>
11:52 am - Tuesday January 26, 2021

የዞን ዘጠኙ በፍቃዱ፣ እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ…(ከኤሊያስ ገብሩ - የዕንቁ መጽሔት ዋና ኣዘጋጅ)

በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም ከጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ጋር በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነውዕንቁ መጽሔት ላይ ነበር – እሱ ማኔጂንግ ኤዲተር እኔ ደግሞ ዋና አዘጋጅ ሆኜ፡፡ ከትውውቃችን ቀን ጀምሮ በፍቄ እንጂ በፍቃዱ ብየው እንኳን አላውቅም፡፡
በፍቃዱ ሳውቀው በጣም ረጋ ያለ፣ ትሁት፣ ሰውን በአክብሮት ብቻ የሚያናግር፣ አስተዋይ፣ ሰውን የሚረዳ፣ የራሱን ሀሳብ፣ አቋምና ዕምነት በቀላሉ የሚያስረዳ፣ የተለየ የሰዎችን ሀሳብ፣ አቋምና ዕምነት በጨዋ ደንብ የሚያከብር (ይሄን ዐይነት ባህሪ ብዙ ሰዎች ጋር መመልከት አልቻልኩም)፣ በሀሳቦች ላይ ውይይት የሚወድ፣ ጊዜውን በአግባቡ ከፋፍሎ ለሚወዳቸው ሥራዎቹ የሚሮጥ፣ ራሱን በዕውቀት፣ በወቅታዊ መረጃዎችና በተለያዩ ሥልጠናዎች ማበልጸግ የሚወድ እጅግ ቅን ልጅ ነው፡፡
በመጽሔቷ ላይ ለአምስት ወራት ያህል አብረን ሰርተን ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያቶች ሀታታዊም ሆነ ግለ-ሃሳባዊ ጽሑፎችን ለማሰናዳት ጠቃሚ ወቅታዊ መረጃዎችን መሰብሰብ ይወድዳል፡፡ በመረጃዎቹ ላይ ከባልደረቦቹ ጋር መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ ስብሳባዎች ላይ ውይይት ከፍቶ ሐሳቦችን መለዋወጥም ልምዱ ነበር፡፡ ይህን ዓይነት ልምድ ለየትኛውም ነጻ ጋዜጠኛ ወሳኝ ነው የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ በቢሮ ጠረጼዛ ላይ ተጀምረው በቢሮ ጠረጼዛ ላይ የሚጠናቀቁ ጽሑፎችን የሚያሰናዱ፣ ለመስክ ሥራ መልፋት የማይወዱ “ጋዜጠኞች” እና ጸሐፊያን በሀገራችን መኖራቸውንም አውቃለሁ፡፡
በፍቃዱ እና …ጭንቀቱ
የትኛውም የህትመት ውጤት በውስጡ ከሚይዛቸው የጽሑፍ ይዘቶች ባሻገር ለንባብ የሚሆን መስህብ ያለው የፊት ገጽ ግራፊክ ዲዛይን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ግነት ባልበዛበት መልኩ የህትመቱን ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ እና ጉዳዮች የሚያሳይ ጥሩ የግራፊክ ዲዛይን በብዙ አንባቢያን ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ አጠያያቂ አይመስለኝም፡፡
የሕትመት ውጤቶች የፊት ገጽ ግራፊክ ዲዛይን ከልብ ሲያስጨንቃቸው ከተመለከትኳቸው ጥቂት የሙያ አጋሮቼ መካከል አንዱ በፍቃዱ ነው፡፡ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች ከሀገር ውጭ ወጥቶ ሲመለስ፣ ሁሌ በጀርባው እና በትከሻው በሚያነግታት ቦርሳው ውስጥ የተለያዩ ሐገራትን መጽሔቶች እና ጋዜጦች ይይዝ ነበር – በፍቃዱ፡፡ እነዚህን የህትመት ውጤቶች ለእኛ ለባልደረቦቹ በኤዲቶሪያል ስብሰባ ወቅት እና መደበኛ ባልሆኑ ግንኙነቶች ወቅት ከቦርሳው አውጥቶ ስለጽሑፎች ይዘት፣ ስለሕትመት ጥራቶች፣ ስለፊት እና ውስጥ ገጾች ግራፊክ ዲዛይኖች የፈጠራ ጥበብ በተመሥጦ ለማስረዳት ሲሞክር ከልቡ ነው፡፡
ሰልፎች ላይ አጣሁት
በ2006 ዓ.ም በመዲናችን አዲስ አበባ አና በተለያዩ የክልል ከተሞች ከተመለከትናቸው ሁነቶች መካከል አንዱ ጥቂት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደረጉት እና ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡
