ ሁኔታ እና ስለወደፊቱ እጣ ፈንታ በስፋት ያብራሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ መሪ – ፕ/ር መረራ ጉዲና  ከተሰብሳቢው ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።

“አዋጁ እና ኮማንድ ፖስቱ ሕዝባዊ አመጹን ያበርደዋል ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ፣ ሃገሪቱ አሁን በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆንዋን ገልጸው አሁን ያለው ሁኔታ ላይ እንዲህ ይሆናል ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸው፣ነገሮች በሁሉም አቅጣጫ ሊሄዱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ችግሮች እስካልተፈቱና የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እስከልተመለሱ ድረስ ሁኔታው ወደ እርስ በርስ እልቂት ሊወስደንም ይችላል። ይላሉ።

በይፋ አልተነገረም እንጂ ኮማንድ ፖስቱ ከአዋጁ በፊትም የነበረ የኢህአዴግ አሰራር እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምእራባውያን ስላላቸው ሚና ተጠይቀው፣ እኛ የቤት ስራችንን ካልሰራን ምእራቡ አለም ምንም ሊረዳን አይችልም። እኛ ካልሰራን እንኳን ምእራቡ አለም እግዚአብሄርም አይረዳንም። ብለዋል።

በዚህ ወቅታዊ የሀገር ጉዳይ ላይ የተዘጋጀ የውይይት ገለጻ ሲሰጡ በዲፕሎማሲው እና በአለም አቀፍ ህብረተሰብ በአንድ በኩል፣ በሃገር ውስጥ የተጀመሩት በርካታ የ”እርቅ” እንቅስቃሴዎችን በስፋት ቃኝተዋል።

በአለም አቀፉ ህብረተሰብ እና በምእራባውያን ሃገሮች በኩል አሁን ለተቃዋሚዎች በር ተከፍቷል ይላሉ ፕ/ር መረራ ጉዲና። በጋራ ሆነን በአንድ ቋንቋ የመናገሩ ህብረታችን ግን አሁንም ፈተና ላይ ነው።

በቅርቡ በአውሮፓ ህብረት ጥሪ ተደርጎላቸው ሃገሪቱ ስላለችበት መስቀለኛ መንገድ በስፋት ተናግረዋል። አሜሪካ በነበሩበት ግዜም ከሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጋር “አትላንቲክ ካውንስል” ከተባለው የአሜሪካ ቲንክ ታንክ ቡድን ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። በዚህ ውይይት  ሄርማን ኮኽን እና የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺል የተገኙ ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በህብረት  ያለመንቀሳቀስ ትኩረት ስቦ እንደነበር ይናገራሉ።

ገዥውን ፓርቲ ከተቃዋሚዎች ጋር ለማግባባት ሰባት የሚያህሉ የእርቅ እና ሰላም ቡድኖች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል። አብዛኞቹ የ”እርቅ” ቡድኖች ባህላዊውን የ”አንተም ተው ፣ አንተም ተው” ሚና እንኳን የማይጫወቱ አንድን ወገን ብቻ ለመጫን የተቋቋሙ መሆናቸውንም ይተቻሉ።

ስለ ቀድሞው ተማሪያቸው እና ስለ አሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ወርቅነህ ገበየሁ ተጠይቀው፤  በምርጫ ውድድር ይጠቀምበት የነበረው ስም ወርቅነህ ገበየሁ ነገዎ ሲሆን በትምህርት በት ያለው ፋይል ላይ ደግሞ ወርቅነህ ገበየሁ ወልደ ኪዳን እንደሆነ ገልጸዋል። ይህንን ጉዳይ በሁለተኛው መጽሃፋቸውም ላይ መጥቀሳቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በሃገር በት በኦሮሞ እና በአማራው ህብረተሰብ እየተፈጠረ ያለው ትብብር እነ ጌታቸው ረዳን ሳይቀር በአደባባይ ወጥተው እንዲናገሩ ያደረገ ትልቅ የታሪክ አሻራ መሆኑን ገልጸው፣ በውጭ ያለውም ወገን የቀድሞ ሂሳብን ማወራረድ አቁሞ፣ በወደፊቱ የሃገሪቱ ሁኔታ ላይ እንዲወያይ ምክር ሰጥተዋል።

በቪዲዮ የተቀረጸው ሙሉ ውይይት በቅርቡ ይለቀቃል።

Filed in: Amharic