>

ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስና የመታሰቢያ ሃውልታቸው ጉዳይ [ቅዱስ-ሃብት በላቸው፤ ከአድላይድ-አውስትራሊያ]

Abune Petrosሰሞኑን አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ሹም በሸገር ኤፍ ኤም ራድዪ ጣቢያ ቀርበው በከተማው ውስጥ ሊሰራ ስለታቀደው አነስተኛ የባቡር መስመር ዙሪያ ሲናገሩ፣ የብፁእ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት እንደሚነሳ በይፋ መግለፃቸው የብዙዎችን ቁጣ የቀሰቀሰና ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑትን አቶ አበበ ምህረቱ “ከስሩ የባቡር መተላለፊያ ዋሻ ስለሚገነባ፤ ግንባታው እስኪያልቅ ድረስ ሃውልቱ ለጥቂት ጊዜያት ተነስቶ ከዋሻው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ቦታው ይመለሳል” በማለት በራድዪ ፋና በኩል ቢናገሩም ያቀረቡት ምክኒያት ግን በማሕበረሰባችን ዘንድ ተዓማኒነት ያስገኘላቸው አይመስልም።
አገራችን የዓለማችን ቀደምት የሰው ልጅ መኖሪያ መሆኗን ማመሳከሪያ የሆነችው የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ-አካል ከአምስት ዓመታት በፊት አሜሪካ ገብቶ ሲቀር፣ እድሜ ጠገቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የአገር ቅርስ የሆነው የዋልድባ ገዳም የስኳር አገዳ እርሻ ልማት በሚል ሕልውናው ሲደፈር፣ ሌሎችም የማንነታችን መገለጫ የሆኑ ብርቅዬ አገራዊ ቅርሶቻችን በስርዓቱ አቀንቃኞች እየተዘረፉ በዶላር በመቸብቸብ የውጭ አገር ሙዚየሞች ማድመቂያ ሲሆኑ፣ እንዲሁም ቀደምት አባት እናቶቻችን ለአገራችን አንድነት፣ ነፃነትና ሕልውና ሲሉ የከፈሉት መስዋዕትነት ተገቢውን ክብር ሲነፈገው፤ እየተመለከተ ያለ ትውልድ ካልጠፋ አቅጣጫ ከ67 ዓመታት በፊት የቆመውን የብፁእ አቡነ ጴጥሮስ የመታሰቢያ ሃውልትን የሚያስነሳ ፕሮጀክት ተቀርጾ ሲቀርብለት ተቃውሞውን ቢያሰማ አይፈረድበትም።
ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የመቶ ብር ኖታችን ላይ የነበረው የአባት አርበኛ ምስል እንዲነሳ ያደረገ የሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ፣ ዛሬ ድንገት ተነስቶ ሕያው የጀግንነት ታሪክ ሰርተው ያለፉትን የሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ብጹእ አቡነ ጴጥሮስን ሃውልት፣ ያውም ሕይወታቸው በግፍ ከተቀጠፈበት ታሪካዊ ቦታ “ለጊዜው አንስቼ ስጨርስ መልሼ እተክለዋለሁ” ስላለ ብቻ ማን ሊያምነው ይችላል?
