>
5:13 pm - Monday April 19, 1413

ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፡ የግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞ [በዘላለም ክብረት፦ዞን ፱]

Zelalem Kibret (Kilinto)ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ ይሄው 25 ዓመታት እየሆነው ነው፡፡ ይሄም በጆን አቢኒክ ቋንቋ ኢሕአዴግን በኢትዮጵያ የሪፐብሊክ ታሪክ (ከዘውዱ አገዛዝ በኋላ) ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆየው ስርዓት ያደርገዋል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን በወጣበት ወቅት የዓለም ፖለቲካዊ ምህዳር ከግራ ወደ ቀኝ ያደረገው ሽግግር ኢሕአዴግ ይዞት የመጣውን ቀይ የፖለቲካ ጥብቆ ባንዴ አውልቆ የምዕራቡ ዓለም መለያ የሆኑትን ባለ ነጭ፣ ሰማያዊና ቀይ የፖለቲካ ጥብቆ በግድ እንዲለብስ የተገደደበት ነበር፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ይሄን የኢሕአዴግን የርዕዮተ ዓለም ግርታ (confusion) ‹የግራ ፍሬቻ እያሳዩ ደብረ ብርሃን የደረሱት የኢሕአዴግ መሪዎች በፍጥነት ወደ ቀኝ ታጥፈው አዲስ አበባ ገቡ› በማለት ውብ አድርገው ይገልፁታል፡፡ ይህ ድንገተኛ የፖሊሲ ለውጥ ነው በመጀመሪያዎቹ አስር የስልጣን ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱን ‹በግምት› ሊባል በሚችል መልኩ ያለወጥ ፖሊሲ እንዲመራት ያደረገው፡፡ ዴሞክራሲን በሚመለከት ግን ከዚህም በባሰ ደረጃ እስከ አሁን ድረስ ወጥ ሊባል የሚችል ፖሊሲም ሆነ ‘6ርምጃ ማግኝት ከባድ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
እንግዲህ የመንግስት ፖሊሲ የሌለ ወይም ግልፅ ባለሆነ ጊዜ መንግስቱን የሚመሩት ግለሰቦች የሚሰጡት አስተያየትና ሃሳብ ውስጥ ነው ፖሊሲውንና ርምጃውን የምናገኝው፡፡ ኢሕአዴግን በሚመለከትም ይህ የመሪውን ግለሰብ ቃል መከተል የፖሊሲውን አመላካች ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ስሜትና ፍላጎትም የኢትዮጵያ ፖሊሲ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ዘልቋል ማለት ይቻላል፡፡ ችግሩ ግን የመለስ ስሜትና ፍላጎት በየጊዜው ተቀያያሪ መሆኑ ነበር፡፡
መለስ አንድ ኢትዮጵያን ከ1983 እስከ 1993 ለአስር ዓመታት የገዙ ሲሆን በዚህ ጊዜ በብቸኝነት ስልጣን ለመቆጣጠር የማያስችሉ ውስጣዊ ሁኔታዎች የነበሩ በመሆኑ በአፍ ደረጃ የዚህ ጊዜው መለስ ‹ዴሞክራት› መስለው ይታዩ ነበር፡፡ መለስን አንድን ከዴሞክራሲ ጋር በተገናኝ በሚገባ የሚገልፃቸው በጥር 1983 በኢሕአዴግ የመጀመሪያው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እንዲህ በማለት የተናገሩት ንግግር ነው፡

ህዝቡ ያልተገደበ የዴሞክራሲ መብት አለው እስካልን ድረስ ይህ መብት የመናገርን መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የመጻፍን መብት፣ የመቃወምን መብት ሁሉ ያካተተ መሆን አለበት፡፡ የፈለገውን ፖርቲ መመስረት መብቱ ነው፡፡ አንድ ብቻ ይበቃሀል፣ ሶስት ብቻ ይበቃሀል ወይም አርባ አራት ብቻ ይበቃሀል ተብሎ የሚገደብ ነገር አይደለም፡፡ እንደፈለገው ራሱን በነጻ ማደራጀት ይችላል፡፡ የራሱን አቋም የሚያራምድበት፣ የፈለገውን ሀሳብ ይዞ ቢያስፈልገው ፓርቲ መመስረት ይችላል፡፡ ይሄ የዴሞክራሲ መብቱ ነው፡፡

መለስ ሁለት ደግሞ ኢትዮጵያን ከ1983 እስከ 1998 ድረስ የገዙ ሲሆን በዚህ ጊዜም የውስጥ የፓርቲ ሽኩቻውን በድል አጠናቀው ዴሞክራሲን ለውስጠ ፓርቲ የመታገያ/የማጥቂያ ዘዴ በማዋል ለውጭ ተመልካቾች ደግሞ ራሳቸው ዴሞክራት አስመስለው ያቀረቡበት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው መለስ በነሃሴ 16፣ 1993 በኢሕአዴግ አራተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ፡

ዴሞክራሲን የመከተል ጉዳይ የተሻለ አሰራር መከተል ወይም ያለመከተል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጥገኛ ዝቅጠትን ለመመከት የሚያስችል ሃያል ትጥቅ የመያዝ ወይም ያለመያዝ ጉዳይ ነው፡፡

