>
5:13 pm - Monday April 19, 4630

የሕወሃት ብጥብጥ እና ሽሽት- ከውስጥ አዋቂ ምንጭ [ክንፉ አሰፋ]

TPLF logo 2           ሕዝባዊ አመጹ ያመጣውን ቀውስ ተከትሎ በህወሃት ከፍተኛ አመራር ውስጥ ከፍተኛ መበጣበጥ እና የርስ-በርስ ፍጥጫ መከሰቱን ከታመነ የውስጥ አዋቂ ምንጭ  መረጃ  ደርሶናል። ­­­

“አመራሩ ክፉኛ  ከመከፋፈሉ የተነሳም የርስበርሱ ችግራቸው ላይ ተወጥረዋል።”  ይላል መረጃው። ቀንደኞቹ የህወሃት አባላት ስርዓቱ እንዳበቃለት ስለተገነዘቡ ንብረት እና ልጆቻቸውን በማሸሽ ላይ ናቸው።

ሕዝቡ ሁሉ እንደተፋቸው በግልጽ እየነገራቸው ስለተገነዘቡ፤   የህወሃት የደህንነት አባላት ሕዝቡን ተተው የራሳቸውን ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሰልሉ ተነግሯቸዋል። “ተጠርጣሪ” የኦህዴድ እና ብአዴን አባላት በነዚህ ሰላዮች ስለተከበቡ በፍርሃት መወጠራቸውን ከራሳቸው አንደበት እየተሰማ ነው።

የርስበርስ ውጥረቱ የተከሰተው ወቅታዊ ችግሩን እንዴት እንፍታ በሚለው ሃሳብ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሙሉ በመጥራት የአንድነት መንግስት እንመስርት በሚለው ሃሳብ ላይ ስምምነት ተወያይተው ውሳኔ ካስተላለፉ በኋላ በዚህ የተከፋው ቡድን  ባነሳው ተቃውሞ እንደሆነ መረጃው ጠቁሟል። ይህ ቡድን ችግሩን  በውይይት ሳይሆን በመሳርያ ሃይል ለመፍታት ለብቻው መክሯል። ውይይታቸው ሁሉ ዛቻ እና ስድብ አዘል ንግግሮችም እንደነበሩበት ምንጫችን ጠቅሷል።

በውሳኔው መሰረት ተቃዋሚዎች በቤተመንገስት ይጋበዛሉ ተብሏል።  ለማዘናጋትም ተብሎ ይሁን ወይንም በፍርሃት የመጣው ይህ  ሃሳብ ግዜው አልፎበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ወታደራዊ ካምዮኖች የአጋዚ ወታደሮችን እና ከባድ መሳርያ ጭነው ከህወሃት ነጻ ወደ ወጡት ስፍራዎች እየጎረፉ ነው። ማብቅያ የሌላቸው እነዚህ የጭነት መኪናዎች እየተጓዙ ያሉት የውጭ ጠላትን ለመመከት ሳይሆን የገዛ ሕዝብን ለመደምሰስ ታቅዶ እና ታስቦ ነው።  አለ የተባለው ሁሉ የህወሃት ሰራዊት ወደ አማራው ሕዝብ ተልኮ እመንገድ ላይ ታግቷል። በአሁኑ ሰአት ሌላው አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን ቢኖር ከአጋዚ ነጻ ይመስላል።

ሕዝባዊ አመጽ በተቀጣጠለባቸው ስፍራዎች (በተለይ በጎንደር እና ጎጃም) ያሉ የሰራዊት አባላት በሕዝቡ ላይ እንዲተኩሱ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር።      ችግር ግን አለ። ይህ ትዕዛዝ ከአካባቢው የሰራዊቱ አባላት ተቀባይነት አላገኘም። ልዩ ፖሊስ በመባል የሚታወቁት የአካባቢው ፖሊሶች እና  ወታደሮች የከህዝብ ጎን መቆምን መርጠዋል። በአካባቢው ያሉ የሰራዊቱ አባላት በህዝብ ላይ አንተኩስም ብለዋል። ይልቁንም ልዩ-ፖሊሶች ህዝብን ከአጋዚ ገዳዮች በመከላከል ላይ እንዳሉ ነው የሚሰማው።

በተለይ በጎንደር እና ጎጃም ሕዝቡ አስቀድሞ መንገዶችን በሙሉ ዘግቶ የአጋዚ ገዳዮች ወደ ስፍራው እንዳይገቡ አድጓቸዋል። ይህ ባለመሳካቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የውስጥ በረራውን አቁሞ የአጋዚ ሠራዊትን ወደ ባህርዳር እንዲያመላልስ ታዝዟል።በበርካታ ስፍራዎችም ሕዝቡ ራሱን ለመከላከል በመፋለም ላይ ይገኛል።

ሃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ ቁጭ ብሎ፤ በምክትሉ ነው የሚመራው። ለእያንዳንዱ የሚፈስ ደም፣ ለእያንዳንዱ የጦር ወንጀል፣ ለእያንዳንዱ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል… የመጀመርያ ጠያቂው እሱ መሆኑን ዘንግቶት ግን አይደለም።

ላለፉት 25 ዓመታት በጥቂቶች የተረገጠ ህዝብ ብሶቱ ከመብዛቱ የተነሳ ገንፍሎ ወጥቷል።  ጎንደር እና ጎጃም ክፍለ ሃገራት ከዘረኛው የህወሃት አገዛዝ ነጻ ወጥተዋል። በአንዳንድ ስፍራዎች ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ ቢሆንም ሁኔታው ለህወሃት እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነበት ከስፍራው የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ውጥረት እንደሰፈነ ነው። በሃገሪቱ የሚያስፈራ ድባብ ሰፍኗል።  የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በእጅጉ እየተዳከመ ነው። የውሃ፣  የመብራት፣ የስልክ እና ኢንተርኔት መቋረጥ ህዝቡን እጅግ አስመርሮታል።  አንድ ሊፈነዳ ያለ ነገር እንዳለ ይሰማል። ሕዝባዊ አመጽ በቀጠሮ አይመጣም። ብሶቱ መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ይፈነዳል።

የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰዓታት ከቤቱ ወጥቶ በሩ ላይ ብቻ ቢቆም፣  አሁን የሚደነፉበት ዘራፊዎች  ሁሉ ሃገር ለቀው ይጠፋሉ።

Filed in: Amharic