>

የተጀመረውን የትጥቅ ትግል የሚቃወሙት እነማን ናቸው? ለምን? [አዜብ ጌታቸው]

(ሲሞላ ሲሞላ ጨዋታችን ሌላ ሲጎል ሲጎል ሰው አንቀን ሊገል)

የሰላማዊ ትግል ስኬት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ ምርጫ ነው። በዚሁ መሰረት የ2002 ምርጫ በ0.04% ተጠናቀቀ። በ2007 ተስፋ ያልቆረጡ ወገኖች 0.04%ን ለማሻሻል ሰሩ። ውጤቱም 0.04 ቷንም ያሳጣ ሆነና አረፈው። ገዢው ፓርቲ 100 ውንም ጠቅልሎ ወሰደው።

ይህን ተከትሎም “ሰላማዊ ትግል” እንደ አማራጭ የትግል ስልትነት መወሰዱ አከተመ። ተስፋው ተሟጠጠ። ይህ ማለት ደግሞ ሁለተኛውን የትግል ስልት ማለትም ትጥቅ ትግልን ያለተወዳዳሪ ብቸኛው ተመራጭ የትግል ስልት ያደርገዋል።አደረገውም።

አሁን ያለነው እዚህ ደረጃ ላይ ነው። በኔ እምነት ወያኔ በራሱ ግዜ የትግል ስልት ልዩነቶቻችንን ወደ አንድ አስማሚ አቅጣጫ የገፋቸው ይመስለኛል።

ይህ በእንዲህ እያለ የከሰመው የትግል ስልት ልዩነት(በሰላማዊና በትጥቅ ትግል መካከል የነበረው) ድንገት መልኩን ለውጦ በትጥቅ ትግሉ ጓዳ ዘው ብሎ ገባ። በትጥቅ ትግሉ አካሄድ ላይ ልዩነት ወይም ተቃውሞ አለን የሚሉ ወገኖች ተነሱ።ልብ በሉ! ልዩነቱ በትጥቅ ትግል ጓዳ ውስጥ እንጂ በትጥቅ ትግል በሚያምኑ ወገኖች መካከል አይደለም።

በትጥቅ ትግል ጓዳ ውስጥ ያለ ያካሄድ(በሻቢያ በኩል ይኬድ አይኬድ) የሚል ልዩነት ከሆነ መነጋገርና መወያየት ያለባቸው በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ወገኖች ብቻ መሆን ይገባቸዋል። ከትግል ስልትነት በራሱ ግዜ በከሰመው በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ወገኖች በትጥቅ ትግሉ የአካሄድ ልዩነት ውስጥ ገብተው መወያየት የለባቸውም። ሲጀመር ትጥቅ ትግል የሚለውን መሰረታዊ ሃሳብ ስለማይቀበሉት በትጥቅ ትግል ጓዳ ያለውም የአካሄድ ልዩነት የነሱ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። የሆነው ወይም እየሆነ ያለው ግን ይህ ነው።

የሰላማዊ ትግሉ በር ሲዘጋ ገሚሶቹ ደጋፊዎቹ በትጥቅ ትግል ጓዳ ዘው ብለው የአካሄድ ልዩነት አለን ማለት ጀመሩ። ይህን ድርጊት በምሳሌ ሳስቀምጠው፤ በግዚአብሄር መኖር የማያምን አንድ ሃይማኖት የለሽ ሰው፤ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይና በፕሮቴስታንት መካከል በሚነሱ ልዩነቶች አንዱን ወገን ደግፎ ለመከራከር እንደመሞከር ያለ ይመስለኛል። ይህ ሃይማኖት የለሽ ሰው ማውራት ከመጀመሩ በፊት ክርስቲያን መሆን ይገባዋል። የሰላማዊ ትግል ደጋፊዎችም እንደዛው።

ላለፉት 10 ዓመታት በሰላማዊ ትግልና በትጥቅ ትግል መካከል ያለው ልዩነት ሳይፈታን፤ ዛሬ የሰላማዊ ትግሉ ከአማራጭ የትግል ስልትነት ረድፍ (በአገዛዙ 100% አሸናፊነት) ተሰርዞ የትጥቅ ትግሉ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ብቅ ሲል፡ ጭራሹኑ የሚዘገንን መቆራቆስና መጠላለፍ ወደ በዛበት ቅራኔ የመገባቱም እንቆቅልሽም ይህው ነው ። በትጥቅ ትግል የማያምነው ወገን ጓዙን ጠቅልሎ በትጥቅ ለመታገል በተሰለፉ ወገኖች ጓዳ ዘው ብሎ ስለ ትጥቅ ትግሉ አካሄድ ልወያይ ማለቱ።

አንደኛው ወገን፡ ትጥቅ ትግል ተገቢና ብቸኛው አማራጭ ነው! ብሎ የተግባር እንቅስቃሴ ጀምሯል።

ሁለተኛው ወገን ትጥቅ ትግል ብቸኛ አማራጭ ቢሆንም በአስመራ በኩል መሄድ የለባችሁም የሚል የተቃውሞሃሳብ እያቀረበ ነው።ልብ በሉ! ባለ ጉዳይ አይደለምና በአስመራ በኩል መሄድ የለብንም አላለም። አሳቢው ሌላ ተግባሪው ሌላ ።

ባጠቃላይ ላለፉት ሁለትና ሶስት ወራት እየታየ ያለው የመጠላለፍ አካሄድ የ24 ዓመቱ ግፍና በደል በፈጠረው “ለለውጥ የመነሳሳት” ብርቱ ስሜት ላይ ውሃ የሚያፈስ፤ ትልቁን ጠላት ወያኔን የዘነጋ ዘግናኝ አካሄድ የተስተዋለበት ነው። ከመቼው ግዜ በከፋና በሚያሰጋ መልክ የጦዘ ተስፋ አጨላሚ መጠላለፍ።

