>

ሰምሃር መለስ የገባት መተካካት - ተቃዋሚዎች ያልገባቸው መታደስ! [ክንፉ አሰፋ]

የአፈና ግዜ አዋጁን ተከትሎ፤ የሕወሃቱ ፋና ብሮድካስቲንግ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተናገደው “የውይይት መድረክ” አዳዲስ ኩምክናዎችን ይዟል። ልደቱ አያሌውን በመሪ ተዋናይነት ያሳተፈውን ይህን አዲስ የበረከት ስምኦን ድራማ ብዙም ሰው አላየውም። ሕዝቡ ፋና ሚባል ነገር እንደሬት መርሮታል። ገሚሶች ደግሞ በ “ቃና”ው “ጥቁር ፍቅር” ድራማ ተጠምደዋል። በዚህ ድራማ ልደቱ አያሌው መሪ ገጸ-ባህሪይ ተላብሶ ይተውን እንጂ እንደወትሮው ቀልብ ሊስብ አልቻለም። በኢትዮጵያ ታሪክ ወያኔ መድብለ ፖርቲን የፈቀደ ድርጅት እንደሆነ በሙሉ አፉ ሲናገር እሱ አላፈረም። ከሱ ይልቅ የተሸማቀቁት እነ በረከት እና ስብሃት ናቸው። በልባቸው አበስኩ ገበርኩ እያሉ… ጌታዎቹ ሃዘን ሲሰማቸው እሱ ያለቅሳል። በዚህ አቋሙ ከሶስተኛው መንገድ ወደ አንደኛው የተሸጋገረ ይመስላል ልደቱ። ለነገሩ እንጂንለሱ መገለባበጥ አዲስ ጉዳይ አይደለም!

ልደቱ አያሌው ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ወደ ልማታዊ ባለሃብት እንደገባ ነበር የምናውቀው – የሃብቱ ምንጩ ግልጽ ባይሆንም። እንደ ፕ/ር ኤፍሬም ይሳቅ የሕወሃት የመከራ ጊዜ ደራሽ እና አስተንፋሽ ለመሆን መጣሩ አይደንቅም። ሕዝባዊ አመጹን ማውገዙ ግን ከሃይለኛ ማእበል ጋር አላትሞታል።”ጥናታዊ ጽሁፍ” ያቀረበው የአስታራቂነትን ሚና ለመጫወት ከሆነም ማስታረቅ፣ የተበደለን ሕዝብ እየኮነኑ አይደለም። ህወሃት ሕዝብን በጅምላ ገድሏል። አንዴ የተገደለውን ሕዝብ ደግሞ መግደል ምን ይሉታል? መጨረሻውን ፈጣሪ ያሳምርለት።

የዚህ ውይይት አላማ ግልጽ ነው።ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በግብጽ እና ሻእቢያ ላይ ጣት ማውጣቱ ያዋጣቸው አልመሰለም። ስለዚህ የተወጠረውን ለማስተንፈስ፣ የተለመደ አቅጣጫ ማስቀየስ፣ እና ሕዝብን ለማዘናጋት መሞከር ከመጣር አልተኙም ። በውይይቱ የተገኙትም አይነተ ብዙ ናቸው። ጉዳዩ የገባቸው፣ ጉዳዩ ያልገባቸው እና ግራ የገባቸው ሰዎች ተሳትፈዋል።

ሃይሌ ገብረስላሴ እና ሳምሶን ማሞ የነበረከት ደባ በደንብ ከገባቸው ተሳታፊዎች ዋነኞቹ ናቸው። የኢትዮጵያ ችግር በውይይቱ እጅግ ተጋንኖ እንደቀረበ በቀልድ እያዋዛ ተናገረ ሃይሌ። አንዴ ተኑሮ ለሚታለፍባት አለም እንዲህ አጎብዳጅ መሆን ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። የማያልፍ ነገር የለም። ይህ ስርዓትም በእርግጠኝነት ያልፋል። እንደ ሃይሌ እና ቀነኒሳ ያሉ አድርባዮች ይህ ያከበራቸው ህዝብን ነገ እንዴት ቀና ብለው እንደሚመለከቱት ወደፊት የምናየው ይሆናል። በፈጣሪ አምሳል የተሰራን ሰው አትግደሉ ብሎ የመርናገር ሞራል ከሌላቸው፣ ዝምታም እኮ መፍትሄ እንኳን ባይሆን አማራጭ ነበር። ዝምታ ወርቅ ነው። እነሱ ግን እንደበቀቀን ህወሃቶች የሚሉትን የ”መልካም መስተዳደር” አሲዮ ቤሌማ ደጋግመው ይዘፍኑልናል።

