>

የስድስት ሰዓት ሴት ተጠያቂዎች [በማሕሌት ፋንታሁን]

ጥቂት ስለ ቃሊቲ የሴቶች መቆያ እና ማረሚያ ቤት

Ethiopia-Woman-Prisoners. -Mahilet Fantahunየማይቻል ነገር እንደሌለ በተግባር ለማየት ከሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዱ የእስር ቤት ሕይወት ነው። እስር ቤት እንገባለን የሚል እሳቤ በአይምሯችን ውስጥ ስለማይኖር በአብዛኛው ከተለመደው የኑሮ ዑደት (መወለድ፣ ማደግ፣ መማር፣ መሥራት፣ ማግባት፣ መውለድ፣ ማደርጀት እና መሞት) እና ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተን ነው የግል አቋማችንን የምንቀርፀው። “ከሰው ጋር መተኛት አልወድም/አልችልም፤ እንቅልፍ አይወስደኝም”፣ “ስፕሪስ ሳልጠጣ መዋል አልችልም”፣ “የቀዘቀዘ ምግብ አልወድም”፣ “ሲጃራ ሳላጨስ መኖር አልችልም”፣ “በቀን ቢያንስ ሁለት ፊልሞችን ካላየሁ አልደሰትም”፣ “እከሊትን/እከሌን ሳላይ መዋል አልችልም”፣ “ጨለምለም ካላለ ወደ ቤት መግባት አልወድም”፣ “መብራት ካልጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም” እና የመሳሰሉ የማይለወጡ የሚመስሉን አቋሞቻችን ፈተና ውስጥ የሚወድቁት የእስር ሕይወትን ‹ሀ› ብለን ስንጀምር ነው። ብዙ አልችልም ብዬ የማስባቸውን ነገሮችን ችዬ ስለወጣሁበት ስለ ቃሊቲ የሴት እስረኞች ግቢ ጥቂት ልበላችሁ።

በቃሊቲ እስር ቤት ግቢ ውስጥ ከሚገኙት 8 ዞኖች ሁለቱ የሴት እስረኞች የሚኖሩበት ነው። በአንደኛው ዞን በቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሴቶች በሌላኛው ደግሞ የተፈረደባቸው ሴቶች ይኖሩበታል። ልዩ ጥበቃ ወይም የቅጣት ቤት የሚባሉ ቤቶች አሉ። ወይም በተፈለገበት ሰዓት ይሠራሉ። ለምሳሌ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከማንም እስረኛ ጋር እንዳትገናኝ 5ት ሰው ብቻ የሚኖርበት የቅጣት ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው። ISISን በመቃወም ከተጠራው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ሚያዚያ ወር 2007 የታሰሩ ሴቶች ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ ለብቻቸው በተሠራላቸው ቤት ይኖሩ ነበር።
በቀጠሮ ዞን ደግሞ 5 ቤቶች ያሉ ሲሆን በፍርደኛ ግቢ 6 ቤቶች አሉ።አንድ ቤት ውስጥ ከ 40 እስከ 120 እስረኞች ይኖራሉ። ቀጠሮ ግቢ ከአንዲት አነስተኛ ሱቅ በስተቀር ሌላ ምንም ስለሌለ የተለያዩ ነገሮችን ለመገበያየት እና ፀጉር ቤት ለመጠቀም ፍርደኛ ግቢ መሄድ ግድ ይላል። ቤተሰብ መጠየቂያ ቦታው የፍርደኛ ግቢን አቋርጦ የሚገኝ ቦታ በመሆኑ፤ በቤተሰብ መጠየቂያ ሰዓቶች (ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2:30 እስከ 6:00 ከሰዓት ከ7:30 እስከ 10:00 እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ከ2:30 እስከ 6:00)፤ ቀጠሮ ክልል የሚገኙ እስረኞች ከፍርደኛ ክልል ማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ይችላሉ። በቀጠሮ እና ፍርደኛ ክልል መሐል 200 ሜትር ገደማ ርቀት ያለው ሲሆን በየግቢዎቹ በር እና ማማዎች ላይ ጠባቂ ፓሊሶች አሉ። ዞኖቹ (ቤቶቹ) ከአስተዳደር ጀምሮ በእስረኞች በተመረጡ የእስረኛ ኮሚቴዎች ይመራል። በየቤቱ ለሊት የሚደረግ ጥበቃ አለ። ሮንድ ይባላል። እያንዳንዷ እስረኛ ተራዋ በደረሰ ቀን ለሁለት ሰዓት ከሌላ አንድ እስረኛው ጋር ይጠብቃል። ከለሊቱ 5:00 ሰዓት እስከ 7:00 እና ከ7:00 ሰዓት እስከ 9:00 ሮንድ ተረኞች የሚጠብቁበት ሰዓት ነው። የእስረኞች ቆጠራ በቀን ሁለቴ ይካሄዳል። የጠዋት ገቢ ፓሊሶች ከጠዋቱ 12:00 ላይ፤ 11:30 ላይ ደግሞ የማታ ገቢ ፓሊሶች ቆጥረው ይረከባሉ።
የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች
ከላይ የጠቀስኳቸው የእስረኛ “መብቶች” እኛ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ጋር ሲደርስ ቅንጦት ይሆናሉ። እንኳን በውናችን በሕልማችንም አናስበውም። “ይቺም ቂጥ ሆና ለሁለት ተከፈለች” ዓይነት ነገር ነው። ያም መብት ተብሎ ተሸራርፎ ሲሰጠን እና ስንከለከል “All animals are equal but some are more equal” የሚለው አባባል ትዝ ይለኛል። የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ማለት በሽብር ወይም በአመፅ ማነሳሳት የሚል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በቀጠሮ ክልል ሆነው የሚከታተሉ ወይም ተፈርዶባቸው ፍርደኛ ክልል ያሉ ሴቶች ማለት ናቸው። ስያሜው የመጣው ከቤተሰብ ጋር ከምንገናኝበት ሰዓት የተወሰደ ነው። የምንጠየቀው 6 ሰዓት ላይ ብቻ ሲሆን እኔ በቆየሁባቸው ጊዜያት ከ10 ደቂቃ እስከ 30 ደቂቃ ለሚሆን ቅፅበት ነበር። የመጀመሪያዎቹ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ለ5 ደቂቃ ብቻ ይገናኙ እነደነበር ሰምቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪም የምንጠየቀው በቅርብ ቤተሰቦች ብቻ ነው። ያለንበት ዞንም ሆነ ቤት በኮሚቴነት መመረጥም መምረጥም አንችልም። ሮንድ ጥበቃ እኛን አያካትትም። ፍርደኛ ግቢ ሄዶ መገበያየት ይናፍቀናል። ቢበዛ የ6 ሰዓት ተጠያቂ ያልሆነ (ኖርማል) እስረኛ እንድንልክ ቢፈቀድልን ነው። ሆኖም ግን አስጠጪ እስረኞች ሰበብ ፈልገው የሚላኩትን ኖርማል እስረኞች ለአሸባሪ ይላላካሉ የሚል ክስ ስለሚያቀርቡባቸው፤ የሚላክልን ማግኘት እስቸጋሪ ነው።
Ethiopia-Woman-Prisoners. -Mahilet Fantahunክሊኒክ እና ፀጉር ቤት ለመሄድ ስንፈልግ ለብቻችን አጃቢ ተመድቦልን ነው። የምትመደብልን አጃቢ ፀጉር ቤት ውስጥ ገብታ ተሰርተን እስክንጨርስ ጠብቃ ይዛን ትመለሳለች። ይሄ ሲገርመን የሆነ ጊዜ ላይ ፓሊሶች የሚሰሩበት ፀጉር ቤት እንድንጠቀም መመሪያ ተላለፈ። ይህ መመሪያ ከተላለፈ በኋላ የሆነ ቀን ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ፀጉር ቤት ለመሄድ ጠይቃ፤ አጃቢዋ እየወሰደቻት የተላለፈውን መመሪያ ስትነግራት “እኔ እስረኛ ነኝ። ለምንድነው የፓሊስ ፀጉር ቤት የምሰራው? ይቀራል እንጂ!” ብላ ፀጉሯን መሠራቱን ትታ ተመለሰች። እስክትወጣ ድረስም በአቋሟ እንደፀናች ነበር። ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬም የሚደርስብንን መገለል በመቃወም ፀጉሯን በመላጨት መልዕክት አስተላልፋአለች።
