>

ዴሞክራሲና የዘውግ ብሔርተኝነት [በናትናኤል ፈለቀ]

ዞን ፱
Natinael Feleqeበኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1983 ዓ.ም በኋላ የሀገሪቱን ስልጣን የያዘው ሕወኃት/ኢሕአዴግ መራሹ አገዛዝ ሀገሪቱን መልሶ ለማዋቀር ትከክል ብሎ ያሰበውን በዋነኝነት ቋንቋን ማዕከል ያደረገ የዘውግ ፌደራል ስርዓት ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ይህም በቅርብ ጊዜ የሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የዘውግ ማንነት ተኮር ውይቶች ጎልተው አደባባይ እንዲወጡ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የሀገሪቱን የፖለቲካ ልሂቃን ውይይት መድረክ የተቆጣጠረው የዘውግ ማንነት ተኮር (ብሔርተኝነት) አጀንዳ ልሂቃኑ በሚያሳዩት የፅንፈኝነት ባህሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ አምባገነናዊ ቢሆንም በለውጥ ምክንያት ከስልጣን ቢወገድ በሚፈጠረው ክፍተት (Vacuum) ጊዜ ውስጥ የዘውግ ማንነት ተኮር የእርስ በርስ ግጭት ሊነሳ ይችላል ብሎ በመፍራት አምባገነናዊ ባህሪውን ይዞም ቢሆን ሕወኃት/ኢሕአዴግ መራሹ አገዛዝ “ይቆይልን” የሚል አስተያየት ያላቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሁን ሀገሪቱ ውስጥ አለ ብለው የሚያምኑትን የዘውግ ተኮር ግጭቶች ስጋት ለመቆጣጠር “ልፍስፍስ ስለሆነ አምባገነናዊ ስርዓት አሁን ላለንበት ተጨባጭ የማኅበራዊ-ፖለቲካ ሁኔታ ተመራጭ ነው” የሚሉ ሃሳቦችም ይሰማሉ፡፡
በርግጥ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስተያየቶች የሚሰነዝሩ ሰዎች ሀገሪቱ እስከመቼ በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ብትቆይ እንደሚሻልና ምን ሲከሰት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ግልፅ የሆነ የመፍትሄ ሀሳብ አብረው ሲሰነዝሩ አይሰማም፡፡ አንድ ነገር ግን ግልፅ ነው፡፡ ሀገሪቱን ለአምባገነናዊ ስርዓት ለተራዘመ ጊዜ መተው መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች የዘውግ ማንነት ተኮር የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የሚነሱ ጥያቄዎችን የሀገሪቱን ሉዓላዊ ግዛት አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚችሉ በማሳየት ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚያስፈልጋት ይሞግታል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስለተፈጠረ ብቻ በዘውግ ብሔርተኝነት ምክንያት የሚፈጠር የግጭቶች ስጋት ተኖ ይጠፋል ማለት አይቻልም፡፡ ጽሑፉ ለማስረዳት የሚሞክረው ዴሞክራሲያዊ መንግስት (ስርዓት) በኢትዮጵያ ውስጥ ሲገነባ ችግሩ አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ አስጊ እንደማይሆን እና ከኢትዮጵያ በፊት ተመሳሳይ ስጋት የነበረባቸው ሀገራት ዴሞክራሲን ተጠቅመው ችግሩን እንዴት እንዳለፉት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴትና በማን ይመጣል የሚሉት ጥያቄዎች በዘውግ ብሔርተኝነት ጥያቄ መልስ ማግኝት ውስጥ ግብዓቶች ቢሆኑም ከዚህ ጽሑፍ ወሰን (Scope) በላይ ናቸው፡፡
የዘውግ ማንነት ተኮር የፌደራል ስርዓት ለምን ኢትዮጵያን ይበታትናል?
