>

አንዳንድ ስህተቶች፣ አዲስ አይን ማውጣት፣ ወደውስጥ መመልከት ያሻል፤ [ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ]

Bedilu Waqjira DRበረታችንን ክፍቱን አናሳድርም፤ ያረባነውን፣ ያሰባነውን አውሬ ሊቀራመትብን፣ ሌባ ሊነዳብን ይችላል፡፡ ምን ብናሳድጋቸው፣ ምን ብናሰባቸው እንሰሳት ናቸውና ለነዳቸው ይነዳሉ፤ ጥርሱን ካገጠጠ አውሬም ራሳቸውን ሊከላከሉ አይቻላቸውም፡፡ ሰው ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ራሱን ይከላከላል፤ ይጠብቃል፡፡ ሰው ለነዳው አይነዳም፤ የሰበከውን አይከተልም፡፡ በዚህም የተነሳ በበረታችን እንዳሉት ከብቶች፣ ላሳደግናቸው ልጆቻችን አንሰጋም፡፡ ልጆቻችንን ለመስረቅ ቀድሞ ህሊናቸውን፣ ማስተዋላቸውን መስረቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም፤ በስነምግባር ኮትኩተን ያሳደግናቸው ልጆቻችንን፣ ማንም በአፍታ ሰበካ ከጎጇችን ሊሰርቃቸው አይችልም፡፡ አስራ ስምንት አመት አብሮን የኖረ ልጃችንን የአፍታ ሰባኪ ካሸፈተብን፣ ድሮም አብሮን አልነበረም ማለት ነው፡፡ በስነምግባርና በእውቀት አንጸን አላሳደግነውም ማለት ነው፡፡ ከብብታችን ለመሽሎክ ‹‹ተከተለኝ›› በይ ጠሪ እየጠበቀ ነበር ማለት ነው፡፡ . . . እና ይህ ሲሆን ወላጅ ሰራቂውን፣ ወይም ልጁን መኮነን የለበትም፤ መጠየቅ ያለበት ራሱን ነው፡፡ ለአስራ ስምንት አመታት ያነጽኩት ግምብ እንዴት በአንድ ቀን ሰበካ ይናዳል? ወይስ ራሴ የገነባሁ መስሎኝ ሳፈርሰው ኖሬያለሁ? ወይስ መስሎኝ እንጂ ከቶም ያነጽኩት ግምብ አልነበረም? ምን ብንበድለው ነው ያሳደግነው ልጃችን ፊቱን ያዞረብን?. . . . ወዘተ. የመሳሰሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ አለበት – ወላጅ፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች የሚገኘው መልስ እድሜው ገፍቶ ላላረጠ ወላጅ፣ ቀጣይ ልጁን እንዴት ማሳደግ እንዳለበት ትምህርት ይሆናል፡፡
.
ኢህአዴግም ማድረግ ያለበት እንዲሁ ነው፡፡ ለሀያ አምስት አመታት ያስተዳደረው ህዝብ (ወጣትም ይሁን ጎልማሳ) ለተቃውሞ አደባባይ ሲወጣ፣ መጠየቅ ያለበት ራሱን ነው፡፡ ለሀያ አምስት አመታት ያስተዳደረው ህዝብ፤ መንገድ ሰራሁለት፣ ትምህርት አስፋፋሁለት፣ ድህነቱን ቀነስኩለት የሚለው ህዝብ፤ በግዳጅ ለጦርነት ከመማገድ አዳንኩት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቼ ስራ ፈጠርኩለት የሚለው ወጣት፣ መንገድ ዘግቶ፣ ድንጋይ ወርውሮ፣ ለተቃውሞ ሲወጣ፣‹‹በአሸባሪዎችና በጸረሰላም ሀይሎች ስብከት ተደልሎና ተወናድዶ ነው›› የሚል ምክንያት ማቅረብ ውሀ አያነሳም፡፡ እና ኢህአዴግ ራሱን መጠየቅ አለበት! ከጫንቃው ላይ ደርግን ያህል ግፈኛ መንግስት ያስወገድኩለት ህዝብ፣ ያስተማርኩትና ስራ የፈጠርኩለት ወጣት፣ በቀናት የሽብርተኞች ስብከት ተደልሎ ለጥፋት ሊነሳ ይችላል? ከቻለስ ስለምን በአሸባሪዎች ከንቱ ስብከት ተቃወመኝ? እኔ ሬዲና ቴሌቪዥን ይዤ፣ እየተሸሎከለኩ የሚሰብኩ ሀይሎች፣ እንደምን ተሰሚነት አግኝተው አመጽ ሊነሳ ቻለ? ከእኔ ልማታዊ- ተግባር የእነሱን ሽብራዊ ስብከት ስለምን ተቀበለ? ወይስ ስራ እየፈጠርኩለት፣ ድህነቱን እየቀነስኩለት አልነበረም? . . .ወዘተ. የመሳሰሉ በርካታ ጥያቄዎች ለራሱ ማቅረብ አለበት፡፡
