>
5:13 pm - Tuesday April 19, 4140

ጆሮና ቀንድ [ዲያቆን ዳንኤል ክብረት]

Daniel_Kibret.አንድ ጥጃ የሚያሳድግ ሰው ነበር፡፡ ጥጃውን ሲፈልግ ጆሮውን ይጎትተዋል፣ ሲፈልግ በዱላ ይዠልጠዋል፣ ሲፈልግ ጨው እያላሰ ይስበዋል፣ ሲፈልግ ደግሞ በገመድ አሥሮ ያስከትለዋል፡፡ በዚህ መንገድ ሄዶ ጥጃው አደገና ወይፈን ሆኖ ቀንድ አበቀለ፡፡ የጥጃውም ባለቤት እንደለመደው በዱላ ሊመታው፣ ጆሮውን ሊጎትተው፣ በዱላም ሊዠልጠው ተነሣ፡፡ ያን ጊዜ ጥጃው አፍንጫውን ወደ መሬት አስነክቶ አኩረፈረፈና እንደ ስፔን በሬ ተወርውሮ በቀንዱ ወጋው፡፡ ሰውየውም ወገቡን ይዞ እየተጎተተ ቤቱ ደረሰ፡፡
ታሞ ሊጠይቁት የሄዱ ጎረቤቱ የሆነው ነገር ሰሙና ‹ወዳጄ የጆሮና የቀንድን ዘመን እንዴት መለየት አቃተህ?› አሉት፡፡ ‹የጆሮና የቀንድ ዘመን ምንድን ነው?› አላቸው ወገቡን አሥሮ እየተገላበጠ፡፡ ‹በመጀመሪያ የበቀለን ጆሮ በኋላ የመጣ ቀንድ በለጠው› ሲባል አልሰማህም፡፡ ጥጃው መጀመሪያ ጆሮ ብቻ ስለነበረው ያልከውን ሁሉ ይሰማህ፣ ይታዘዝህ ነበር፤ ብትመታው ይችላል፣ ብትጎትተው ይከተላል፣ ብታሥረው ይታሠራል፡፡ ጆሮ ብቻ ስለነበረው መስማት ብቻ ነበር የሚችለው፡፡ በኋላ ግን ቀንድ አበቀለ፡፡ ቀንድ ካበቀለ በኋላ እንደ ድሮው እጎትተዋለሁ ብትል አይሆንም፡፡ አሁን ከተስማማው ይቀበልሃል፤ ካልተስማማው ግን መዋጋት ይጀምራል፡፡ አሁን አንተ ያደረግከውን ማድረግ የሚቻለው በጆሮ ዘመን ነው፡፡ በቀንድ ዘመን እንደዚህ ማድረግ ሞኝነት ነው፡፡
ሁሉም ነገር የጆሮና የቀንድ ዘመን አለው፡፡ በሀገራችን አንድ መንግሥት ሲተከል ሕዝቡ የጆሮ ዘመን ይሰጠዋል፡፡ ዝም ይላል፣ ይሰማል፣ ይቀበላል፤ አልጋው እንዲረጋ፣ ዙፋኑ እንደዲጸና ይተጋል፤ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬም ነገ ይሻላል ብሎ በተስፋ ይጠብቃል፡፡ ባያምንም ይቀበላል፤ ባይስማማም ይተባበራል፤ ባይግባባም አብሮ ይሠራል፡፡ ይሄ የጆሮ ዘመን ነው፡፡ ብልህ መሪ ከጆሮ ዘመን በኋላ የቀንድ ዘመን እንደሚመጣ ያውቃል፡፡ ስለዚህም ሥርዓት ሠርቶ፣ ሕግ አጽንቶ፣ አገር አልምቶ፣ ሕዝብን አስማምቶ ይጠብቃል፡፡ በጆሮ ዘመን ያልሠራውን ሥራ በቀንድ ዘመን እሠራለሁ ቢል የሚያምነው የለም፡፡ እንደ ቀድሞው ዝም ብሎ የሚሰማ፣ አሜን ብሎ የሚቀበል፣ እሺ ብሎ የሚከተል፣ ጎንበስ ብሎ የሚጎተት አይገኝም፡፡ ለተስማማው ጆሮውን ላልተስማማው ቀንዱን ያቀርባል፡፡ ሥራውን በግድ ብተትሠራ እንኳን ትግሉ ብዙ ነው፡፡ ሕዝብ ቀንድ ከማብቀሉ በፊት እንደ ቀንዱ ዘመን ማድረግ እንደማይቻለው ሁሉ፣ ቀንድ ካበቀለ በኋላም እንደ ጆሮው ዘመን ማድረግ አይቻልም፡፡ ራሱ ቀንድ አብቃዩም እንደ ድሮው ልሁን ቢል እሺ አይለውም፡፡ ያላወቁትን እንዳላወቁ፤ ያልሰሙትን እንዳልሰሙ፣ ያላዩትን እንዳላ፣ ያልደረሱበትን እንዳልደረሱ መሆን አይቻልም፡፡ ለውጥን ፈልገህው ብቻ አታመጣውም የቀንድ ዘመን ሲሆን ሳትፈልግም ትለወጣለህ፡፡
