>

ማኅበረ ቅዱሳንና አራቱ ፈታኞች [ዶክተር ተክሉ ኣባተ]

Mahbere kidusan -logoማኅበረ ቅዱሳንን በሚገባ ያወቅሁት የዛሬ 20 ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ የመጀመሪያ ድግሪ ተማሪ እያለሁ ነው። ማኅበሩ ገና በእግሩ ለመቆም ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ። ማኅበረ ቅዱሳን (ከዚህ በኋላ ለማሳጠር ያህል ማቅ ወይም ማኅበሩ እያልኩ እጽፋለሁ) ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ በዩኒቨርስቲው ዋና ግቢ ያሉትን ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በሚገኘው ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ባቋቋሙት ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ጋበዘ ። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ በሰንበት ትምህርት ቤት ተሳታፊ ስለነበርኩና የዕውቀትም ጥማት ስለነበረብኝ የማኅበሩን ግብዣ በታላቅ ደስታ ተቀበልኩት።

ከቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንና ሰንበት ትምህርት ቤቱ ጋር በመተባበር ለኛ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ልዩ መርሐ ግብር ተዘጋጀልን። እንዲያውም ትምህርት አሰጣጡ በደረጃ ሆነ ። ልክ ዩኒቨርስቲው እንደሚያደርገው በባች የተከፋፈለና ተከታታይነት ያለው የጠለቀ ትምህርተ ሃይማኖት ይሰጥ ጀመር ። እኔ ያለሁበት ባች አዳራሹ አይበቃውም ነበር። ቆሞና መሬት ላይ ቁጭ ብሎ የሚማረው ወንበር አግኝቶ  ከሚቀመጠው ይበልጣል። ልክ እንደ መደበኛው ትምህርት ኮስተር ብሎ ማስታወሻ መያዝ የተለመደ ነው ። ስም ቁጥጥርም ማለትም አቴንዳስ ነበረ። እንዲያውም እኔ ራሴ ለረጅም ጊዜ ስም ተቆጣጣሪ ነበርኩ ። አስተማሪዎቻችን ደግሞ በብዛት በወቅቱ የማኅበረ ቅዱሳን ዋናዎቹ ይሁኑ እንጅ ከቅዱስ ማርቆስና ከሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት የሚጋበዙም አባቶችና ወጣት ሰባኪዎች አሉ። አገልግሎት እየሰፋ መጥቶ በየእሑዱ በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ሌላ ተጨማሪ የትምህርት መርሐ ግብር ተዘጋጀልን።

በዚህ ሁኔታ ለአራት ዓመታት ያህል ምንም ሳላቋርጥ በማቅ ተምሬአለሁ ። እንዲሁም ማቅ በየወሩ በቤተ ክህነት አዳራሽ የሚያካሂደውንም ታላቅ ጉባዔ በንቃት ተከታትያለሁ። ይህን ጉባዔ በሚታደመው ህዝብ ብዛትና በጉባዔው በሚገኙ ብፁዓነ ሊቃነ ጳጳሳት ምክንያት በተለዬ ሁኔታ እወደው ነበር። አስታውሱ! ያሁኑን አያድርገውና ያኔ አንድን ጳጳስ በቅርብ ርቀት ማየት መቻል በራሱ እንደ መታደል ይቆጠር ነበር። አሁን ግን ጳጳሳትን ለማየትም ሆነ ለማግኘት ያን ያህል ጉጉት የሚታይ አይመስለኝም።

በአራት ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታዬ መንፈሳዊና ዓለማዊ የዕውቀት ዘርፎችን አጣጥሜ ሄጃለሁ  ። ማቅ የሚያቀርባቸው የሃይማኖት ትምህርቶች የተደራጁና የተናበቡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርም ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ ። አስተማሪዎች በሚያስተምሯቸው ትምህርቶች የጠለቀ ዕውቀት እንዳላቸው ያስታውቃል። ይበልጥ እኔን የሚስበኝ ግን ስለኢትዮጵያና ስለቤተ ክርስቲያን ፍቅር እንዲኖረን የሚያደርጉት ጥረት ነበር ። በፍጹም እምነትና መቆርቆር የኢትዮጵያንና የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ተግዳሮቶች ያስተምራሉ። ይህ ጥረታቸው ፖለቲካዊ ትኩሳት ማቃጠል ለጀመረው የስድስት ኪሎ ተማሪ ልዩ ትርጉም ነበረው። ይህም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች ውስጥ ዋናው ነው ለማለት ያስችላል።

