>
5:13 pm - Saturday April 19, 6628

“ኢሕአዴግ ቢወርድ ማን ይተካዋል?” [በፈቃዱ ዘ ኃይሉ]

BefeQadu Z. Hailuአገሪቱ ውስጥ “ኮሽ” ባለቁጥር የሚሰሙ የ“ይርጋ” ድምፆች አሉ። ስጋታቸው፣ ሕዝብ “ገዢው መረረኝ፣ ለውጥ አማረኝ” ባለ ቁጥር፣ ‘ገዢውን ማን ይተካዋል?’ የሚል ነው። ማስረጃቸው፣ “አንድ የረባ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም” የሚለው ነው። እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱ ሰዎች የችግሩን ሰፈፍ (surface) እንጂ ምንጩን የማይጠይቁ ናቸው።

1ኛ፣ ተቃዋሚዎች ማን እንዲኖሩ ፈቀደላቸው?

መንግሥት መመሥረት የሚችሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሉም። ምክንያቱም የገዢው ፓርቲ እንዲኖሩ አልፈቀደላቸውም። ፈቃድ ሰጪ፣ ፈቃድ ነሺ፤ ከሳሽ፣ መስካሪ፣ ፈራጅ፤ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚ፣ ሕግ አስፈፃሚ የሆነው ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች የመደራጀት ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ፣ ሕዝብ የማደራጀት፣ ርዕዮተዓለማቸውን የማስተዋወቅ፣ በጀት የማሰባሰብ፣ ጽ/ቤት የመክፈት፣ ከሕዝብ ጋር የመወያየት ዕድላቸውን ሁሉ በመዝጋቱ – አዎ የምንተማመንባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም። የምንፈልገውን ዓይነት የተቃዋሚዎች ቡፌ እንዲኖረን የስርዓተ መንግሥቱ ፍልስፍና ሊፈቅድልን ይገባል። የአብዮታዊ ደሞክራሲ መንግሥታዊ ፍልስፍና ደግሞ ይህን አይፈቅድም። የ“ይርጋ” ድምፆች የሚያነሱት ጥያቄ ለውጥ እንዳይመጣ ለመሟገት ሳይሆን ለውጥ እንዲመጣ ለመታገል ሊያነሱት የሚገባ ጥያቄ ነው።

2ኛ፣ ኢሕአዴግ የረባ ፓርቲ መሆኑ ነው?

ኢሕአዴግ ሰባት ሚሊዮን አባላት ያሉት ፓርቲ ነው። በቀጥታ አባልነት ከተመዘገቡ እነዚህ ሰዎች ውጪ የተለያዩ የደጋፊ ሊጎችን አቋቁሟል፦ የኢሕአዴግ ደጋፊ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ነጋዴዎች፣ ወዘተ…። በአንድ ለአምስት ጥርነፋ በየጠረጴዛው ዙሪያ ለመገኘት ይሞክራል። በኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ሥም ሰፈሩን ሁሉ ይሰልላል። የመንግሥት ተቋማትን ለምሳሌ ሲቪል ሰርቪሱን፣ ከዚያም በላይ መከላከያ እና ደኅንነቱን፣… እንደልቡ ያዛል፣ ፕሮግራሙን ያስፈፅምባቸዋል። የበጀትም ሆነ፣ ርዕዮተዓለሙን የማስፋፋት ምኅዳራዊ ገደብ የለበትም። እንዲያም ሆኖ ግን ሥልጣኑን በኃይል ከማቆየት በቀር ሕዝባዊ ይሁንታን ማግኘት አልቻለም፤ መፈራት እንጂ መወደድ አልሆነለትም። ነገር ግን አገር እያስተዳደረ ነው። አገሪቱን የሚያስተዳድረው በብቃት አይደለም። ቢሆን ኖሮ እዚያም እዚህም እንደፈላ ሽሮ የሚንተከተክ ሕዝባዊ አመፅ ባልበጠበጠው። ኢሕአዴግ አገር ማስተዳደር የቻለው አሁን ካሉት ተቃዋሚዎች የተሻለ ሆኖ ሳይሆን ሁሉን ባሻው መልኩ ማስኬድ የሚያስችል ሥልጣን ስለተቆጣጠረ ነው።

ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይህን ሁሉ ሥልጣን ባይቆጣጠርና አሁን እንደሚያፍናቸው ተቃዋሚዎች የሚያፍነው አካል ቢኖር ኖሮ እንደፓርቲ ሰርተፍኬቱን እያደሰ መዝለቅ እንደሚችል እጠራጠራለሁ። እንዲያውም ግንባሩ አራት ፓርቲዎችን አቅፎ ሳምንት እንኳን መቀጠል አይችልም ነበር። የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ በራሱ የሚሰጠው ጥንካሬ አለ። ኢሕአዴግ አገር ማስተዳደር የቻለው፣ ብቁ ስለሆነ ሳይሆን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉት ሠራተኞች ወደዱትም ጠሉትም ስለሚሠሩለት ነው። ስለዚህ የ“ይርጋ” ድምፆች ስጋት ይህንንም ከግምት ውስጥ ያስገባ ስጋት አይደለም።

3ኛ፣ ኢትዮጵያ ሰው የላትም?

ተቃዋሚዎችም፣ ኢሕአዴግም ውስጥ አንቱ የተባሉ፣ የምንተማመንባቸው ሰዎች ማጣታችን እውነት ነው። ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ሰው የላትም ማለት አይደለም። መንግሥቷ እና የፖለቲካ ስርዓቷ ሰዎቿን ገፉባት እንጂ! ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምሁራን ድርቅ አለባቸው፤ ምሁራን ተቃዋሚዎች ግን በየቤታቸው እና ተቋማቱ ውስጥ አሉ። ተቃዋሚዎች የገንዘብ እጥረት አለባቸው፤ ተቃዋሚ ባለሀብቶች ግን አሉ። የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ኢትዮጵያ ውስጥ በሠላም እንደማያኖራቸው ይፈራሉ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተቀላቅለው ለውጥ ማምጣት የሚችሉም የሚፈልጉም ሰዎች አሉ።

እነዚህ ሰዎች እንዲመጡ፣ የፖለቲካ ስርዓቱ መለወጥ አለበት። ሕዝብ በጉልበቱ መንግሥታትን ማስጨነቅ አለበት። ሠላማዊ አመፅ አንዱ የሕዝብ መንግሥትን ማስጨነቂያና የሥልጣን ሰጪና ነሺ ማን እንደሆነ ማስታወሽያ ነው። ማመፅ የሕዝብ መብት ነው፤ መግዛት ግን የመንግሥታት መብት አይደለም። ሕዝብ የሚመጥነውን መንግሥት መምረጥ ይችላል፤ መንግሥት ግን የሚገዛውን ሕዝብ መምረጥ አይችልም። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሕዝብ (ብዙኃኑ) ያሸንፋል። ያኔ ኢትዮጵያ የሚመጥኗትን ፖለቲካ ፓርቲዎች ማፍራት እንደምትችል እና እንደማትችል እናያለን። ያ ሳይሆን ቀርቶ ወደ እርስበርስ ጦርነት የምንገባ ከሆነ፣ መንስዔው የተቃዋሚዎች ድክመት ሳይሆን የገዢው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይነት ነው።

Filed in: Amharic