>

አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል…. [ኣንዱዓለም ቡከቶ ገዳ]

doctorate-graduateበርእሱ የተጠቀሰው የክቡር ዶ/ር ጥላሁን ቆየት ያለ ዘፈን ነው……” ……አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል……” ይላል….እኔም ሰሞኑን “አንዳንድ ነገሮች” እንዲሁ ግርም እያሉኝ ነው……አሁን ባለፈው እለት የምሰራው አጥቼ ቤቴ ቁጭ ብዬ ጋዜጣ አገላብጥ ነበር…..ስለ ሪዮ ኦሎምፒክ ክቡር ዶ/ር ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ የሰጠውን ቃለመጠይቅ አነበብኩ…እውነቱን ለመናገር የሪዮ አሎምፒክ የአትሌቶች ምርጫ አስጊ ነው!… እነ ክቡር ዶ/ር መሰረት ደፋር አንድ ነገር ካላደረጉ ከዚህ ቀደም በነ ክቡር ዶክተር ደራርቱ ቱሉ ጊዜ ያገኘነውን ድል የምንደግመው አልመስል እያለኝ ነው….ስፖርት ማንበብ ሲሰለቸኝ ራዲዮ ከፍቼ ማዳመጥ ስጀምር በአጋጣሚ የክቡር ዶ/ር አስቴር አወቀ “ስኳር ስኳር” የሚለው ዘፈን ሸገር ኤፍ ኤም ላይ እየተንቆረቆረ ነበር ፡፡ክቡር ዶክተር አስቴርን በጣም ብወዳትም ይህ ዘፈኗ በተለይ ግጥሙ (ስኳር እንደዚህ በጠፋበት ሃምሳ ግዜ ስኳር ስኳር ማለቷ ስለማይመቸኝ ) ጣቢያውን ወደ ሀገሬ ጣቢያ(ፋና ኤፍ ኤም የአሰላ የኦሮምኛ ፕሮግራም ) ቀየርኩት …የተወዳጁ የክቡር ዶ/ር አሊቢራ “ኒንዴማ ኒንዴማ” ጣእመ ዜማ ይንቆረቆራል….የክቡር ዶ/ር አሊቢራ ዘፈን እና የክቡር ዶ/ር ኪሮስ አለማየሁ ዘፈኖች ኦሮምኛም ሆነ ትግርኛ በማይችሉ አድማጮች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑበት ሚስጥር ግልጽ ነው… ሁለቱንም ተፈጥሮ የሚገርም ድምጽ አድላቸዋለች….በመሃል የፈረደበትን ኢቲቪ ስመለከት በቅርቡ የተጠናቀቀውን ” መለከት ” ድራማ የተመለከተ የተመልካች አስተያየት እየተሰጠ ነው… ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ አበበ(“ፋዘር” ይሏቸዋል ሲያቆላምጧቸው) የሆኑ ችግኝ ተካይ ሰውዬን ገጸባህሪ ወክለው የተጫወቱት ፓርት አርአያነቱ በብዙዎች እየተደነቀ ነበር ፡፡ድራማው አስተማሪነቱ ቢበዛም ጥሎብኝ አልወደውም ነበር….. ቻናሉን ወደ ኢቢሲ3 ሳደርግ “ቆየት ያሉ ጣእመ ዜማዎች” በሚለው ፕሮግራማቸው የክቡር ዶ/ር ንጋቷ ከልካይ “ሰውነቷ “የሚለው ተወዳጅ ዜማ እየታየ ነበር…አይ ድምጽ! …..በእውነቱ ከድሮዎቹ ሴት ዘፋኞቻችን ክቡር ዶ/ር ንጋቷ እና ክቡር ዶ/ር ማሪቱ ለገሰ ይመቹኛል….. ከወንዶች እንደ ክቡር ዶክተር ማህሙድ አህመድ የትዝታ ዘፈኖች የሚመቸኝ ባይኖርም ግን ከምንም በላይ ደግሞ ለሀገራችን ሙዚቃ እንደ ክቡር ዶክተር” የሙዚቃ ሰው” ሙላቱ አስታጥቄ ባለውለታ የለም ባይ ነኝ….ጎሽ ቲቪው ላይ መለከትን በተመለተ የነበረው ፕርግራም አለቀ….አሁን ደግሞ “ሳይንስና ቴክኖሎጂ” ፕሮግራም የጀመረ ሲሆን ስለስፔስ ሳይንስ በሀገራችን መስፋፋትና ጥቅሙ ሀላፈው ክቡር ዶ/ር ተፈራ ዋልዋ አጠር ያለ ማብራሪያ እየሠጡ ነው …..ኢቲቪ 2 ላይ ደግሞ ክቡር ዶ/ር አዲሱ ለገሰ ስለ”ግንቦት ሃያ ፍሬዎች” ቃለመጠይቅ እየሰጡ ሲሆን ዶክተሩ የትግሉ አለኝታ ስለነበሩት ክቡር ዶ/ር መለስ ዜናዊ ደጋግመው አወሱ ……..ከሳቸው ለጥቆ ክቡር ዶ/ር ስብሃት ነጋ(አቦይ ስብሃት ) እንደማንኛውም የክብር ዶክትሬት ተሸካሚ ረጋ ብለው እና ስለ ክቡር ዶከተር መለስ የትግል ሚና ተጋኖ ሲቀርብ ዘወትር እንደለመደባቸው ቆጣ ብለው በትጥቅ ትግሉ ክቡር ዶ/ር መለስ ዜናዊ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ታጋይ ህይወቱን ሳይሰስት እንደገበረ አንድን ሰው ብቻ ማግነን ተገቢነት እንደሌለው አስታወሱ……በዚህ ነጥብ ላይ የክብር ፕሮፌሰር ሳሞራም የበኩላቸውን ሀሳብ አከሉ……ሌሎችም
