>

ጋዜጠኛ አበበ ገላው የኢሳት አለም-አቀፍ ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ

Abebe Gelaw G8 meeting(ኢሳት ዜና) — የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ቦርድ ለኢሳት አለም-አቀፍ አዲስ ዳይሬክተር መሾሙን ይፋ አደረገ። የቀድሞውን የኢሳት አለም አቀፍ ዳይሬክተር አቶ ነዓምን ዘለቀ በክብርና በምስጋና የሸኘው የኢሳት ቦርድ ጋዜጠኛ አበበ ገላው የኢሳት አለም አቀፍ ዳይሬክተር እንደሆነ ከኤፕሪል 1 ፥ 2016 ጀምሮ መሾሙን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በካሊፎርኒያ ግዛት ሲልከን ቫሊ የሚገኘው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከኢሳት አስተዳደር ቦርድ በተሰጠው ሹመት መሰረት በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዋሽንግተን በመምጣት ሙሉ ጊዜውን በኢሳት ውስጥ እንደሚሰራም ለመረዳት ተችሏል።

እኤአ ከ2011 ጀምሮ እስከ 2013 በኢሳት ውስጥ ሲያገለግል የነበረው ጋዜጠና አበበ ገላው፣ ላለፉት 3 ሳምንታት ካሊፎርኒያ ግዛት ሲልከንቫሊ በሚገኝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል።

የኢሳት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ነዓምን ዘለቀ ሙሉ ጊዚያቸውን በኢሳት ውስጥ ለማሳለፍ በስራ መደራረብ ሳቢያ ባለመቻላቸው አዲስ ዳይሬክተር ሲያፈላልግ የቆየው የኢሳት ቦርድ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከተገመገሙ ዕጩዎች ውስጥ ለቦታው ብቁ ሆኖ በመገኘቱ በዳይሬክተርነት መሾሙን አስታውቀዋል።

ቦርዱ ኢሳትን በዳይሬክተርነት ለረጅም ዓመታት ለመሩት ለአቶ ነዓምን ዘለቀ እንዲሁም ካለበት ተደራራቢ ሃላፊነቶች በተጨማሪ የኢሳትን ዳይሬክተርነት በተጠባባቂነት ለወራት ሲመራ ለቆየው ለአክቲቪስት ታማኝ በየነ ምስጋናውን አቅርቧል።

Filed in: Amharic