>
4:03 am - Thursday October 22, 2020

የሃይለማርይም እንባ እና የኔ አጭር ዘገባ [ ሄኖክ የሺጥላ ]

Hailemariam Desalegnአቶ <ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር> ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ ጠቅላይ ሚንስቴር ፣ ጠቅላይ ሚንስቴር የሚሸት ነገር ተናገሩ ፣ ልል አልኩና ፣ እስኪ ከመቸኮል ፣ ምን አዲስ ነገር ተናገሩ ? ህዝቡ የማያውቀውን ፣ ወይም ህዝቡ ያጣውን እና ከመሪው መስማት የሚሻውን ምን አዲስ ነገር ተናገሩ ?

እንገምግማቸው ( ማለቴ ከተፈቀደለን ) ፣ እንደ እሳቸው ንግግር ፍቃድ የተሰጠን ይመስላል ።

ንግግራቸው በከፊል ይህንን ይመስል ነበር ( የመጀመሪያው ክፍል ብየዋለሁ )

አሁን ጥናቱ ከሰጠን ኢንፑት አንዱ እና ትልቁ የዚህን ችግር ዴብዝ በአግባቡ አመራሩ እንዲያይ ፣ በውስጡ ድንጋጤ እንዲፈጠር ፣ ለማድረግ የሚያስችል ፣ ከመፈከር የዘለለ ” ከዚህ በፊት መልካም አስተዳደር ችግር አለ ፣ እዛ ጋ ችግር አለ ፣ መሬት ላይ ችግር አለ ፣ ገቢዎች ላይ ችግር አለ ፣ እእእ ፣ ጨረታ ግዢ ላይ ችግር አለ ፣ ከሚባለው አልፈን ፣ ሪሊ ምንድነው ያለው የሚል ፣ ሳምፕል ሊሆን ይችላል <ኢት ዳዝንት ማተር> ፣ ሁሉን አካባቢ አጥነትህ አይደልም ችግር የምታውቀው ፣ ሳይንሳዊ የሚያስብለውም ይሄ ነው ፣ ሳይንሳዊ የሚያስብለውም ጥናቱ ሪፕረዘንታትቪ መሆኑን መራዳት ላይ ብቻ ነው ። በዚህ ደረጃ አጥኒዎቹ እእእ ሙያተኞች እና ሁለቱም መስሪያ ቤቶች ያመጡት ውጤት ከልብ ልንቀበለው የሚገባ ውጤት ነው ነው ። የመጀመሪያው ጉዳይ እኔ እዛ ላይ ነው ያለው ነው ። አሁንም ሊፕ ሰርቪስ ካ ለ ( ሽርደዳ ካለ ) ፣ ይሄ ነገር ፣ ሄዶ ሄዶ መደናቀፉ አይቀርም ። ስለዚህ ከልብ ተቀብለን ( ዋልታ መልዕክቱን ይቆርጠዋል ) ።

ማናቸውም ልማታዊ መንግስት ፣ < ፕሮግሬሲቭ የሆነ > ፣ አገር ፓርቲ የሚመሩ አካላት ፣ የመጀመሪያው ጉዳይ በውስጣቸው የሚፈጠረው ጉልበት ነው ፣ ይሄ በውስጥ የሚፈጠርው ጉልበት ባግባቡ ካልተፈጠረ በስተቀር ፣ ሄዶ ሄዶ < ተከላውሶ > መቆሙ አይቀርም ፣ ይሄ ነገር በጣም < ትሬትኒንግ > ነው ። በጣም < ሲርየስም > ነው ፣ ከውስጣችንም ልንቀበለውም የምንገደድበት ጉዳይ ነው ፣ የሚል ነገር መጀመሪያ መሰመር አለበት ። ለኔ በያንዳንዱ አካባቢ — በሁለት ከፍለን ማየት አለብን ይሄን ጉዳይ ። ይሄ ጥናት ያመጣቸው ፋክቶችን መሰረት አድርገን ጠራርገን የምንፈታቸው ን መፍታት አለብን ። አንደኛው መጀመሪያው ። ፈጣኑ ደሞ ፣ ህብረተሰቡ ውስጥ በፐርሴፕሽንም በሪያሊትም የመጡ ጉዳዮችንን ካላቃለልን እና < እውነትም ተስፋ አለው!> ፣ ወደሚል ደረጃ በስፋት ገብተን አብረን እንፈታል ወደሚል አቋም ካልወሰድነው ሕዝቡን < ፎር ሃው ሎንግ ሻል አይ ቶክ> ስለ መልካም አስተዳደር እንፈታለን የሚል ነገር እስከመቼ ነው ማውራት የምችለው ፣ ሁላችንስ እስከመቼ ነው ምናወራው ? ሶ በሁለት ከፍለን ነው ማየት ያለብን ፣ የመጀመሪያው ሕዝቡን ተስፋ ሊያስጭር የሚችል ኢሚዴት ፣ እንደተባለው ካምፔን ( ንቅናቄ ) ፈጥረን ፣ ህዝቡ ተስፋ ፈጥሬአለሁ ብሎ ፣ ከዚህ በሗላ ከናንተ ጋራ እሟሟታለሁ የሚልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የመጀመሪያ ሥራ መስራት አለብን ።