አረ ውውው… ኤጭ! አሁንስ እኛ ሀገር የክብር ዶክተር በዛ አትሉም እንዴ…?!
…… በእውነት አሁንስ “መሃይም” ማየት ናፈቀኝ!…..ሂሂሂ… በዛ ላይ እኔም ዶክትሬት አማረኝ ….ሁሉም በየወገኑ በየጎጡ ዶክትሬቱን እየታደለ ስለሆነ ለኔም አርሲ ዩኒቨርስቲ ለባለፉት አስራ ሁለት ወራት በፌስ ቡክ ያደረኩትን ተጋድሎ ምናምን ጠቅሶ አንድ ዶክትሬት ቢገጨኝ ይደብራችኋል?! ! ታዲያ ምን እጠብቃለሁ?!….(ለአሌክስም ከደሴ ዩኒቨርስቲ ይገጨው ከፈለገ)….ከዚህ በላይ …!በዛ ላይ “ሁ ማይነስ ሁ “ነው ነገሩ! በነገራችን ላይ ግን ምነውሳ የኦሮሚያ ዩኒቨርስቲዎች በገዛ ወገኖቻቸው ላይ ቋጠሩ?! እነ ኩማ እነ አባዱላ …አስቴር ማሞ ምናምንም ዶክትሬት ይገጫቸው እንጂ!…ነው ወይስ ለዚህም ነገር ትእዛዙ ከፌደራል ነው የሚመጣው…?! “ለህወሃት ታጋዮችም ቢሆን እንደዚህ በቁጥ ቁጥ ከሚሰጥ በህይወት ላሉ ታጋዮች በሙሉ አንድ ግዜ በአዋጅ በአክሱምና በመቀሌ ዩኒቨርስቲዎች ስም አንድ ላይ የክብር ዶከትሬት ቢሰጥ አይሻልም?” የሚል ለእኔ ለራሱ የክብር ዶክትሬት የሚያሰጥ ሃሳብ አለኝ….
ብቻ ለማንኛውም ግማሹ በሸመታ ግማሹ በክብር ስም ጥቂቱ ብቻ በስራ ዶክትሬት በዶክትሬት በመሆኑ አሁን አሁን ሰው ስተዋወቅ ሰውየው “ዶ/ር” የሚል ማእረግ ከሌለው “ምኑ ድንጋይ ራስ ነው?!” ማለት ሁላ ጅምሬአለሁ …ግን ሁሉም ዶክተሮች ሲተዋወቁን በደፈናው “ዶክተር” ሲሉ “የስራ” እና የግዢው(የትምህርት ዶክትሬቶች ምድብ ውስጥ) እንዲሁም ሀቀኛው እና ዘረኛው(የክብር ዶክትሬቶች ምድብ ውስጥ) ግራ እንዳያጋባን አጠራሩ እና አጻጻፉ ላይ ልዩነት ቢደረግ የምትል ሌላ ዶክትሬት የምታሰጥ በሳል ሀሳብ አለችኝ….ለምሳሌ ሌባዎቹ ዶክተሮች “ዶክተር ሌባ” ቢባሉና ይህም ለአጠራር እንዲያመች አጠር ተደርጎ “ዶክሌ” ቢባሉ… ሸማቾቹ ባለስልጣን ዶክተሮቻችን “ዶክሼ” … በዘር የወሰዱትን ዘረኞች “ዶክዜ”..ምናምን እያልን በላባቸው የሰሩትን ብቻ ዶክተር ብንል እንዲህም የክብር ዶክትሬት ይገባቸዋል የምንላቸዉን ጥቂት ሰዎች ብቻ “ዶክኬ” ወይም “ዶኬ” ብንላቸው ወይም ምንም ባንላቸውስ?! አረ ኤዲያ ! እንግዲህ ይሄ የእኔ አየዲያ ነው ጀለሶቼ ……ከአምስት እስከ ስድስት ሰአት ድረስ ሙስሊም ወዳጆቼን እንኳን አደረሳችሁ ለማለት በሚመጥን የኢድ ፓስት እመለሳለሁ….ወደጆቼ በበአልማ መደበር የለም ይህ የነቆራው ቅምሻ ሲሆን ለእኔ ደግሞ ማሟቂ (ስትሬቺንግ) ነው…..ገና ፈታ እንላለን….ከሌሎቻችሁም ጋር በኋላ እንገናኝ …እኔም ቲቪ እና ራዲዮና በዶክተር ብዛት ስላሰለቸኝ ቁርስ እስከሚደርስ ድረስ እና ወደ ጽሁፍ ከመሄዴ በፊት ወደ መጻፍ መደርደሪያዬ ሄጄ እጄ የገባልኝን መጻፍ ላነብ ነው …..በአጋጣሚ ከላይኛው መደዳ ሁለት መጻፍ አነሳሁ ፡፡አንደኛው የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል “ተረትና ምሳሌ” ሲሆን ሌላኛው የክቡር ዶ/ር አዲስአለማየሁ “ተረት ተረት የመሰረት” የሚለው ነው፡፡ የቱን ላንብብ?
እስከዛው ይመቻችሁ

Filed in: Amharic