በማለት የተናገሩት ንግግር ነው፡፡
መለስ ሶስት ደግሞ ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ እስከ 2004 መጨረሻ ወይም እስከ አሁን ድረስ በስልጣን ላይ የነበሩት/ያሉት (እንደተመልካቹ ነው) ሲሆኑ ዴሞክራሲ ይሉት ጉዳይ የማይሆን ነገር ነው በማለት ከምዕራባዊያን ጋር በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ፍጥጫ ውስጥ የገቡት ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሄን ዘንድ መለስ በኢሕአዴግ ስድስተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፡

በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ አጀንዳችን ሌሎች ስላሉት (ምዕራባዊያኑን ለማለት ነው) የምናደርገው አጀንዳ አይደለም። ለራሳችን ለአገራችን ህልውና ፤ ለልማታችን ቀጣይነት ወሳኝ ነው ብለን በማመናችን ነው።

ብለዋል፡፡
መለስ ሶስት ከምርጫ 97 ወዲህ ከተለያዩ የውጭ የሚዲያ ተቋማት ይቀርብላቸው ለነበረው የሃገሪቱ የዴሞክራሲያዊነት ጉዳይ ጥያቄ ሲመልሱ አንዴ “To impose democracy from outside is inherently undemocratic” እያሉ ምዕራቡን ዓለም በተዘዋዋሪ ሲጎሽሙ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በቀጥታ ምዕራቡን ዓለም “Democratic transformation for us is not mimicking some facets of Western governance” እያሉ ሲያስጠነቅቁ፤ ሲያሻቸው ደግሞ የምዕራቡን ዓለም መሪዎች “We will democratize Ethiopia not to please Tony Blair or anybody else; we will democratize Ethiopia because it is good for us” በማለት በቀጥታ ስም እየጠቀሱ ሲገረምሙ፤ ባስ ሲል ደግሞ የምሁራኑን ረጅም ጊዜ የፈጀውን የዴሞክራሲና – ዕድገት ግንኙነት ምይይጥን “There is no direct relationship between democracy and growth” በማለት ቁርጥ እያደረጉ ዴሞክራሲን የርዕዮተ ዓለም አጀንዳ በማድረግ ቀጥተኛውን ጥያቄ አዟዙረው ጠያቂውን በተከላካይነት ቦታ በማስቀመጥ ‹ይመልሱ› የነበሩ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ መለስ አንድም ሆኑ መለስ ሁለትን አናገኝም፡፡
መለስ 1.0 እንዲህ ብለው ቢያልፉም፤ እርሳቸውን የተኩት (በራሳቸው ቋንቋ የመለስን ውርስ አስቀጣዩ) መለስ 2.0 ወይም ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመለስ ሶስት ብዙም የተለየ ሃሳብ ባይኖራቸውም ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት ያደረጓቸውን ቃለ ምልልሶች ስንመለከት ከመለስ ሶስት ትንሽ በተለየ መልኩ የመለማመጥ ባህሪን እናያለን፡፡ ምሳሌ ብንመለከትም፡

Something has to be understood that this is [we have] a fledgling democracy. Democracy cannot be built within a few years of time. We have to learn lots of things. But the thing is, we believe we are on the right track. [Though] there are number of [adequate] rooms for improvement [parties].

ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ከተለያዩ አምስት የውጭ እና የሃገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የዴሞክራሲ ሁኔታ ተጠይቀው የመለሱት በጣም ተቀራራቢ የሆነ መልስ በአንድ አንቀፅ ሲጠቃለል ነው፡፡ መልሳቸውን ስንመለከት ከተጠየቁት ጥያቄ ተከትሎ ለሚመጣ ሌላ ‹አፋጣጭ› ጥያቄ መከላከያ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ‹ዴሞክራሲያችን ገና ጨቅላ ነው፣ ብዙ ማደግ እንዳለበት እንረዳለን – ነገር ግን ትክክለኛውን መሰረት አስቀምጠናል› የሚል ሆኖ እናገኛለን፡፡
እንግዲህ ‹ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ነች ወይስ አይደለችም› የሚለው ጥያቄ አሁን ብዙም የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ ባይሆንም፤ ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ከላይ በተጠቀሱት አግባብ መልስ እየሰጠ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉት ዋናዎቹ ሹመኞች በግፍ አገዛዝ ተማረው ትግል ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ (ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ) ያለውን የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ‹ኦዲት› ማድረጉ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከጨቅላነት መች ይወጣል? በርግጥስ ሶስቱ (የዘውዱ፣ ወታደራዊውና የአሁኑ) ስርዓቶች ዴሞክራሲን በሚመለከት ያሳዩት ይህ ነው የሚባል ልዩነት አለን? ለመሆኑ ዴሞክራሲ ነብስ የሚዘራው ምን ሲከሰት ነው? የሚሉትን እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን እንመልስ ዘንድ ያለፉት 45 ዓመታትን መረጃ (data) (የ45 ዓመታት ዳታን ለምን እንደመረጥኩ ከታች አስረዳለሁ) በማየት ከላይ የተጠየቁትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞክራል ፅሁፉ፡፡
‹ሰምና ወርቅ ዴሞክራሲ›
በዚህ ፅሁፍ የዴሞክራሲ ምንነትና የትርጉም አተካራ ውስጥ ለመግባት አልተሞከረም፡፡ የተለያዩ ሊቆች በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ትርጉሞች ሲሰጡት የነበሩ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በዜጎች ይሁንታ ተመርጦ የዜጎችን መብት የሚያስከብር ስርዓት መዘርጋት የዴሞክራሲ ምንነት ተደርጎ ቢወሰድ የማይስማማ ቢኖር እንኳ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ይሄም ሆኖ ‹አንድ ሀገር ምን አይነት ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል?› ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ‹ዴሞክራሲ ምንድን ነው?› ከሚለው ጥያቄ በላቀ ደረጃ አወዛጋቢና ዘመናትን ተሻግሮ የመጣ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከትናንት እስከዛሬ (በተለይ በገዥዎቿ) ‹የምዕራቡን ዓለም አይነት ዴሞክራሲ ገልብጠን የምናመጣ አይደለንም፤ (ምንም እንኳን በሕገ መንግስቶቿ ከምዕራብ የዴሞክራሲ እና የነፃነት አስተሳሰብ የተለየ ነገር ባትደነግግም) እኛ ዴሞክራሲን የምናየው በራሳችን አውድ (context) እና አግባብ ነው› በሚል ‹ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› አሰፍናለሁ በሚል በዓለም መድረክ እየታየች ትገኛለች፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› ምን አይነት እንደሆነ ገዥዎቹ ማብራራት ባይችሉም፤ ምሁራን ግን ይሄን ጉዳይ ለመግለፅ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡
የዳውሰን ኮሌጅ የፍልስፍና ዶክተሩ መምሬ መናሰማይ ይሄን ‹የኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› ጉዳይ ‹ሰምና ወርቅ ዴሞክራሲ› በማለት ይገልፁታል፡፡ ሰሙ ከላይ የሚታየው መሰረቱን ምዕራቡ ዓለም ያደረገው የምርጫ ዴሞክራሲ (Electoral Democracy) (በአሁኗ ኢትዮጵያ የምርጫ አምባገነንነት (Electoral Authoritarianism) ሆኗል ይሉታል) ሲሆን፤ ወርቁ ደግሞ ‹ኢትዮጵያዊያን ከምዕራቡ ዓለም የሚስተካከል የራሳችን የሆነ ታሪክና ባህል ስላለን ዴሞክራሲያችን ያን የራሳችን የሆነን ማንነት ማንፀባረቅ አለበት የሚል ነው› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሃሳብ ከነኔሬሬ እና ኑኩሩማህ ‹African Democracy› የሚጠቅስ ቢሆንም፤ በዚህ አግባብ ወርቁ ምን ማለት እንደሆነ ብዙም ግልፅ አይደለም፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› ኖረም አልኖረም ኢትዮጵያ የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ሶስት መንግስታት ስር የተለያዩ የዴሞክራሲ አመላካች የሆኑ ጉዳዩችን (ምርጫ እና የዜጎች መብትን በዋነኛነት) በሕግ ደንግጋለች፡፡ ከነዚህ ዴሞክራሲን አመላካች ከሆኑ መብቶች አንፃር የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ርምጃ ወደፊትና ወደኋላ ማየቱ ከምን አይነት ዴሞክራሲ? ውዝግብ ጀርባ ያለውን እውነታ ይነግረናልና እሱን እንመልከት፡፡
የግማሽ ምዕተ ዓመት የዴሞክራሲ ጉዞ