መሃል አዲስ አበባ ላይ የቆመው ግዑዙ የብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት አንደበት ባይኖረም ላስተዋለው ሰው ብዙ የሚናገረው ነገር ያለው ሕያው ምስክር ነው። ለአገር ነፃነት፣ክብር፣ህልውና፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያዊነት ሲሉ ሕይወትን ያሕል ዳግመኛ የማትገኝ ነገር በመስዋዕትነት አሳልፎ መስጠት አቻ የማይገኝለት ክቡር ነገር መሆኑን ላለፈው፣ አሁን ላለውም ሆነ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ መልዕክት የሚያስተላልፍ ታላቅ ቅርሳችን ነው።
ብፁእ አቡነ ጴጥሮስ የተወለዱበት ፍቼ ከተማ ላይ በስማቸው ቤተ-ክርስቲያንና ሃውልት ተተክሎላቸዋል። ይኸው በሕዝብ ትብብር የታነፀው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና የመታሰቢያ ሃውልታቸው ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በይፋ የተመረቀ ሲሆን፤ ለግንባታው የሚያስፈልገውን የገንዘብ ወጪና ቁሳቁስ ለማሟላት በርካታ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በራሳቸው አነሳሽነት ተደራጅተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በወቅቱ በታተመ አንድ የቤተክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ይህም አቡነ ጴጥሮስ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ቢሆኑም የከፈሉት ኢትዮጵያዊ መስዋዕትነት ግን የሌሎች ዕምነት ተከታይ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ክብር የሚሰጠው ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።
በሞት የተለየን ብርቅዬው ኢትዮጵያዊ የስነጽሁፍ ሰውና የታሪክ ተመራማሪ ብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድሕን “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የተሰኘ ቲያትር አዘጋጅቶ ለተመልካች አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። የዚህን ቲያትር ድርሰት እንዴት ሊፅፈው እንደቻለ በአንድ ወቅት አጋጣሚውን በዚህ መልኩ ነበር የገለፀው።
«አቡነ ጴጥሮስ ለሊቱን በግራዚያኒና በባንዶች አሽከሮቹ አኮርባሽ በገነተ-ልዑል ጉድጓድ ቤት ውስጥ ሲገረፉ፣ ሲመረመሩ፣ “ኢትዮጵያን ከድተህ በሞሶሎኒ እመን!” ተብለው ሲተለተሉ አድረው፣ በማግስቱ ጠዋት ባደባባይ በጥይት ተደብደቡ። በግራዚያኒ ትዕዛዝ እሩምታ ተኩሰው ጭንቅላታቸውን በጥይት የጠቀጠቋቸው ኢጣሊያኖቹ ያሰለጠኗቸው የሰሜን ባንዶች ወንድሞቻትን ናቸው።
«አቡነ ጴጥሮስም “እንኳንና የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ምድሪቷም ጭምር ለፋሺሽት እንዳትገዛ!» ሲሉ አውግዘው ሞቱ። በልጅነቴ በአምቦ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በ15 ዓመቴ ክቡር ዘበኛ ካዴት ልገባ ጠፍቼ ስመጣ፣ አዲስ አበባ መዳረሻ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት አጠገብ ከትሬንታ ኳትሮ ወርጄ፣ አባቴ ስለ አቡነ ጴጥሮስ የእረኝነት እድሜና የጀግንነት ጀብድ በከፍተኛ አድናቆት ያጫውተኝ የነበረው ትዝ ብሎኝ ሃውልቱ ስር ቆሜ ቀረሁ።
«ይህ ከሆነ ከአስር ዓመት በኋላ አለቃችን ክቡር የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሃዋርያት እዚያው የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት የሚገኝበት ስፍራ የሚገኘው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ስብሰባ ጠርተውን ቢሮአቸው አምሽተን ስንወጣ፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ አንድ ሞቅ ያለው የተበሳጨ ጀብራሬ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ላይ ሽንቱን እየሸና “አንት ድንጋይ! … እሸናብሃለሁ…! “ ሲል በልጅነት ደም ፍላት ዘልዬ ከጀብራሬው ጋር ግብግብ ገጠምኩ።
«ድንጋይ አይደለም! … ድንጋይ ነው..» በሚልም በቡጢ ተቃመስን። መጨረሻም ከስብሰባው የተበተኑ ሰራተኞች ገላገሉንና እየተበሳጨሁ ወደ ቤቴ ገባሁ። ለሊቱን አልተኛሁም፣ “ጴጥሮስ ሕያው ናቸው ለማለት፣ ጴጥሮስ ያችን ሰዓትን ስጭር አደርኩ።»

አቡነ ጴጥሮስ ማናቸው?

