>

አንድ አፍታ በሸዋሮቢት እስር ቤት [በላይ ማናዬ]

ነገረ ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ ላምበረት አካባቢ በሚገኘው ሰሜን በር መናሃሪያ ከጓደኛዬ ጋር የጉዞ ትኬታችንን በእጃችን አስገብተን ‹‹ሸዋሮቢት! ሸዋሮቢት›› በሚል መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ (በተለምዶ ቅጥቅጥ የሚባል መኪና) ውስጥ ገብተን ቦታችንን ይዘናል፡፡ ለጉዟችን ሻንጣ አልያም ከበድ ያለ ሸክም አልያዝንም፡፡ ሸዋሮቢት ለመሄድ ካለምኩ ረዘም ያለ ጊዜ ቢያልፈኝም ለመተግበር ዛሬን (ነሃሴ 7/2007 ዓ.ም) መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ወደ ሸዋሮቢት የምሄደው እዚያ ርቀው የተወሰዱ የህሊና እስረኛ ወንድሞቼን ለመጠየቅ ነው፡፡ ጓደኛየም ሆነ እኔ ሸዋሮቢት የሚገኘውን የፌደራል ማረሚያ ቤት አናውቀውም፡፡ ስለሆነም የሚያውቁ ሰዎችን መማተራችን አልቀረም፡፡

የጉዞ መኪናችን ገና መናሃሪያውን ሳይለቅ ከተቀመጥንበት ወንበር ኋላ ያለ ወንበር ላይ የተቀመጡ አንዲት እናት ደጋግመው የድካም ትንፋሽ ሲተነፍሱ በመስማቴ ዞር አልኩ፡፡ አፍንጫየን ትኩስ የቤት ዳቦ ሽታ ስቦ አስቀረው፡፡ እኒህ እናት እንደኛው ሸዋሮቢት የታሰረ ሰው ሊጠይቁ እየሄዱ መሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡ የድካም ትንፋሻቸውን እንደገና ሲተነፍሱ ሰማሁ፤ የመማረርና የመሰላቸት ትንፋሽ! እኒህ እናት እኔና ጓደኛየ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንሄድበትን የሸዋሮቢት እስር ቤት ስንቴ ተመላልሰውበት ይሆን ስል ራሴን ጠየቅሁኝ፡፡
የአንድ ሰው መታሰር (በተለይ በግፍ ለሚታሰሩ) ምን ማለት እንደሆነ ከታሳሪው በላይ በዙሪያው ያሉት ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ሊገነዘቡት እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ እኒህ በጉዞ ላይ ያገኘኋቸውን እናት ስመለከት ከታሳሪው የበለጠ ለእናትየዋ ሀዘንና ርህራሄ ተሰምቶኛል፡፡ ከአዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀትን ትራንስፖርት ከፍለው፣ ስንቅ አዘጋጅተውና ተሸክመው እስረኛውን መጎብኘት ምንኛ ከባድ ሸክም ነው!?