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የሚባል ድርጅት በአዲስ መልክ አደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የተመለሱት ሌንጮ ለታ በጻፉት አንድ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ወደስልጣን ሲመጣ የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ (setting) የዘውግ ማንነት መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓትን እንዲከተል ከታሪክ የተረከበው የውዴታ ግዴታ እንደነበር እና ብቸኛ ሀገሪቱን ከመበታተን ለማዳን የሚችል ስርዓት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ እንደሌንጮ ትንተና ከሆነ የዘውግ ማንነት ጉዳይ ገዢ ሕዝብን የማደራጅያ (mobilizing) ሀሳብ አድርገው የፈጠሩት በዘውግ ማንነታችን ምክንያት ጭቆና ደርሶብናል ብለው የዘውግ ማንነት ተኮር ድርጅቶችን የመሠረቱ ቡድኖች ሳይሆኑ ከዛ በፊት ዘውግ ተኮር ጭቆናን የፈፀሙ ሀገሪቷን ይገዙ የነበሩ ቡድኖች ናቸው በማለት የዘውግ ማንነት ተኮር ንቅናቄዎችን ቀድሞ ለተፈጠረ ችግር ምላሽ ብቻ እንደሆኑ ያስቀምጣሉ፡፡
ሌንጮ በጽሑፋቸው የፌደራል ስርዓቶች በተፈጥሯቸው የአገር ግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ ጥንካሬ እንደሚያንሳቸው፣ የፌደራል ስርዓቱ የተዋቀረው ደግሞ የዘውግ ማንነትን (ቋንቋን) መሠረት አድርጎ ከሆነ የበለጠ ደካማ እንደሚያደርገው አትተዋል፡፡ የሌንጮን ሃሳብ የሚያጠናክር ተሞክሮ ለመጥቀስም የዓለም ግዙፏ ዲሞክራሲ ህንድ ከታላቋ ብሪታኒያ ቀኝ ግዛት ተላቃ ከፓኪስታን ጋር ፍቺ ከፈጸመች በኋላ ሃገሪቷን በጠቅላይ ሚነስትርነት ያስተዳድሩ የነበሩትጆዋሃርላል ኔህሩ “የገንጣይነት ስሜትን ያበረታታል እና ሀገሪቷን ወደ በለጠ መከፋፊል ያመራል” በሚል ምክንያት የሕንድ ፌደራል ስርዓትን ቋንቋን መሠረት አድርጎ መልሶ ለማዋቀር ይነሱ የነበሩ ምክረ ሃሳቦችን ለመቀበል ፍላጎት እንዳልነበላራቸው አቱል ኮህሊ የተባሉ የሕንድ ማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ “Can Democracies Accommod-ate Ethinic Nationalism? Rise and Decline of Self-determination Movements in India” በሚልርዕስ ባስነበቡት የጥናት ጽሑፍ ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡ ኔህሩ የኋላ ኋላ ግን የታሚል ቋንቋ ተናጋተናጋሪዎች የራሳቸው ፌደራል ግዛት (Tamil Nadu) እንዲኖራቸው ያነሱትን ጥያቄ ተቀብለው የታሚል ቋንቋ ተናጋሪዎች ግዛት እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡ የሰጉት የመበታተን አደጋ ግን አልተከሰተም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች በዘውግ ማንነት የተዋቀረ የፌደራል ስርዓት ለሀገሪቱ ግዛት አንድነት ተፈጥሯዊ አደጋ እንደሚጋብዝ የሚያረጋግጥ ቢሆንም በመጀመሪያ ሀገሪቱን ሆን ተብሎ ለመበታተን የተቀመረ ሳይሆን በወቅቱ ሥለጣን በእጃቸው የነበረው ልሂቃን አረዳድ መሠረት ቀደም ብለው የነበሩት የታሪክ ክስተቶች የጫኑት የውዴታ ግዴታ እንደነበረ፣ እንዲሁም በሁለተኛነት ደግሞ የመበታተን እና የግጭት አደጋው መኖሩ የግዛት አንድነቱን መበታተን የማይቀር (inevitable) ዕጣ ፈንታ እንደማያደርገው ያስረዳሉ፡፡
