>
5:13 pm - Saturday April 19, 6836

በደርግም በህወሓትም ያለለፈላት ሓውዜን፤ የሐውዜን ህዝባዊ ስብሰባ ተሰረዘ! (ኣብርሃ ደስታ ከሓውዜን)

ሰኔ 15, 1980 ዓም በግፍ የተጨፈጨፈው የሐውዜን ህዝብ እስካሁን ድረስ የመሰብሰብ መብቱ እንደተነፈገ ነው። የህወሓት ባለስልጣናት የሐውዜንን ሴራ እንዲታወቅ አይፈልጉም፣ የህዝቡ በደል እንዲጋለጥ አይፈልጉም፣ ህዝብ ለነፃነቱ እንዲታገልና እንዲደራጅ አይፈልጉም። ምክንያቱም ካወቀና ከተደራጀ መብቱ ይጠይቃል፣ ለነዚህ ጨኳኝ ገዢዎች አይምበረከክም። ለዚህም ነው ህዝብ እንዲሰበሰብ የማይፈልጉ። መስዋእት የተከፈለው ለምንድነው?

ዓረና ፓርቲ ከሐውዜን ህዝብ ጋር ለመወያየት ለዛሬ ዓርብ ግንቦት 15, 2006 ዓም ቀጠሮ ይዞ ነበረ። እሮብ የተሳካ ቅስቀሳ አድርገናል። የመንግስት መስርያቤቶች ተዘግተው ባለስልጣናት የዓረና በራሪ ወረቀት የሚቀበል ህዝብ ያስፈራሩ ነበር። ወረቀት ተቀብለው እንዲቀዱት ታዘው ፍቃደኛ ያልሆኑ አርሶአደሮች መታሰራቸውንም መረጃ ደርሶኛል። ትናንት ሐሙስ ግን ቅስቀሳ እንዳናደርግ ዕንቅፋት ፈጠሩ። ስብሰባ ለማካሄድ አዳራሽ ተፈቀደላቹ እንጂ ለመቀስቀስ አልተፈቀደላችሁም አሉን። ዓርብ ጧት በማይክሮፎን እየቀሰቀስን ወደ መሰብሰብያ አዳራሽ ስንሄድ ሁለት ታርጋቸው የተነቀለ ሞተሮች ሁለት አባሎቻችን ገጩ (ከባድ ጉዳት አልደረሰባቸውም)። ጉዳት ካደረሱ ባለስልጣናት አንዱ “ሶኬት” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አደጋ የደረሰባቸው የዓረና አባላት ደግሞ አቶ ፍሰሃ ፀጋይና መምህር ክፍሎም ኃይለሚካኤል ናቸው።

አዳራሹ ተከፍቶልን ህዝብ እየተፈተሸ መግባት ሲጀምር ግን የቀበሌ ሴቶችና የተወሰኑ ህፃናት በወረዳው አስተዳዳሪዎች እየተመሩ የህወሓት ባንዴራ ይዘው ሰልፍ አካሄዱ። እየተሳደቡ ህዝብ ወደ አዳራሽ እንዳይገባ በሩ ዘጉት። ለሰብሰባ የመጣ ሰው ይሰደብና ይደበደብ ጀመር። ወደ 500 የሚጠጋ ህዝብ ለመሳተፍ የመጣ ሲሆን በረብሻው ተበትኗል። ህዝባዊ ስብሰባውም ተሰርዟል። የሓውዜን ህዝብ ከተጨፈጨፈ ከ26 ዓመት በኋላም የመሰብሰብ መብቱ አልተከበረለትም።

የሐውዜን ወረዳ ፖሊስ ግን ባልተለመደ ሁኔታ ሕገመንግስታዊ ግዴታው ተወጥቷል። ባለስልጣናቱ የዓረና አባላትን ለመምታት የሞከሩ ሁሉ ከፖሊስ ሲጋጩ አጋጥሞናል። ባለስልጣናትና የተወሰኑ በነሱ የተላኩ ወጣቶች ረብሻ ለመፍጠር ሲሞክሩ ፖሊስ ፀጥታ ለማስከበር ጥረት ሲያደርግ ነበር። በፖሊሶችና በባለስልጣናት መካከል ግልፅ የሆነ ልዩነት ነበር። ፖሊስ እኛን ለመጠበቅ ሲተጋ ባለስልጣናቱ ግን ችግር ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር። የሓውዜኑ ጉዳይ ዓዲግራት ከተፈፀመው ወንጀል ጋር ይመሳሰላል። ልዩነቱ የዓዲግራት ፖሊስ በባለስልጣናቱ ትእዛዝ የሚሰራ ሲሆን የሐውዜን ፖሊስ ግን ፀጥታ ያስከብር ነበር።

ላደረገልን ትብብር የሐውዜን ፖሊስን እናመሰግናለን። ከሐውዜን ባለስልጣናት ግን ለፍርድ የሚቀርቡ ይኖራሉ። እኛን ለመሳደብ፣ ለመግደል፣ ምግብ ለመከልከል ሞክረዋል። አልጋ ለመከልከል ሞክረው ግን አልተሳካላቸውም።

የሐውዜን ህዝብ ጥሩ አቀባበል ሲያደርግልን ባለስልጣናቱ ይናደዱ ነበር። የሐውዜን ህዝብ የለውጥ ፍላጎት የሚደንቅ ነው። የሐውዜን ህዝብና ፖሊስ እንዲሁም የቅዱስ ላሊበላ ሆቴል ባለቤትን እናመሰግናለን።

Filed in: Amharic