>

በሳውዲ የሃዘኑ ቤት ምክክሮች እና የመካ ሃበሾች ሮሮ ! (የማለዳ ወግ - ነቢዩ ሲራክ)

የሳውዲ ነዋሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተገናኘ በራሱ በማህበረሰቡና በሃገሩ ጉዳይ ዙሪያ ” ያገባኛል ” ሲል ሰብሰብ ብሎ ግልጽ የሚወያይ የሚመካከርባቸው አጋጣሚዎች ውስን ናቸው ። ውስን ከሆኑት መገናኛና መሰብሰቢያ አጋጣሚዎች ዋንኞቹ ደግሞ የሃዘንና የደስታ አጋጣሚዎች ለመሆናቸው ጠንቋይ መቀለብ የለብዎትም። በተለይም በሃዘን ላይ ሃዘን ደራሹ ሰፊ ጊዜን ተቀምጦ ስለሚያስተዛዝን በሰፊው ጊዜ በርካታ ጉዳዮች እየተነሱ ይጣላሉ። ምንም እንኳን በአብዛኛው አጋጣሚ የሚነሱ ጉዳዮች ከፍሬ ከርስኪው ፍልስፍናና ዘባተሎ ፖለቲካ ጀምሮ በሳል የተባሉ የማህበረሰቡ መሰረታዊ ኑሮ ውይይት ምክክሮች በመድረኩ መልኮች ናቸው።
በሃዘን ቤት በአስተዛዛኙ በኩል እንደ ጊዜ መግደያና ሃዘንተኛውን ሃዘን መረሳሻነት ከሚነሱት ውይይቶች መካከል ዘባተሎ የሚባሉትን ከግለሰብ ቡጨቃ ሃሜት እሰከ ጥላቻን መሰረት ያደረጉትን ውይይቶች ይስተዋላሉ። ከፍ ከፍ ሲል ከከባቢ ፖለቲካ ጀምሮ አለም አቀፉን የሃይል ሚዛን የሚነካካ ውይይት አጀንዳ ተካቶ ወጉ ይወገወጋል።
በዚህ ማዕቀፍ ወሬው ሲደራ ከሃይማኖት ጋር የተቆራኘው ፖለቲካና ፍልስፍናው የወጨመርና የሃዘኑ ቤት ትዕይንቶችም ናቸው። ውይይቱ እንዲህ አግድሞ ከሄደና ከስሜት ያልጸዳ ከሆነ ደግሞ ለአፍታም ቢሆን በጠባቧ ቤት አደገኛ መርዝ ሆነው ወደ ፍጥጫ የሚያመሩበት በርካታ አጋጣሚዎችን ተመልክቻለሁ። በዚህ መሰል ቅኝት የተቃኙት የሃዘን ቤት ውይይትና ምክክሮች ወደ ግጭት እና ንትርክ ሲያመሩ ማየት ደግሞ ያማል ።
በሃዘን ቤት ውይይት ወጋወጉ መድረግ ወደ ሃገር ፖለቲካ ሲያመራ ደግሞ ክፍፍል ሙግቱ ይከራል። ፖለቲካው ቀርቶ በሰንካላ ግልጋሎቱ የሚነሳው የሳውዲ ሪያድ ኢናባሲና የጀዳ ቆንስል ድክመት ሳይነሳ የማይቀር አፍ መፍቻ ነው ብል ማጋነን አይሆንም ። በነዋሪው የሚደርሰው መብት ገፈፋና በሚጎድለው መብት ጥበቃ ተነስቶ ሁሉም ሳይስማማ የሚለያይባቸው አጋጣሚዎች የሉም ማለትም ይቻላል። እነ “እንቶኔ” በውይይቱ ካሉ በችግራችን ዙሪያ “አንድ ድምጽ ይኑረን!” የሚለውን ነዋሪ ሃሳብ ያላጉታል። የሃዘን ቤት አንድ ጥግ መድረኩ ያቆሽሹታል። ለሚሰነዘረው ውሃ የሚያነሳ ሂስ መልስ ባይኖራቸውም በነጻነት ሃሳቡን የሚያራምደውን ወገን በተዘዋዋሪ መንገድ በፍርሃት ያሾሩታል። ሃሳቡን በነጻነት የሚገልጸውን ዜጋ “የተቃዋሚ፣ የድምጻችን ይሰማ አባል” እና “አሸባሪ ” የሚል ታርጋ ተለጥፎብህ “ከነቤተሰብህ ወደ ሃገር ቤት መግቢያ መንገዱን ያሳጡናል !” ብለው በፍርሃት ስጋት ወገናቸውን ያሸማቁታል።