Abune Petros-orginal picture on wikipediaበ1885 ዓ.ም በፍቼ ላይ የተወለዱት ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ዓለማዊ ስማቸው ኃይለማርያም ነበር። ከስጋዊው ይበልጥ መንፈሳዊው ሕይወት የማረካቸው አቶ ኃይለማርያም ግን በጾም በፀሎት መወሰን ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም በቃኝ ብለው ምንኩስናን የተቀበሉት በ1909 ዓ.ም ገና በወጣትነታቸው ዕድሜያቸው ነበር። ከዚህ በኋላም በ1910 ዓ.ም በወላሞ ወረዳ በደብረ መንክራት ገዳም፣ እንዲሁም በ1916 ዓ.ም በዝዋይ ሃይቅ ደሴቶች ላይ በሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ገዳማት ውስጥ በመምሕርነት አገልግለዋል። በ1921 ዓ.ም በብቃታቸው ተመርጠው በግብጽ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ እጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሾሙት 4 ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት አንዱ ናቸው።
አቡነ ጴጥሮስ ፋሺሽት ኢጣሊያ አገራችንን በድፍረት በወረረበት ዘመን በሰሜን ጦር ግንባር ዘምተው ነበር። ሆኖም ጦሩ ሳይሳካለት ቀርቶ ወደኋላ ሲያፈገፍግ እርሳቸው ደብረ-ሊባኖስ ገዳም ገቡ። ከዚያም ሆነው የሰላሌን አርበኞች በስብከት ያነቃቁ ጀመር። በዚህም ለኢጣሊያ የገቡና በኢጣሊያ አገዛዝ ያመኑ የቤተክርስቲያኗ ቀሳውስት አቡነ ጴጥሮስ ማጥላላታቸውን አቁመው ለኢጣሊያ እንዲገቡና በፋሺሽቱ ጦር ላይ የሚነዙትን ስብከት እንዲያቆሙ በቃልም ሆነ በፅሁፍ ይመክሯቸው ጀመር። ይህ ሃሳብ ግን በርሳቸው ዘንድ ፈፅሞ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።
አዲስ አበባ ከተማ በጠላት ወራሪ ጦር ቁጥጥር ስር ከዋለችበት ከሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም ጀምሮ አንድም ቀን ሰላም ወርዶባት አያውቅም። በራሳቸው ጊዜ ተነሳስተው በመሸፈት በዱር በገደሉ በጎበዝ አለቃ ተደራጅተው የሚዋደቁት አርበኞች ከዛሬ ነገ ይይዟታል እየተባለ በፍርሃት ድባብ ተወጥራ ነበር። በተለይም የመጀመሪያው ወር ለኢጣሊያኖቹ የጭንቅ ጊዜ እንደነበር ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” ሲል ባሳተመው መፅሃፉ ልዩ ልዩ ምንጮችን በመጥቀስ ያብራራዋል።
“ማርያ ጃኮኒያ ላንድ” የተሰኘች ፀሃፊ በሳተመችው መፅሃፍ ውስጥ ሃምሌ 18 ቀን የያዝኩት ማስታወሻ በማለት በወቅቱ በከተማዋ የሰፈነውን አስፈሪ ድባብ ስትገልጽ « ….. በየቀኑ ከተማዋ እንደምትጠቃ ይነገራል። እንደሚወራው የክረምት ወራት እስኪያልቅ ድረስ ሰላም የለም ይላሉ። አበሾች ባልታሰበና ባልታወቀ ቀን ገበያውን እንደሚወሩት ይነገራል …. » ብላለች።
ታዲያ እንደተፈራውም አልቀረ ከቀናት በኋላ ከተማዋ ተወረረች። ዞሊ የተባለ ሰው “ላ ኮንኮይታ ዴል ኢምፔሮ በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሃፍ “ …. አዲስ አበባ ከተማ በሰሜናዊ ምዕራብ፤ እንዲሁም በደቡባዊ ምስራቅ በኩል ሃምሌ 28 ቀን በሁለት አቅጣጫ በኢትዮጵያውያኑ ጦር ተወረረች።» ሲል ጽፏል።
