>
5:13 pm - Sunday April 18, 0297

የነፍጠኞች ፖሊቲካ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

ነፍጠኛነት ባህላችን ነው፤ ፖሊቲከኛነት አዲስና ባዕድ የትግል ዘዴ ነው፤ ፖሊቲከኛነትና ነፍጠኛነት ተቃራኒ ተግባሮችን ያመለክታሉ፤ ተቃራኒ ተግባሮች አብዛኛውን ጊዜ ተቃራኒ ዘዴዎች ያስፈልጋቸዋል፤ ለምሳሌ መፍጨትና መቡካት ተቃራኒ ተግባሮች ናቸው፤ መፍጨት ሲበታትን፣ ማቡካት ሰብስቦ ያያይዛል፤ የሚፈጭ ሰው ማቡካት ይችላል፤ እንዲሁም ማቡካት የሚችል ሰው መፍጨት ይችላል፤ ፈጪ አቡኪ መሆን የሚችለውን ይህል ወይም አቡኪ ፈጪ መሆን የሚችለውን ያህል ነፍጠኛ ፖሊቲከኛ ወይም ፖሊቲከኛ ነፍጠኛ መሆን ይችላል ወይ? መልሱ ግልጽ ነው፤ አይችልም፤የነፍጠኛ ትግል በተመንጃ ነው፤ የፖሊቲከኛው ትግል በቃላት፣ በንግግር ነው፤ በሌላ አነጋገር የነፍጠኛ በዱላ፣ የፖሊቲከኛ ትግሉ በመላ ነው፡፡
የፖሊቲካ ሥልጣንን ነክሶ ይዞ ሕዝብን በሕዝብ በዱላ እያደባደቡ በማሸነፍም ሆነ በመሸነፍ የሥልጣንን ክብር ማግኘት በጭራሽ አይቻልም፤ በዱላ ትግል በሁለቱም ወገን ያሉ ወጣቶች ይጎዳሉ፤ በተሸናፊው በኩል የተሰለፉ ወጣቶች የመረረ ኑሮአቸውን የሚጀምሩት ወዲያው ነው፤ መቃብራቸውም ሆነ ቁስላቸው ክብር የለውም፤ የየግሉ አበሳና ለቅሶ ሆኖ ይቀራል፡፡
በድል አድራጊው በኩል የተሰለፉ ወጣቶችም ቢሆኑ ማርና ወተት የሚያገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው፤አብዛኛዎቹ ያለ ማጋነን ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ጠመንጃ ተሸክመው በወገናቸው ደረት ላይ ሳንጃ ደቅነው እየወጉና እያሰቃዩ በየዕለቱ ከርሳቸውን ለመሙላት ያለፈ ኑሮ የላቸውም፤ ወይም እውነቱን ፍርጥ አድርጎ ለመግለጽ ዘጠና ከመቶ የሚሆነው ከአሸናፊው ወገን ያለ ወጣት አሥር ከመቶ ለሚሆነው አሽከር ወይም ሎሌ ሆኖ ወገኑን በስቃይ እየጠበሰ ለሆዱ የሚያድር ይሆናል ማለት ነው፡፡
አብዛኛውን አሸናፊንም ሆነ ተሸናፊውን የሚያዋርደው ወይም ክብርን የሚነሣው የአሸናፊና የተሸናፊ ትግልም ሆነ የትግሉ ውጤት ከአብዛኛው የአገሩ ሕዝብ ፈቃድ ውጭ የተደረገ የጉልበተኞች ግብግብ ነው፤ እንዲህ ያለ ግብግብ የሚደረገው ከሕዝቡ ጋር ሳይሆን በሕዝቡ ላይ ነው፤ሁለቱም ተደባደቢ ወገኖች የሕዝብ ወገን መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ሆኖም ተፎካካሪዎቹ እርስበርሳቸው የሚታገሉት በዱላ እንደሆነ ሁሉ ከሕዝብም ጋር ያላቸው ግንኙነት በዱላ ነው፤ የሁለቱም መሠረታዊ እምነትም ሆነ ዓላማ፣ መሣሪያም ሆነ ዘዴ ዱላ ብቻ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዴ ዱለኛነታቸው ድንበር እየጣሰ የሌሎች አገሮችን ሉዓላዊነት ይነካል፤ በዛሬው ጊዜ በዓለም ውስጥ ዋና ዱለኛ አገር አሜሪካ ነው፤ በሱ ጥገኝነትና በሱ ጥላ ስር ያሉ አምባ-ገነን አገዛዞች በበኩላቸው ዱለኛነትን ይለምዳሉ፡፡
የሕዝብን የገነፈለ ዓመጽ ከዱለኛነት ጋር እንዳናዛምደው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ አንድ ሕዝብ በማይሰማ ደነዝ አገዛዝ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሲቆይ ተደብቆ የነበረው ሁሉ ገሀድ ይወጣል፤ በእንግሊዝኛ አንድ የአነጋገር ፈሊጥ አለ፤ የግመሉን ወገብ የሰበረው ሰንበሌጥ ይባላል (the straw that broke the camel’s back)፤ ሰንበሌጥ በእውነት የግመልን ወገብ የመስበር አቅም ኖሮት አይደለም፤ ነገር ግን ጭነቱ ተከምሮ፣ ተከምሮ በመጨረሻ የግመሉ ወገብ ሊሸከመው የማይችለው ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚጨመር ሰንበሌጥ የተከመረውን ሸክም ከመጠን በላይ ያደርገውና የግመሉን ወገብ ይሰብረዋል፡፡
አበሳና ግፍም ከዓመት ዓመት እየተከመረ፣ ኑሮ እየከረረ፣ ከሞት ይልቅ ስቃይ እየመረረ፣ የግመሉን ወገብ እንደሰበረው ሰንበሌጥ ለዘመናት በሕዝብ ላይ በተከመረ ግፍ ላይ አንድ ግፍ ጣል ማድረግ የግፍ ግንፋሎትን ይፈጥራል፤ ትእግስት ይደርቃል፤ ጨዋነት ዋጋ ያጣል፤ እንኳን ሰው ድንጋይም ይገነፍላል፤ እሳተ ገሞራ የሚባለው በመሬት ውስጥ ያለው ድንጋይ ሙቀት ሲበዛበት እየቀለጠ መሬትን ሰንጥቆ ሲገነፍል ነው፤ ሕዝብም እንዲሁ ነው፤ ግፍ ሲበዛበት፣ ዙሪያው ገደል ሲሆንበት ይገነፍላል!
መገንፈል በሞት ውስጥና በሞት መሀከል መተራመስ ነው፤ ልዩ ኢላማ የለውም፤ በመንገዱ ላይ የሚያገኘውን ሁሉ ይጠብሳል፤ ሀሳብም፣ ስሜትም የለበትም፤ንዴት ብቻ ነው፤ አደጋውም ያለው እዚያ ላይ ነው፡፡

Filed in: Amharic