በዚህ እና በመሰል አውድ በሚናጡ ሃዘን ቤቶች እግር ከጣልዎ እዚያ ያደረሰዎን እግር ረግመው ፣ የሄዱበትን የማጽናናት ጉብኝት ረስተው ” የሟችን ነፍስ ይማር !” ብለው እንኳ እንዳይመለሱ ቀልብዎትን ይነጥቁዎታል። ሃዘንተኛውን የሃዘን ተካፋይ መሆንዎን ሳይገልጹ በብስጭት ወደ ቤተዎ መመለስዎ አይቀሬ ነው ። ይህ መሰሉ አጋጣሚ ጎድዎታልና ደግመው ሃዘን ቤት የሚባል መሄድ እስኪያስጠላዎ ሊያማርሩት ይችላሉ ።
ከዚህ በተጓዳኝ ነዋሪው በሃዘን ቤቶች ሲገናኝ ቀልብ ሳቢ ከሆነ ማህበራዊ አጀንዳ ጀምሮ አስተማሪና እና አነቃቂ በሆኑ አለማዊና ሰማያዊ ትምህር የታጀቡ የሚሆኑበት አጋጣሚ በመልካም መድረክነቱ ይጠቀሳሉ። የሳውዲው ሃበሻ የሃዘን ቤት ውይይት፣ በስብጥር የማህበረሰቡ ክፍሎች የሚነሱ በመሆኑ ከሚነሱት ምክክር ሃሳቦች ጠቀም ያለ ትምህርትና ተሞክሮ የሚስተጋባባቸው መድረክም ናቸው። በመልካሙ መድረክ ሳውዲን እንደ ሃገሩ ቆጥሮ ሶስት ጉልቻን መስርቶ ፣ ልጅ ሃብት ንብረት አፍርቶ ከሚኖረው ስደተኛ በሃገር በህጋዊ ስም በተመሰረቱ ኤጀንሲ ተብየ ደላሎች ተታለው ሳውዲን እስካጥለቀለቋት ግፉአን የኮንትራት ሰራተኞች አበሳ የሚነሱትን ምራቅ የሚያስውጡ ውይይቶች ጀሮ ገብ መሆናቸውን የታዘብኩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። ዳሩ ግን… ዳር የሚያደርሳቸው የለም! አንዱ ወዳጀ በዛሬው የሃዘን ቤት ውሎየ እንዳለው እና እኔም አሳምሬ እንደማውቀው የተነሱትን የማህበራዊ ችግሩ መፍትሄ ጠቋሚ ሃሳቦች ከሃዘን ቤት መድረክ ውይይት አያልፉም። አንኳር አንኳር የሆኑ ማህበራዊ ችግሮች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው ዳር የደረሱበት አጋጣሚ ቀርቶ የጋራ ግንዛቤ ያገኙና ሰምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ከተወያዩ ጋር አብረው ስለመቆየታቸው ያጠራጥራል። ከሃዘን ቤቱ ስንወጣ ያ ሁሉ ቁም ነገር ሁሉ ከሃዘኑ ቤት በር ሲወጡ እንደ ጉም ይበናል ! ያ ባይሆን ውይይት ምክክሮች የሚያደርሳቸው ተገኝቶና ሰሚ ቢያገኙ ችግራችን በመቅረፉ ረገድ ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይገድም ።