ሁለተኛ እንደው ሪ- ኢንቨንት ማድረግ የለብንም ፣ መሬት ላይ እኮ የመሬት ሪ-ፎርም ፣ ምርጥ የመሬት ሪ-ፎርም አዘጋጅተን በ አይ-ቲ የተደገፈ ፣ እያንዳድኑ ፓርስል የሚታወቅበት ፣ ምን የሚሆንበት ፣ ምን የሚሆንበት ፣ ብለን ካርታ ስናነሳ ፣ ምን ስንል ፣ ምን ስንል ፣ ከርመን ፣ መዓት ዓመት በሱ ላይ ስንከላወስ ከርመን ፣ ውጤት ሳናመጣ ቀርተናል ብለን ገምግመናል ፣ ሌላ አሁን ደሞ ካርታ እየሰራን ፣ ሌላ አምስት ዓመት የምንቆይበት ጉዳይ ሊኖር አይገባም ። አለን ሪፎርም ፕሮግራሞች እኮ አሉን ፣ ይሄ መንግስት፣ ድርጅታችን ፣ የ ሪ-ፎርም ፕሮግራሞች ብሎ የያዟቸው እኮ ፣ ስቴት ኦፍ ዘ አርት ናቸው ፣ አለማቀፍ ስታንዳርድ የጠበቁ ሪፎርሞች ናቸው እኮ ፣ ሌላ ሪ-ኢንቨንት ለማድረግ አይደለም መሄድ ያለብን ፣ የያዝነውን ፣ የያዝናቸውን —ማንኛውም ሪ-ፎርም እኮ ሁል ጊዜ ከአንድ ደረጃ ወደ አንድ ደረጃ ያድጋል ፣ የመጀመሪያ የያዝነውን ሪ- ፎርም ግን መጀመሪያ ተግባራዊ ማድረግ አለብን ፣ መቼ አደረግን መሬት ላይ ፣ አዋጅ ፣ የሊዝ አዋጅ ወጥቶ ፣ ስለቀረቀርነው ሪፎርም አደረግን ማለታችን ነው ? አይደለም ! ኢት ኢዝ አ ቱል ሪፎርሙን ማስፈጸም የሚያስ— የሚያስችል አዋጅና እና ደንብ ነው እንጂ የወጣው ሪፎሩሙ በሌለበት አይሰራም ። ስለማይሰራም ነው ፣ ያንን ስንዘጋ ጨረታ አምጥቶ ጨረታዋን ማጫወት ጀምሯል ፣ ካርታ እዛ ላይ ይጫወታል ። ጨረታ ሲባል ማነው ጨረታ የ-ከኪራይ ሰብሳቢነት ነጻ ነው ያለው ? ሁሉ ጨረታ አይደለ እንዴ አገር እያበላሸ ያለው ? ስለዚህ ጨረታ በራሱ ኢሙዩን አይደለም ፣ አሰራሩ ሙሉ ሆኖ ተግባራዊ ሲሆን ነው ጨረታውም ሊያዝ የሚችለው ፣ ሰውም ሊያዝ የሚችለው ፣ ሁሉ ነገር ሊሆን የሚችለው ። ስለዚህ በሁለት ከፍለን እንሂድ የተባለው ትክክል ነው ፣ በዚህ እንሄዳለን ፣ የጀመርነውም ይሄን ነው ። የመጀመርያው ጉዳይ ፣ አሁን አጥኚዎች ያመጡጧቸውን በሳምፕል ደረጃ የተቀመጡትን ነገሮች ውደ ማኗል እንቀይርና ፣ ይሄ ማኗል ተግባራዊ የሚሆንበት በማኗሉ ሰልጥኖ ሰው ወደ ንቅናቄ የሚገባበትን ሁኔታ እንፍጠር ፣ የመጀመሪያው ጉዳይ ። ከስራ ስፈጻሚ ጀምረን እንተማመን ፣