.
ይህ ካልሆነና፣ ኢህአዴግ ችግር በተፈጠረ ቁጥር፣ ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር፣ ‹‹አሸባሪዎችንና ‹‹ጸረልማት ሀይሎችን›› ተጠያቂ የሚያደርግ ከሆነ፣ችግሩን ከስሩ አልመረመረምና ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ይልቁንም እንዲህ ያለው ራስን ነጻ ማውጣትና ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ፣ እብሪትን ስለሚያጸና ሀይልን ወደመጠቀም ይገፋፋል፡፡ ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል በተፈጠረው ችግር የደረሰው የሞት አደጋም ሰበቡ ይኸው ነው፡፡ ኢሕአዴግ እውነት ‹‹ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ከህዝቡ ወገን ባልሆኑ ሀይሎች ነው›› ብሎ የሚያምን ከሆነ፣ የተወናበደው ተቃዋሚ ላይ፣ ተወናብዶ እንጂ የእኔ ነው የሚለው ተቃዋሚ ላይ መተኮስ የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ኢህአዴግ በተቃውሞ የሚደርሰውን የሰላም መቃወስና የንብረት መውደም የመከላከል ሀላፊነት እንዳለበት አልዘነጋሁም፡፡ ግን በምንም መንገድ የሰው ህይወት መጥፋት የለበትም፡፡ በየሀገሩ ከተሞችን ያነደደ ተቃውሞ ያለምንም ህይወት መጥፋት ሲያልፍ አይተናል፡፡ የፈረሰው ድልድይና ህንጻ መልሶ ሲገነባም አይተናል፤ የሞተ ሰው ግን ተቃውሞው አልፎ ሰላም ሲወርድ፣ ከመቃብር ሲነሳ አልተመለከትንም፡፡
.
አብዛኛውን ጊዜ ኢህአዴግ በተቃውሞ ወቅት የሚደርሱ የሞት አደጋዎችን ምክንያታዊ ለማድረግ፣ በፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን እንደመግፍኤ ያቀርባል፡፡ ይሁንእንጂ ይህ ተቀባይነት የሚኖረው፣ አማጺው በነፍስወከፍ ጠመንጃ ታጥቆ የወጣ እንደሁ ነው፤ ይህ ከሆነ ጉዳዩ ጦርነት ሆኗል ማለት ነውና ከፖሊስም በላይ የጦር ሰራዊት ሊገባበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚው ዱላና ድንጋይ ይዞ ቢወጣም እንኳን፣ በድንጋይና በዱላ ንብረት ቢያወድም፣ ፖሊስ ላይ ጥቃት ቢሰነዝር እንኳን፣ ጥይት ተኩሶ መግደል ተገቢ አይደለም፡፡ ፖሊስ ህዝብ ጠባቂ ነው፤ ህዝቡን የሚጠብቀው ደግሞ ከሌባና ከቀማኛ ብቻ ሳይሆን፣ ከህዝቡና ከራሱ ከፖሊሱ ጭምር ነው፡፡ ፖሊስ መኪና አቃጠልክ፣ መስታወት ሰበርክ ብሎ ህዝቡ ላይ የሚተኩስ ከሆነ፣ ህዝቡን ከራሱ ከህዝቡ አልጠበቀውም፡፡ ፖሊስ እኮ እኔን ከራሴም ሊጠብቀኝ ሀላፊነት አለበት፤ ለዚህ ነው እራሱን ሊያጠፋ የተዘጋጀን ሰው ፖሊስ መረጃ ካለው፣ ሊያስጥለው ሀላፊነት ያለበት፡፡ ፖሊስ በድንጋይ ፈነከትከኝ ብሎ፣ ህዝብ ላይ የሚተኩስ ከሆነም ከራሱ ከፖሊስ አልጠበቀውም፡፡ ፖሊስነት በማንኛውም ሁኔታ ህዝብን የማስቀደም ታላቅ ሀላፊነት ነው፡፡ ይህ ሲሆን፣ ፖሊሶቻችንን ስለኛ ስለሚከፍሉት መስዋእትነት እንወዳቸዋለን፡፡ የምንወዳቸው ከሆነ ደግሞ ስለኛም ደህንነት ቢሆንም እንኳን እንዲጎዱ አንፈልግምና እንሳሳላቸዋለን፤ እንጠብቃቸዋለን፡፡ . . . እናም በመጨረሻ በምንም ሁኔታ ውስጥ እንዳንጎዳ ይጠብቁናል፤ እኛም እንዲሁ አንጠብቃቸዋለን፡፡

Filed in: Amharic