>

ከትናንት ወዲያ፣ ትናንትና ዛሬ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroዛሬ ላይ ቆሜ ወደኋላ ሳይ የትናንት ወዲያው ይናፍቀኛል፤ ትናንት ወዲያን አይቼዋለሁ፤ አውቀዋለሁ፤ ትናንትንም አይቼዋለሁ፤አውቀዋለሁ፤ ዛሬንም እያየሁትና እያወቅሁት ነው፤ ከትናንት ወዲያ በጃንሆይ ዘመን የአገዛዙ ነቃፊ ነበርሁ፤ የወደፊቱን የማየት ችሎታ ስለሌለኝ የጃንሆይን አገዛዝ ነቃፊ ነበርሁ፤ በትናንት ወዲያ ላይ በጃንሆይ ዘመን ላይ ቆሜ ዛሬን የማየት ችሎታ ቢኖረኝ የጃንሆይን አገዛዝ ነቃፊ አልሆንም ነበር፤ ትናንትን፣ የደርግን ዘመን ከዛሬው ከወያኔ ዘመን በመሠረቱ እምብዛም የማያለይ በመሆኑ አይናፍቀኝም፤ የዛሬው የወያኔ ዘመን አስመረረኝ፤ ምርር ብሎኛል፤ እንዳልሰደድ ቀዳማዊ ምኒልክ ያለውን ተከታይ ነኝ፤ እንዲህ ብሏል፡–

‹‹እናቴንና አገሬን እተው ዘንድ አይቻለኝም፤›› እናቴ ‹‹በጡቶቿ አምላኛለችና››፡፡

እናትና አባቴ የኢትዮጵያን ምድር ሆነዋል፤ አባቴ በማይጨው ዘምተው በጥይት ቆስለዋል፤ የመርዙንም ጋዝ በትንሹ ሳንባቸውን ሳይጠብሰው አልቀረም፤ ይቺን እናትና አባቴ አፈር የሆኑላትን አገር ትቼ መሰደዱ ስለማይሆንልኝ እየመረረኝ የመድኃኔ ዓለምን ምሕረት እጠብቃለሁ፡፡

ለምን የጃንሆይ ዘመን ይናፍቅሃል? ለሚለኝ የምሰጠው መልስ የሚከተለው ነው፤ በጃንሆይ ዘመን ኢትዮጵያ የታሪክ ክብርዋ ርዝራዥ ነበረ፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን ችሎ በነጻነት የኖረ፣ በተደጋጋሚ የመጡበትን የተለያዩ ወራሪዎች እያሳፈረ የመለሰ ቆራጥ፣ ጀግናና ኩሩ ሕዝብ መሆኑን ዓለም በሙሉ አምኖ የተቀበለው ጉዳይ ነበር፤ በዘመኑም ከተባበሩት መንግሥታት ጦር ጋር ኮሪያ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከአሥራ ሰባት አገሮች አንዱ ቢሆንም አንድም ምርኮኛ፣ አንድም ሬሳ በጠላት እጅ ሳያስገባ የተመለሰ ብቸኛ ጦር ነበር፤ ያኮራል፡፡

ከኢትዮጵያ ለመውጣት ቪዛ ማግኘት ቀላል ነበር፤ በዚያን ጊዜ ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊ ነው ለመሰደድ የሚያስብ? አሜሪካ በየዓመቱ የሚመድበውን የኢትዮጵያን የስደት ድርሻ የሚጠቀሙበት ጥቂቶች ግሪኮችና አርመኖች ነበሩ፤ አርባ ሺህ ግድም ጦር ይዛ የምትፈራ፣ ደሀ ሕዝብ አቅፋ የምትኮራና የምትከበር፣ ጮሃ ሳትናገር የምትሰማ አገር ነበረች፤ እምነት የሚጣልበት የጨዋ ሕዝብ አገር ነበረች፤ ይህ ነው የናፈቀኝ!

ዛሬ በየጋዜጣው ላይ የማነበውና የማየው ፎቶግራፍ አሳፈረኝ! ውርደቱ አንገፈገፈኝ! ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ ምንም ማድረግ አለመቻሌ፣ ኢምንትነቴ ያንገበግበኛል፤ አንድ ወጣት በባቡር መንገድ ላይ ወድቆ አምስትና ስድስት ፖሊሶች እየተሻሙ በዱላ ሲደበድቡት፣ በጫማቸው ቦታ ሳይመርጡ ሲረግጡት እነዚህ ከኛው የተወለዱ፣ በእኛው ባህልና እምነት ያደጉ፣ ለሕዝብ ደኅንነት የተሰማሩ ናቸው ወይ? የሚፈጽሙት ግፍ ጀግንነት ይመስላቸው ይሆን ወይ? ልጆች ያላቸው ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው እነዚህን የግፍ ምስሎች በጋዜጣም ሆነ በቲቪ ሲያዩ እንደሚያማቸው ይገነዘባሉ ወይ?
በሚያዝያ 30/1997 በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በጨዋነት ወጥቶ በጨዋነት ተበተነ፤ ለምን አይቀጥልም? እስከመቼ ተፈራርተን እንኖራለን? በሠለጠነ መንገድ መነጋገር አልቻልንም፤ በሰላማዊ ትግል መነጋገር አልቻልንም፤ በግድ ወደሕገ አራዊት መግባት አለብን?

Filed in: Amharic