የእንግሊዝ ለጋሲዪን የነበረው ፓትሪክ ሮበርትስ ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ባስተላለፈው መልዕክት “….. የኢትዮጵያውያኑ ኃይል በምዕራብ በኩል አጠቃ። ኢትዮጵያውያኖች ከባድና የሚያስገርም ውጊያ አደረጉ … ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየተጠጉ በመምጣትም ውስጡ ጥቅጥቅ ካለው ደን ውስጥ ሲገቡ የኢጣሊያ ተከላካይ ወታደሮች ጉዳት አደረሱባቸው። ሁለት ቀን ሙሉ በጀግንነት ተዋግተው መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያውያኖቹ ይዘውት የነበረውን ቦታ ለቀው ሲያፈገፍጉ ጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ ተማረኩ። አቡነ ጴጥሮስ ከተማዋ ድረስ የመጡት ከአርበኞቹ ጋር ሲሆን፣ የተያዙትም በጦርነቱ ውስጥ ሳሉ ነው። … » ብሏል።
“ፓጃሊ” የተሰኘ በወቅቱ የኮሪየር ዴላ ሴራ ጋዜጠኛ “ድአሪዮ አ.ኦ.አ.” በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሃፍ «…. ኃምሌ 30 ቀን በጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበት በአደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ። ይህም ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ተፈጠረ። በዚህ ጊዜም ኢጣሊያኖቹ በመስጋት ጉዳዩ በጋዜጣ እንዳይወጣ ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ። ለኛም ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጠን። ማንኛውም ጋዜጠኛ አቡኑ ተገደሉ ብሎ ወደ ኢጣሊያ አገር ቴሌግራም እንዳያደርግ ሲሉም አስጠነቀቁን፤ ነገር ግን አቡኑ ታሰሩ ብላችሁ ዜናውን ማስተላለፍ ትችላላችሁ አሉን።
«አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ እዚያው ነበርኩ። ጴጥሮስ ረጅምና ብሩህ ገፅታ ያላቸው ሰው ናቸው። ጥቁር ካባ ለብሰዋል፤ በጉዞው ምክኒያት ልብሳቸው ሁሉ በጭቃ ተበላሽቷል። …..የሆቴል ቤቱ ባለቤት ግሪካዊው ማንድራኮስ የአቡኑን ንግግር ለጋዜጠኞቹ ያስተረጉም ነበር። አቡኑም በሚገባ የመከላከያ ሃሳባቸውን ሰጡ።
«የሞት ፍርዱም በተፈረደባቸው ጊዜ በፀጥታ አዳመጡ፣ በቀኝ እጃቸው በሰማያዊ ጨርቅ የተሸፈነ መስቀል ይዘዋል። …የሞት ፍርዱ ከተፈረደ በኋላ ኢጣሊያኖቹ የመግደያውን ስፍራ ለማዘጋጀት ወደ ገበያ ሄዱ። ቦታው ተዘጋጅቶ ሲያልቅም አቡነ ጴጥሮስ ወደዚያው ተወሰዱ።
«እርሳቸውም ፊታቸውን ወደተሰበሰበው ሰው አዙረው ቆሙ። በሕዝቡና በአቡነ ጴጥሮስ መካከል ለኢጣሊያ ያደሩ ያገር ተወላጆች (ባንዶች) ቆመው ሕዝቡ እንዳይጠጋቸው ይከላከላሉ።
« ….. አቡነ ጴጥሮስ ሰዓታቸውን አውጥተው አዩ፤ ወዲያውም አጠገባቸው ያለው የኢጣሊያ ወታደር ለመቀመጥ እንዲፈቅድላቸው ጠየቁ፤ ወዲያው ግን ቀና ብለው ሰገነት ላይ ወደተቀመጥነው ጋዜጠኞችና መኳንንት ካዩ በኋላ የመቀመጥ ጥያቄያቸውን ትተው ቀጥ ብለው በመቆም ከፊታቸው ላሉት ገዳዮቻቸው ተመቻቹላቸው። አቡኑ ረጋ ብለው ተራመዱ፤ ካራሚኚዬሮቹም ከመግደያው ቦታ እስኪቆሙላቸው ጠበቁ። ከቦታው ሲደርሱ አንድ አስተርጓሚ ተጠግቷቸው “አይኖ እንዲሸፈን ይፈልጋሉን?” ሲል ጠየቃቸው። እርሳቸውም “የናንተ ጉዳይ ነው! እንደወደዳችሁና እንደፈቀዳችሁ አድርጉ! ለኔ ማንኛውም ቢሆን ስሜት አይሰጠኝም!” ሲሉ መለሱለት።
«ከዚህ በኋላ አራቱንም ማዕዘን በመስቀላቸው ባረኩ። በሕዝቡም ፊት እንደቆሙ እንዲህ አሉ። “ፋሺሽቶች የአገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሉ እውነት እንዳይመስላችሁ። ሽፍታ ማለት ያለአገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የሚገኘው አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺሽት ነው! የኢትዮጵያ ሕዝብ ለርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው! የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን!” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላለፉ።