ይህችን ማስታወሻ እንድጽፍ ምከንያት የሆነኝ በአንድ ጎረቤቴ ሃዘን ልደርስ ጎራ ያልኩበት አጋጣሚ ነው። በዛሬው ሃዘን ቤት ውሎየ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ተገናኝች ከትናንት በስቲያ በሳውዲ ወህኒ ቤት ቆይታው በገዛ ወገኑ ተደብድቦ አካለ ስንኩል የሆነውን ወንድም ጉዳይ አንስተው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸውልኛል። በሆነው ከማዘን አልፎ አስፈላጊ በሆነ ሰአት የእርዳታ እጃቸውን እንደሚዘሩለት ቃል የገቡልኝ በርካቶች ናቸው። በዚህ ወንድም ዙሪያም ብዙ ጠቃሚ ምክክሮች ያደረግን ሲሆን ማህበራዊ ጉዳዮችን ደፍረን እንዳንናገር ቀፍድዶና ተብትቦ ስላያዘን ራስ ወዳድነትና ፍርሃት ጠቃሚ ሃሳብ መለዋወጣችን አልቀረም።
ሃዘን ሊደርሱ ከጅዳ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ከኮረብታማዋ የሙስሊማን ቅዱስ ከተማ የመጡ ወንድሞቸን ጋር የነበረን መልካም ቆይታ ነበር። በውይይቱ መካከል ያካፈሉኝ ሮሮ ያልተለየው መረጃ ይህችን ማስታወሻ እንድጨነቋቁር ዋንኛ ምክንያት በሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ልጠቁም ..
በዛሬው የሃዘን ቤት መድረክ የሰማሁት የመካ ነዋሪ ሰሞነኛ ሳይሆን ለአመታት የሰነባበተ ችግር መሆኑ እርግጥ ነው። ጉዳዩን ከአመታት በፊት እከታተለው የነበረ በመካ ላሉ ኢትዮጵያን የትምህርት ቤት ምስረታ ጉዳይ ነው። ነዋሪው ከአንድም ሁለት ሶስቴ ገንዘብ በተደጋጋሚ ያወጣ ቢሆንም የገንዘቡም የትምህርት ቤት ምስረታው ወሬ ሽታው እንኳ መጥፋት መካዎችን አሳዝኗቸዋል። ምሬታቸውን መዋጮ ያደረጉባቸውን የገንዘብ ደረሰኞች ዋቢ አድርገው መረጃቸውን አጋርተውኛል ። ከሁሉም በላይ ያሳዘናቸው ደግሞ ለጉዳዩ አውቅና ሰጥቶ ይንቀሳቀስ የነበረው የጅዳ ቆንስል ዝምታ አይደለም። ከእነርሱ ይልቅ በሳውዲ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ከበሬታ ያላቸው የተማሩ የተመራመሩ የሃይማኖት አባቶች በተነሳሽነት የጀመሩት ትምህርት ቤት ምስረታና መረጃ አለመስጠታቸውን ነዋሪዎች ገልጸውልኛል ። በተደረጉት ስብሰባዎች በኮሚቴው በኩል ” ፈቃድ ተገኘለት!” ተብሎ የተለፈፈው ትምህርት ቤት ጉዳይ የት ደረሰ ? ሴት እህቶች የአንገት እና የእጣት ወርቃቸውን አየለገሱ የተጠራቀመው በመቶ ሽዎች የሚቆጠር ገንዘብ የት ገባ ? የመካ ሃዘን ደራሾች ጥያቄ ነው ! እኔም ጠቃሚው ውይይት እና ምክክር ከሃዘን ቤቱ ስወጣ አንደጉም ከውስጤ ሳይጠፋ መዘጋግቤ ሰሚ ከተገኘ በሚል የዛሬ የሃዘን ቤት ገጠመኘን ልቋጭ ወደድኩ …የአንድየ ፈቃድ ከሆነ አቅም በፈቀደ መጠን መረጃዎችን ሰባስቤ በማለዳ ወጌ ማውጋታችንም አየቀሬ ነው ባይ ነኝ !
የሟች ነፍስ ይማር !
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ

Filed in: Amharic