>
5:13 pm - Monday April 19, 1886

ኢትዮጵያን የተጣበቁባት ሽፍቶች ጋዜጠኞችን መኖሪያም እያሳጡዋቸው ነው።ኤሊያስ ገብሩ የደረሰበትን ያንብቡ

Elias Gebru 15102006ትናንት አመሻሽ ላይ ከጓደኞቼ ጋር ተጨዋውተን ወደቤት ስገባ የቤት አከራዬ ስልክ ተደወለ። “ኤልያስ ቤቱን ፈልጌዋለሁና እንድትለቅልኝ ልነግርህ ነው” አለችኝ። “ለምን?” አልኳት። አስቂኝና የማታሳምን አንዲት ምክንያት ሰጠችኝ። ከቀናት በፊት ውላችንን በድጋሚ እናድስ ብላኝ ነበር ደስ እያላት። ይህንን አስታውሼ አነሳሁባት። በሶስት ቀናት ውስጥ ምን ተፈጠረ ብዬም ተገርሜያለሁ።

“ይልቅ አሁን የምትነግሪኝን የማያሳምን ምክንያትሽን ሳይሆን በውስጥሽ ያለውንና የደበቅሽውን እውነት ንገሪኝ” አልኳት በንዴት።
“ሰላም እፈልጋለሁ፣ መቼም ሀገሪቷ ላይ ያለው ነገር ይገባሃል” አለችኝ። “የማንን ሰላም ነካሁ? ከአንቺም ጋር በወር አንዴ የኪራይ ክፍያ ልሰጥሽ ነው ለደቂቃዎች የምንገናንኘው!” አልኳት። “እሱ እውነት ነው። ግን….በቃ ልቀቅልኝ!” ብላ ሌላ ምክንያቷን ደረደረች። “ዋናው ነገር ቤት መልቀቁ አይደለም፣ እውነቱን ግን ካንቺ እፈልጋለሁ!” ብያት ተለያየን።

የምር በጣም ተሰማኝ፣ በወቅቱ ተከፍቼም ነበር። ይገርማል! በገዛ ሀገር ተረጋግቶ መኖር የማይታሰብ ሆነብን። ከዚህ ቀድም ሁለቴ ከካዛንቺስ አንዴ ደግሞ ከአራት ኪሎ ግንፍሌ “ቤቱን ልቀቅልን!” ተብዬ ወጥቻለሁ። እንድለቅ የሚነግሩኝ ምክንያትና እውነታው ግን ለየቅል ነበር ጊዜ ካለፈ በኋላ ስሰማ።

ትናንት ማታ በአከራዬ “ቤት ልቀቀልኝ” በሚለው ንግግራ ብቻ አልነበረም የተገረምኩት፤ ተናድጄ እቤት እንደገባሁ ቴሌቭዥን ስከፍት አንዱም የቲቪ ቻናል አይሰራም ነበር። ጥዋትም ሞከርኩት ለውጥ የለም። ጠበቃ ተማም አባቡልጉ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያወጋን ቁም ነገር ናፍቆኝ ነበረና ቤቴን ጥዬ ወጣሁ።

እሺ የት ሄደን እንኑርላቸው?! ያው በውድ ሃገራችን 2ኛና 3ኛ ዜጉች ከሆንን ሰንብተናል!

በውድ ሀገራችን መከራው ምንም ቢጸናም እንኳ፤ ለነጻነት ለሚደረገው ትግል የምችለውን ሁሉ ከማድረግ አልገታም!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

Filed in: Amharic