ዴሞክራሲ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ረጅም ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ጉዳይ ቢሆንም ዓለማቀፋዊው የዴሞክራሲ መስፋፋት (democratization) ግን በዋናነት ያለፉት 60 ዓመታት ውጤት ነው ማለት ለብዙሃኑ የሚስማማ ሃሳብ ነው፡፡ ይሄን መስፋፋት ተከትሎም የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ሀገራትን እርስ በርስ በግልፅ በተቀመጡ መስፈርቶች በመገምገም ደረጃ መስጠትና ትችት ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ከነዚህ ዓለማቀፍ የዴሞክራሲ ደረጃ አውጭ ድርጅቶች መካከል Polity IVVanhanen’s Index of Democracy እና The Economist Intelligence Unit (EIU) ወዘተ የሚያወጧቸው ዓመታዊ ሪፖርቶች በብዙ አካዳሚያዊ ዓለም እንደ ዋነኛ ምንጭነት እየተጠቀሱ የብዙ ጥናታዊ ፅሁፎች ግብዓት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሪፖርቶችም ሆኑ ብዙ ምሁራን ከሁሉ በላቀ የሀገራትን የዴሞክራሲ የዕድገት ደረጃ እንደ አሜሪካዊው ድርጅት ፍሪደም ሃውስ (Freedom House) በታማኝነት (ዴቪድ ካምቤል እንዳሉት)፣ በብቃት (EIU በዓመታዊ ሪፖርቶቹ እንደሚገልፀው)፣ በቀዳሚነትና በተመራጭነት (ፍራንሲስ ፉኩያማ እንዳሉት) እና በአስደናቂ ሁኔታ (ፋሪድ ዘካሪያ እንዳሉት) ለረጅም ጊዜ በግልፅነት እያስቀመጠ ያለ ድርጅት የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሃገራትን የዴሞክራሲ ደረጃ ለመለካትም እንደ ፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ‘Freedom in the World’ ያለ መመዘኛ ማግኝት ከባድ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ልክም ለመመዘን ከዚሁ ከፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ‘Freedom in the World’ አንወጣም፡፡ ነገር ግን ይሄን መመዘኛ ስንጠቀም አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንደ ቀድሞው ወታደራዊ መንግስት ሁሉ ‹ፍሪደም ሃውስ የራሱን አጀንዳ ይዞ በሃገራችን [የቀለም] አብዮት ለማስነሳት ይጥራል› በማለት እንደሚከሰውና በውጤቱም ሊስማማ እንደማይችል እየታወቀ ነው፡፡ እንዲያውም የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊና ዘጠኝ ጓደኞቹ ላይ ‹በፍሪደም ሃውስ የሽብረተኝነት ድርጊት ስልጠና ወስዳችኋል› የሚል አስገራሚ ክስ መቅረቡ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሂደት ለመመዘን የፍሪደም ሃውስን ዓለማቀፍ መመዘኛ የተጠቀምኩት በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ፡
1. መመዘኛው ‘peer reviewed ጥናት’ ከመሆኑም ሌላ አንድ ጥናት ሊያሟላ የሚገባውን ገለልተኝነት፣ ግልፅነትና አጠቃላይ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ፣
2. ላለፉት 45 ዓመታት (በኢትዮጵያ ደረጃ የሶስት መንግስታትን የዴሞክራሲ ሪከርድ ማለት ነው) በዝርዝር ሁኔታ የተለያዩ ሀገራትን ሪከርድ በመመዝገብ ደረጃ የሚሰጥ በመሆኑ (ከፍሪደም ሃውስ በተሻለ ለዚህን ያህል ጊዜ የዴሞክራሲ መረጃ የያዘ ሌላ ተቋም አለ ማለት ይከብዳል)፣
3. የዴሞክራሲ መለኪያ መስፈርቶቹ ግልፅና ውጤቱም ከነዝርዝሩ ግልፅ የሚደረጉ መሆኑ፣
4. ምዘናው በዋናነት ከተፃፉ ሕጎች ይልቅ መሰረት የሚያደርገው በተግባር ዜጎች ያሏቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመሆኑና
5. የፍሪደም ሃውስ መለኪያ መስፈርቶች መሰረታቸው በ1948 በወጣው የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የዚሁ ድንጋጌ ፈራሚ አባል እና ባለፉት ሶስት ሕገ መንግስቶቿም የድንጋጌውን ዋነኛው መብቶች ያካተተች መሆኑ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ፍሪደም ሃውስ ከ1972 (ከዚህ በታች ያለው የዘመን አቆጣጠር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ነው) ጀምሮ በከፍተኛ ትጋት የሁሉንም የዓለም ሀገራት የዴሞክራሲ ሪከርድ ፖለቲካዊ መብቶች (Political Rights) እና የሲቪል መብቶች (Civil Liberties) በሚሉ ሁለት መስፈርቶች በመክፈል፤ የፖለቲካ መብቶችን በአስር መጠይቆች እንዲሁም የሲቪል መብቶችን በአስራ አምስት መጠይቆች በመመዘን ከአንድ እስከ ሰባት ባሉ ደረጃዎች ይመድባል፡፡ (እያንዳንዱ ደረጃዎች ምን ማለት እንደሆኑ እዚህ ላይ መመልከት ይችላሉ) በዚህም መሰረት አንድ ያመጣ ሀገር ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሀገር ሲሆን ሰባት ያመጣ ሀገር ደግሞ ጨቋኝ እና አፋኝ ስርዓት ያለበት ሀገር ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ወደ አንድ የተጠጉ ሀገራት ዴሞክራሲያዊና ለዜጎቻቸው መልካም የሆኑ ስርዓቶች ያሉባቸው ሲሆን፤ ወደ ሰባት የተጠጉት ደግሞ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ለዜጎቻቸው ጭቆናን ያሸከሙ ስርዓቶች ያሉባቸው ሀገራት ናቸው፡፡ አጠቃላይ ምደባውም ነፃ/ዴሞክራሲያዊ (Free)፣ ከፊል ነፃ/ዴሞክራሲያዊ (Partly Free) እና ነፃ ያልሆነ/ኢ-ዴሞክራሲያዊ (Not Free) በሚሉ ሶስት መደቦች ይመድባል፡፡
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ከፍታና ዝቅታም ከዚሁ የፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ሪፖርት አንፃር ስንፈትሸው፤ ፍሪደም ሃውስ የዴሞክራሲ ደረጃውን ማውጣት በጀመረበት 1972 የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከአስር ዓመት የሚበልጥ እንቅስቃሴ ፍሬ በማፍራት ላይ የነበረ ሲሆን፤ የዘውዱ ስርዓትም ለመውደቅ እየተንገዳገደ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡
ፍሪደም ሃውስ ሪፖርቱን ማውጣት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዘውዱ ስርዓት የቆየው ለሶስት ዓመታት ሲሆን በነዚህ ሶስት ዓመታት ውስጥ ከውጭና ከውስጥ በነበረበት ጫና ትንሽ ላላ የማለት አዝማሚያ በማሳየት በሶስቱ ዓመታት ውስጥ በፖለቲካዊ መብቶች ረገድ በ1972 እና በ1973 ያስመዘገበው 5 ሲሆን፣ በሲቪል ነፃነት ረገድ ደግሞ በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ 6 አስመዝግቧል፡፡ በቀጣዩ 1974 በተገላቢጦሽ በፖለቲካ መብቶች ዙሪያ 6 በማምጣት ያሽቆለቆለ ሲሆን በሲቪል መብቶች ረገድ ደግሞ በማሻሻል 5 ነጥብ አስመዝግቧል፡፡ ይሄም የዘውዱን ስርዓት ከጨቋኝ አምባገነናዊ ስርዓት የሚያስመድበው ሁኖ አልፏል፡፡

በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የዘውዱ ስርዓት የመጨረሻ ዓመታት የዴሞክራሲ ደረጃ
የዘውዱን ስርዓት የተካው ወታደራዊው መንግስት በዴሞክራሲ ረገድ በ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ልፈፋ እየተመራ በ1975 እና በ1976 ከንጉሱም ስርዓት በባሰ ወደ ታች በመውረድ በማምራት 7 ነጥብ በማስመዝገብ ፍፁም አምባገነንነቱን ማረጋገጥ ጀምሮ (በዚህ ጊዜ ውስጥ በሲቪል መብቶች ዙሪያ 6 ነጥብ አስመዝግቧል)፤ አቢዮቱ ‹ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት› በተሸጋገረበት 1977 ፍፁም አምባገነናዊነቱን በሚያሳይ መልኩ ዴሞክራሲን አርቆ በመቅበር በፖለቲካም ሆነ በሲቪል ነፃነቶች ረገድ የመጨረሻውን 7 ነጥብ አስመዝቧል፡፡

በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የወታደራዊው ስርዓት የ17 ዓመታት የዴሞክራሲ ደረጃ
ወታደራዊው መንግስት ለቀጣዮቹ አስራ አንድ ዓመታት (ከ1977 – 1987) ዓለም ላይ የመጨረሻውን ደረጃ በመያዝ በፖለቲካዊ መብቶችም ሆነ በሲቪል ነፃነቶች ዙሪያ ዝቅተኛውን 7 ነጥብ አስመዝግቦ በመቀጠል፤ የ1987ቱን ሕገ መንግስት ተከትሎ በ1988 እና በ1989 በፖለቲካዊ መብቶች ረገድ ትንሽ ተሻሽሎ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት 6 ነጥብ አስመዝግቦ በስልጣኑ የመጨረሻ ዘመን 1990 ተመልሶ ወደ መጨረሻው 7 ነጥብ በማሽቆልቆል ዙፋኑን ተገዶ አስረክቧል፡፡ ወታደራዊው መንግስት በዴሞክራሲያዊነቱ ላይ ይቀርቡበት የነበሩትን ተቃውሞዎች አንዴ ‹ዴሞክራሲያዊ መብት ለጭቁኖች አሁኑኑ ማለት ትጥቅ አስፈቺ መፈክር ነው› (አዲስ ዘመን፣ ጥር 1970) እያለ፣ ሌላ ጊዜ ሌኒናዊውን ‹የጭቁኖች ዴሞክራሲ ከጭቁኖች አምባገነንነት ተለይቶ አይታይምን› በአደባባይ እያተጋባ (አዲስ ዘመን፤ ታሕሳስ 1970)፣ ሲያሻው ‹የአሁኑ ዓለም የዴሞክራሲ ጥያቄ የቀኝ መንገደኞች ሸፍጥ ነው› (አዲስ ዘመን ሕዳር፣ 1970) በማለት በግርድፉ ዴሞክራሲን የምዕራቡ ዓለም ሃሳብና ሴራ አድርጎ በማቅረብ ለትክክለኛ የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ቅንጣት ታክል ጥረት እንኳን ሳያደርግ በማያስቆጭ ሁኔታ ከስልጣን ተወግዷል፡፡
ወታደራዊውን ስርዓት በሃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣው ኢሕአዴግ በሽግግሩ ዘመኑ (1991 – 1994) ወቅት ከወታደራዊው ስርዓት በተሻለ ሁኔታ ከተጠበቀው ያነሰ ቢሆንም (ከሶሻሊስቱ ዓለም ሽንፈት ጋር ተያይዞ ጊዜው ዓለም ላይ ዴሞክራታይዜሽን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተስፋፋ የነበረበት ወቅት በመሆኑ) የተሻለ ሆኖ በመገኝት በፖለቲካዊ መብቶች ረገድ 6 ነጥብ በማስመዝገብ በሲቪል ነፃነቶች ዙሪያ ደግሞ 4 እና 5 ነጥቦችን አስመዝግቦ አጀማመሩን ያሳመረ ሲሆን፤ ይህ አካሔድ ተሻሽሎ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት መፅደቅን ተከትሎ ባሉት ሶስት ዓመታት (1995 – 1997) በፖለቲካዊ መብቶች ዙሪያ 4 ነጥብ በማስመዝገብ፤ በሲቪል ነፃነቶች ደግሞ በሽግግሩ ጊዜ የነበረውን የ5 ነጥብ ውጤት ይዞ ቀጥሏል፡፡ ይህ ሂደት ቀጥሎ በ1998 በ45 ዓመታት የዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ በጣም ጥሩ የሆነውን በፖለቲካዊም በሲቪል ነፃነቶች 4 ነጥብ አስመዝግቧል፡፡
በሌላ በኩል የኢሕአዴጓን ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን የዴሞክራሲያዊነት ልክ ስናነፃፅረው እጅግ አሳፋሪ ውጤት ላይ ያደርሰናል፡፡ የ2015ን ምዘና ብቻ እንኳን ብናየው የዛሬዋ ኢሕአዴግ እያስተዳደራት ያለችው ኢትዮጵያ ኢሕአዴግ አርዓያና አጋር የሆነው የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ከሚያስተዳድራት ቻይና ቀጥላ እንዲሁም የፑቲኗን ሩስያ በሶስተኝነት አስከትላ በዓለም ላይ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ሁለተኛዋ አምባገነን ሀገር (The second largest dictatorship) ሁና እናገኛታለን፡፡ በሌላ አነጋገር ሕንድ በዓለም ትልቋ ዴሞክራሲ (ከሕዝብ ቁጥር አንፃር) ነች እንደምነለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ኢ-ዴሞክራሲ ነች እንደማለት ነው፡፡ ይህ በፍፁም ደስ የሚል ሪከርድ አይደለም፡፡

በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የኢሕአዴግ የ25 ዓመታት የዴሞክራሲ ደረጃ
ነገር ግን ይህ ሂደት ብዙም ሳይቆይ ከ1999 እስከ 2009 ባሉት ጊዜያት በፖለቲካዊም ሆነ በሲቪል መብቶች ረገድ መጀመሪያ ካሳያቸው በጎ ዝንባሌዎች በመውረድ 5 ነጥብ ያስመዘገበ ሲሆን፣ የዚህ ማሽቆልቆል ሳያንስ ከ2010 ጀምሮ እስከ 2015 ድረስ በሁለቱም ጎራዎች (በሲቪልም ሆነ በፖለቲካዊ መብቶች) አሽቆልቆሎ ወደ 6 ነጥብ ወርዷል፡፡ ይሄም ኢሕአዴግ በስልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ ዘመናት ላይ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ይመራል ተብሎ ተጥሎበት የነበረው ተስፋ በገመምተኝነት ቆይቶ አሁን እንደ ቀደምቱ ስርዓቶች ወደ ፍፁማዊ ጭቆና ስርዓትነት ራሱን አውርዷል፡፡
ይህ ውጤት ምን ይነግረናል?
የከላይ ያየነው ምዘና እና ውጤት በዋናነት አሁን ስላሉ የዴሞክራሲ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምን ይነግረናል; ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ሲሆን፤ ከላይ በግርድፉ ያቀረብነው መረጃ በተለያየ አይን ስናየው የተለያዩ እውነታዎችን ይነግረናል፡፡
‹ኢሕአዴግ ራሱን ካለፉት ስርዓቶች ጋር እያወዳደረ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ከሚል ለምን ከሌሎች ሀገራት ጋር አወዳድሮ አይነግረንም?›
የሚለው ጥያቄ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሁሌም ‹ኢሕአዴግ አስከፊውን የደርግ መንግስት ገርስሼ …› ማለት ሲጀምር የሚሰጥ አስተያየት ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ ባየነው ዳታ መሰረት በዴሞክራሲያዊነት ረገድ የኢሕአዴግ ልጆች ‹መረረን› ብለው ከጠሉት የዘውድ ስርዓትና ሊፋለሙ በርሃ ከወረዱበት ‹ወታደራዊ መንግስት ይሻላሉን› ለሚለው ጥያቄ መልሳችን አሉታዊ ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት (ከ2013 – 2015) ያስመዘገበችው የዴሞክራሲያዊነት ውጤት (በፖለቲካዊ መብቶችም ሆነ በሲቪል ነፃነት ረገድ 6 ነው ያስመዘገበችው) ኢትዮጵያ በዘውዱ አገዛዝ የመጨረሻ ዓመታት (1972 – 1974) ካስመዘገበችው ውጤት (በፖለቲካዊ መብቶችም 6 እንዲሁም በሲቪል ነፃነት ረገድ 5 ነበር ያስመዘገበችው) ያነሰ እንዲሁም ከወታደራዊው መንግስት ጋር ተቀራራቢ/እኩል የሆነ የዴሞክራሲ ደረጃን ነው፡፡

በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የኢትዮጵያና የጋና የዴሞክራሲ ዕድገት በንፅፅር
ይህ ደግሞ ኢሕአዴግ ከሌሎች ሀገራት (በተመሳሳይ አጀማመር የጀመሩትን የኢትዮጵያንና ጋናና የዴሞክራሲ ሂደት በንፅፅር መመልከት እንችላለን) ብቻ ሳይሆን ካለፉት የኢትዮጵያ ስርዓታት ጋርም ቢሆን ራሱን ቢያወዳድር ዞሮ ዞሮ ከላይ ከደረስንበት መደምደሚያ ላይ መድረሳችን አይቀርም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ መች የመዳን ተስፋ ያያል? መችስ በጠና ይታመማል?
ምንም እንኳን ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ከላይ የቀረበውን መረጃ ተመልክተን ኢትዮጵያ ውስጥ ለዜጎች በዴሞክራሲ ረገድ ምቹ የሚሆነው ጊዜና አስከፊ የሚሆነው ወቅትስ የትኛው ነው? ለሚለው ጥያቄ በግርድፉም ቢሆን ምላሽ መስጠት ያስችለናል፡፡ የውጤቱን ከፍታና ዝቅታ ተመልክተን ለዴሞክራሲ ምቹ የሆኑት ጊዜያት በዋናነት የሽግግር ጊዜያት (ለምሳሌ 1972 – 1974 ያሉት ጊዜያት)፤ እንዲሁም ሀገሪቱ አጠቃላይ ትኩረቷን ወደ ሌላ ጉዳይ (ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት – 1998 እና ተከታዮቹ ዓመታት) እንደሆኑ የሚታይ ሲሆን፤ ጭቆናውና የዴሞክራሲ እጦቱ ደግሞ የሚባባሰው ስልጣን ሙሉ ለሙሉ በአንድ ሰው እጅ በምትገባበት ጊዜ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ ኮሎኔል መንግስቱ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ወደ ሞት አሰናብተው ሊቀመንበር ከሆኑበት 1977 ጀምሮ እስከ ደርግ ውድቀት ጊዜ ድረስ እንዲሁም መለስ ዜናዊ የውስጥ ጠላቶቻቸውን በግምገማ ጠራርገው – ተቃዋሚዎቻቸውን ደግሞ ከአደባባዩ ጠራርገው ካስወገዱበት ከ2010 በኋላ ያለው ጊዜ ማንሳት እንችላለን፡፡ ይሄም ዴሞክራሲ ስርዓታቱ ስልጣንን እስኪያጠናክሩ ድረስ ትንፋሽ መያዣ (buffer) ሃሳብ እንጅ በዘላቂነት እንደ ሕልም ሲይዙት ያልነበረና አሁንም ያልያዙት መሆኑን ነው፡፡
ዴሞክራሲስ በኢትዮጵያ ተቀልብሷል?
ኢትዮጵያን ከአርባ ዓመታት በላይ ያጠኑትና በቅርቡ በሞት የተለዩት ኖርዌጅያኑ ሴግፍሬድ ፓውስዋንግ በ2004 በፃፉት “Aborted or nascent Democracy? Structural reasons for the failure of democratization in Ethiopia” የተባለ ፅሁፋቸው በኢትዮጵያ የተካሔዱትን ምርጫዎች ገምግመው ‹ኢትዮጵያ በቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት ያገኘችውን ‹ዴሞክራሲያዊ› የመሆን እድል ለዲሞክራሲ አስፈላጊ የሆነውን የተቋማት (institutions) ግንባታ ማካሔድ ሳትችል በመቅረቷ ተጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ጉዞ ተቀልብሷል› ብለው ነበር፡፡ ፓውስዋንግ ይሄን ከፃፉ በኋላ ኢትዮጵያ ሶስት ‹ምርጫዎችን› ያካሔደች ብትሆንም ፓውስዋንግ ከታዘቧቸው ሁለት ምርጫዎች በባሰ መልኩ ሄዶ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ በአንድ ፓርቲ እጅ ስር ወድቃለች፡፡ ፓውስዋንግ ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት ‹ያለ ተቋም ዲሞክራሲ የለም› በማለት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ መቀልበሱን የነገሩን ሲሆን አሁን ደግሞ ዴሞክራሲ መንፈሱ እንኳን የተሰደደ ይመስላል፡፡ ከላይ ባየነው መረጃ መሰረትም ኢሕአዴግ በ1990ዎቹ ያሰመዘገበውን የራሱን የዴሞክራሲ ከፍታ ቁልቁል ገፍቶ አሁን ከዘውዱ አገዛዝ የመጨረሻ ዘመናት እንኳን ባነሰ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ በመግቢያችን የጠቀስናቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹fledgling democracy› ካሉት በተቃራኒው የሆነ እውነታ ነው፡፡ ታዲያ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ተቀልብሷል ማለት ያንሳል እንዴ?
ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው የዴሞክራሲ ቅልበሳ (democratic reversal) ለተንታኞች አስቸጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ የዴሞክራሲ መጠናከር (democratic consolidation) እና የዴሞክራሲ ቅልበሳ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ‹ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ከፓርላማዊ ስርዓት በባሰ መንገድ በቀላሉ የዴሞክራሲ ቅልበሳ ያጋጥመዋል› እንዲሁም ‹ለዴሞክራሲ ቅልበሳ ዋነኛው ምክንያት ደካማ የኢኮኖሚ እድገት ነው› በማለት ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ኢትዮጵያ አሁን ፓርላማዊ ስርዓት ዘርግቻለሁ ባለችበት እና የኢኮኖሚ እድገቴ ከዓለም ቀዳሚ ነው በምትልበትና አንዳንድ ዓለማቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ‹እውነት› ነው ባሉበት ጊዜ ይህ ቅልበሳ ሲያጋጥም ፓርላማዊ የተባለው ስርዓትን እውነተኛነት (genuineness) መጠራጠራችን አይቀርም፤ እንዲሁም አወዛጋቢውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉዳይ የበለጠ እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡
‹ግን እኮ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት አለ›
ኢሕአዴግ ስለዴሞክራሲ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ‹ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕገ መንግስት ቀርፀን በተግባር ላይ አውለናል፤ የዘመናት ጭቆናም ከሕገ መንግስታችን መፅደቅ ጋር ተያይዞ ላይመለስ ተወግዷል› ይላል፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ዋነኛ ምንጭ በማድረግ የፍሪደም ሃውስን ዓመታዊ ሪፖርት ለመጠቀም የተፈለገበት አንዱ ምክንያት መለኪያው በዋናነት ትኩረቱ የተፃፉ ሕጎች እና መብቶች ላይ ሳይሆን የመብቶች ተግባራዊነት ላይ መሆኑን ከላይ የጠቀስን ሲሆን፤ ውጤቱም በተግባራዊነት ረገድ ኢሕአዴግ ካለፉት ስርዓቶች ያልሸሸ መሆኑን ማየት ያስችለናል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ካሉት 106 አንቀፆች መካከል 31 የሚሆኑት ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚደነግጉ ናቸው፡፡ ይሄ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የተሻሻለው የዘውዱ ስርዓት ሕገ መንግስትም (1955) ከነበሩት 131 አንቀፆች መካከል 29 የሚሆኑት፤ እንዲሁም የ1987 የኢሕዴሪ ሕገ መንግስት ከነበሩት 119 አንቀፆች መካከል 28 የሚሆኑት ስለ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያው መብቶች የሚደነግጉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሶስቱም ስርዓቶች ሕገ መንግስታዊነት (constitutionalism) በሌለበት ሕገ መንግስት ምንም እንደሆነ ነው የሚያስረዱን፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው 1998 ኢትዮጵያ በ45 ዓመታት የዴሞክራሲ ታሪኳ መልካም ውጤት ያሳየችበት ዓመት ነበር፡፡ በዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ደግሞ መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው የፎሪን አፌርስ ጆርናል በዳን ኮኔል በፍራንክ ስሚዝ የተፃፈ ‹Africa’s New Bloc› የተባለ ፅሁፍ አስነብቦ ነበር፡፡ ፅሁፉ በዋናነት ‹የአፍሪካ የጨለማው ዘመን እያበቃ ነው፤ ዴሞክራሲ በአፍሪካ ማበብ ጀምሯል ለዚህም ተግባር አዲሱ የአፍሪካ የመሪዎች ትውልድ (የኢትዮጵያው መለስ፣ የኤርትራው ኢሳያስ፣ የዩጋንዳ ሙሴቬኒ እንዲሁም የሩዋንዳው ካጋሜ) ሊመሰገን ይገባል› በማለት አብስረው ነበር፡፡ ከዚህ ፅሁፍ በኋላ በመጋቢት 1998 ‘Democracy in Africa: The New Generation of African Leaders’ በሚል ርዕስ በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ‹ሂሪንግ› ቀርቦ ነበር፡፡ በሂሪንጉ ወቅት በጊዜው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሃፊ የነበሩት ዶ/ር ሱዛን ራይስ ስለ አዲሱ የአፍሪካ የመሪዎች ትውልድ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡ ሲሆን ከጥያቄዎቹ አንዱ ለሆነውና በሚዙሪው ሴናተር እና በሂሪንጉ መሪ ጆን አሽክሮፍት ለቀረበላቸው ‹ለመሆኑ እነዚህ አዳዲስ መሪዎች ከሀገራቸው ውጭ ያላቸው ተፅዕኖ ምን ያክል ነው? ከአሜሪካስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን ይመስላል?› ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፡