ጉዟችን ጠዋት ለአንድ ሰዓት ሩብ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ተነስተን ወደ ሸዋሮቢት አድርገናል፡፡ በጉዟችን ከታዘብኩትና አሰልቺ ሆኖ ካገኘሁት ጉዳይ ዋነኛው በየጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት እንድንቆም መገደዳችን ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ተነስተን ሸዋሮቢት እስክንደርስ ስድስት ጊዜ በፖሊስ (በአብዛኛው በትራፊክ ፖሊስ) እንድንቆም ተደርገናል፤ የተጋነነ ቢመስልም ሀቁ ግን ይህን ያል ጊዜ መቆማችን ነው፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ ሁላችንም ከመኪና እንድንወርድ ታዝዘን ፍተሻ ተካሂዶብናል፡፡ ይሄ ሁሉ ጋጋታ ለምን እንደሆነ ግን ማንም ያወቀ የለም፡፡ ቁም ይባላል፣ ሹፌሩም የታዘዘውን ይፈጽማል፡፡ ይህን የተመለከቱ አንድ ከአጠገቤ የተቀመጡ አባት ‹‹አሁንስ ብሶባቸዋል!›› ሲሉ ሰምቼ ‹‹ከአሁን በፊት እንዲህ አልነበረም እንዴ?›› ስል ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ‹‹ኸረ ተወው ልጄ!›› ከማለት ውጭ ተጨማሪ ነገር መናገር አልፈለጉም፡፡
በእርግጥ ወደ ሸዋሮቢት ለመሄድ ስነሳ የራሴ የሆነ መጠነኛ የጸጥታ ስጋት ሳያድርብኝ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም እንኳንስ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሰሜን የሚደረግን ጉዞ ሰበብ አግኝተው ይቅርና አዲስ አበባ ላይ አንድ ወዳጄን ይዘው ‹‹ግንቦት ሰባትን ልትቀላቀል ወደ ኤርትራ ልትሄድ ስትል ነው የተያዝከው›› ብለውት ነበር፣ ሳያፍሩ! (አሁን ያ ወዳጄ ከእስር ተፈትቷል፡፡) ስለሆነም ፍተሻው ብዙም አላስገረመኝም፡፡ ከአንድ ወር በፊትም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑ አምስት የሸዋሮቢት ነዋሪዎች ‹‹ለግንቦት ሰባት አባላትን ትመለምላላችሁ›› በሚል ጥርጣሬ ተይዘው ወደ ማዕከላዊ መምጣታቸውን ሰምቼ ስለነበር ሸዋሮቢት መጓዝ እንደድሮው ሊሆን እንደማይችል ግምቱ ነበረኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ በጠዋት ተነስተን ስድስት ሰዓት አካባቢ ሸዋሮቢት ደረስን፡፡ ከመኪናችን ስንወርድ እኒያ ከኋላየ የነበሩትን እናት ዞር ብየ አየኋቸው፡፡ የተሸከሙት ስንቅ ክብደት እንዳለው በማየቴ ተቀብያቸው ከመኪና አወረድኩላቸው፡፡ ደጋግመው የድካም ትንፋሽ ያስወጣሉ፡፡ ባጃጅ ይዘን ማረሚያ ቤቱ ጋ ደረስን፡፡ ሰዓቴን ሳይ ስድስት ሰዓት ሆኗል፡፡ ቃሊቲና ቂሊንጦ እስር ቤቶችን አስታውሸ ‹‹ከሰዓት ነው የምንገባው ማለት ነው?›› ብዬ ስጋት ገባኝ፡፡ ግን ስጋቴ ልክ አልነበረም፡፡ ሸዋሮቢት ሙሉ ቀን እስረኛን መጠየቅ ይቻላል፣ ምሳ ሰዓትን ጨምሮ፡፡ እናም በቀጥታ ወደበሩ በማምራት አስፈላጊውን ፍተሻ ካደረግን በኋላ የምንጠይቃቸውን ሰዎችና የሚገኙበትን ዞን አስመዘገብን፡፡ ሸዋሮቢት ሌላው መልካም ነገር በተለያዩ ዞኖች የሚገኙ እስረኞችን በተመሳሳይ ቀን መጠየቅ መፈቀዱ ነው፡፡ ስለሆነም በዞን አንድ እና በዞን ሦስት የሚገኙ ሦስት እስረኞችን ማለትም ናትናኤል ያለምዘውድ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና ፋንቱ ዳኜን አስመዝግበን ገባን፡፡

መጀመሪያ የገባነው ዞን አንድ ወደሚገኘው ናትናኤል ያለምዘውድ ነበር፡፡ ናቲን አስጠርተን እስኪመጣ ትንሽ ደቂቃዎችን በትዕግስት መጠበቅ ነበረብን፡፡ ናቲ ስስ ማልያና ቁምጣ ብቻ ለብሶ ከእርቀት ሲመጣ አየነው፡፡ አለባበሱ የሸዋሮቢትን ሙቀት ያገናዘበ መሆኑ ነው፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ ስላየሁት ደስ ብሰኝም የታሰረበትን ምክንያት ሳስብ ግን ወዲያው ስሜቴ መረበሹ አልቀረም፡፡ ናትናኤል ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መንግስት የአይኤስ የሽብር ድርጊትን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ በመንግስት ላይ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን ስለገለጸ ከ3 ዓመት በላይ እስር የተፈረደበት የህሊና እስረኛ ነው፡፡ ሰው ወንድሙ በሽብር ቡድን ስለታረደበት በተሰማው ቁጣ ምክንያት መንግስትን ‹‹ሰደበ›› ተብሎ ይህን ያህል እስር ቅጣት ይፈረድበታል፡፡

ናትናኤል ያለምዘውድ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ስለጤንነቱና እዚያ ስላለው አያያዙ ለደቂቃዎች አወራን፡፡ በተለይ በቅርቡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ሸዋሮቢት ተገኝተው ከጠየቁት በኋላ በእስር ቤቱ አስተዳደር የደረሰበትን ጉዳይ ሲያወጋን የሚጠበቅ ቢሆንም እኔና ጓደኛየ መገረማችን አልቀረም፡፡ ‹‹እነ ይልቃል ከመጡ ወዲህ ቢሮ አስጠርተው‹አርፈህ ብትታሰር ይሻልሃል› ብለውኛል›› አለን ናቲ ሳቅ እያለ፡፡

