>

ጳጳሶችና ስደት [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

profeser Mesfen Weldemariam Quateroእንዲያውም ርእሱን ካህናትና ስደት ብለው ይሻላል፤ ካህናት የሁሉንም ሃይማኖቶች መሪዎችን ይመለከታል፤ ዓላማዬም ሁሉም የሃይማኖት መሪዎችን የሚነካ ነው፤ ነገር ግን የእኔ እውቀት በክርስትናው ላይ ጎላ ያለ በመሆኑ የክርስቲያኖቹ መሪዎች ላይ ያተኮርኩ ቢመስልም ሁሉንም ይመለከታል፤ በተለይ መነኩሴዎች ላይ የማነጣጥርበትም የተለየ ምክንያት አለኝ፡፡

በመጀመሪያ አንድ መሠረታዊ ነገር ላብራራ፤ እንደማንኛውም ሰው ስለፍርሃትና ስለጥቃት አውቃለሁ፤ በተለያዩ መንገዶች በመርማሪዎች የተሰቃዩ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ የጻፉትንም አንብቤአለሁ፤ ከሁሉም በላይ ፍርሃት የግል መሆኑን አውቃለሁ፤ በዚህም ምክንያት ሰውን ለምን ፈራህ ብሎ መውቀስም አስቸጋሪ መሆኑ ይገባኛል፤ ስለዚህም ይህንን የምጽፍበት ምክንያት የተሰደዱትን ለመውቀስና እነሱን ዝቅ አድርጌ ራሴን ከፍ ለማድረግ አይደለም፤ ከቃሌ በቀር ይህንን የማረጋግጥበት መንገድ የለም፤ እንዲህ ያለው ዓላማ ምንም ትርፍ የለውም፡፡

የኔ ዓላማ ሁለት ነው፤ አንደኛ የሚቀጥለው ትውልድ ሽሽትንና ስደትን እንደባህል እየወሰደው እንዳይቀጥልና የኢትዮጵያ መራቆት እንዳይባባስ እሪ! ለማለት ነው፤ እሪ! በማለት በተለይ የወጣቶቹን ትኩረት ለመሳብና ከሽሽትና ከስደት ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ ለማሳሰብ ነው፤ ይህንን ለማድረግ ስሞክር የማኅበረሰባዊ ግዴታዬ እስከዛሬ የተሰደዱትን ሰዎች የዜግነትም ሆነ የማኅበረሰባዊ፣ የሃይማኖትም ሆነ የታሪክ፣ የፖሊቲካም ሆነ የኑሮ ኃላፊነትን፣ ተጠያቂነትንና የወላጆችን ክብር አነሣለሁ፤ በዚህ ጽሑፍ ላይ የማተኩረው ከላይ እንደገለጽሁት በካህናት ላይ ነው፡፡

በክብረ ነገሥት ልጀምር፡–

‹‹ለካህናትሰ ሰመዮሙ ጼወ፤ ወዓዲ ለካህናት ሰመዮሙ መኅቶተ፤ ካዕበ ሰመዮሙ ብርሃኖ ለዓለም፣ ወካዕበ ሰመዮሙ ጸሐየ ዘያበርህ ጽልመተ እንዘ ክርስቶስ ጸሐየ ጽድቅ ውስተ አልባቢሆሙ፤

ወካህንሰ ዘቦቱ ልቡና ይገሥጾ ለንጉሥ በእንተ ምግባራት ዘርዕየ ወዘኢርእየሰ እግዚአብሔር ይፈትን ወአልቦ ዘይወቅሶ፤

ወዓዲ ኢይሕምይዎሙ አሕዛብ ለጳጳሳት ወለካህናት እስመ ደቂቀ እግዚአብሔር ወሰብአ ቤቱ እሙንቱ በእንተ ዘገሠጾሙ በእንተ ኃጢአቶሙ ወጌጋዮሙ፤

ወአንተኒ ኦ ካህን ለእመ ርኢከ ዕውቀ ኃጢአቶ ለብእሲ ኢትኅፈር ገሥጾቶ ኢያፍራህከ ሰይፍ ወኢስደት፡፡

 

እስቲ ዳዊት ያልደገሙት ይኮላተፉበት! ፍሬ ነገሩ ክብረ መንግሥት በመጀመሪያ ካህናትን በጣም ይክባቸዋል፤ ጨው አላቸው፤ መብራት አላቸው፤ የዓለም ብርሃን አላቸው እውነተኛው ጸሐይ ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ ስላለ ጨለማን የሚያበራ የዓለም ብርሃን ይላቸዋል፡፡

ክብረ ነገሥት ክቦ፣ ክቦ አያቆምም፤ ይቀጥልና የካህናትን ግዴታ ይናገራል፤ ልቡና ያለው ካህን በሚያያቸው ጉዳዮች ንጉሡን ይገሥጻል፤ የማያየውን ጉዳይ ግን እግዚአብሔር ይመረምራል፤