«በመጨረሻም ጴጥሮስ ፊታቸውን ወደግድግዳው እንዲያዞሩ ተደረገ። እርሳቸውን ቀድሞ በመግደል ክብር የሚፈልጉ ስምንት ካራሚኜሮች ከጴጥሮስ 20 እርምጃ ያሕል ርቀው በርከክ አሉ። በአስተኳሹ ትዕዛዝም የተኩስ እሩምታ ከፈቱባቸው። አቡነ ጴጥሮስም ጀርባቸው በጥይት ተበሳሳና ከመሬት ወደቁ። ወዲያውኑ አንድ ኢጣሊያዊ ካፒቴን ሃኪም መረመራቸውና “ይሄ ቄስ አልሞተም!” ብሎ ተናገረ። በዚህ ጊዜ የካራሚኜሮቹ አለቃ ተጠግቶ በሶስት ጥይት ጭንቅላታቸውን በመደብደብ ጨረሳቸው። አስገዳዩ ኢጣሊያዊ ኮሌኔልም የአቡነ ጴጥሮስን አስከሬን ማየት ቀፎት እንደ ዕብድ ተፈናጥሮ ከመቀመጫው በመነሳት “የት ነው የሚቀበረው?!” ሲል ጮኸ። ሬሳቸውም ከከተማ ውጭ በሚስጢር ተቀበረ።» ሲል የኢጣሊያዊውን ጋዜጠኛ እንዲሁም ሌሎች ምንጮችን በመጥቀስ ጳውሎስ ኞኞ ታሪካቸውን በመጽሃፉ ከትቦልን አልፏል።
መቼስ የአገሩን ልማትና የወገኑን ብልፅግና የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ አለ ቢሉኝ አላምንም። ሕወሃት/ኢሕአዴግ ግን የልማቱን ዕቅድ የሚነድፈው ከጥፋት ጋር መሆኑ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። በቅርቡ እንኳን ምትክ መጠለያና ቦታ ሳያዘጋጅላቸው በላፍቶ የ30 ሺህ ምስኪኖችን ቤት በሃይል ደርምሶ ማባረሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ምናልባት እዚያ ቦታ ላይ ከ30 የማይበልጡ ቱጃሮች ያማረ ቪላ ገንብተውበት አለማቸውን እንዲቀጩበት ይሆናል እነርሱን ማፈናቀል ያስፈለገው። የተነሳሁበት ርዕስ ይህ ስላልሆነ እንጂ ብዙ መሰል የልማት ጥፋቶችን መዘርዘር ይቻላል።
የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ የሆኑት አቶ አበበ ምህረቱ «የንድፈ ሃሳቡ ዲዛይን ወደ ትግበራ ሲገባ ከባቡር መስመሩ ጋር በቀጥታ በተገናኘ የሚፈርስ ምንም አይነት ህንጻ የለም” ሲሉ ባለፈው መስከረም ወር የገዥው ፓርቲ ሃብት በሆነው በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በግልጽ ቃል ገብተውልን ነበር። ታዲያ ዛሬ ምን ተገኘና ነው ካልጠፋ አቅጣጫና መስመር ለአገር መሞት ክብር መሆኑን የሚያስተምረንን ግዑዙን የሰማዕተ ጽድቅ ዘ-ኢትዮጵያ የብፁእ አቡነ ጴጥሮስን ሃውልት ሕልውና የሚዳፈር የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋት የታለመው?
ታዋቂው ፀሃፊ ዲያቆን ዳንዔል ክብረት የሃውልቱን መነሳት አስመልክቶ አስተያየታቸውን በመሰንዘር ላይ ካሉ ሰዎች አንዱ ነው። ይህንኑ አስመልክቶ ሰሞኑን ባስነበበን ፅሁፉ፦
“የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ተነሥቶ የት ነው የሚቀመጠው?
ማን ነው የሚያነሣው?
የቅርስ ባለሞያዎች ተሳትፎ ምን ያህል ነው?
በቆይታው ጊዜ የሚደረግለት ጥንቃቄስ?
ሲመለስስ የት ነው የሚቆመው? አሁን ከሚሠራው የባቡር መሥመር ጋር ባለው ተዛምዶ የወደፊት አቋቋሙ ምን ይመስላል? ሲል ጠይቋል። የዲያቆን ዳንኤል ጥያቄዎች ደግሞ እኔን ጨምሮ የበርካታ ኢትዮጵያውያን አንገብጋቢና ወቅታዊ ጥያቄዎች ናቸው። እዚህ ላይ ላክልበት የምሻው ጥያቄ ቢኖር ለምን ያሕል ጊዜስ ነው ተነስቶ የሚቆየው? የሚል ነው። ጉዳዮ በቀጥታ የሚመለከተው አካል ለነዚህና ለመሰል ጥያቄዎቻችን በአፋጣን ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባል እያልኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በያለንበት ሆነን ጉዳዩን በቅርበትና በትኩረት እንከታተለው ዘንድ መልዕክቴን ማስተላለፍ እሻለሁ።

Filed in: Amharic