ስድስት ሰዓት ላይ ቤተሰብ ልንጠይቅ ስንወጣ እና ስንገባ በአጃቢ ነው። ቤተሰብ ስናወራም የምናወራውን የሚሰሙ ከኛም ከቤተሰባችንም በኩል ፓሊሶች ይቆማሉ። ቤተሰብ ለማገናኘት ከሚወስዱን አጃቢ ፓሊሶች በማይሰሙት ቋንቋ ከቤተሰብ ጋር ማውራት አይቻልም። ከግቢያችን ስንወጣም ሆነ ወደ ግቢያችን ስንገባ ከኖርማል እስረኞች በተለየ ብርበራ ይካሄድብናል። ቤተሰብ ልንገናኝ ስንሄድ ፍርደኛ ክልል ያሉ የሚያቁን እስረኞችን ጋር በዓይን እንኳን ሰላም መባባል አይቻልም። እነሱም ሰላም ካሉን የተለያየ ቅጣት ይደርስባቸዋል። እኛ በምናልፍበት ሰዓት ከቤት እንዳይወጡ መከልከል፣ በካቴና መታሰር እና በአጃቢ መንቀሳቀስ የተለመዱት ዓይነት ቅጣቶች ናቸው። ባስ ሲልም እስከ አመክሮ መከልከል ይደርሳል። ማንኛውም ዓይነት ጽሑፍ የተጻፈባቸው ማስታወሻ ደብተሮቻችን በፍተሻ ወቅት ይወሰዳሉ። ፍተሻዎች እኛ ላይ እና ከኛ ጋር ይቀራረባሉ የሚባሉ እስረኞች ላይ ይበረታል። በፍተሻ ወቅት እራሳቸው ሳንሱር አድርገው ያስገቡት መጽሐፍ ሳይቀር ይወሰድብናል። መጽሐፍት ሳንሱር ሰበብ እንዳይገቡ/እንዲመለሱ ይደረጋል። ከሚገቡልን መጽሐፍት የሚመለሱት ይበልጡ ነበር። ሌሎች እስረኞችን በማይመለከት “ሕግ” በመተዳደራችን የተነሳም፤ በእስረኞችም ሆነ በፓሊሶች ዘንድ እንደ ልዩ ፍጡር ነው የምንታየው።
ቤተሰቦቻችንም ሊጠይቁን ሲመጡ የሚደርስባቸው እንግልት ከሁሉ የከፋ ነው። እኛ እስረኞች በመሆናችን የመጠየቂያ ሰዓታችን መቼም ሆነ መቼ ለውጥ የለውም። ጠያቂዎቻችን ግን ከ6 ሰዓት በፊት ግቢ ውስጥ መድረስ አለባቸው። አንድ ደቂቃ እንኳን አሳልፈው በር ላይ ቢደርሱ የሚሰማቸው የለም። በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቻችን በር ደርሰው ሳያዩን የሚመለሱባቸው ቀናት ጥቂት አይደሉም። በ6ሰዓት ተጠያቂዎች እና ጠያቂዎች ላይ የሚደርሰው በደል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
በሕገ መንግሥታችን አንቀፅ 21 ላይ በጥበቃ ስር እና ተፈርዶባቸው በእስር ስላሉ ሰዎች መብት ሲያስቀምጥ ምንም አይነት ልዩነት አላስቀመጠም። ወንዶች ጋር ከታዋቂ ጋዜጠኞች፣ የፓርቲ አመራራት እና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በስተቀር የስድስት ሰዓት ተጠያቂ የሚባል ነገር የለም። ከተመሳሳይ ወንጀል ከተከሰሱ/ከተፈረደባቸው ወንዶች ጋር እንኳን በእኩል አይደለም እንታይ የነበረው። በዚህም በሕገመንግስቱ አንቀፅ 35 የተደነገገውን የሴቶች ከወንዶች ዕኩል የመታየት መብት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር መጣሱን ማየት ይቻላል። እነዚህ በሕገ መንግሥት የተደነገጉ መብቶች፤ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር እየተጣሰ እንዳለ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ብናሰማም ተገቢውን ምላሽ አናገኝም። ወይ በማረሚያ ቤት አስተዳደር ጉዳይ አያገባኝም ይላሉ፣ ወይም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጥበት ያዛሉ። የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ኃላፊዎች በአካልም ተገኝተውም፤ በጽሑፍም የስድስት ሰዓት ተጠያቂ የሚባል ነገር እንደሌለ እና ከሌሎች እስረኞች በተለየ አናያቸውም ብለው ዓይን ያወጣ ውሸት ይዋሻሉ። እነዚሁ ኃላፊዎች ወደ ግቢ ሲመለሱ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ብለው በማስታወቂያ አስጠርተው ይሰበስቡንና ፍርድ ቤት መናገራችን ለውጥ እንደማያመጣ ይነግሩናል።
ታዲያ እራሱ መንግሥት ለሴቶች አስከበርኩ ያለውን መብት እራሱ እየጣሰ፤ ግን ደግሞ በየዓመቱ የሴቶች ቀን እያለ ስለ ሴቶች መብት መደስኮር በፍፁም የማይጣጣም እና የኢሕአዴግን መንግሥት ግብዝነት የሚያሳይ ነው።
በቃሊቲ የስድስት ሰዓት ተጠያቂ የነበሩ እንዲሁም አሁንም እዛው ያሉ ሴት እስረኞች* ዝርዝር የሚከተሉት ናቸው።
1. እማዋይሽ ዓለሙ – በ2001 ሚያዚያ ወር ጀምሮ በእስር ትገኛለች። መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ተንቀሳቅሳችኋል በመባል በእነ ብርጋዴል ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ከተከሰሱት ውስጥ አንዷ ስትሆን የዕድሜ ልክ ፍርድ ተፈርዶባት በቃሊቲ የምትገኝ ነች።
2. ሒሩት ክፍሌ – ከ2003 ሰኔ ወር ጀምሮ በእስር ትገኛለች። በነኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ከተከሰሱት 5 ሰዎች አንዷ ናት። የሽብር ክስ ተመስርቶባት 14 ዓመት ተፈርዶአባት በቃሊቲ የምትገኝ ነች።
3. ጫልቱ ታከለ – ትውልዷ እና ዕድገቷ ምስራቅ ወለጋ ነው። ከኦነግ ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በ2000 ከታሰሩ በርካታ ኦሮሞዎች መሃከል አንዷ ናት። የተፈረደባት 12 ዓመት ሲሆን፤ ከ7ዓመት በላይ በእስር አሳልፋለች። አሁን በቃሊቲ ትገኛለች።
4. ባጩ መርጋ – የ18 ዓመት ፍርድ ተፈርዶባት በቃሊቲ የምትገኝ።
5. ቢፍቱ – የ18ዓመት ፍርድ ተፈርዶባት በቃሊቲ የምትገኝ።
6. ድርቤ (ቦንቱ) ኢታና – በ2002 በራሷ ሥም በተከፈተው መዝገብ (እነ ድርቤ ኢታና) ከተከሰሱት 7 ሰዎች አንዷ ስትሆን የሞት ፍርድ ተወስኖባት በቃሊቲ የምትገኝ።
7. ኡርጌ አበበ – በ2002 እነ ድርቤ ኢታና መዝገብ ከተከሰሱት 7 ሰዎች አንዷ ስትሆን የሞት ፍርድ ተወስኖባት በቃሊቲ የምትገኝ።
8. ሃዋ ዋቆ – የቦረና ልጅ ናት። በ2003 በነበቀለ ገርባ መዝገብ ከተከሰሱት 9 ሰዎች አንዷ ናት። በሽብር ተከሳ 5 ዓመት ተፈርዶባት የነበረ እና በ2007 ግንቦት ወር አካባቢ ፍርዷን ጨርሳ የወጣች።
9. ሂንዲያ ኢብራሂም – የሶማሌ ተወላጅ ስትሆን በሽብር ወንጀል ተከሳ 6 ዓመት ተፈርዶባት የነበረ። ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አካባቢ ፍርዷን ጨርሳ የወጣች።
