>

ኢሰመጉ ከየት ወዴት? [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

አምስት ዓረፍተ ነገሮች
profeser Mesfen Weldemariam Quateroኢሰመጉ መንፈሳዊ ተልእኮ ያለው መንፈሳዊ ድርጅት ነው፤ ዓላማው በሰው ልጆች መሀከል የሚከተሉትን ተልእኮዎች መዝራት ነው፡–
1.1. እኩልነትንና ነጻነትን
1.2. ፍቅርንና ስምምነትን
1.3. ፍትሕንና ሕጋዊነትን
1.4. ሰላምንና ማኅበረሰባዊ እድገትን
1.5. የእውነትንና የእውቀትን ብርሃን ማስፋፋትን

ኢሰመጉ የተቋቋመው በሁለት ምክንያቶች ነው፤–
2.1. የደርግ አገዛዝ ወድቆ አዲስ መንግሥት በአዲስ ሥርዓት ይመሠረታል በሚል ተስፋ አዲሱ ሥርዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደትክክለኛ አቅጣጫ እንዲመራ ለመርዳት ነበር፤
2.2. የኢትዮጵያን ሕዝብ በመብት ጉዳይ ለማንቃትና ራሱን ከተገዢነት ወደገዢነት ደረጃ እንዲለውጥ ለማስቻል ነበር፡፡
ለትውልድ የሚተላለፍና ስምን ሲያስጠራ የሚኖር ሥራ ለመሥራት ሀበት ጥሩ መሣሪያ ነው፤ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሰዎች ለኢሰመጉ ሀብት ማውረስን ቢለምዱ የኢሰመጉ ዓላማዎችን ለማስፋፋትና ማኅበረሰባችንን ወደተሻለ አቅጣጫ ለመግፋት የተሻለ ኃይል ይኖር ነበር፤ ከውጭ ሰዎችም ጥገኛነት ለመውጣትና ራሳችንን ወደሰውነት ደረጃ ለመግፋት ያስችለን ነበር፡፡

እንዲያም ሆኖ በአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ጠንካራ በጎ መንፈስን ብቻ በታጠቁ ጥቂት ሰዎች፣ በትንሽ ገንዘብ አዲስ የትውልድን አቅጣጫ የሚያመለክት ሥራ የሠራ ከኢሰመጉ ጋር የሚወዳደር ድርጅት የለም፤–

4.1. ከውጭም ከውስጥም የተሰነዘረበትን ዛቻና ግፊት ተቋቁሞ ቀጥ ብሎ ዓላማውን ሳይስት የቆየ
4..3. ቢከሳም ሕይወቱን ያላጣ ድርጅት ነው፤
4.4. የኢሰመጉ መክሳት የማኅበረሰቡን መክሳት የሚያመለክት ነው፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማኅበረሰቡ ኢሰመጉን በሚገባ ባለመደገፉና እንዲከሳ በማድረጉ ራሱንም አከሳ፤ ራሱን ጎዳ፤ እስከዛሬ አንድም ባለሀብት ለኢሰመጉ ቀዋሚ ሀብት ያወረሰ አለመኖሩ አስተሳሰባችን ከግለሰብ ወደማኅበረሰብና ወደትውልድ አለመሸጋገሩን ያመለክታል፤
4.5. እስከዛሬም ድረስ ቢሆን ማኅበረሰቡ የኢሰመጉን መንፈሳዊ ተልእኮ በትክክል ተገንዝቦ ኢሰመጉን በመርዳት ራሱን ለመርዳት የሚያስችለው ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም፡፡

በዚህ በዓል ላይ እኔ ያረቀቅሁትን የኢሰመጉን ደንብና ቃል ኪዳን ሁለት የሕግ ባለሙያዎች፣ ወርቁ ተፈራና ዓሥራት ገብሬ ብዙ ጊዜ አጥፍተውበት በማሻሻላቸውና የባለሙያ ሥራ በማድረጋቸው፣ በተጨማሪም የመጀመሪያው የኢሰመጉ ቢሮ በዓሥራት ገብሬ ቢሮ ውስጥ ሆኖ የሱ ጸሐፊም የኢሰመጉን ሥራ እንድትሠራ በማድረግ ያበረከተው እርዳታ ኢሰመጉ በራሱ እግር እስቲቆም ድረስ ደግፎታል፡፡

መደምደሚያ

የኔ ትውልድ አንድ በአንድ እያለ በመመናመን ላይ ነው፤ የእኔም ተራ እየደረሰ ነው፤ ለኢሰመጉ የማወርሰው መሬትና ቤት የለኝም፤ መጻሕፍት ሞልተውኛል፤ የአዋሳ ሕዝብ አሁን ኢሰመጉ ያለውን የመጻሕፍት ቤት ለሕዝብ የሚጠቅም ሊሆን በሚችልበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ቤት ቢያገኝለት አብዛኛዎቹን ለአዋሳ ለማውረስ ወስኛለሁ፤ ቤትና አስተናባሪ ከአልተገኘለት ውርሱን ለማስፈጸም አስቸጋሪ ይሆናል፤ በአዲስ አበባ ብዙ አማራጭ የመጻሕፍት ቤቶች ስላሉ የአዋሳን ኢሰመጉ መጻሕፍት ቤት ማጠናከሩ የተሻለ ይመስለኛል፤ በተጨማሪም ከኢሰመጉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ አዋሳ በጣም ልቆ የቆየ በመሆኑ ለማበረታታት ነው፤ ከአዋሳ ነዋሪዎች መሀከል አንድ ቤተ መጻሕፍቱን በስሙ ለማስጠራት የሚፈልግ ሰው ለኢሰመጉ አንድ ቤት የሚሰጥ ወይም የሚያወርስ እንዲገኝ ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡
በመጨረሻም ለዛሬ በዓል
በስደት ላሉት ለአበበ ወርቄና ለዓሥራት ገብሬ
በሕመም ምክንያት በመሀከላችን ላልተገኙት አንዳርጋቸው ተስፋዬና ለጌታቸው ተሰማ
በሕይወት ለሌለው አብረ-አደጌ ወርቁ ተፈራ፣ ነፍሱን ይማረው፤
ለቸርነቱ ወደር ለሌለው ጓደኛዬ አባተ የኔው — ኢሰመጉ ከስዊስ አምባሳደር ጋር ውዝግብ በተነሣበት ጊዜ መኪናዬንም ቢሆን ሸጬ አሥር ሺህ ዶላርህን እመልስልሃለሁ ያልሁትን በጋዜጣ እንብቦ፣ እቤቴ ድረስ መጥቶ የአሥር ሺህ ዶላር ቼክ ጽፎ ‹‹መኪናህን እንዳትሸጥ፤ ያውልህ አፍንጫው ላይ ወርውርለት!›› ያለኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሰው ነው፤ ነፍሱን ይማረው፡፡

በነዚህ በስድስት ሰዎች ስም የአምስት ወር ጡረታዬን አውጥቼ የአምስት መቶውን ብር ቲኬት በስማቸው በመግዛት ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡

ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡

Filed in: Amharic