ሌላው ጉዳይ አባልነትን ይመለከታል። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን ማቅ አዘጋጅቶ  ቢያቀርብልንም አባል እንድንሆን አብዝቶ የምንመከረው ግዳጃችን እንደሆነም የሚነገረን ግን በምንኖርበት ወይም በምንሠራበት አጥቢያ ላለ ቤተ ክርስቲያን ነው ። ከዚያም የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆነን እንድንገለገልና እንድናገለግል እንመከራለን ። የማቅ አባል እንድንሆን የተጨቀጨቅንበት ጊዜ የለም ። በመሆኑም ማቅ ማለት በቤተ ክርስቲያን ስር ያለ የወጣቶች  ስብስብ እንደሆነ ብቻ ነበር የምንረዳው ።

ከምረቃ በኋላ በሥራ ዓለም እያለሁ ማቅ ባስተማረኝ መሠረት በአጥቢያዬ ባለ ቤተ ክርስቲያንና ሰንበት ትምህርት ቤት ተመዝግቤ ተገልግያለሁ ። አገልግያለሁም። የማቅ አባል ግን አልነበርኩም ። አይደለሁምም ። ባጠቃላይ ማቅን በደንብ አውቀዋለሁ ማለት እችላለሁ። በተለይም ማቅ ማን እንደሆነና ምን ፣ እንዴት፣ ከማን ጋርም እንደሚሠራ በተጨባጭ ለማየት ችያለሁ።

ከዚህ ተሞክሮዬ በመነሳት ስለማቅ መጻፍ እንዳለብኝ ተሰማኝ ። ለመጻፍ ያነሳሱኝ ዝርዝር ምክንያቶች ግን በርካታ ናቸው። አንደኛ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማቅን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎች በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተለቀዋል። ጽሑፎቹ በተወሰነ ደረጃ አስተማሪ ቢሆኑም የማቅን ሁለንተናዊ ተግዳሮቶች በሚገባ አላሳዩም። ሁለተኛ ጽሑፎቹ ማቅን እነማን እንደሚፈትኑት ተጎጅዎችም እነማን እንደሆኑ በበቂ ሁኔታ አላመላከቱም። ሦስተኛ ጽሑፎቹ ለማቅ ፈተናዎች መቋቋሚያ ስልቶችን በመጠቆም ዙሪያ ውሱንነት አለባቸው ። አራተኛ ከዚህ በፊት ስለማቅ የቀረቡት ጽሑፎች ወገንተኛነት ይንጸባረቅባቸዋል ። ማቅን በሚደግፉ አልያም አብዝተው በሚቃወሙ ሰዎች የተጻፉ ናቸው።  አምስተኛ ከዚህ በፊት ስለማቅ የተጻፉ ጽሑፎች ሁለተኛ የመረጃ ምንጮችን ብቻ ተጠቅመዋል ። ይህ ደግሞ ጉዳዮችን በጥልቀት ለማየት አያስችልም  ። ስድስተኛ በአሁኑ ወቅት ማቅ በኢትዮጵያም በውጭውም ዓለም ለየትና ጠንከር ያሉ አጣብቂኞች ውስጥ ይገኛል   ። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ስለማቅ መጻፍ ወቅታዊ ከመሆኑም ባሻገር አገራዊና ሃይማኖታዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ። አገራችን ኢትዮጵያም ያለችበትን ሥርዓትና ሁኔታ በመጠኑ ያሳየናል።

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ማቅን በቋሚነት የሚፈትኑ ብርቱ አካላት እነማን እንደሆኑና ለምን እንደሚፈትኑት ማብራራት ነው ። ማቅን ለማዳከም ከተቻለም ለማጥፋት በሚደረገው የተቀናጀ ዘመቻ ተጎጅዎች እነማን እንደሆኑም ይህ ጽሑፍ ያመላክታል። በመጨረሻም ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ስለኢትዮጵያ አገራችን ያገባናል የሚሉ አካላት ሊያጤኗቸው የሚገቡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ይጠቁማል ። እንዲሁም በዘርፉ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ሰዎችንም ያነሳሳል።

