>
5:13 pm - Monday April 20, 5514

የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስብሰባ [ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም]

(ይህ ጽሑፍ ሪፖርተር ጋዜጣ በጻፈው ግምገማ ላይ የተመሠረተ ነው፤ የምጠቅሰው ሁሉ ከዚያው ነው፤ ብዙ ቪድዮዎችን ለማየት ሞክሬ አፈናው ከባድ ስለሆነ አልቻልሁም፡፡)

profeser Mesfen Weldemariam Quateroአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሥልጣን ውጭ ያሉ ሰዎችን ሰብስቦ ለማነጋገር የመወሰኑን ሀሳብ መንፈስ ቅዱስ ሹክ ያለው ይመስላል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስና በኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሀከል ጣልቃ የገባና መልእክቱን የለወጠው ኃይል አለ፤ ‹‹በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት — ስለኢትዮጵያ ሕዳሴ›› መነጋገር የሚለው ሀሳብ በመሠረቱ ጠቃሚና ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ሆኖም ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸውና የሚያገባቸው ‹‹ምሁራን›› ብቻ ናቸው የሚል ቅዠት የለኝም፤ በተለይ ምሁራን ማለት ‹‹እኛው … ነን›› እንዳለው ከሆነ!

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር ሁሉ እያለቀሱ የሚኖሩት  ምሁራን አይደሉም፤ ችግሩን በትክክል ሳይረዱ ስለመፍትሔ ማሰብ የጉልበተኞች መንገድ መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን፤ መፍትሔ የሚፈልግ ሰው ሰብስቦ ማነጋገር የሚያስፈልገው ችግሩ በየዕለቱ የሚገርፋቸውን የሚወክሉ ሰዎችን ነው፤ የተወሰኑ ምሁራን ለመፍትሔው ስለሚያስፈልጉ በታዛቢነት ቢኖሩ ጥሩ ነው፤ እንደዚያም ሆኖ ችግሩን የሚናገሩ ሰዎች ከፍርሃት ነጻ የሚሆኑበት መድረክ መኖሩን ማረጋገጥ ያሻል፡፡

አሁን አቶ ኃይለ ማርያም ያደረገው ስብሰባ ከጥቂት ዓመታት በፊት መለስ ዜናዊ ካደረገው እምብዛም የተለየ አይደለም፤ የመለስም ሆነ የኃይለ ማርያም ዓላማ ከሥልጣን ውጭ ከሆኑ ዜጎች ጋር በአገር ጉዳይ ላይ ለመመካከር፣ ለመከራከር፣ ለመወያየትና ወደስምምነት ላይ ለመድረስ አይደለም፤ በእንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ውስጥ ይህ ሊሆን አይችልም፤ ጉልበተኞቹ እንደተለመደው የሚፈልጉት ሀሳባቸውን በጉልበት ለማጽደቅ ነው፤ ከተጋበዙት መሀከል አንድ ሰው ተነሥቶ ጋዜጠኞችን ሁሉ አስራችሁ፣ ጋዜጦቹን ሁሉ አግዳችሁ፣ የተለያዩ ድርጅቶች ሕዝቡን እየሰበሰቡ እንዳያወያዩ እየከለከላችሁ፣ የሃይማኖት መሪዎች እንኳን በነጻነት እንዳይሠሩ እያደረጋችሁ እኛን የመረጣችሁን እንድትነግሩን ነው? ወይስ እንድንነግራችሁና ነገ ቃሊቲ እንድንገባ ነው? ብሎ ቢጠይቅ መጋረጃው ይቀደድ ነበር፤ ይህ ጥያቄ ወይም አስተያየት ከተሰብሳቢው ቢሰነዘር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ‹‹ፖሊቲከኛው ጥግ ጥጉን ይዞ ከመታኮስ ባለፈ … ዴሞክራሲያዊ ባህል ማዳበር እንዳቃተው …›› ብሎ መናገር አይደፍርም ነበር፤ ‹‹ፖሊቲከኛ›› የተባለውን መተኮስ ያስተማረው ማነው? ተብሎ ቢጠየቅ ምን ይመልሳል፤ መለስ ዜናዊን ጠይቄው ነበር፤ ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው›› ነው ያለው!