ናትናኤል ጋር የነበረንን ቆይታ አሳጥረን ዞን ሦስት ወደሚገኙት ስንታየሁ ቸኮልና ፋንቱ ዳኜ ማምራት ነበረብን፡፡ በተለይ በዚያው ዕለት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ትራንስፖርት እንዳንቸገር በማሰብ ቆይታችንን ማሳጠር ግድ ይለን ነበር፡፡ ዞን ሦስት ልንገባ በር ላይ ስንደርስ በድጋሜ ካልሲ ማውለቅን ያካተተ ጠበቅ ያለ ፍተሻ ተደረገብን፡፡ ፍተሻውን አልፈን ስንታየሁንና ፋንቱን አስጠራን፡፡ በተመሳሳይ ከእነሱም ጋር ስለጤንነታቸው ከጠየቅን በኋላ ‹‹እንዴት ነው የሸዋሮቢት የእስር ሁኔታ?›› አልናቸው፡፡ ግራና ቀኝ ያሉ ፖሊሶች ጆሯቸው ሲቆም ይታወቀናል፡፡ ስንታየሁ ‹‹ከፍተኛ የመረጃ ጥማት አለብን፡፡ ያው በኢቲቪ ‹ቶርች› እንደረጋለን›› ብሎ ፈገግ አለ፡፡ ፋንቱ በበኩሉ እነ ይልቃል ጠይቀዋቸው ከሄዱ ወዲህ የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች እንደተከፉና ልክ እንደ ናትናኤል ተጠርተው ‹‹አርፋችሁ ታሰሩ›› መባላቸውን ነገረን፡፡ በነገራችን ላይ ስንታየሁ ቸኮልና ፋንቱ ዳኜም ከሚያዝያ 14ቱ ሰልፍ ጋር በተያያዘ የተፈረደባቸው ናቸው፡፡

ከሦስቱም እስረኞች ጋር የነበረን ቆይታ በጊዜና ባለው የጸጥታ ሁኔታ ባይገደብ ብዙ ጉዳዮችን ባወጋን ነበር፡፡ አንድ ሁሉም በተመሳሳይ የነገሩን ጉዳይ ግን በድርቁ ምክንያት ያደረባቸውን ስጋት ነው፡፡ ‹‹ዝናብ የት አለ!? ሁለት ጊዜ ብቻ መሰለኝ እስካሁን የዘነበው፤ ዝናብ የለም›› ነበር ያለን ናትናኤል፡፡ ‹‹ሸዋሮቢት ዝናብ የለም…ያልታደለ ገበሬ ሊጎዳብን ነው›› በማለት ስንታየሁ በትካዜ ተውጦ ነግሮናል፡፡ እኛም በጉዟችን ወቅት አብረውን መኪና ውስጥ ከነበሩ ሰዎች የተረዳነው ይሄንኑ ነው፡፡ ከተማዋ ደረቅና ወበቃማ አየር ነው የሚነፍስባት፡፡ በእርግጥ ከሸዋሮቢት ወደ አዲስ አበባ በተጓዝን መጠን የዝናቡ ሁኔታ የተሻለ መሆኑን አይተናል፡፡ ዳሩ ግን ከሸዋሮቢት ወደ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ያለው ሁኔታ አስጊ መሆኑን ነው የተገነዘብነው፡፡
የሸዋሮቢት ቆይታችን አጭር ነበር፡፡ ቢሆንም ግን የእኛ እዚያ መገኘት ለወዳጆቻችን (ለግፍ እስረኞች) ምን አይነት ስሜት እንደፈጠረ በማየታችን በጉዟችን ደስተኞች ነን፡፡ በነገራችን ላይ የሸዋሮቢት እስር ቤት ፖሊሶች አዲስ አበባ ቃሊቲና ቂሊንጦ ካሉት ጋር ሲተያዩ ብዙ ልዩነቶች እንዳሉ አስተውለናል፡፡ የሸዋሮቢቶቹ ቅንነት ይታይባቸዋል፡፡ ፍተሻ ሲያደርጉም ሆነ መረጃ ሲጠየቁ በጎነታቸው አብሮ አለ፡፡ ስራቸውን በአንጻራዊነት ሰብዓዊነት በተላበሰ ሁኔታ ሲያከናውኑ አይተናል፡፡ እናቶች የተሸከሙትን ስንቅ ተቀብሎ በመሸከም እስከ መጠየቂያው ቦታ ያደርሳሉ፡፡ ለጠያቂ ተገቢውን ክብር ይሰጣሉ፡፡ ለዚህ መልካም ስራቸው (ጨዋነታቸው) ማመስገኑም ተገቢ ነው፡፡ ዝዋይ፣ ቃሊቲና ቂሊንጦ (ሁሉም ባይሆን) የሚያመናጭቁን ፖሊሶችም ከሸዋሮቢቶቹ ቢማሩ አይጎዳቸውም፡፡

ለማነኛውም፣ የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ዜጎችን ማሰሩ ለውጥን አያስቀርም፡፡ ስለ ነጻነት ዋጋ የሚከፍሉም ድካማቸው ከንቱ አይሆንምና ብርታቱን ይሰጣቸው ዘንድ እመኛለሁ፡፡ ወዳጆቼ! ከሸዋሮቢት ወደ አዲስ አበባ በአካል ስመለስ መንፈሴ አብሯችሁ ቀርቷል፡፡
በርቱ!!

Filed in: Amharic