የዘውግ ብሔርተኛነት እና አምባገነናዊ ስርዓት (ሕወኃት/ኢህአዴግ)
የዘውግ ማንነቶች ከሌላ ዓይነት የማደራጃ (mobilizing) ማንነቶች (cleavages) ለምሳሌ – ከመደብ አንጻር ሲወዳደሩ ቀላል እና ምቹ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሃይማኖት ወይንም ደግሞ ቋንቋን የመሳሰሉ ማንነቶችን መሠረት አድርገው የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን አጀንዳ አድርገው የሚነሱ ቡድኖች ከሌሎች ዓይነት ቡድኖች አንጻር የተሻለ ማህበራዊ ውስብስብነት (social complex) ለምሳሌ፡- የሀብት እና የሥራ ክፍፍልን በውስጣቸው ስለሚይዙ እራሳቸውን ግዛት መመሥረት እንደሚችል ሙሉ ማኅበረሰብ ለማየት ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡
የዘውግ ማንነት ብዙሃነት ባለበት ሀገር ውስጥ የራስን እድል በራስ ለመወሰን የዘውግ ማንነታቸውን መሠረት አድርገው ተደራጅተው የሚነሱ ቡድኖች መኖራቸው የሚጠበቅ እውነት ነው፡፡ ይህ እውነታ የእርስ በርስ ግጭት እና የመበታተን ፍርሃትን በመንዛት ስልጣን ላይ ለመቆየት ለሚልጉ አምባገነኖች ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አሁን እንደሚስተዋለው የማዕከላዊ መንግስቱን ስልጣን የያዘው ቡድን በተለያዩ የዘውግ ማንነቶች መካከል የጨቋኝ እና ተጨቋኝ ታርጋ በመለጠፍ የእርስ በርስ ግጭት ስጋትን በማጋጋል የከፋፍሎ መግዛት ስልትን እየተገበረ ይገኛል – ከአማራ ዘውግ የነበሩ የገዢ መደብ ቡድኖች የፈጸሙትን ጭቆና እንደሽፋን በመጠቀም፡፡
ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ እራሱን ከተጨቆኑት ወገን አድርጎ ለመሳል ሚሞክርም በተግባር የሚያደርገው ግን የ ሚያረጋግጠው ይህንን አይደለም፡፡ ተጨቁነናል በማለት የዘውግ ማንነትን መሠረት አድርገው የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የተነሱ ንቅናቄዎችን ለማፈን ሲሞክር ነው የሚታየው፡፡ ለአብነት ያህል፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/፣ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ /ቤሕነን/፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ጋሕነን/ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባት /ኦነግ/ን የመሳሰሉ የዘውግ ማንነትን መሠት አድርገ ከተደራጁ ንቅናቄዎች ጋር አሁንም እልባት ያላገኘ ግጭቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ ስልጣን ላይ ያሉ አምባገነኖች እንደሚያደርጉት ሕወኃት/ኢህአዴግ መራሹ አገዛዝ እነዚህ የበለጠ ስልጣን እና የሃብት ቁጥጥር ጥያቄን የሚያነሱ ቡድኖችን በኃይል በመጨቆን የንቅናቄዎቹን ጥያቄዎች ለማፈን እየጣረይገኛል፡፡ እነዚህ የኃይል እርምጃዎች በተለይ በኦጋዴን አካባቢ እጅግ አሰቃቂ እንደሆነ በተለያየ ግዜ የሚወጡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ የመንደሮች መቃጠል፣ የሰላማዊ ወንዶች መገደል የሴቶች መደፈር በዋናነት በተጋጋሚ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