እዚያ ለተሰበሰቡት ‹‹ምሁራን›› ፖሊቲከኛው ‹ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር› አቅቶታል ሲል መልስ ተሰጥቶት እንደሆነ አላውቅም፤ ካልተሰጠው ግን የያዘው ሰይፍ ግለቱ ‹ምሁራኑን› እንዳቀለጣቸው ሌላ ማስረጃ አያስፈልግም፤ ሀሳብን የመግለጽን ነጻነት፣ የመደራጀትን፣ የመሰብሰብን፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን በማይቻልበት፣ በፖሊቲካው ቀርቶ በሃይማኖትም በኩል ሰዎች በነጻነት መወያየትና መሪዎቻቸውን የመምረጥ መብት ተነጥቀው ባለበት አገር ጩኸቴን ቀሙኝ እንደሚባለው ምንም ሥልጣን የሌላቸውን የተቀናቃኝ ክፍል ፖሊቲከኞች የዴሞክራሲ ባህል አላዳበሩም ብሎ ለመውቀስ የሚችልበት መድረክ በእርግጥ ‹የምሁራን› ሊሆን አይችልም፤ አቶ ኃይለ ማርያም የበዳይ ወቃሽ በመሆኑ ላይ ይገፋበታል፤ ‹‹ዓመጽ የማይቀሰቅስ የሀሳብ ብዝኃነት እንዴት ነው እዚህ አገር መፍጠር የሚቻለው?›› ብሎ ይጠይቃል፤ በአዳራሹ ውስጥ የተሰበሰቡት ሁሉ በአንድ ላይ ‹‹በነጻነት!›› ብለው ቢጮሁ ያስተምሩት ነበር፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም አያይዞም ‹‹የሀሳብ ልዩነት ብዙ አያስፈራንም፤ የሚገለጹበት መንገድ ነው የሚያስፈራው››፣ ‹‹ከኋላ ጦር አሰልፎ ከፊት በሀሳብ ልፋለም .. የሚለው ነው ያስቸገረን፤›› ተቀናቃኞቹ ጦር እንዳላቸው አግአዚ ይመስክር!

አቶ ኃይለ ማርያም ‹‹በአንድ ትውልድ የተጣመመ የፖሊቲካ ባህል ተሸክመን ቁርሾን ለዚህ ትውልድ እያስተላለፍን ነው፤›› ያለው እውነት አለበት፤ እሱ በዚያ ‹‹የተጣመመ የፖሊቲካ ባህል›› ባመጣው ትውልድ ውስጥ ነበረ? ነበረም አልነበረም ዛሬ እሱ የሚያገለግለው ያንን ትውልድ እንደሆነ የተገነዘበ አይመስለኝም፡፡

በአቶ ኃይለ ማርያም ንግግር ውስጥ የሚያስገርመውና ግራ የሚያጋባው ጣል አድርጎ ያለፋት አንዲት ዓረፍተ ነገር ነች፡– ‹‹አንድ ትልቅ ነጋዴ የራሱ እስር ቤት አለው ቢባል ታምናላችሁ?›› ማመን የሚያስቸግረኝ አንድ የትልቅ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን መናገሩ እንጂ በጉልበተኞች አገር አንድ ጉልበተኛ የራሱ እስር ቤት ቢኖረው ምን ያስደንቃል!

የሪፖርተር አንባቢዎች በሰጡት አስተያየት፡—

6 ከመቶ የሚሆኑት ተደስተዋል፤

4 ከመቶ           አልተደሰቱም፤

71 ከመቶ          የተሻለ የሚፈልግ፤

በሪፖርተር መረጃ መሠረት የአቶ ኃይለ ማርያም ስብሰባ የራሱን ተከታዮች እንኳን በከፊልም ያላስደሰተ ይመስላል፤ ምናልባት የመንፈስ ቅዱስን ሹክታ አክብሮ እንደገና እንዲያስብበት ይርዳው፡፡

Filed in: Amharic