>

''ባልጠበቁት ቦታና ሁኔታ ካጋጠመኝ እገታ ወጥቻለሁ።ግንቦት ሃያ የሚባል በዓል የማናከብርብት ጊዜ ያምጣልን!'' (ኣቶ ኣስራት ኣብርሃ )

የሆነውን ሁሉ ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም። ትንሽ ዕረፍት ማድረግና ተረጋግቶ ማስታወስ የሚያስፈልገኝ ነገር ነው። ባልጠበቁት ቦታና ሁኔታ ካጋጠመኝ እገታ ወጥቻለሁ።ይኸውን በዛሬ ዕለት ኢህአዴግ “ፍትህና ዴሞክራሲ አመጣሁላችሁ እያለ በሚለፍፍበት” ዕለት የግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት እንጂ የህግ የበላይነት የሚባል ነገር በዚች ሀገር እንደሌለ ይህ አሁን ያጋጠመኝ ነገር በራሱ ከበቂ በላይ የሆነ ምስክር ነውና በከንቱ ምንም ለውጥ ላይኖር ነገር ለዴሞክራሲና ለፍትህ ብለው የወደቁት ወገኖቼ ባሰብኳቸው ጊዜ ትልቅ ሀዘን ነው የሚሰማኝ። ግንቦት ሃያ የሚባል በዓል የማናከብርብት ጊዜ ያምጣልን!

በመጨረሻም፣ ከገባሁበት እገታ እንድወጣና ያለሁበትን ቦታ እንዲታወቅ የቻላችሁት ሁሉ ጥረት ያደረጋችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ የአንድነት አመራሮች፣ የአረና ወዳጆቼ፣ በአጠቃላይ ስለፍትህ ብላችሁ አጋርነታቸሁ ላሳችሁኝ ሁሉ እጅግ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። በዚች ሀገር ሁኔታ ተስፋ እንዳልቆርጥ ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ እንደእናንተ ያሉ ፈፅሞ በማንም ላይ ጥቃት እንዲደርስ የማይፈቀዱ ዜጎች መኖር ነው። እንደዚሁም ከበሰለ ንፍሮ ውስጥ እሳቱንና ውሀን ተቋቁሞ የሚዘልቅ ጥሬ እንደሚገኝ ሁሉ፣ በዚህ ፍትህ አልባ ጨለማ በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ለህሊናቸው ያደሩ ወጣት ዳኞች አጋጥሞኛልና እነርሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ምንም እንኳ እነርሱ እንደፈታ ከወሰኑልኝ ከ24 ሰዓት በኋላ ብፈታም፤ ሕጉን ለማስከበር ያደረጉት ጥረት ግን ሳላደንቅ አላልፍም።
ይኸው ሌላ የድል ቀን፣ ሌላ የነፃነት ቀን ይናፍቀን ዘንድ ሆነናልና፤ ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ተፈርጀው በግፍ የማይተሳሩባትና የማይደበደቡባት፤ የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን የምናደርገውን ትግል ፍሬ አፍርቶ፣ የዚህ ሁሉ ሰቆቃ መዝጊያ ያደረግንበት ቀን የምናከብርበት፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያለ ልዩነት የምናከብረው የነፃነት ቀን ያምጣልን።

 

Filed in: Amharic