Let me mention in particular in this regard Prime Minister Meles of Ethiopia, President Isaias of Eritrea, and President Museveni of Uganda. These leaders have come together with a vision for not only Eastern and Central Africa, but the continent as a whole, that we largely support. It is a vision of self reliance, of sustained economic growth and prosperity, and of a sustainable form of democracy that takes into account the particular histories of individual countries but does not compromise on fundamental principles of respect for human rights.

በማለት ነበር የመለሱት፡፡ ሱዛን ራይስ ይሄን ባሉ በሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ እስከ ዛሬ ድረስ ያላለቀውን ጦርነት ጀምረው ብዙ እልቂት ተከስቷል፡፡ ሱዛን ‹ዘላቂ የዴሞክራሲ ችግኝ ተክለዋል፤ ለአፍሪካም ምሳሌ ሁነዋል› ቢሏቸውም፤ ኤርትራም ወደ አዘቅት ወርዳለች የኢትዮጵያም የዴሞክራሲ ጉዞ ዘላቂ መሆን አይደለም ያለውን እንኳን ማስጠበቅ አቅቶት አፈር መልበሱን እያየን ነው፡፡
ሲጠቃለልም የመሪ ግለሰቦች ስሜት በፖሊሲነት ሲመራው የነበረውና እየመራው ያለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ‹መሪዎቻችን› የሚምሉበት የተቀደሰ ቃል ከመሆን አላለፈም፡፡ የግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞም በዜሮ ተባዝቶ ዛሬ ብዙ ነገሮች እያስፈሩ ሄደዋል፡፡ ተስፋ እንዳናደርግ ደግሞ አዳዲስ ቀናት አዳዲስ መከራን እንጂ ዴሞክራሲያዊነትን ይዘው እየመጡ አይደለም፡፡
Filed in: Amharic