ይብዛም ይነስም በብዙ ውጣ ውረድ ተቃዋሚዎች የሚያደርጓቸው ሰላማዊ ሠልፎች እና ሰልፎችን ለማድረግ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንደ ዜጋ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠሯቸው ሰላማዊ ሰልፎች ሁሌም በሥርዓቱ ፈተና፣ ተግዳሮትና አፈና እንደገጠመው ነው፡፡ …
በፍቃዱን እንደኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ካከበርኩለት አቋሙ አንዱ የህዝብ ድምጾች በሚሰሙባቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በነቃ መንፈስ መገኘት መቻሉ፣ መታዘቡና ይህንንም በሕትመት እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መዘገብ መቻሉ ነው፡፡ (አንዳንድ ጋዜጠኞች እና ጸሐፊያን ተምኔታዊ የአብዮት ናፍቆትን በብዕራቸው ይከትባሉ፣ በስንት ትግል በሚገኙ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ግን ድርሽ ሲሉ አይታይም፡፡ ይህ ለእኔ ግምት ላይ የሚጥል ትልቅ ተቃርኖ ነው፡፡)
በቅርቡም ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ ህዝብን ያማረሩ የማኅበራዊ አገልግሎት ችግሮች እንዲስተካከኩ በማለም የጠሯቸው ሰላማዊ ሰልፎች ነበሩ፡፡ በሁለቱም ሰልፎች ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ቀዳሚው ሰልፍ የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ግን በፍቃዱን በጣም አሰብኩት፡፡ ሰልፉ ላይ የለም! እዝነት ተሰማኝ፡፡ በፍቃዱ በዚህ ሰልፍ ላይ ተገኝቶ መዘገብ ያልቻለው ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር እስከአሁን ድረስ ጥርት ብሎ ባልታወቀ የወንጀል ጉዳይ በፖሊስ ተጠርጥሮ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በመታሰሩ ምክንያት ነው፡፡
የፋሽስት ግራዚያኒ ሐውልት በጣሊያን መቆሙን ተከትሎ በባለዕራይ ወጣቶች ማኅበር አነሳሽነት እና በሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ በአምስት ኪሎ አደባባይ የሰማዕታት ሐውልት አካባቢ በተጠራው ሰልፍ ላይ ከተገኙት እና ለአንድ ቀን ያህል ለእስር ከተዳረጉት ሰዎች መካከል በፍቃዱ አንዱ ነበር፡፡ በፍቃዱ እንደሀገር ወዳድ ዜጋ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በትኩረት እንደሚከታተል እና ስለሀገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ስለሚያስብ ይመስለኛል እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የሚገኘው፡፡
ነፍሱ ወደየት ታደላለች?
በተፈጥሮ እያንዳንዳችን ለነፍሳችን ቅርብ የሆኑ ነገሮች አሉን፡፡ ከዚህ አኳያ በፍቃዱን ሳስበው ወደውስጤ ወዲያው የሚመጣልኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ መጽሔቷ ሥራ ላይ በነበረው ቆይታ አስተውዬ ስመለከተው ነፍሱ ለማኅበራዊ ሚዲያ በጣም ቅርብ ሆና አይቻታለሁ፡፡
ሁላችንም የሥራ ባልደረቦች መጽሔቷን ለመዘጋጀት ሥራዎችን ተከፋፍለን እንሰራ ነበር፡፡ በተለይ ማተሚያ ቤት ለመግባት ሁለት ቀናት ሲቀሩ የሥራው ውጥረት ከፍ ያለ ነው፡፡ በፈቃዱም ከሚጽፋቸው ጽሑፎች ባሻገር ሌሎች ጽሑፎችን አርትዎት ያደርጋል፡፡ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር፣ ጽሑፎች እየጻፈም ሆነ አርትኦት እያደረገ ሞባይሉን በመክፈት ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ወዲያው ወዲያው መከታተሉ ነበር፡፡ ይሄን ልምዱን በተደጋጋሚ ማየቴ ለብቻዬ ፈገግታን ይጭርብኝ ነበር፡፡ ለመጽሔቷ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍቃዱ ማሕተመወርቅ እና ለአዘጋጁ በሪሁን አዳነ ‹‹የበፍቄ ነፍስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነች›› በማለት ፈገግታዬን አጋርቻቸው ነበር፡፡ እነሱም እየሳቁ ሃሳቤን መጋራታቸውን አስታውሳለሁ፡፡