ሳምሶን ማሞ ሲናገር የክበበው ገዳን አዲስ ቀልድ ያስታውሳል።

በአሜሪካ ሃገር ዋይት ሃውስ በር ላይ ቆመህ “ኦባማ ይውረድ” እያልክ ብትውል የሚነካህ የለም። ሲባል የሰማው ክበበው ገዳ እኛስ ሃገር ቢሆን አራት ኪሎ ቤተ መንግስት በር ላይ ቆመህ “ኦባማ ይውረድ!” እያልክ ብትጮህ ማን ይነካሃል? ብሎ ነበር ክበበው ገዳ።

“እኔ አቶ በረከት ስምዖን ቢሮ ገብቼ እንደፈለኩ ተሳድቤ እወጣለሁ። ይህንን ያህል ነፃነት አለ።” ይለናል ይህ የስርዓቱ ተደጋፊ ሳምሶን ሞሞ። አዎ ይህ ሰው ይሳደባል። አቶ በረከትን ቢሮ ድረድ ሄዶ ተሳድቦ ቢሆን ኖሮ ግን 34 ጥርሶቹን አናያቸውም ነበር። ደፋሩ ሳምሶን ባለፈው ሳምንትም በዚሁ መድረክ ላይ ቀርቦ ሕዝብን በጅምላ ተሳድቧል። አቶ በረከትን ሊሳደብ እንደማይችል ግን ሕጻን ልጅም ይገምታል። የሚደንቀው ታዲያ በስድብ እና በመብት መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን አጥርቶ የማያውቅ ይህ ሰው መድረኩን ይዞት ሲቀልድ ማየቱ ነው። እርግጥ ነው። ዝሆን ላይ የሚጮህ ሞኝ ውሻ ብቻ ነው። ሆድ ከፊት ለመሰለፍ አይፈራም ይሉ የለ አፍሪካውያን።

ሕዝብ መሬት ላይ ነው። እነሱ ሰማይ ላይ። መሬት ላይ የተኛ ግዜው እስኪያልፍ ሊረጋገጥ ይችላል። መሬት ላይ የተኛ እወድቃለሁ ብሎ አይሰጋም። ዛሬ ሰማይ ላይ ያሉት ግን እዚያው አይቀሩም። ነገ መውረዳቸው የተፈጥሮም ህግ ነው።

ሰምሃል መለስ

ሰምሃል መለስ

የመለስ ዜናዊ ልጅ ሰምሃል መለስ ግራ የተጋባች ተሳታፊ ትመስላለች። ግን አጠር ብላ የረዘመች መልእክት አላት። በህወሃት ውስጥ ያለውን የስልጣን ሽኩቻ ብቻ ሹክ ብላ አላለፈችም። ስልጣንችሁን ላለማስነካት ከምትንደፋደፉ ስልጣኑን ለኛ ስጡን ብላለች።

አባትዋ ከማለፉ በፊት ስለመተካካት ብዙ ተናግሮ ነበር። ሰምሃር ይህንኑ ቃል እንደ ፈጣሪ ቃል አምና ተቀብላለች። ይህ ብቻ አይደለም። የህወሃት ስልጣን እንደ ርስትና ጉልት በውርስ እየተላለፈ ይቆያል ተብሎም ተነግሯታል። ጸጉርዋን የሽፍታ አስመስላ ስልጣኑን ከነበረከት ለመቀበል ብዙ የጠበቀች ነው የሚመስለው። በዚያ ሰሞን ጠመንጃ ይዛ የቶክስ ልምምድ ስታደርግ የተነሳችው ፎቶም ተለቆ ነበር። ይህም በህወሃት መመዘኛ ከርክክብ ቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ መሆኑ ነው።

የመተካካት እና የቅብብሎሹ ወሬ ከአቶ መለስ ጋር ተቀበሮ በጥልቅ ተሃድሶ አዲስ ዜማ መተካቱን ግን ሰምሃር የሰማች አይመስልም። ይህች ወጣት ስብሰባው ላይ የተሳተፈችው የእናቷ አዜብ ጎላን ሃሜት ይዛ ነው የሚለው ንግግራቸው የሚያስኬድ ቢሆንም፤ መልእክትዋ ግን ግልጽ ነው። እስዋም ገና የለውጥ ሳይሆን የጥገና መፍትሄ ላይ ናት።

