>

ሰቆቃ ዘኢትዮጵያ [ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ፥ፒ ኤች ዲ፥ (የሁማኒቲስ ፕሮፌሰር)]

Prof. Fikre Tolosaድንግሊትዋ ኢትዮጵያ
ክብርዋ ተገሰሰ፥
ብፁእ ሰብእናዋ ተበረቃቀሰ፥
ቅድስቲት ኢትዮጵያ
ያ ቅድስናዋ ከንግዲህ ረከሰ።
ክብርት ወ ‘ምክብርትዋ፥
ውርደትዋ ዋ! ባሰ።
በሮች መስኮቶችዋ፥
ብለው ብርግድግድግድ፥
ርኩስና ገባ፥
ጠፋና የሚያግድ።

ገባም በቂዛዛ ባሉት ቴሌሺዥን፥
ገባ በስእሎች በሚንቀሳቀሱ፥
ነፍስ በሚያሳድፉ፥
የወሲብ ነዲድን እየቆሰቆሱ፥
ሴት ሆነ ወንድነት፥
ወንድ ሆነ ሴትነት፥
ፆታ ተለዋውጦ፥
በፍናፍንትነት።
ግልብጥብጡ ወጣ፥
ተፈጥሮ ተሽሮ፥
ምግባር ቅድስና፥
በንዋይ ፍቅርና ገንዘብ ተሸርሽሮ።
ያውሮፓን ግብስብስ፥
ያሜሪካንን ጥንብ፥
ሁሉ ይልስ ጀመር፥
ቁስል እንዲልስ ዝንብ።

ሻሽ ጠምጣሚውና፥
ቆብ አድራጊው ሁሉ የቅዱስ ተወካይ፥
ሆነና ዐለማዊ፥ ከስጋም ስጋዊ፥
እንኳንስ ሊያነፃ ራሱ ነው ተበካይ።
ራሱ የተጣላ
እንኳንስ ሊያስታርቅ፥
ራሱ ያልታረቀ፥
እንኳን ምእመን ሊያርቅ፥
ጭራሽ ምእመን ሆንዋል፥
የቀወሰን ካህናት ሽቅብ የሚያስታርቅ።
ዬ! ዬ! ለኢትዮጵያ፥ ዬ! ዬ!
ዬ! ዬ! ለማምዬ!
ሀገረ ቅዱሳን
ወረርዋት ርኩሳን።

በመስኖ እሚመራው
አጥቶ ወንዛወንዙ፥
ልምላሜ መሃል እያገረሸበት፥
የድርቅና ጠኔ አያልቅም መዘዙ።

እስር ቤቱ ሞልቶአል
ካፍ እስከገደፉ፥
የ 40 ዐመት ትግል፥
ወዮ ሆነ ትርፉ።

ይነጉዳል ወጣቱ፥
ጥሶ ድንበር ኬላ፥
ከዚህ ሞት ያኛው ሞት
ብሎ ቢሆን መላ።
እናትና አባቱን እሱ እንደመጦር፥
በደካማዎቹ በእነሱ ሲጦር፥
እፍረትና ፀፀት እየፈላለጡት፥
የባእድ ሰይፍ መርጦ ከራስ ህሊና ጦር።

ለኛ የሚል ጠፍቶ፥
ሁሉ ለኔ ለኔ፥
ትዮጵያዊነት ወድሞ፥ ዘውገኝነት ሰፍኖ፥
ሁሉ ለጎሳዬ፥ ሁሉ ለወገኔ።

በገዥና ተገዥ፥
ጥልቅ ገደል አለ በሁለቱ መካከል፥
አንዳይገናኙ የሚያራርቃቸው፥
እሳተ ነበልባል ሆኖ እሚከላከል።

ላንት እንፈጥራለን የምድር ላይ ገነት፥
እያሉት ምስኪኑን አለፈ 50 ዐመት፤
በሱ ስም የመጡት ኖሩ ንጂ በገነት፥
እሱ ያቃትታል፥ ወድቆ ከእጦት ፅልመት።

ለማኝ ይለምናል
ብሶበት ከጥንቱ፥
አሁን ቁጥሩ በዝቶ፥ ስጋውን ሊመግብ፥
ስጋውን ይሸጣል ራብ ጠንቶበት ሴቱ።
የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘር ቀርቶ ወንድነቱ፥
ወንዱም ተሰማርቶአል ሊያድር በዝሙቱ።

ታግሎ ነበር ወጣት ለነፃነት፥ ፍትህ
ከፍሎበት መስዋእት፥ በጮርቃ ህይወቱ፤
ደልቶት ሊኖር ሲችል፥ የተሰደደበት፥
ቁምስቅሉን ያየበት የታለ ውጤቱ?

ውሃ፥አፈር፥ ማዕድን፥ ተንበሽብሸው ውስጥዋ፥
ምን ሲባል ይወራ ጦቢያ መማቀቋ፥
ምንድነው ትርጉሙ፥
በርስበርስ ጦርነት ዝንታለም ማለቋ?

እስከመቼ ይሆን ይህ ሁሉ ሰቆቃ
ይሄ ሁሉ ዋይታ እንዲህ የሚቀጥል፥
ብዙው ካፈር ወድቆ አፈር እየላሰ፥
ባየር የሚንሳፈፍ ጥቂቱ ቅምጥል?

መቼ ነው የሚያቆም
የእምባና ደም መፍሰስ፥
መች ነው ፍትህ ገኖ፥
በደል ተደምስሶ ጡር የሚገረሰስ?
መቼ ነው ኢትዮጵያ ዳግም ምትቀደስ፥
መቼ ነው እምዬ ልጆችዋ ተፋቅረው፥
ክብርዋ ተመልሶ ዳግም ምትታደስ?

Filed in: Amharic