የበፍቃዱን ብዕር በጥቂቱ
ዕንቁ ቁጥር 89፣ መጋቢት 2005 ዓ.ም ላይ ‹‹ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና አቶ በረከት ስምኦን›› በሚል ርዕስ የሀሳብን ነጻነት አደጋ ላይ መሆኑን በተመለከተ ጥሩ መጣጥፍ አስነብቦ ነበር፡፡ እንዲህ ቀነጨብኩት፡-
‹‹ከ20 ዓመታት በፊት ፓርቲዎቻችሁ ሕወሐትም ሆነ ብአዴን ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ሕይወታቸውን የገበሩለትን ጦርነት ያካሄዱት፣ ኢትዮጵያውያን ‹ጀርባቸውን ሳይመለከቱ› በነጻነት አመለካከታቸውን እና ሐሳባቸውን እንዲያንጸባርቁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብዙዎች ደማቸውን ያፈሰሱለት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ የተሰየመለት (አንቀጽ 29) ‹የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት› ከኢትዮጵያውያን እጅ ቀስ በቀስ አፈትልኮ እየወጣ መሆኑ ቢያሳሳስበኝ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡
…ክቡራን ሚኒስትሮች፣ መንግሥት የዜጎችን ሐሳቦች፣ ጋዜጦችንና ጦማሮችን በተደራጀ መልኩ እያሰሰ እና እያነበበ የሕዝቦችን ብሶት እና ችግር ተረድቶ ለመፍትሔው መረባረብ ሲኖርበት፣ ዜጎች መረጃዎቹን እንዳያወጡ እንቅፋት መሆንን ከመረጠ በየት በኩል ኃላፊነት የሚሰማው ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻለዋል? መንግሥት በምሳሌነት የሚሳየውን ሥርዓት ከሕዝብ እንዴት መጠበቅ ይቻለዋል? እንግዲህ እነዚህን ጥያቄዎቼን በቅን ልቦና ተረድታችሁ ለጥያቄዎቼ ሁሉ መልስ እንደምትሰጡኝ በማመን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (2)ን በመጥቀስ ደብዳቤዬን እቋጫለሁ››
ለሥራ ጉዳይ ኬንያ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ በቁጥር 94፣ ሰኔ 2005 ዓ.ም ላይ ደግሞ ‹‹ናይሮቢን በአዲስ አበባ አይን›› በሚል ርዕስሥር እንዲህ ብሎ ነበር፡-
‹‹ …ስለአዲስ አበባ እና ናይሮቢ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ገጹ አይበቃም፡፡ …ናይሮቢ በሌቦች እና አልፎ አልፎ በሽብር የምትታወክ ከተማ ስትሆን አዲስ አበባ ግን በአብዛኛው የጨዋታዎች እና ሰላማዊ የመሆኗ ነገር አስደሳች ነው፡፡ ችግሩ አዲስ አበባ ገና ፍዝዝ፣ ድንግዝ ያለች እና መነቃቃት የሚቀራት መሆኑ ነው፡፡›› ከዚህ ጽሑፍ በግልጽ ለመረዳት የቻልኩት በፍቃዱ ሽብር ሳይሆን ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነው፡፡
በሰኔ 2005 ዓ.ም፣ ቁጥር 93 ላይ፣ ‹‹የልማታችን ጥፋቶች›› በሚል ርዕስ የልማት አካሄዶችን በምክንያታዊነት እንዲህ በማለትም ተችቷል፡-
‹‹በቂ ጥናት ሳይደረግባቸው ወደተግባር የሚገባባቸው ሥራዎች የመንግሥትን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ሊያከስሩ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ …ግንባታዎችን ከማስጀመር እና ከማስጨረስ እኩል ለአገልግሎት የመዋላቸው ነገር ሊታሰብበት ይገባል፤ አለበለዚያ የልማት ሥራዎች ከላስቲክ ጀበናነት የበለጠ ትርጉም የሌላቸው ሊሆኑ ነው›› ይህንን የበፍቃዱን የሀሳብ ድምዳሜ በግሌ የምጋራው ሃቅ ነው፡፡
በፍቃዱ (በፍቄ) መታሰርህ ብቻ ሳይሆን እጆችህ በካቴና ታስረው አራዳ ፍ/ቤት ሳይህ ጥልቅ ሀዘን ቢሰማኝም ጠመንጃ በወደሩ ፖሊሶች መካከል ከአንተ ያየሁት የፈገግታ ብልጭታ መንፈሰ ጠንካራነትህን አሰይቶኛል፡፡ አይዞን! እውነት ታሸንፋለች፡፡

Filed in: Amharic