ሌላ ጥሩ የቅርብ ግዜ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የራሳቸውን ዕድል በራስ ለመወሰን /ሃይማኖታዊ አስተምህሮችን እና መሪዎችን በነፃነት ለመምረጥ/ ያነሱትን ጥያቄ ሕወኃት/ኢሕአዴግ መራሹ አገዛዝ ያስተናገደበት መንገድ ነው፡፡ ከ3 ዓመት በፊት ንቅናቄው ሲጀመር ጥያቄውን ይዘው ከመንግስት ጋር እንዲደራደሩ በእምነት ተከታዩ የተመረጡት መሪዎች አሁን እስከ 22 ዓመት የሚደር የእስር ቅጣት ተላልፎባቸው በማረሚያ ቤት ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የሕወኃት/ኢሕአዴግ እርምጃዎች የራስን ዕድል ለመወሰን የተደራጁ የዘውግ ማንነት ተኮር ድርጅቶች ውስጥ ቆምንለት ለሚሉት የዘውግ ማኅበረሰብ የበለጠ የሚጠቅመውን በድርድር ለማስገኘት የሚጥሩትን መካከለኞች (mo-derates) ወደ ጎን እንዲገፉና ጽንፈኞች ወደፊት እንደመጡ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
አምባገነናዊ ስርዓቶች በፍፁም ስጣናቸውን ለማጋራት ወይንም ከስልጣናቸው ላይ ቆርሰው ለመስጠት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም በፈቃደኝነት ስልጣን ለሌላ ያስተላለፈ ወይንም ከሚቆጣጠረው ማዕከላዊ ስልጣን ቆርሶ ለአካባቢ/የክልል መንግስት ያከፈለ የለም፡፡ ስለዚህም አምባገነናዊ ስርዓት የዘውግ ማንነት ብዝሃነት ባለበት ሃገር ውስጥ የዘውግ ማንነት ተኮር ግጭት ስጋትን ያባብሳል፡ እንዲሁም ግጭቶችን ወደማይፈቱበት የጭቆና እና የብጥብጥ አዙሪት ይከታል እንጂ ዘላቂ ሰላምን እና አብሮ መኖርን የሚያረጋግጥ ስርዓት አይደለም፡፡
የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝም የዘውግ ማህበረሰቦችን ጥያቄ ላለፉት 24 ዓመታት ያስተናገደበት መንገድ ጥያቄዎቻቸውን የመለስ ሳይሆን እንደውም ለማፈን በመሞከር ቅሬታቸው ውስጥ ለውስጥ እንዲብሰለሰል የሚገፋና በግዜ መፍትሄ ካልተሰጠው የሃገሪቷን የወደፊት እጣ ፈንታ ጨለማ የሚያደርግ ውጤት ይዞ ሊመጣ የሚችል አድርጎታል፡፡
አሁንም ቢሆን የሃገሪቷን አጠቃላይ መረጋጋት አደጋ ውስጥ የመክተተ አቅም የላቸውም እንጂ የስልጣን እና የሃብት ቁጥጥርን ለማሳካት በተቋቋሙ የዘውግ ማንነት ተኮር ንቅናቄዎች እና በማእከላዊ አገዘዙ መካከል (ከኦነግ እና አብነግን ከመሳሰሉ ቡድኖች ጋር) እንዲሁም በዘውግ ማኅበረሰቦች መካከል (በቅርቡ እየበረከተ የመጣው በነባሮች (natives) እና መጤዎች መካከል ያለውን የመሰለ) ደም እያፋሰሱ ያሉ ግጭቶች የሃገሪቷ ፖለቲካ ላይ ጥላ እያጠሉ ይገኛሉ፡፡
እስካሁን ካነሳናቸው ሀሳቦች በመነሳት እነዚህ የሃገሪቷ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ ያሉ ግጭቶች አምባገነኑ የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ እያስወገዳቸው/እየተከላከላቸው ሳይሆን ጭራሽ እያባባሳቸው እንደሆነ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት እውነታዎች መረዳት የሚቻለው አምባገነናዊ ስርዓቶች የውግ ተኮር ግጭቶችን ለመቆጣጠር የተሻሉ ስርዓቶች ናቸው የሚለው መከራከሪያ እንደሃልዮትም ሆነ በተግባር ሲፈተሽ በዓይነ ህሊና የተፈጠረ (imagined/perceived) ነው እንጂ እውነተኛ (real) አይደለም፡፡
መፍትሄው ዴሞክራሲ