እንግዲህ በዚህ ንግግር ውስጥ የተጠቀሱ አብይ ወይም አንኳር ነጥብ ምንድን ነው ? እኔ እንደሚመስለኝ መንግስት ሕዝብ ፊቱን እንዳዞረበት ከተረዳ ቢያንስ አስር ዓመት ሆኖታል ( በይበልጥ የምርጫ 97 የምርጫ ውጤት በቂ ማሳያ ነው ) ፣ ያም ሆኖ ይዝቡን በተለያዩ ማባበያዎች < ኮንዶሚኒየም ፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ ፣ ገለመኔ ፣ ገለመኔ > በማለት ከጋን ሙሉ ወተት ውስጥ በሽራፊ ገል እየጠለቀ ያቀመሰው እንደማይቀበቃ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ የምር ወያኔ የሚባለው ነገር እንደበቃው በደንብ ተረድተዋል ። ይህ ባይሆን ኖሮ ምርጫውን 100% ባሸንፉ ( ወይም አሸነፍን ብለው ባወጁ ማግስት በሚባልበት ደረጃ ላይ ) ፣ ይሄን ሞክረን ፣ ይሄን ሞክረን ፣ ይሄን አድርገን ፣ አመታታት ለፍተን — አረ እንደውም የሳቸውን አባባል ልድገመው
< ” መሬት ላይ እኮ የመሬት ሪ-ፎርም ፣ ምርጥ የመሬት ሪ-ፎርም አዘጋጅተን በ አይ-ቲ የተደገፈ ፣ እያንዳድኑ ፓርስል የሚታወቅበት ፣ ምን የሚሆንበት ፣ ምን የሚሆንበት ፣ ብለን ካርታ ስናነሳ ፣ ምን ስንል ፣ ምን ስንል ፣ ከርመን ፣ መዓት ዓመት በሱ ላይ ስንከላወስ ከርመን ፣ ውጤት ሳናመጣ ቀርተናል ብለን ገምግመናል”> ይላሉ ። አዎ መዓት ዓመት፣ መዓት ግዜ ፣ በመዓት ነገር ተንከላውሳችሁ ቀርታችሗል ። እርሶ ራሶ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን < ፣ ኮሪያ ፣ ቻይና ፣ ብራዚል እና ወዘተ ጭምር እናንተን ሰልችተዋል > ። ለምን ?ምክንያቱም <ተንከላውሳችሁ > ስለቀራችሁ ፣ ለምን ? ህብረተሰቡ ውስጥ በፐርሴብሽንም ይሁን በሪያሊቲ ደረጃ ያሉትን ችግሮች መፍታት አይደልም መራድት ስላቃታችሁ ። ይቅሉንም እርሶ እንደሚሉት ስርዓቱ የግልጽነት ( ትራንስፓረንሲ ) ችግር ስላለበት አይመስለኝም አሁን ያለበት የችግር አረንቋ ወይም ቋት ውስጥ የወደቀው ። በነገራችን ላይ ድርጅቶ < በ ትራንስፓረንሲ አይታማም !> እንደውም በዓለም ላይ በግልጽነት የእርሶን ድርጅት የመሰለም ያለ አይመስለኝም ። ለምሳሌ ምርጫውን በ 100 ፐርሰንት አሸንፌአለሁ ብሎ ለማለት ፣ ይህንንም ለዓለም ለመንገር አንዳች አለማመንታት እኮ የወጣለት ግልጽነት ነው ። መቶ ፐርሰንት ነው ያሸነፍነው ፣ መቶ ፐርሰንት ነው ! ግልጽ መንግስት !

የሆነ ቦታ ላይ ደሞ እንዲህ ይላሉ

< ለኔ ሁለተኛ ከባድ ፈተና የሚሆነው እዚህ እናወራለን እንጂ ፣ ከወጣን በሗላ የተለያየ የራሳችንን ኔትዎርክ እንዳይነካብን እንከላከላለን ፣ አንዱ ትልቁ በሽታ ! ስለዚህ መቆረጥ ካለበት መቁረጥ ነው > ። እንዴ ጋሽ ኃይሌ ምነው ረሱት እንዴ ይሄ ኔት ወርክ እኮ ነው 100 ፐርሰንት የመረጦት እና ያስመረጦት ። ኔት – ወርኩ እንዲቆራረጥ ከፈለጉ እርሶ አይድከሙ ፣ ለኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርኩን ኮንትራት ይስጡት ፣ እሱ አሳምሮ ይቆራርጥሎታል!

