>

የዕንቁ መጽሔት ዋና ኣዘጋጅ ኤሊያስ ገብሩ በዋስ ተለቀቀ

በየ15 ቀኑ ለንባብ በምትቀርበው ዕንቁ መጽሔት በዋና አዘጋጅነት ይሰራ የነበረው ጋዜጠኛና ደራሲ ኤልያስ ገብሩ በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ እንዲቀርብ መታዘዙን መዘገባችን ይታወሳል። ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ከስራው ጋር በተያያዘ በእንቁ መፅሔት በተፃፈ ፅሑፍ ከማዕከላዊ ቃሉን እንዲሰጥ በስልክ በተደረገለት ጥሪ ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ/ም ወደስፍራው ቢያቀናም ማረፊያው ማዕከላዊ ነበር።

ይሁን እንጂ  ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ከኣራት ቀን የማዕከላዊ ቆይታ በሁዋላ በዛሬው ዕለት በዋስ መፈታቱን ለማወቅ ችለናል።የኤሊያስ ገብሩን መታሰርና፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የጋዜጠኞችን መዋከብና ለእስር መዳረግ ያሳሰባቸው፥ ዓለም ኣቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) ” ኤሊያስ ገብሩም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ። ጋዜጠኞችን ያለኣግባብ ማዋከብና ማሰር መቆም ኣለበት።” በማለት መግለጫ ማውጣታቸው ኣይዘነጋም።

 

Filed in: Amharic