>

ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ በልጆቿ አኩሪ መሰዋዕትነት ዳግም ትነሣለች!!!
ሰማያዊ ፖርቲ 
Blue partyከአምባገነኑ የደርግ አገዛዝ ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያ ከአገዛዝ ወደ ህዝባዊ አስተዳደር ትሸጋገራለች የሚሉ ወገኖች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያ ሣይሆን ቀርቶ ሀገራችን ባለፋት 25 ዓመታት በአንድ ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ መዳፍ እጅ በመውደቋ በከፍተኛ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል እየተናወጠች እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችን ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖብናል፡፡
ከሀገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ከ50% በላይ በህወኃት ኢህአዴግና ለአገዛዙ ቅርበት ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ በመሆኑም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ የበይ ተመልካች ሆኖ የቀን ጨለማ ውጦታል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሥራ እድል ተነፍገው አፋላ የሥራ ዘመናቸውን በጭንቀት ተውጠው ኑራቸውን ይገፋሉ፡፡ ሁሉም የንግድ ዘርፎች በህወሃትና ጋሻ ጃግሬዎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸውና በለየለት የአገዛዙ አድሎ ምክንያት በኢትዮጵያ ውሰጥ በላቡና በልዩ የፈጠራ ችሎታው ነግዶ ማትረፍና ሀብት ማፍራት የማይታሰብ ሆኗል፡፡ ገበሬዎች ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ በሀገራቸው ሠርቶ የመኖር መብት ተነፍገው አባቶቻቸው በደምና በአጥንታቸው ጠብቀው ያቆዩት መሬት በጥቂት የህወሃት /ኢህአዴግ ልዩ ተጠቀሚዎች ኪስ ማደለቢያ እየሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የመንግስት ሠራተኞች በተማሩትና በአካበቱት የሥራ ልምድ ለሀገራቸው ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋፅኦ በህወሃት አግላይና ዘረኛ ፖሊሲ ምክንያት መክኗል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ፋና ወጊ የነበረች ብትሆንም በህወሃት /ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዋርዳለች፡፡ በህወሀት አድርባይነትና ዝቅተኝነት ምክንያት የባህር በሮቿን አጥታለች፡፡ በዚህም ምክንያት ካጣችው የኢኮኖሚ ጥቅም በተጨማሪ በዓለምም ሆነ በቀጠናው የነበራትን ተፅኖ ፈጣሪነትና ክብር አጥታለች፡፡
ዜጐች በየሄዱበት ሀገር በውርደት ይገደላሉ፣ አሁን የተፈጠሩ ትናንሽ ሀገሮች ሁሉ ሉዓላዊነታችንን በመድፈር ድንበራችን
ጥሰው በመግባት ዜጐቻችንን አፍነው ይወስዳሉ፣ ግድያ ይፈፅማሉ፣ ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የራሳችን መከላከያ ሰራዊት ለሌሎች ጥቅም አስከባሪነት በመሰዋት በምትኩ ለአገዛዙ የሥልጣን እድሜ ማራዘሚያና ለባለጊዜዎች ኪስ ማድለቢያ ገንዘብ ማስገኛ እየዋለ ነው፡፡ በመሆኑም ባለፋት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ሉዓላዊ ክብር በእጅጉ ተሸርሽሯል፡፡ በተጨማሪም አገዛዙ በመሠረታዊ ባህሪው አውዳሚነት የተጠናወተው በመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪክ አምርሮ ይጠላል፤ እውቀትና አዋቂዎችን እንደጦር ይፈራል፤ ሽምግልናንና ኃይማኖትን ያዋርዳል ፤የዜግነት ክብርና አንድነትን በማቃለል ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ እንዳይተማመኑ የጥላቻ መርዝ ይረጫል፡፡ በዚህም የአገዛዙ እኩይ ተግባር ምክንያት በአሁኑ ሰዓት አኩሪ ሀገራዊ እሴቶቻችን እየወደሙ በምትኩ ሌብነት፣ ዋሾነት፣ ግለኛነት ፣ ዘረኝነት፣ ዝርክርክነትና አባካኝነት መገለጫዎቻችን እየሆኑ ነው፡፡ ይህ አስከፊ ጉዞ በአስቸኳይ ካልተገታ ኢትዮጵያ እንደሀገር የመቀጠሏ ሁኔታ እጅግ አጠራጣሪ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፋት 25 ዓመታት ይህ አገዛዝ አደብ እንዲገዛ ከዚያም አልፎ ወደ ህዝባዊ አስተዳደር እንዲሸጋገር ብዙ መስዋትነት ከፍሏል፣ ብዙዎች ተገድለዋል፣ አካላቸውን አጥተዋል፣ ከስራ ተባረዋል፣ በግፍ ታስረዋል፣ የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ለአገራችን የምንመኘው ህዝባዊ አስተዳደር ባለመስፈኑ ትግላችንን አጠናክረን የነበሩብንን ድክመቶችና የስትራቴጂ ስህተቶች ካገኘናቸው ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ለድል እንድንነሣ ለሁሉም የዴሞክራሲ ኃይሎችና የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ግንቦት 19 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም

Filed in: Amharic