ይቀጥላሉ < በብሄር የምንከላከል ከሆነ አይሰራም ፣ በአብሮ አደግነት የምንከላከል ከሆነ አይሰራም ፣ በተለያየ ጥቅም ተሳስረን የምንከላከል ከሆነ አይሰራም > ።
እንዴ ጌታው ሰራ እኮ ፣ 25 ዓመት ሰራ ! ዛሬ ምን ነክቶት ነው የማይሰራው ? ሲሰራ የኖረበትን መንገድ አይሰራም ብሎ መተቸት ምን ማለት ነው? እንደ እርሶ አባባል እኮ ፣ 95 ከ 100 የሚሆነው የመከላከያ ጀነራል ካንድ ብሔር የወጣ/ የመጣ ነው፣ ስለዚህ እንደ ሀገር መከላከያ አይሰራም እያሉ ነው ። በስልጣን ላይ ያሉት ( የህወሓት አስኳል ) ከአንድ አካባቢ የመጡ ናቸው ( ምናላባት ያንድ ሰፈር ልጆች ናቸው) ፣ ስለዚህ እነሱም አይሰሩም ! እያሉ ነው ። እነ ጉና ፣ ዔፈርት ፣ ሞሶቦ ፣ መስፍን እንደስትሪያል ፣ እና ወዘተ ፣ የህወሃት እና ህወሃትን የሚደግፈው “የትግራይ ህዝብን” በጥቅም ያስተሳሰሯቸው የንዋይ ምሰሶዎች ስለሆኑ አይሰሩም! እያሉን እኮ ነው ያሉት ? ያሉት ይገባዎታል ወይስ ይገ-ባዎታል ?

ይቀጥላሉ
< አድርግ ስለተባለ ሰው የሚያደርግበት የሚመስል ፣ የህዝብ ውይይት ፣ የህዝብ ተሳትፎ ነው ያለው ? > እኔ ልሙት ? ከመለስ ቀብር ፣ ከአባይ ቦንድ ግዢ እና ከምርጫው ሌላ ፣ ሕዝቡን ምን አድርግ ብላችሁት ነበር ? ለነገሩ ሶስቱም በጣም የሚሰለቹ ነገሮች ነበሩ ፣ ሁለቱ ላይመለሱ ሄደዋል ፣ ሶስተኛው ዛሬም አለሁ እያለ ይፎክራል ። እሱንም አንድ ቀን አልተሳካልንም ብላችሁ ስትሉ መስማታችን አይቀርም ፣ ከዚያ በፊት < ካልፈረሳችሁ !> ።

አሁንም ቀጠሉ

< ኢህአዲግ ድል ካደረገበት ነገር አንዱ ሰው ፕሮሃቢት ድ ሳይሆን የሚሰማውን ነገር አፍረጥርጦ መናገሩ ነው! > እንዴታ ፣ እኔ ተመስገን ደሳለኝ አፍረጥርጠው ተናግረውማ አይደል በኢህአዲግ የተሸለሙት ? እነ እስክንድ ነጋ ፣ እነ አንዱዓለም አራጌ ፣ እነ ውብሸት ፣ እነ ወዘተ የሚሰማቸውን ፣ ያለ አንዳች ገደብ በመናገራቸው አይደል እንዴ ዛሬ በነጻነት በሕዝብ መሃል ፣ ከህዝብ ጋ እየኖሩ ያሉት ? ልክ ኖት ኢህአዲግ ድል ካደረገበት ነገሮች ውስጥ አንዱ እርሶ እንዳሉት ሰው ያለ ገደብ የሚሰማውን አፍረጥርጦ የመናገር መብት እንዲኖረው ማድረጉ ነው ።

ለማንኛውም ይሄም አፈ ጮሌነት አይሰራም ! ይልቅ እኔን የገባኝ ፣ በካርታ ፣ በጨረታ እና ወዘተ ስም በቅርቡ የሚራገፉ ባለስልጣናት አሉ ማለት ነው ። ስራቸው ያውጣቸው !

ማጠቃለያ

ይሄ የርሶ ንግግር አይሰራም ፣ ምክንያቱም ሕዝብ ያልመረጠው መንግስት ስለ ሕዝብ ነጻነት ማውራት አይችልምና ። ይህ የርሶ ደርሶ ቋጥኝ መፋቅ ጥፍሮትን ያስጨርሶ ይሆናል እንጂ ፣ ተራራውን ( የህዝቡን ልቦና ) ፈቀቅ አያደርገውም ፣ ምክንያቱም አይሰራማ ! በውስጣችሁ ስለሚፈጠረው አዲስ ጉልበት ፣ ስለ አዲስ ሕዝብ መነቃቃት እና እናንተን ስለመከተል ብዙ ልትሸርቡ ትችላላችሁ ፣ ልታሴሩም ትጥራላችሁ ግን እሱም አይሰራም ። ውሃ ማቆር አልሰራም ፣ ውጤት ተኮር አልሰራም ፣ አንስተኛ እና ጥቃቅን አልሰራም ፣ ገጠርን መሰረት ያደረገው የልማት እቅድ አልሰራም ፣ ግብርና መር የልማት ፖሊሲ አልሰራም ፣ ራስ አገዝ የገበሬዎች ማህበር አልሰራም ፣ አዲሱ < የተስፋ ካምፔን> ( ” መነቃነቅም “) አይሰራም ። ለምን ቢሉ እርሶ እንዳሉት እናንተ ተንከላውሳችሁ ቀርታችሗልና !

ቸር እንሰንብት !
ሄኖክ የሺጥላ

Filed in: Amharic