እንደ ሰምሃር ነገሮችን ሳያላምጡ እየዋጡ፣ ቅዠት ሁሉ ህልም መስሎ እየታያቸው፤ ሕወሃትን እንደ ንጉሳዊ ስርዓት ለማስቀጠል የሚፈልጉ ደፋሮች ጥቂት አይደሉም።

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ኢንጅነር ይልቃል በዚህ ስብስብ የተሳተፉበት ምክንያት ግን አልገባኝም። ድራማውን ለማሟሟቅ ከልሆነ በስተቀር የእነሱ በዚያ መገኘት ፋይዳ አይታይም። እርግጥ ነው ሁላችንም ይህንን ውይይት እንድንመለከት ያደረገን የ እነሱ መሳተፍ ነበር።ግና ከምርጫ ክርክር ግዜ የተናገሩትን ያህል እንኳን በዚህ ውይይት ሲናገሩ አልሰማንም። እነሱ እዚህ እያወሩ ባሉበት ቅጽበት አጋዚ ጦር በጠራራ ጸሃይ የቤት ለቤት ዘረፋ፣ አፈና እና አስገድዶ መድፈር ላይ ተሰማርቷል። ከውይይቱ በፊት – እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቅድመ ሁነታዎችን ማስቀመጥ ነበረባቸው።

ሕዝብ ጥገና ወይንም ተሃድሶ ሳይሆን ለውጥ ነው የፈለገው። ሕወሃት፣ የማይታደስ፣ የማይሻሻል፣ ከስህተት የማይማር እንደሆነ ብዙ ግዜ ነግረውናል። ጅምላ ግድያ እየፈጸመ ካለ ከዚህ ስርዓት ጋር ቁጭ ብለው ዲስኩር ማድረግ ምን ሊጠቅም እንደሚችል ከእኛ በላይ እነሱ ያውቁታል። ሕዝብ እና ሕወሃት የማይታረቅ ቅራኔ በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ እነሱ ራሳቸው የውይይት ግዜ አብቅቷል ሲሉ የሰማን መስሎኝ ነበር።በረከት ስምኦን እና ልደቱ “ብቃት ያለው ተቃዋሚ ልንፈጥር አልቻልንም” የሚሉን ይህንን እያስተዋሉ ይሆን?

አቦይ ስብሃት እንደተባለው ቀምቅመው መድረክ ላይ ይውጡ እንጂ፣ የሚናገሩት ሁሉ ቅኔ አዘል ነበር። ሰምና ወርቅ ያለው ቅኔ። “መረራ እና ይልቃል ጓደኛሞች ናቸው። የፖለቲካ ፓሪቲ አይደሉም!” ያሉት ያለምክንያት አልነበረም። ያንን ሁሉ ተናግራችሁ ስታበቁ እዚህ በኛ ጉባኤ ላይ ምን ትሰራላችሁ? ማለታቸው ይመስላል። ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ ሕወሃት ለፍትህ እንጂ ለድርድር እና ለውይይት የሚቀርብ ስር ዓት እንዳልሆነ ነው የቅኔው ወርቅ የሚጠቁመን። የህወሃት መክሠም እና መጥፋት ምኞታቸው መሆኑን የማብሰራቸው ቅኔ ግን ሰምም ሆነ ወርቅ የለውም።

ሽማግሌው ስብሃት ቀጠሉ “እናንተ ሕዝቡን አታውቁትም። እኛ እንኳን ግማሹን የኢትዮጵያ ሕዝብ አናውቀውም!” ብለው አረፉ። የማያውቁትን ሕዝብ ለ 25 አመት የሙጥኝ ይዘውት ኖሯል።

“ከፊትህ የሚጠብቅህን መንገድ ለማወቅ ተመላሾቹን ጠይቅ።” ይላሉ ቻይናውያን። ላስተዋለው ትልቅ አባባል ነበር። ለተመክሮውም የደርግ ውድቀት ብቻ በቂ ነው። እነሱ ግን ከታገሉት ደርግ በመቶ እጥፍ ብሰው ተገኙ። ወትሮውን ቁጭ ያሉበት መጥበሻ ሲግል እንደማሽላ መፈንዳት ግድ ነውና እስከመጨረሻው እስትንፋሳቸው ይናገራሉ። እኛም እንደ ኮሶ እያንገሻገሸን የሚሉትን መስማቱን አልተውንም።

… በሚቀጥለው ጽሁፌ ሰለ አፈና ግዜ አዋጁ እና ሰለ አጋዚ አ የምለው አለኝ። እስከዚያው ቸር እንሰንብት።

Filed in: Amharic