አንባቢዎቼ ጥቂት ጉዳዮችን እንዲገነዘቡልኝ ግን እፈልጋለሁ ። ይህ ጽሑፍ ማቅንም ሆነ ሌላ አካልን ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ የተዘጋጀ አይደለም ። ያሉ እውነታዎችን ከግል እይታዬ በመነሳት በትንተና መልክ ለአንባቢ ማስገንዘብ እንጅ። ምንም እንኳን በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ ማቅ በብዙ ጥረት ካስተማራቸው ሰዎች አንዱ ብሆንም ይህ ታላቅ ውለታ ሚዛናዊነቴን እንድስት ግን አያደርገኝም  ። ካለኝ መረጃና ግንዛቤ በመነሳት ማቅንም ሆነ ሌሎችን አካላት ያለ ምንም አድሎ ፣ ፍርሃትና ይሉኝታ እሞግታለሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው ግን ለኢትዮጵያ አገሬና ለኦርቶዶክስ ሃይማኖቴ ካለኝ ፍቅር የተነሳ  ብቻ ነው ። አንባቢዎቼም ሲያነቡና ሃሳብ ወይም አስተያየት ሲሰጡ ከዚህ ጉዳይ አንጻር ብቻ  እንዲሆን አሳስባለሁ።

ወደዋናው ቁም ነገር ከመግባቴ በፊት ግን ሁሉም አንባቢዎቼ ማቅን በተመለከተ መጠነኛና ተመሳሳይ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ ስለማቅ ጥቂት ጠቅለል ያሉ ነጥቦችን አነሳለሁ።

ጥቂት ስለማኅበረ ቅዱሳን ማንነት

ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ አባላት ያሉት ማቅ ከሁለት ዓስርት ዓመታት በፊት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና በአባቶች ምክክር እንደተመሰረት ይታወቃል ። ዓላማውም ወጣቱ ትውልድ ሃይማኖቱን በሚገባ ዐውቆ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በመላ ሕይወቱ ራሱንና ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግል ማገዝ ነው ። መተዳደሪያ ደንቡም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆለት በይፋ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ስር አገልግሎቱን ጀመረ። አገልግሎቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ቢያተኩርም ገዳማትን ፣ የተረሱ አብያተ ክርስቲያናትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም ሰንበት ትምህርት ቤቶችንም በማገዝ ይታወቃል ። በሚያሳትማቸው መንፈሳዊ መጽሐፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች እንዲሁም መዝሙሮችና በቋሚነት በሚያዘጋጃቸው ጉባዔዎች የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ይበልጥ ተደራሽ አድርጓል።

አባላቱም በከተሞች፣ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እንዲሁም በአውሮፓ ፣ በሰሜን አሜሪካና በሌላውም ዓለም ሳይቀር በልዩ ሰንሰለት ተዋቅረው በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ እያገለገሉና እየተገለገሉ ይገኛሉ  ። እያንዳንዱ ተራ የሚባል አባል ሳይቀር «በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል!» የሚል መፈክር ይዞ  ይጓዛል ። አባላት ልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ በመግባት በዓመታዊ እቅድ እየተመሩ ሥራቸውን  ያከናውናሉ። የሁሉም ክፍል ሥራ አፈጻጸምና ገንዘብ አጠቃቀም በኦዲትና በቁጥጥር ኮሚቴ ይገመገማል ። አባላት በየጊዜው ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከዋናው ቢሮ ገለጻ ይደረግላቸዋል። መመሪያ ይሰጣቸዋል።

ማኅበሩ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማ ፣ ቀኖናና ትውፊት መጠበቅና ለትውልድ ሳይበረዝ መተላለፍ አብዝቶ ይሠራል ። አምስት ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጎን ካለው ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ በመላው ዓለም ያለውን አገልግሎቱንና አባላቱን ይቆጣጠራል፣ ያስተዳድራል፣ ይመራል።

ዳሩ ግን ማቅ ከምስረታው ጀምሮ ተቃውሞና እንግልት ተለይቶት አያውቅም ። የተለያዩ አካላት የማቅን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር፣ ለማዳከምና ከተቻለም ፈጽሞ ለማጥፋት ይጥራሉ ። እነዚህን አካላት ፈታኝ ብያቸዋለሁ። እንደሚታወቀው ፈተና በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም ሕይወት ብዙ አይወደድም ። ፈታኙ በተፈታኙ ላይ የበላይነት አለው ። ፈተናውን ማቅለል ማክበድም ይችላል ። እንደዚህም ሁሉ ማቅን በተለያዩ መንገዶች የሚያስጨንቁ የተለያዩ አካላት አሉ። እነዚህ አካላት እነማን ናቸው? ማቅን የሚያስጨንቁበት መሠረታዊው ምክንያትስ ምንድን ነው? በዚህ በማስጨነቁ ሂደት የሚጎዳው ማቅ ብቻ ነውን? ለመሆኑ ማቅ ለኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ጠቃሚ ነው? ፈተናዎችን ለማለፍስ ከማቅ እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ምን ይጠበቃል?

ይቀጥላል!

 

 

Filed in: Amharic