ሕዝብ ጳጳሳትንና ካህናትን ማማት ተገቢ አይደለም፣ ስለምን የእግዚአብሔር ልጆችና ቤተሰቦች ናቸው፤

ካህን ሆይ አንተ ግን የሰውን ኃጢአት ስታይ መገሠጽን አትፍራ፤ ሰይፍም ሆነ ስዴት አያስፈራህ፡፡

ዳዊትን የደገመ ሁሉ እንደሚያውቀው ፡- ኢይፈርሆ ለእኩይ እስመ አንተ ምስሌየ፤ ይላል፤ አንተ ከኔ ጋር ነህና አልፈራም ማለት ነው፤

እንግዲህ ይህ የክብረ መንግሥት ትእዛዝ በጣም ግልጽ ነው፤ የክርስቶስም ትእዛዝ በጣም ግልጽ ነው፤ ተራራውንም ማዘዝ ትችላላችሁ ይላል፤ ለደቀ መዛሙርቱ ስለእምነታቸው ጎዶሎነት ደጋግሞ ተናግሯል፤ እንግዲህ ስደት የቅንጣት ታህል እምነት መጉደል ያመጣው ፍርሃት አይደለም? ሽሽት የራስን አካላዊና መንፈሳዊ ኃይል መካድ አይደለም? ‹‹እስመ አንተ ምስሌየ››ን መካድ አይደለም? መትረየስ ፊት የቆሙትን ጴጥሮስን መካድ አይሆንም?

ወይስ የኛዎቹ ጳጳሳትና ካህናት ሌላ መመሪያ አላቸው? ወይስ አንድ አጭበርባሪ ሰባኪ ልጆቼ እንዲህ አታድርጉ፤ እንዲህም አታድርጉ እያለ ሲሰብክ አንድ በጣም የሚያውቀው ሰው ትኩር ብሎ ሲመለከተው ዓይን ለዓይን ሲጋጠሙ ማርሽ ለወጠና ልጆቼ እኔ እንደምላችሁ አድርጉ እንጂ እኔ እንደማደርገው አታድርጉ አለ ይባላል፡፡

ወደሐዲስ ኪዳንም ገብቶ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፤ ግን በጣም ያሳፍራል፤ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያፈርሁት አንድ ባሕታዊ በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገደለና በቤተ ክርስቲያን እንዳይቀበር የተደረገው ሙከራ ነው፤ ሁለተኛው በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሙጢኝ ያሉትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  መስቀል የለበሱ ሰዎች አሳልፈው ሲሰጧቸው ነው፡፡

የተሰደዱና ያልተሰደዱ ካህናት ብሎ መለየቱ ዋጋ የለውም፤ ዋጋ የለውም የሚባለው በምእመናኑ፣ በበጎቹ፣ ዓይን ሲታይ ነው፤ በጎቹን ጥለው የሸሹትም ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘሀበነ ዘንተ ፀጋ በመዋዕለ ስደትነ።›› እያሉ ለራሳቸው ይኖራሉ፤ ያልሸሹትም በሥጋ ነው እንጂ በመንፈስ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር መሆናቸው ያጠራጥራል፤ በአንድ በኩል ሲታይ ሁለት ሲኖዶሶች የሚባሉት በአካል የሚገኙት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መሆናቸው ነው እንጂ በመንፈስ አንድ ናቸው፤ የዝንጀሮ ቆንጆ!

ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆችን በትምህርት ስታሳድግ የኖረች፣ ደሀዎችን፣ ስትረዳ አሮጊቶችና ሽማግሌዎችን ስትትጦር፣ እናትና አባት የሌላቸውን ልጆችን እያስተማረች የምታሳድግ፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች ስትጠብቅ የኖረች ዛሬ በብዙ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚደረገውን ስትፈጽም የኖረች ነች፤ መንፈሳውያን ሰዎች በነበሩባት ጊዜ፤ ዘመናዊነት በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ እንዳልሆናት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱም አልሆናትም፤ የዛሬ ሃምሳና ስድሳ ዓመት ግድም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የሠለጠኑትና በኋላም ነገረ መለኮት እንዲማሩ ወደወጭ የተላኩት ሁሉ እያደናቀፋቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመርዳት አልቻሉም፤ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ግን ባልተጠበቀበት መስክ ሙያተኞችን አፍርቷል፤ በሕዝብ ‹‹ደኅንነት››ና በጦር ሠራዊት ታላላቅ መኮንኖችን አበርክቷል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉት ካህናት-ጳጳሳት ‹‹በዶልቼ ቪታ›› (መለስ ታምራትን ሲያባርረው ስኳር ያለው) ተንደላቅቀው በመኖር ከአገር ውጭ ካሉት አያንሱም፤ አንዳንዶቹም ቀሚስ ለባሾች እዚያም እዚህም እየረገጡ አማርጠዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ይቺን ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ለትንሣኤ ማብቃት ያሻዋል፤ እግዚአብሔር ይርዳን!

ስደትን በሚከተሉት ቀልዶች አሳምረውታል!!!

‹‹በሥጋ እንጅ ከቅድስት አገራችን የተሰደድነው፣ ከቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን አልተሰደድንም።››

‹‹የክርስትና ሃይማኖት እንደ ዓለማዊ መንግሥት የግዛት ወሰን የለውምና።››

Filed in: Amharic