10. ኡሜማ አሕመድ – የሶማሌ ተወላጅ ስትሆን በሽብር ወንጀል ተከሳ 6 ዓመት ተፈርዶባት የነበረ። ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አካባቢ ፍርዷን ጨርሳ የወጣች።
11. አበራሽ ኢቲቻ – በ2000 ላይ ለኦነግ የገንዘብ ዕርዳታ በማድረግ እና የኦነግ አባል ናችሁ ተብለው በነኢንጂነር መስፍን አበበ መዝገብ ከተከሰሱት 16 ሰዎች ውስጥ አንዷ ናት። አስር ዓመት ተፈርዶባት በ2007 ሰኔ ወር ላይ ፍርዷን ጨርሳ ከእስር ተለቃለች።
12. ህደያ ከድር – በ2006 ነሐሴ ወር በረመዳን ፆም ወቅት ተቃውሞ በነበረባቸው ጁምአ ቀናት በአንዱ ቀን ከመንገድ ላይ ተይዛ ከእህቷ ራቢያ ከድር ጋር የታሰረች። 5ወር ተፈርዶባት የነበረ ሲሆን ፍርዷን ጨርሳ የወጣች።
13. ራቢያ ከድር – በ2006 ነሐሴ ወር የረመዳን ፆም ወቅት ተቃውሞ በነበረባቸው ጁምአ ቀናት በአንዱ ቀን ከመንገድ ላይ ተይዛ ከእህቷ ህደያ ከድር ጋር የታሰረች። 5ወር ተፈርዶባት የነበረ ሲሆን ፍርዷን ጨርሳ የወጣች።
14. ሃያት አሕመድ – ከሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ ከአዳማ ከተማ ከተያዙ ሙስሊሞች አንዷ ናት (በእነ አብዱላዚዝ መዝገብ)። በ2005 የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ወስዳ ውጤቷን በመጠባበቅ ላይ እያለች ነው የድንገቴ እስር የገጠማት። በእስር ሆና ክሷን ለዓመት ከስምንት ወር ስትከታተል ቆይታ በነፃ ተለቃለች። (ማእከላዊ 4 ወር ቆይታለች)
15. ፈቲያ መሐመድ – ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎች ዩንቨርስቲ እና ኮሌጅ ተይዘው ከታሰሩት ውስጥ ናት። ለዓመት ከስድስት ወር ያክል ክሷን በእስር ሆና ስትከታተል ቆይታ 6 ወር የተፈረደባት ሲሆን ከተፈረደባት የፍርድ ልክ በላይ በእስር በመቆየቷ በጥቅምት ወር 2007 ከእስር ወጥታለች። (ማእከላዊ 4 ወር ቆይታለች)
16. መርየም ሐያቱ – ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ እና ከወልቂጤ ኮሚቴውን ለመተካት ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው ከተያዙት (እነ ኤልያስ ከድር) ውስጥ አንዷ ናት። መርየም በ2005 መጨረሻ አካባቢ ከወልቂጤ ነው የተያዘችው። ከሁለት ዓመት አራት ወር የፍርድ ቤት መንከራተት በኋላ በታኅሳስ ወር 2008፣ 7ዓመት ተፈርዶባት ቃሊቲ የምትገኝ። (ማእከላዊ 4ት ወር ቆይታለች)
17. ሃያተልኩብራ ነስረዲን – ከ5ት ወር የማዕከላዊ ቆይታ በኋላ ‹የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ› የተባለ ‹የሽብርተኛ ድርጅት› ጋር ግንኙነት በማድረግ በሚል ሐምሌ ወር 2007 ላይ ክስ ከተመሰረተባቸው 20 ሰዎች ውስጥ አንዷ ሆና ቃሊቲ እስር ቤት ገባች። ከወራት በፊት ችሎት እንዲቀየርላቸው ያመለከቱ ሲሆን፤ እስካሁን አቤቱታቸው ባለመመለሱ የዐቃቢ ሕግ ምስክሮችን መሰማት አልተጀመረም።
