>

ዛሬ አቶ በቀለ ገርባ በውስጥ ካኒቴራ፣ በቁምጣና በባዶ እግራቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ [ኤሊያስ ገብሩ]

‹‹የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ሕይወታችን የከፋ አደጋ ላይ ነው፤ …ለቀጣይ ቀጠሮ መገኘታችንምም እርግጠኞች አይደለንም››
‹‹ወደጨለማ ክፍል ወሰዱን፡፡ ከመካከላችን የተወሰኑትንም ክፉኛ ደበደቧቸው››
‹‹እንደዜጎች እየተቆጠርን አይደለም››
አቶ በቀለ ገርባ
—————
እነ ጋሽ በቀለ ፍርድ ቤት በዚህ መልኩ ነበር የቀረቡት photo Taddy Habesha‹‹በባለፈው ቀጠሯችን ለብሰን ፍርድ ቤት ልንቀርብ የነበረውን ጥቁር ልብስ አውልቁ ተባልን፡፡ አናወልቅም አለን፡፡ የፈለግነውን የመልበስ ሕገ-መንግስታዊ መብታችን ነው፡፡ ጥቁር ልብስ የለበስነውም፤ ከ50ሺህ በላይ የአንድ ብሄር ተወላጆች እስር ቤት መገኘታቸውንና በዚህ ዓመትም በጥቂት ወራት ውስጥ ከ200-300 የሚደርሱ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች መገደላቸውን በማዘን ለመግለጽ ነው፡፡ ድርጊታችንም ይሆን የነበረው የፍርድ ቤትን አሰራርን ምንም በማይነካ መልኩ በሰላም ነው፡፡ ይሄ አይሆንም ተብለን ዛቻና ስድብ ተደሰብን፡፡

ትናንት ከሰዓት በኋላ ዛሬ ፍርድ ቤት የምንቀርብ ሰዎች ለይተን ከየክፍላችን እንድንመጣ ተደረገ፡፡ ልብሶቻችንንም ይዘን እንድንወጣ አደረጉ፡፡ ከልብሶቻችን መካከል ጥቁር ልብስ እየተፈለገ ተወሰደ፡፡ እኛም ‹ልብሶቻችንን በሙሉ ልትመልሱልን ይገባል› ብለን ጠየቅን፡፡ ወደጨለማ ክፍል ወሰዱን፡፡ ከመካከላችን የተወሰኑትንም ክፉኛ ደበደቧቸው፡፡ የተደበደቡት ሰዎች እዚሁ ስላሉ ለችሎቱ መናገር ይችላሉ፡፡ ልብሶቻችን ሜዳ ላይ ተበትኖ ስለነበረ ሌሎች እስረኞች የሚፈልጉትን ወሰዱ (ተቀራመቱት)፡፡ የተረፈውን አምጥተው ክፍላችን ውስጥ አስቀመጡት፡፡
ዛሬም ድረስ ምግብ አልበላንም፡፡ እጆቻችን ጥዋት ድረስ በካቴና ታስሮ ነበር፡፡ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ድርጊት ነው የተፈጸመብን፡፡ የኦሮሞ ተወላጅ ብቻ እየተመረጠ ተደብድቧል፡፡ የታሰርንበት ቦታ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ተቋም ነው፡፡ ‹አንተ ነህ እንዲህ የምታደርገው፡፡ እናገኝሃለን› ብለውኛልም፡፡ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ/ ተቀያሪ ማቆያ ቦታ ያዘጋጅልን፡፡ አሁንም ተመልሰን ቂሊንጦ ስንሄድ ምን እንደሚደርስብን አናውቅም፤ ስጋት አለን፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እስካልተቀየሩ ድረስ ሕይወታችን የከፋ አደጋ ላይ ነው፤ በጣም ያሰጋናል፡፡ ለቀጣይ ቀጠሮ መገኘታችንምም እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ቤተሰቦቻችን እንዳያዩን እየተደረገ ነው፡፡ ዛሬም ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከገባን በኋላ ሰዎች እንዳያዩን ተደርጓል፡፡ እንዲህ የተድበሰበሰ ነገር መንግስት ለምን ይሰራል? እንደዜጎች እየተቆጠርን አይደለም፡፡››

[ይህንን ልብ የሚነካ ንግግር ከአንድ ሰዓት በፊት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቆመው ሲናገሩ ያደመጥኳቸው በጸረ-ሽብርተኝነት ወንጀል ተከስሰው ከ22 ሰዎች ጋር የፍርድ ሂደታቸውን የሚከታተሉት አቶ በቀለ ገርባ ነበሩ፡፡ አቶ በቀለ በዛሬው የችሎት ወሎ ከፊል ሰውነታቸውን የሚሳይ የውስጥ ነጭ ከነቴራ (ፓክ-አውት)ና ጥቁር ቁምጣ ለብሰው በባዶ እግራቸው ነበሩ፡፡ (ሌሎች አምስት ተከሳሾችም ተመሳሳይ አለባበስ ለብሰው ነበር) በቅርብ ርቀት እንዳየኋቸው ከሆነ፣ የግንባራቸው ደምስር ጎሎቶ ይታያል፡፡ እንቅልፍ አለመተኛታቸውንም ፊታቸው ይናገራል፡፡ በችሎቱ የነበሩ ከ10 በላይ ወታደሮች (መሳሪያ የታጠቁም ጭምር) የአቶ በቀለን ንግግር በተመስጦ ሲዳምጡ አስተውያለሁ፡፡ …እንግዲህ 25 ዓመታትም ታልፎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ በእስረኞች ላይ አንድም ይህንን ይመስላል፤ ማዘን ብቻ!]

Filed in: Amharic