አገር ብቻ ሳይሆን ድርጅት፣ ማኅበር፣ ፓርቲና ተቋምም ቀንድ ያበቅላሉ፡፡ በጆሮ ዘመን አባሉ ሁሉ ይሰማሃል፤ ትእዛዝ ከበላይ እግር ወደላይ ብሎ ያምናል፡፡ አንድ ቦታ የበሰለውን በልቶ፣ አንድ ቦታ የተጠመቀውን ጠጥቶ፣ የተባለውን ሁሉ ሰምቶ፣ ውደድ የተባለውን ወድዶ ጥላ የተባለውን ጠልቶ ይኖራል፡፡ በአንድ ዓላማ የተመመ፤ በአንድ አቋም የቆመ፤ አንድ ግብ የጨበጠ፤ በአንድ መመሥመር የሠለጠ የሚመስልበት የጆሮ ዘመን አለው፡፡ እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ አንድ ሆኖ ተካክሎ የሚታይበት፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ የሚመስልበት ዘመን አለ፤ያኔ አባሉና አካሉ የተግባባና የተስማማ የመሰለው ተግባብቶና ተስማምቶ ብቻ አይደለም፡፡ ጊዜው የጆሮ ጊዜ ስለሆነ ነው እንጂ፡፡
የቀንዱ ዘመን ሲመጣ ጠያቂ፣ መርማሪ፣ ተከራካሪ፣ ሞጋች ተች፣ ይበዛል፡፡ በፊት የጣመው አሁን ይመረዋል፤ በፊት ያስደሰተው አሁን ያስከፋዋል፤ በፊት ዝም ያለው አሁን ያስጮኸዋል፣ በፊት የታገሠውን አሁን ይሰለቸዋል፡፡ በፊት የፈራውን አሁን ይደፍረዋል፡፡ በፊት የተወውን አሁን ያነሣዋል፡፡ ‹ቀኝ ኋላ ዙር› ስለተባለ ብቻ አይዞርም፡፡፡ አባል ስለሆነ ብቻ የድርጅቱን ነገር ሁሉ አይቀበልም፡፡ መለኮታውያን ናቸው ያላቸውን መሪዎቹን ሰው አድርጎ መመልከት ይጀምራል፡፡ ላመነው ነገር እንኳ ቢሆን ተጨማሪ ማስረጃ ይፈልጋል፡፡ የጥንቱን ትርክት ብትተርክ፣ የጥንቱን ዘፈን ብትዘፍን፣ የጥንቱን ፉከራ ብትፎክር እንደ ሞኝ ይቆጥርሃል፡:፡ ያ ሁሉ የጆሮ ዘመን ታሪክ ነውና፡፡ በዚህ ጊዜ ለምን እንደ ጥንቱ ጆሮውን ስንጎትተው አልተጎተልንም፣ ስንመታው ለምን አልሄደም፣ ስንስበው ለምን አልተሳበም፤ ስንቆነጥጠው ለምን አልተቆነጠጠም ብለው የሚያስቡ ዘመንን ማንበብ የማይችሉ ናቸው፡፡ አሁን የቀንድ ዘመን ነው፡፡ የጆሮ ጊዜ አልፏል፤ ማሳመን ማግባባት፣ ማስረዳት፣ ይፈልጋል፡፡ መስማት ብቻ ሳይሆን መሰማትም ይሻል፡፡
እርጅና በየዘመኑ ነው፡፡ ልጅነት በዘመኑ ያረጃል፤ ወጣትነትም በጊዜው ይጠወልጋል፤ ድርጅትና ማኅበር፤ ተቋምና ፓርቲ በዘመናቸው ያረጃሉ፡፡ ብልህ እንደ ንሥር ያድሳቸዋል፡፡ እንደ እባብ ቆዳ ለዘመኑ የሚመጥን ልብስ ያለብሳቸዋል፡፡ በጆሮ ዘመን የሠሩበትን በቀንድ ዘመን እንሠራበት አይሉም፡፡ እባብ ያድግና ቆዳው አላላውስ ሲለው ቆዳውን ገሽልጦ ጥሎ ለዕድገቱ የሚስማማ ቆዳ ይለብሳል፡፡ ድርጅትና ፓርቲም እንዲህ ካልሆኑ እርጅናው ሞትን ያመጣል፡፡ የጆሮ ዘመን ሲያረጅ ለቀንዱ ዘመን ተዘጋጅ፡፡
ቤተ እምነቶች በዘመናችን ያልተረዱት ቁም ነገር ይሄ ነው፡፡ አንተ ምእመን ነህ ዝም ብለህ ገንዘብህን ስጥ፣ የምንልህን ብቻ ተቀበል፣ ለምን? የት? መቼ? እንዴት? ብለህ አትጠይቅ፤ አባቶችህ ከአንተ በላይ ያውቃሉ፤ አገልጋዮቹ ከአንተ ይሻላሉ፤ አትከራከር፣ ቁጣ፣ መቅሰፍት፣ መዓት ይወርድብሃል፣ ስለተባለ ብቻ የሚቀበልበት የጆሮ ዘመን አልፏል፡፡ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሰጠው ገንዘብ የት እንደዋለ ማወቅም ይፈልጋል፤ አባቶቹን ማክበር ብቻ ሳይሆን ክብራቸውን ሲጠብቁ ማየትም ይፈልጋል፤ የሚባለውን መስማት ብቻ ሳይሆን ለሚባለው ነገር ማስረጃም ይሻል፤ ይመዝናል፤ ያመዛዝናል፤ የጥንቱን ከዛሬው፣ ድርጊቱን ከሕጉ ያመሳክራል፤ በሕጋዊው ቤት ሕገ ወጥነት፣ በመንፈሳዊው ቤት ዓለማዊነት፣ በእግዚአብሔር ቤት ቄሣር፣ በጽድቁ ቤት ርኩሰት ሲሠለጥን እያየ ዝም የሚልበት የጆሮ ዘመን አልፏል፤ አሁን የቀንድ ጊዜ ነው፡፡
ተገለጠልኝ፣ ታየኝ፣ በራልኝ፣ ወረደልኝ፣ ፈለቀልኝ፣ ሰማይ ደርሼ መጣሁ፤ አሥር ሺ ሰይጣን አወጣሁ ስላልክ ብቻ የሚቀበልበት የጆሮ ዘመን አልፏል፡፡ ይመዝነዋል፣ ይፈትነዋል፤ ያነጥረዋል፣ ያበጥረዋል፡፡ ‹ኩሎ አመክሩ ወዘሠናየ ግበሩ› ነውና የተባለው፡፡ ከቻለ ይሞግትሃል፤ ካልቻለ ትቶህ ይሄዳል፡፡ ዝም ብለህ ተቀበል የሚባልበት የጆሮ ዘመን አሁን የለም፡፡ እንደ ጆሮው ዘመን ወደፈለግከው አዳራሽና ጸሎት ቤት፣ ወደፈለግከው የራእይና የተአምራት ቦታ አትጎትተውም፡፡ አሁን አልሄድም ብሎ ሊወጋህም ይችላል፡፡ በዚህ ዘመን በየቤተ እምነቱ በምእመናኑና በእምነት አለቆች መካከል የምናየው ውጊያ ይሄ ነው፡፡ ወደፈለግነው አቅጣጫ እንጎትታለን በሚሉ የጆሮ ዘመን አለቆችና ‹ቀንዴ ከፍ ከፍ አለ› በሚሉ ቀንድ ባበቀሉ ምእመናን መካከል፡፡
ድርጅትህን ስትመሠርተው ልጅ ስለነበር እንደፈለግክ ታደርገው ይሆናል፡፡ እየሰፋ፣ እያደገ፣ እየተለጠጠ፣ እየታወቀና እየሠለጠነ ሲሄድ ግን ከጆሮው ዘመን አልፎ የቀንዱ ዘመን ላይ ይደርሳል፡፡አንተ ድርጅቱን መምራት ብቻ ሳይሆን ድርጅቱም አንተን ሊወጋህም ይችላል፡፡ ብዙዎች በገዛ ድርጅታቸው ቀንድ ተወግተው ታሥረዋል፣ ከሥረዋል፣ ጠፍተዋል፣ በሽተኞች ሆነዋል፡፡ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፤ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ብልህ ነጋዴ በጆሮው ዘመን ቀድሞ ያስባል፡፡ እንደ ጥንቱ እመራዋለሁ፣ አስተዳድረዋለሁ፣ እኔ እበቃዋለሁ፣ ለዚህ ደግሞ መቼ አንሳለሁ አይልም፡፡ የልጅነቱን ልብስ አሁን ልልበስ እንደማይለው ሁሉ የጥንቱን አሠራር አሁን ልከተል አይልም፡፡ ለቀንዱ ዘመን የሚመጥን አሠራር፣ ሥርዓት፣ አስተዳደር፣ ባለሞያ፣ ሕግ፣ አደረጃጀት፣ የደረጃ ምጣኔና አስተሳሰብን ይገነባል እንጂ፡፡
በሀገራችን ዘመን ተሻግሮ ከልጅ ልጅ የሚተርፍ ድርጅት ያጣነው፣ ባለቤቶቹ ድርጅቱን በጆሮው ዘመን አስተሳሰብ በቀንዱ ዘመን እንምራው ስለሚሉ ነው፡፡፡ ድርጅቱ አድጎ አድጎ ከዐቅማቸው በበላይ ይሆንና ያሳደገው አውሬ እንደሚበላው አዳኝ ያሳደጉት ድርጅት እነርሱንም ይበላቸዋል፡፡ ስንት ዘመን መርቼው፣ ድንጋይ ጥዬ መሥርቼው፣ ላቤን ጠብ አድርጌ እዚህ አድርሼው ማለቱ አይጠቅምም፡፡ ያ የጆሮ ዘመን ነውና፡፡

Filed in: Amharic