>

ለጃዋር መሐመድ! [ኣብርሃ ደስታ]

Jawar Mohammedጃዋር መሐመድ የማከብረውና የማደንቀው ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ነው። በቅርቡ ስለ ኦሮሞና አማራ ህዝብ ትስስር አርቲስቲክ በሆነ የሚያምር ቋንቋ ገልፆታል። ጃዋር እንዲህ ፅፏል

“ኦሮሞ እና አማራ ‹‹እሣት እና ጭድ ናቸው ›› ብላችሁ ክብሪት ለመጫር ለምትቋምጡ የወያኔ ሎሌዎች የሚከተለውን ብትገነዘቡ መልካም ነው፡

1) ኦሮሞ እና አማራ መታየት ያለባቸው እንደ እሳት እና ጭድ ሳይሆን ጎን ለጎን በቅለው ለረጀም ጊዜ አብረው እንዳደጉ ትልልቅ ዛፎች ነው። እነዚህ ዛፎች ለረዥም ግዜ ተጎራብተው ከመኖራቸውና ከግዙፍነታቸው የተነሳ በመሬት ውስጥ የተሳሰሩት ስሮችቸው ምግብ ሊሻሙ ይችላሉ። በአየር ላይ የሚነካኩት ቅርንጫፎቻቸው በንፋስ ጊዜ እርስበእርስ ሊላተሙ ይቻላሉ። ነገር ግን ዛፎቹ ስር የሰደዱና የተዋሃዱ እንደመሆናቸው መቼም ውሃ አያጡምና፣ እንደ ጭድ ደርቀው በክብሪት አሳት አይቀጣጠሉም።

2) ምናልባት ከሁለቱም ዛፎች ደርቀው የረገፉ ቅጥሎችን እና ጭራሮዎችን ተጠቅማችሁ እሳት መለኮስ ካሰባችሁም ጉዳቱ ለናንተው እንደሚያመዝን እውቁ። የምትለኩሱትን እሳት የንፋስ አቅጣጫው በማስቀየረ የወያኔን ስርዓት ወደሚያወድም ወላፈን መለወጥ እንደሚቻል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።”

እኔም እላለሁ። ፅሑፍህ ወድጄዋለሁ። የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ግንኙት ከገለፅከው በላይም ነው። ህዝብ ለህዝብ ለማቀራረብ (እውነታው ለመመስከር) በመቻልህ አመሰግነሃለሁ። ግን ይሄን የኦሮሞና የአማራ ግንኙነት በሌሎች ኢትዮጵያውያንም አለ። በኦሮሞና አማራ ህዝብ ያለው ትስስር በኦሮሞና ሱማሌ፣ በኦሮሞና ጋምቤላ፣ በኦሮሞና ጉራጌ፣ በኦሮሞና ትግራይ፣ በአማራና ዓፋር፣ በአምራና ትግራይ … በሁሉም ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ተመሳሳይ ትስስርና ግንኙነት አለ። ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲህ የተሳሰሩ ናቸው። እርግጥ ነው ስለ ኦሮሞና አማራ ስትፅፍ ስለሌሎችም ተመሳሳይ አመለካከት የለህም ማለት አይደለም። ግን አንድን ብሄር ማስቀደም በህዝቦች እኩልነት አለማመን እንደሚያሳይ ሁሉ ሁለት ወይ ሦስት ወይ አራት ብሄሮች መርጦ ማስቀደምም በእኩልነት ማመን አይደለም። በእኩልነት አታምንም እያልኩህ አይደለም። እያልኩህ ያለሁት የፃፍከው ነጥብ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚመለከት በመሆኑ ከሁለት ብሄሮች ወደ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማደግ አለበት። ምክን ያቱም ሁላችን አንድ ነን፤ የተሳሰርን ነን ። ማንም አይለያየንም። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩል ዓይን እንመልከት።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

It is so!!!

Filed in: Amharic