18. ኤዶም ካሳዬ (ጋዜጠኛ) – በሚያዚያ 17/2006 ተይዛ ማዕከላዊ ለሦስት ወራት ከቆየች በኋላ ክስ ተመስርቶባት ቃሊቲ እስር ቤት ገባች። የኅብረተሰቡን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል አሲራችኋል፣ አቅዳችኋል ተብለው በነሶሊያና ሽመልስ መዝገብ ከተከሰሱት 3 ጋዜጠኞች አንዷ ስትሆን ለዓመት ከሦስት ወር በእስር ሆና ክሷን ከተከታተለች በኋላ ክሱ ተቋርጦላት በነፃ ወጥታለች።
19. ማሕሌት ፋንታሁን – በሚያዚያ 17/2006 ተይዛ ማዕከላዊ ለሦስት ወራት ከቆየች በኋላ ክስ ተመስርቶባት ቃሊቲ እስር ቤት ገባች። የኅብረተሰቡን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል አሲራችኋል፣ አቅዳችኋል ተብለው በነሶሊያና ሽመልስ መዝገብ ከተከሰሱት 6 ጦማሪ አክቲቪስቶች አንዷ ስትሆን ለዓመት ከሦስት ወር በእስር ሆና ክሷን ከተከታተለች በኋላ ክሱ ተቋርጦላት በነፃ ወጥታለች።
20. ርዕዮት ዓለሙ (ጋዜጠኛ እና መምህርት) – በ2003 ሰኔ ወር ላይ ተይዛ ማዕከላዊ ገባች። በነኤልያስ ክፍሌ መዝገብ በሽብር ወንጀል ከተከሰሱት አምስት ሰዎች አንዷ ናት። ከፍተኛ ፍቤት የ14ዓመት ፍርድ ከበየነባት በኋላ ይግባኝ ብላ ክሶች ተሰርዘውላት ቅጣቱ ወደ 5ዓመት ዝቅ አለላት። በደንቡ መሠረት በአመክሮ ጥቅምት ወር 2007 ላይ መለቀቅ ሲገባት፤ በጥፋቷ መፀፀቷን አምና ካልፈረመች አመክሮ አይሰጥሽም ተባለች። የማላምንበት ነገር ላይ አልፈርምም በማለትም ያለአመክሮ ፍርዷን ለመጨረስ ወሰነች። ባልተጠበቀ እና ባልታሰበ ወቅት ከአራት ዓመት እስር በኋላ ሐምሌ 1፣ 2007 ከእስር ተለቀቀች። የመጨረሻዎቹን ሁለት የእስር ዓመታት አምስት የእሷን ሁኔታ የሚከታተሉ እስረኞች ያሉበት ብቻ በቅጣት ቤት ውስጥ ነበር ያሳለፈችው፤ ከእናት እና አባቷ ውጪም በማንም እንዳትጎበኝ ተከልክላ ነበር። በእስር ሆና ‹የኢሕአዴግ ቀይ እሰክብሪቶ› የሚል የቀድሞ ጽሑፎቿ ስብስብ ታትሞላታል፡፡
21. ረዳት ኢንስፔክተር አዜብ ተክላይ – ለኤርትራ የስለላ ቡድን የሃገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ አቀብለሻል ተብላ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ማዕከላዊ ገባች። ከአራት ወር በላይ እዛ ከቆየች በኋላ ምንም ማስረጃ ሳይገኝባት በስለላ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባት ቃሊቲ እስር ቤት ገባች። ክሷን በእስር ሆና ስትከታተል ቆይታ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ጥፋተኛ ተብላ የ7ት ዓመት ፍርድ ተበይኖባታል። ጥፋተኛ መባል አይገባኝም ስትል ጠቅላይ ፍቤት ይግባኟን አቅርባ ተከራክራለች። ለመጋቢት 16/2008 ለብይን ተቀጥራለች።
22. አበበች ጣሙ – የጎንደር ተወላጅ ናት። በጥር ወር 2006 ላይ ተይዛ ማዕከላዊ ገባች። በእነአበበ ካሴ መዝገብ ከተከሰሱት ውስጥ ስትሆን መሳሪያ ደብቀሻል የሚል ክስ ነው የተመሰረተባት። 1 ዓመት ከአምስት ወር በእስር ቆይታ በ2007 ሰኔ ወር ላይ በዋስ ወጥታ ክሷን ስትከታተል ከቆየች በኋላ ጥር ወር 2008 ላይ በነፃ የተሰናበተች።
