>

አንዳንድ ነገሮች (ከአቢይ አፈወርቅ)

አንዳንድ ነገሮች ፣

. . . ዕጹብ ድንቅ ናቸው ፦
እንደ ንጋት ጸሀይ ፣ መንፈስ የሚያሞቁ ፤
እንደ አመሻሽ ጀምበር ፣ ውበት የሚያፈልቁ ፤
የልብ የሚያደርሱ ፣ ለነፍስ የቀረቡ ፤
ከኮተኮቷቸው ፣ ሁሌም የሚያብቡ።
አንዳንድ ነገሮች ፣
. . . ግዙፍ እልፍኝ ናቸው ፦
ሁሉን ያካተቱ ፣ ከባህር የሰፉ ፤
ሁሉ የኔ ‘ሚላቸው ፣ በፍቅር የፋፉ ፤
ውብና ፀዓዳ ፣ ልዩ አዳራሽ ናቸው ፤
እልፍኝ አስካልካዩ ፣ ካላጠበባቸው ።
አንዳንድ ነገሮች ፣
. . . ልዩ ፍቅር ናቸው ፦
እንደ ዓይን ብሌን ፣ እንደ ህጻን ገላ ፤
ወድቆ እንደሚሰበር ፣ እንደልዩ ሸክላ ፤
የሚሳሳላቸው ፣ ለትልቅ ትንሹ ፤
ሁነኛ ተመልካች ፣ ተሟጋች የሚሹ።
ጉድፍ አራጋፊ ፣ ቢያጠፉ መካሪ ፤
የምር ካገኙ ፣ ዓይን ከፍቶ አፍቃሪ ፤
አንዳንድ ነገሮች ፣ ሁሌም ህያው ናቸው ፤
ማደግ ማበብ እንጂ ፣ ሞት የማያውቃቸው::
አንዳንድ ነገሮች ፣
. . . መገበዝ አያውቁም ፦
ቢያጠፉ እንዳላየ ፣ ቢስቱ እንዳልሰማ ፤
በዝምታ አርጩሜ ፣ በ‹ዕውር ፍቅር› ሳማ ፤
ክቦ ከሚያሳንስ ፣ እልፍ ስሜተኛ ፤
ፍቅር ይደረጃል ፣ በአስር ዕውነተኛ።

Filed in: Amharic