በኢትዮጵያ ውስጥ የዘውግ ማንነት ተኮር የፌደራል መንግስታዊ መቃቅር የግዛት መበታተን የማይቀር ዕጣ ፈንታ እንደማያደርገው መረዳት ጠቃሚ የሆነውን ያክል ሃገሪቷ በዘውግ ተኮር የፌደራል ስርዓት በድጋሚ ከተዋቀረች በኋላ ሥሉጣንን ለ24 ዓመታት የሙጥኝ ብሎ የቆየው ሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዛ በአምገነናዊ ባህሪው የተነሳ የራስን ዕድል በራስ ለመወን የተነሱ የዘውግ ማንነት ተኮር ንቅናቄዎች ጥያቄዎችን በማፈን እና በመጨቆን ብቻ መፍትሄ ለመስጠት ስለሚሞክር ግጭቶችን እና የግጭት ስጋትን እያባበሰ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
እስከዚህ ከተግባባን ታድያ ደሞክራሲያዊ ስርዓት የዘውግ ማንነት ተኮር ግጭቶችን እና የመበተን ስጋትን የሚያስተናግድበት መንገድ ባይኖርም እንኳን ከአምባገነናዊ ስርዓት የባሰ የሚያደርገው እና በአምባገነኖች ስንጨቆን መኖርን የምንመርጥበት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል እንረዳለን፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የእንዲገነባ የሚሟገቱ ሁሉ የሙግታቸው መሠረታዊ ምክንያት ዴሞክራሲ የሀገሪቷን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ይፈታል በሚል እምነት ነው፡፡ በዘውግ ማንነት ተደራጅተው የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የሚደረጉ ንቅናቄዎች ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የወቅቱ የሀገሪቱ ቁልፍ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይመስረት ሲባል ይህን ቁልፍ ችግር /ጥያቄ/ በሚገባ የሚመልስበት መንገድ እንዳለው እርግጠኛ መኮን አለት፡፡
አቱል ኮህሊ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው ላነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች የዘውግ ብሔርተኝነትን በሚገባ ማስተናገድ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ኮህሊ እንደሚሉት ዴሞክራሲዎች ውስጥ (በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ዴሞክራሲዎች) የዘውግ ብሔርተኝነትን በሚገባ ለማስተናገድ አጠቃላይ የሃገሪቷ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ሁለት አስፈላጊ ባሕሪያት (proximate variables) ሊኖሩ ይገባል፡፡ የመጀመሪያው አስፈላጊ ባህሪ ጠንካራ ተቃማዊ ማዕከላዊ መንግስት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሀገሪቷን የሚመሩት ሰዎች የዘውግ ብሔርተኛ ቡድኖች የሚያነሱትን ጥያቄ ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆናቸው ነው፡፡
ዴሞክራሲን በእግር ለማቆም ጠንካራ የመንግስት ተቋማት ሊኖሩ እንደሚገባ ግልፅ ነው፡፡ በደንብ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስርዓት፣ ጠንካራ የመወሰኛ ምክር ቤት፣ ገለልተኛ የፍትህ አካላት /ፍ/ቤት እና ፖሊስ/፣ ገለልተኛ ጦር ሰራዊት እና ጠንካራ መገናኛ ብዙሃን ዴሞክራሲን እንደስርዓት የሚያቆሙት አስፈላጊ ተቋማት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግስት መተዳደር ከጀመረች ግዜ አንስቶ ስልጣን የተቆጣጠሩ አገዛዞች የህብረተሰቡ ታችኛው ክፍል ድረስ የሚደርስ ጠንካራ መዋቅር መዘርጋት ችለዋል፡፡ የስርዓቶቹ ጥንካሬ መሠረትም ይህንን መዋቅር ሥልጣን ላይ የመቆየት ዕኩይ ዓላማቸው ባግባቡ መጠቀም መቻላቸው ነው፡ የተዘረጋው መዋቅር ከላይ ወደታች ለሚፈስ ትዕዛዝ ተፈጻሚነት እንዲመች ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአንፃሩ እስካሁን ያሉት አገዛዞች ውስጣዊ (Inherent) በሆነ ባሕሪያቸው ምክንያት መዋቅሮቹ የሚሞሉት በአድርባይ ታማኝነት ስለሚሆን ከታች ወደላይ ሽቅብ የሚወጣው ሰንሰለት ላይ የበላዮች መስማት የሚፈልጉትን ማዕከል ያደረገ መረጃ እና ዘገባ (Report) ስለሚሆን የሚወጣው በዚህ ዘርፍ ውጤታማ አልነበሩም፣ አሁንም አይደሉም፣ ወደፊትም ሊሆኑ አይችሉም፡፡
ደሞክራሲያዊ ስርዓት ሲኖር በአንጻሩ እስካሁን የነበሩት/ያሉት/ አገዛዞች የፈጠሩትን ጠንካራ ቁልቁል መዋቅር እንደ መልካም ጎን በመውሰድ ነገር ግን መዋቅሩን ተቋማዊ በማድረግ የሁለትዮሽ ተዋረዱን/ወደታች እና ወደላይ/ ሚዛናዊ ያደርገዋል፡፡ በይበልጥም በሕዝብ ዘንድ ተቋማቱ ያላቸውን ተአማኒነት ነፍስ ይዘራበታል፡፡
ማዕከላዊ መንግስቱ ጠንካራና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ የሆኑ ተቋማት ባለቤት መሆኑ ለሃገሪቱ ይጠቅማል ብሎ የሚያስብበውን ራዕይ ተፈጻሚ ለማድረግ ያለውን አቅም በእጅጉ ያሳድግለታል፡፡ በተጨማሪም ተቋማዊ ሆኖ የተደራጀ ማዕከላዊ መንግስትን የሚመሩት ሰዎች ስልጣን የሚይዙት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ብቻ ስለሚሆን ስልጣን ቆርሶ ለመስጠት ስጋት የሚሆንባቸው ነገር ይቀንሳል፡፡ ስልጣናቸውን የሚጠብቁት እራሳቸው ሳይሆኑ የመረጣቸው ሕዝብና የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡
ኮህሊ በጥናታቸው እንዳሰፈሩት ጠንካራ ተቋማዊ ማዕከላዊ መንግስትን የሚቆጣጠሩ መሪዎች ከዘውግ ብሔርተኞች ጋር በሚያደርጉት ድርድር ወቅት ቆፍጠን ያለ (Assertive) አቋም ለመያዝ የሚያስችላቸው አቅም ይኖራቸዋል፡፡ የዘውግ ብሔርተኞች ለሚያነሷቸው የግዛት አንድነትን ወይንም የአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ጥያቄዎች ላይ ገደብ ማበጀትም ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የማዕከላዊ መንግስት መሪዎች የዘውግ ብሔርተኞችን ፍላጎት ለማስተናገድ ፈቃደኛ የሚሆኑ ከሆነ የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን በዘውግ ብሔርተኞች የሚደረገው ንቅናቄ እውነተኛ ውጤቶችን የምር በሆነ ማመቻመች (Compromise) ማስገኘት ስለሚችል እየከሰመ ይሄዳል፡፡
ኮህሊ አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታው (Setting) ጠንካራ ተቋማዊ ማዕከላዊ መንግስት መኖሩ እና ስልጣን የተቆጣጠሩት መሪዎች የዘውግ ብሄረተኞችን ጥያቄ ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆናቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች የዘውግ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችንና መበታተንን የሚያስቀሩበትና ለዘላቂ ሰላም መፍትሄ መሆን የሚችሉ አስፈላጊ ባህሪያት እንደሆኑ ቢጠቁሙም ሌሎች ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮችም እንዳሉ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በምሳሌነትም ማዕከላዊ መንግስቱ ከጎረቤት መንግስታት ጋር ያለውን ግንኙነት አንስተዋል፡፡ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት እና ጣልቃ ገብነት ፅንፈኛ የዘውግ ብሔርተኞችን መሣሪያ በማስታጠቅ፣ ስልጠና በመስጠትና መሸሸጊያ የሚሆናቸው ቦታ በማቻቸት የንቅናቄዎቹን እና የግጭቶችን ዕድሜ የማራዘም ሚና ሊጫወት እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡
በተጨማሪም ኮህሊ አንድ አስፈላጊ ትንተና ይሰጣሉ፡፡ የዘውግ ማንነት ተኮር የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የሚደራጁ ቡድኖች እንደማንኛውም የፖለቲካ ዓላማ ያለው ቡድን ማየት እንዳለብን ይመክራሉ፡፡ ሃይማኖትና ቋንቋን የመሳሰሉ የማንነት መገለጫዎች ሕዝብን በቀላሉ ለማደራጀት በማስቻል ከሌሎች ማንነቶች ቢለዩም ጥያቄዎቻቸው በከፊልም ቢሆን ሲሟሉላቸው ተስማምቶ አብሮ ለመኖር የማይችሉ ዓይነት ቡድኖች አይደሉም፡፡ ለዚህ ትንተናቸው ማጠናከሪያ የሚያደርጉት የታሚል ቋንቋ ተናጋሪዎች በ1960ዎቹ በሰላማዊ ድርድር/ታሚል ናዱ/ ግዛትን መመሥረት ከቻሉ በኋላ የሕንድ ፌደራል ስርዓት ውስጥ ዋነኛ እና መገንጠል የማይችሉ አካል ሆነው መቀጠላቸውን ነው፡፡
በኢትዮጵያም ቢሆን ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡ የዘውግ ማንነትን መሠረት አድርገው የተደራጁ ቡድኖችየስልጣን እና የሃብት ቁጥጥር ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎች ከተመለሱ የግጭት እና የመበታተን ስጋቱ እንደሚቀንስ መገመት አይከብድም፡፡ አለማየሁ ገዳ “Does Conflicts Explain Ethiopia’s Backwardness? Yes!” በሚል ርዕስ በጻፉት ጥናት የኦሮሚያና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ተወላጆች የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን በተለያየ ሁኔታ “ተጨቁነናል፣ ሕዝባችንም በሰሜን ኢትዮጵያ ተወላጆች /አሁን ሕወሓት እወክለዋለሁ የሚለው ትግራ እና በቀደሙት ስርዓቶች ደግሞ የአማራ ዘውግ ማኅበረሰብ አባላት አስገባሪነት/ ተጨቁኖ በድህነት እየማቀቀ ነው” በሚል መከራከሪያ እስከመገንጠል የሚደርስ ጥያቄ ቢያነሱም በኦሮሚያና ደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሕዝቦች እ.ኤ.አ ከ1995-2000 ዓ.ም ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በተለካ የድህነት መጠን መለኪያ መሠረት ከሰሜን አካባቢ ካሉት ሕዝቦች የተሻለ ውጤት ማሳየታቸው የልሂቃኑ የምር ጥያቄ ስልጣን መጋራትና የሃብት ቁጥጥር መሆኑን እንደሚያስረዳ እራሳቸው አለማሁ ገዳ፣ ከአበበ ሽመልስ እና ጆን ዊክስ ጋር ሆነው የሰሩትን ሌላ ጥናት ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይም የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር የሚዲያ አውታሮች ከግዜ ወደግዜ ትኩረታቸውን አካባቢው ላይ ያለውን የተጥሮ ሃብት ስለመጠበቅ እያደረጉት እንደመጡ ማርቲን ሹብዬ እና ጆሃን ፒርሰን የተባሉ ስዊዲናዊያን ጋዜጠኞች በ438 በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡
ደሞክራሲ በሁለት እግሩ እስኪቆምስ?
አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ቀደም ብሎ ከነበሩት አገዛዞች በተየ ሁኔታ ከፋፍሎ ለመግዛትና ስልጣን ላይ ለመቆየት እንዲመቸው የዘውግ ማንነት ጉዳይን ከሚገባው በላይ ዋጋ ሰጥቶ ማራገቡ በዘውግ ማኅበረሰቦች መካከል ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መቃቃር ስሜትን መፍጠር እንዲሁም በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ቁንጮ ቡድን ከአንድ የዘውግ ማኅበረሰብ (ትግራይ) ከመሆኑ የተነሳ በሀገሪቱ ካሉ የሌላ የዘውግ ማኅበረሰብ ተወላጆች የዘውግ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ የአገዛዙ ባለቤትና ተጠቃሚ ተደርጎ መታየቱ በሽግግር ወቅት ሊነሳ የሚችል የግጭትና የመበታተን ስጋትን ከፍ እንደሚያደርገው የሚቀርበው መከራከሪያ ውሃ የሚቋር ይመስላል፡፡
ነገር ግን አምባገነናዊ ስርዓት ተወግዶ ተቋማዊ ጥንካሬ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪገነባ ድረስ በሚፈጠረው ክፍተት ግጭትና የመበታተን አደጋ እንዳይከሰት የሚከለክል ያክል ማኅበራዊ መስተጋብሮች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ጥናቶች ይተቁማሉ፡፡ ዶናልድ ሌቪን ታላቋ ኢትዮጵያ በሚለው ጽሑፋቸው ውስጥ በእርስ በርስ ጋብቻ፣ በንግድ፣ በስደትና ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ የዳበረው መስተጋብር ከውስጥ የሚነሱ የመከፋፈል አደጋዎች ብቻ ሳይሆን ከውጭም ለሚቃጡ ጥቃቶች መቋቋም የሚያስችል ስጦታ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የቅርብ ጊዜ ሽግግሮችም የሚመሰክሩትም (የኤርትራን ውስብስብ ታሪካዊ ሁኔታ ትተን) ይህንን ነው፡፡ ይህ ማኅበራዊና ታሪካዊ እውነታ ሌንጮን ጨምሮ በሽግግር ውስጥ ስናልፍ ወደብጥብጥና መበታተን እናመራለን የሚለውን የስጋት ትንተና የተጋነነ እና ተጨባጭ ታሪካዊ ማስረጃ የሌለው እንደሆነ ያሳያል፡፡
መደምደሚያ
አለማየሁ ገዳ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው ማጠቃለያ ላይ ኢትዮጵያን የግጭት መንስኤ ለመሆን የሚያሰጋት ምክንያት ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሽኩቻ እንደሆነ ጠቁመው ይህንንም ስጋት ለመቆጣጠር ብቸኛው አማራጭ የሕዝብ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ፖለቲካዊ መሻሻል (reform) እንደሆነ ይመክራሉ፡፡
በመጨረሻም ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ፈጣን ምላሽ (quick-fix) ያለው ስርዓት ነው የሚል ክርክር ማንሳት ባይቻልም፤ ፈረንጆቹ እነደሚሉት ቀስ በቀስ ግን በርግጠኝነት (slowly but surely) ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ ከጥርጣሬ በላይ የሆኑ ምክንያቶች አሉ፡፡
Filed in: Amharic