23. እየሩሳሌም ተስፋው – የሰማያዊ ፓርቲ አባል የነበረች። በየካቲት ወር 2007 በሰላማዊ ትግል ተስፋ ቆርጣ ሰማያዊ ፓርቲን በመልቀቅ በኤርትራ በኩል ግንቦት 7 ልትቀላቀል ስትል ማይ ካድራ የተባለ ቦታ ላይ ተይዛ ወደ ማዕከላዊ የገባች። ከዛም የሽብርተኛ ድርጅት አባል መሆን የሚል ክስ ተመስርቶባት በቃሊቲ የምትገኝ። እሷ ያለችበት መዝገብ (እነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ) መከላከያ ምስክሮችን ለማሰማት ለመጋቢት 22/2008 ተቀጥረዋል።
24. እየሩስ አያሌው – የ2007ን ሃገራዊ ምርጫ ተከትሎ “ትግሬ አይገዛንም” ብለሻል የሚል ክስ ተመስርቶባት ዓመት ከአራት ወር ተፈርዶባት ግንቦት ወር 2007 ላይ ቃሊቲ ገባች። ከፍተኛ የአይምሮ ጭንቀት ሕመም የነበረባት ሲሆን ምግብም አትበላም ነበር። በየካቲት ወር መጀመሪያ 2008 ላይ በእስር ላይ እያለች እራሷን አጥፍታ ሕይወቷ ያለፈ።
25. ቀለብ ስዩም – ከአራት ወር በላይ ይሆናታል ከታሰረች። ከጎንደር ነው የመጣችው። በሽብር ወንጀል ተከሳ ጉዳይዋን በቃሊቲ እስር ቤት ሆና እየተከታተለች የምትገኝ።
26 ሃዊ ጎንፋ – በሽብር ወንጀል ተከሳ ሦስት ያልተገቡ ዓመታትን በእስር አሳልፋለች። ለሦስት ዓመታት ክሷን በእስር ሆና ስትከታተል ከቆየች በኋላ በነፃ ተሰናብታለች። በማዕከላዊ እና ቃሊቲ የታዘበችውን የሚተርክ RIRRIITTAA የተሰኘ መጽሐፍ እና ሌሎች ሁለት ተጨማሪ መጽሐፍቶችን (HIREE GALGALAA እና CANCALA QABSOO) አበርክታለች።
27. አየለች አበበ – ካጋሞ ጎፋ ዞን ተይዘው አራት ወር ማዕከላዊ ከቆዩ በኋላ የሽብርተኛ ቡድን አባል ናችሁ በመባል በሚያዚያ 27 ቀን 2008 ክስ ከተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት (እነ ሉሉ መሰለ) ውስጥ ናት።
የISIS ቡድን በሊቢያ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ግድያ በመቃወም በሚያዝያ ወር 2006 በተጠራው ሰልፍ ጋር በተያያዘ “ስብሰባ በማወክ”፣ “ሁከት በመፍጠር”፣ እና በመሳሰሉ ክሶች የተመሠረተባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ጭራሽ ሰልፉ ላይ ያልነበሩ (እቤታቸው ወይም ሥራ ገበታቸው ላይ የነበሩ) ይገኙበታል፡፡ በነጻ የተሰናበቱት እንዲሁም ስምንት ወር ፍርድ ተወስኖባቸው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቅጣታቸውን ጨርሰው ከእስር ወጥተዋል፡፡ ቃሊቲ ገብተው የነበሩት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ብሌን መስፍን – (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)
2. ቤተልሔም አካለወልድ
3. ወይንሸት ሞላ (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)
4. ዝናሽ አንከላ
5. ዝናሽ ምትኩ
6. ማሕሌት ኤርሳዶ
7. እኑኪ ኃይሉ
8. ቤዛዊት ግርማ (ጋዜጠኛ)
9. ራሕሙ ጀማል
10. ፍቅር
11. መስከረም ወንድማገኝ (አርቲስት)
12. ዮዲት ኃይለማርያም
13. ሔለን ነዋይ
14. ሜሮን አስማማው
15. ንግሥት ወንዲፍራው (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)
—-
*በመረጃ እጦት የተገደፉ ጥቃቅን ስህተቶች እና ያላካተትኳቸው እስረኞች ሊኖሩ ይችላሉ።

ምንጭ

Filed in: Amharic