>

ከጠንካራ ወንድ ጎን ጠንክራ መቆም የቻለች ኢትዮጵያዊት - ሰርካለም ፋሲል [ኤሊያስ ገብሩ]

Journalist Serkalem Fasil by Elias Gebiruወንድና ሴት ከአዳምና ሂዋን መፈጠር ጀምሮ በተፈጥሮ የሚለያዩበት እውነታ አለ፡፡ ወንዶች ከሴቶች የምንሻልባቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ሴቶችም ከወንዶች የሚሻሉባቸው ነገሮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ለዚህ መንደርደሪያ የሆነኝ፣ ‹‹ከአንድ ጠንካራ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት አለች›› በሚባለው የተለምዶ አነጋገር በከፊል ስለማልስማማ ነው፡፡ ሴት ለወንድ ጥንካሬ ብቻ የተሰራች አይደለችም፡፡ ብሎም አንዲት ጠንካራ ሴት ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ብቻ እንደምትገኝ መገለጹም አሁን አሁን አላሳምንህ እያለኝ ነው፡፡ ጠንካራ የሆኑ ወንዶችም ሴቶችም አሉ፤ ሰነፎችም እንደዚሁ፡፡ ጠንካራ ወንድ ያላት ሴት፤ እራሷም ጠንካራ መሆን ከቻለች ከጀርባው ሳይሆን ከጎኑ እንደሆነች ማመን ጀምሬያለሁ፡፡ ለዚህም ነው፣ ከቀናቶች በፊት በዚሁ በፌስቡክ ገጼ ‹‹ከሁለት ጠንካራ ወንዶች ጎን ጠንክረው መቆም የቻሉ ሁለት እንስት አሜሪካኖች›› ስል ሂላሪ ክሊንተንንና ሚሼል ኦባማን የገለጽኳቸው፡፡
የእኛዋም ሰርካለም ፋሲል (ጋዜጠኛ)ም ከብርቱውና ጠንካራው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጎን በርትታና ጠንክራ መቆም የቻለች እንስት ናት፡፡ በ97 ግርግር ለእስር ከተዳረጉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አሳታሚዎች፣ የሲቪክ ማኅበር አመራሮችና ሌሎች ዜጎች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ የዛሬው አዳጊ ናፍቆት እስክንድር የተወለደው ሰርኬ በታሰረችበት ቃሊቲ ነበር፤ አባቱ እስክንድር ግን ሚስቱንም ሆነ ልጁን ማየት ሳችል ቀርቷል – በወቅቱ፡፡
ከእስር ከወጡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም እስክንድር ለዳግም እስር ተዳርጓል፡፡ እስክንድር በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ፖሊሶች የብረት ካቴና እጁ ላይ ያጠለቁት በልጁ ናፍቆት ፊት ነበር – ናፍቆት እያለቀሰ፡፡ በተደጋጋሚ የእስክንድር እስር ምክንያት የባል፣ የሙያና በሀገር ጉዳይ ላይ የዓላማ ተጋሪ የሆነን ሰው አብሮነት በማጣት ሰርካለም ዛሬም ድረስ በመከራ ውስጥ መፈተኗ አልቀረም፡፡ በመከራ ውስጥ ቃሊቲ የተወለደ ጨቅላ ልጅ፣ አባቱ ዳግም ቃሊቲ ታስሮበት በተደጋጋሚ ቃሊቲ ለጥየቃ መመላላስ ለሶስቱም ፈተና ነበር፡፡ በተለይ ሰርኬ ላይ ፈተናው ያይላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ልጅን እንደእናትና አባት ማሳደግ፣ ባልንና የሀሳብ ተጋሪን ዘወትር ቃሊቲ ተመላልሶ መጠየቅ፣ የቤተሰብ ሕይወትን መምራት፣ የልጇን ናፍቆት አዕምሮ እንዳይጎዳ መጨነቅ ….ሰርካለም ፋሲል ፊት ለፊት የተላተመችበት እውነቷ ነበር፡፡
ሰርካለምን በአካል ሳውቃት ጀምሮ በፈተና ውስጥ ሆና ነው፡፡ እስክንድር ማዕከላዊ ታስሮ አራዳ ፍርድ ቤት ሲመጣ ሰርካለም አለች፡፡ ክስ ተመስርቶ ቃሊቲ ሲገባም ሰርኬ በቃሊቲ ደጃፍና አጥሮች መካከል አለች፡፡ እነእስክንድር፣ አንዷለም አራጌ …ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ ሰርካለም በችሎት ታድማ ትከታተላለች – ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ባለቤት ጋር፡፡ በአጋጣሚ ፒያሳ ለጉዳይ ስሄድ መንገድ ላይ ሰርኬን አገኛት ነበር – ለእስክንድር ስንቅ ለማቀበል በችኮላ ስትሄድ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስክንድር ላይ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት በፈረደበት ዕለት ከሰርኬ ጋር አብሬያት ነበርኩ፡፡ ከልደታ ፒያሳ ድረስም አብረን ነበር የሄድነው – እድለኛ ባልሆነችው መኪናዋ፡፡ ከቴዎድሮስ አደባባይ ፒያሳ ጫፍ ድረስ ስትነግረኝ የነበረውን መቼም ከህሊናዬ አይጠፋም፤ እያንዳንዷ ቃል ዛሬም ድረስ ትዝ ትለኛለች፡፡ ሰርኬ፣ ‹‹የእስክንድር መታሰር የአንድ ቤተ-መጽሐፍት መዘጋት ነው›› ያለችውን እውነታ ለማረጋገጥ ከእስርንድር ጋር 10 ደቂቃዎች ቆሞ መነጋገር መልስ ይሆናል፡፡
እስክንድር ከተፈረደበት በኋላ እኔ እና አቤል ዓለማየሁ (ጋዜጠኛ) ብዙ ጊዜ ቃሊቲ ሄደን እንጠይቀው ነበር፡፡ በጥየቃችን ወቅት ሰርካለም እና ናፍቆት መካከላቸው ያለውን የእንጨት አጥር ተደግፈው እስክንድርን ሲነጋግሩት እንደርስ ነበር፡፡ ስርኬም ‹‹እናንተ አውሩት ብላ›› ቦታ ትለቅልናለች፡፡ ናፍቆት ግን ይቁነጠነጣል፡፡ በጨዋታ መሃል አባቱን ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ አባቱም እየሳቀና ኮስተር እያለ መልስ ይሰጠው ነበር፡፡
የናፍቆትን ጉዳትና ጫና ትልቅ ግምት ውስጥ በማስገባት ሰርካለምና ናፍቆት እስክንድርን ርቀው በስደት አሜሪካ ሊኖሩ ተገደዱ፡፡ እስከማውቀው ድረስ ሰርኬ ከእስክንድር ርቃ ለመሄድ ምንም ፍላጎቱ አልነበራትም፡፡ እስክንድር ግን ለናፍቆት ሲባል መሄድ አለባት ብሎ አስረግጦ ሲናገር ሰምቼዋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና የሰርካም ፋሲል መሆኑ ነው፡፡ በስደት ሀገርም ሆና አካሏ እንጂ ዘወትር መንፈሷ ቃሊቲ እያደረ መሆኑን አምናለሁ፡፡
እነሰርካለም ከሄዱ በኋላ፣ እስክንድር መጠየቅ እስኪከለከል ድረስ በተናጠልም ሆነ ተሰብስበን እንጠይቀው ነበር፡፡ አንዳንዴ ‹‹ለሰርካለም መልዕክት ንገርልኝ›› ብሎኝ ሰላምታ አድርሼለታለሁ፡፡ አንድ ቀን ግን ‹‹ሰርካለም በርቺ! ጠንክሪ! መታገልሽን መቼም እንዳታቆሚ!›› ብለህ ንገራት አለኝ ኮስተር እንዳለ፤ የምሩን ነበር፡፡ እስክንድር እንደዚያ አለ እንጂ ሰርኬ ከሀገር ወጥታ ትንሽ ከቆየች በኋላ በሀሳብ መታገሏን ዛሬም ድረስ አላቆመችም፡፡
ሰርኬን በማኅበራዊ ሚዲያ እንደእኔ በቅርበት ለተከታተላት ወንድም፤ የምር ሀዘኗን፣ ብሶቷን፣ ለቅሶዋን፣ ቁጭቷን፣ ደስታዋን፣ ተስፋዋን፣ እምነቷን …ወዘተ በቀላሉ መገንዘብ ይችላል፡፡ የተለያዩ ስሜቶቿ በውስጧ አልፈው ሲመጡ የምር መሆናቸውን ያሳብቃሉ፡፡ አስተያየት መስጠት ባለፈለገችባቸው ጉዳዮች ላይም የምር ታዛቢ ሆና ዝምታዋንም የምር ታደርገዋለች፡፡ [አይደለ ሰርኬ? lol]
እንደህወሃት/ኢህአዴግ አይነት ጭካኔውን አምርሮ፤ ዜጎችን የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለመጣድና ተስፋ ለማስቀረጥ ቀን ከሌሊት ከሚተጋ ቡድን ጋር አሜሪካ ሆነው ሳይታክቱ ሀሳቦቻቸው፣ ምልከታቸውን፣ አቋሞቻቸውን፣ ስሜቶቻቸውን …ወዘተ ደፍረው ከሚሰነዝሩ ውስን ኢትዮጵያዊ እንስቶች መካከል አንዷ ሰርካለም ፋሲል ናት፡፡
መከራ ሲፈራረቅና ሲበረታ ብዙዎች ይረታሉ፣ ይሸነፋሉ፣ እጅ ይሰጣሉ፣ ተስፋ ይቆርጣሉ፣ አቋማቸውን ይቀይራሉ፣ ይሸሸጋሉ፣ ይጠፋሉ፣ ይሰበራሉ! … ሰርኬ ግን በባህር ዳርቻ እንደሚገኝና በጠንከራ ማዕበል ዘወትር እየተመታ ጠንከሮ እንደሚቆም ሰንበሌጥ የመከራ ማዕበልና ወጀቡን ተቋቁማ ዛሬም ድረስ አለች፡፡ የሰርኬ በመከራ ውስጥ ተፈተነ ጥንካሬ ለሴቶችም ለወንዶችም ምሳሌ መሆን የሚችል መሆኑን አምናለሁ፡፡ ብዙ ብል ደስ ባለኝ …
ግን …ዛሬም ደግሜ እላለሁ፣ ሰርኬ፣ ከጠንካራ ወንድ ጎን ጠንክራ መቆም የቻለች ኢትዮጵያዊት ናት!
ሰርኬ፣ፈጣሪ ተጨማሪ ብርታትና ጥንካሬን ይለግስሽ፣
የፈተና ቀኖችሽም ይጠሩ!

Filed in: Amharic