በዚህ ስሜት ውስጥ እያለሁ የትጥቅ ትግሉን መጀመር የሚያበስር ፊሽካ ተነፋ! የሚለውን ዜና ስሰማ የተጫጫነኝ የተስፋ ቢስነት ስሜት በመጠኑም ቢሆን ቀለል ሲል ታወቀኝ። አንድ ጥያቄ ተመለሰ አልኩ። ራሴን ጨምሮ አብዛኛው ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ የትጥቅ ትግሉ መቼ ነው የሚጀመረው? የሚለውን ጥያቄ ጥቂት ለማይባሉ ግዚያት ሲያነሳ መቆየቱን ልብ ይሏል።

የትጥቅ ትግሉ አለመጀመር በትግሉ አካሄድ ለማያምኑ ወገኖች ተጨማሪ የማጣጣያ ካርድ ሆኖላቸው፡ ውሸት ነው፤ ወሬ ነው….ብዙ ብዙ አሉ። ይህ ደግሞ የነጻነት ፈላጊውን ወገን ተስፋ ጨለማ ውስጥ አስቀመጠው።

እናም ይህ ጥያቄ መልስ ሲያገኝ በመጠኑም ቢሆን ስሜት መነቃቃቱ ግድ ነው።

ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አርበኛውን ተቀላቀሉ! የሚል ዜና ሰማሁ።ሁለተኛው ጥያቄ ተመለሰ አልኩ። አሁንም ራሴን ጨምሮ የዶ/ር ብርሃኑ አሜሪካ ተቀምጦ በምስራቅ አፍሪካ የሚደረግ ትግል መሪ መሆን ከሞራል አኳያ ለአብዛኛው ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ሊዋጥ የሚችል አልነበረም። ይህም ትግሉን ለማይደግፉት ወገኖች ሌላ የማደብዘዣና የማጣጣያ ካርድ ሆኖ ቆየ።ይህ በእንዲህ እያለ ዶክተሩ ድንገት አስመራ ተከሰቱ ሲባል ሁለተኛው ጥያቄም መልስ አገኘ አልኩ።

እርግጠኛ ነኝ ዶ/ር ብርሃኑም ሆኑ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች አስመራ መግባት በሃገር ቤትም ሆነ በውጭው ዓለም የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ የትግል መንፈስ በዚህ ደረጃ እንደሚያነቃቃ ቀደም ብለው ተረድተውት ቢሆን ኖሮ እስከዛሬም አይቆዩም ነበር።

አዎ! ዶ/ር ብርሃኑ የኢኮኖሚክስ ምሁር እንጂ የጦር ጀኔራል አይደሉም።የውጊያ ስልት ነድፈው፤ ፍልሚያውን ይመራሉ ተብሎ ስለማይጠበቅ፤ አሜሪካም ተቀመጡ አስመራ በትግሉ ሂደት ላይ ብዙም ለውጥ አይኖረውም የሚል እሳቤ ተይዞ ቆይቶ ሊሆን ይቻላል፡ይህን ሃሳብ በቁሙ ሲያዩት እውነት ይመስላል። ምናልባትም የዶክተር ብርሃኑ አሜሪካ መቆየት ምክንያት ይኽው ይሆን ይሆናል። ነገር ግን የሳቸው አስመራ መግባት ሎጅክ ሊገልጸው የማይችል የመንፈስ መነቃቃት ፈጥሯል።

ዶክተር ብርሃኑ ከማንም በላይ በተደላደለ ህይወት ውስጥ የሚገኙ፤ እንደ ሁላችንም ቤተሰብ ያላቸው ሆነው ሳለ፤ ሁሉንም እርግፍ አድርገው ዱር ቤቴ ማለታቸው በራሱ በከፍተኛ የሞራል ማማ ላይ ያቆማቸዋል። አቶ አንዳርጋቸው በህዝብ ልብ ውስጥ የገነቡት ፍቅርና ክብር መሰረቱ ይኽው ነው፡፤ “ራስን ለህዝብ አሳልፎ መስጠት”።ራሳችን ልንከፍለው የማንደፍረውን ክቡር የህይወት መሥዋዕትነት ለመክፈል የተሰለፉ ዜጎችን ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ጥያቄ ማክበር የሞራል ግዴታ ይመስለኛል።

እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከእንግዲህ በኋላ የትግሉ ውጤት ምንም ይሁን ምንም! ሻቢያ ይታመንም አይታመንም! ትግሉ የሚጠይቀውን የመጨረሻ መስዋዕትነት ለመክፈል የተሰለፉ ወገኖች በሙሉ ከማናችንም በላይ ክቡር ናቸው።

መስዋዕትነቱን ለመክፈል ከተሰለፉት ወገኖች ጋር ያለንን የሃሳብ ልዩነት በተገቢውና በጨዋ መልክ ከመግለጽ ባሻገር የተሰለፉለትን ክቡር ዓላማ የሚያኮላሽ ተግባር የምንፈጽም ከሆነ ራሳችንን ልንመረምር ይገባል። አለመደገፍ መብት ቢሆንም እንቅፋት መሆን ግን መብት አይደለም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፡አንዲትም አፍራሽ ቃል ከመተንፈሳችሁ በፊት የቆማችሁበትን የሞራል እርከን ልታስተውሉ ይገባል። ይህን ካልኩ በኋላ ወደ ዛሬው ጽሁፌ አብይ ጭብጥ ልንደርደር፦

ትጥቅ ትግሉ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ብቅ ማለቱን ተከትሎ የተቃዋሚው ጎራ የትግል ስልት ልዩነት መደብዘዝ ወይም መክሰም ሲገባው ጭራሽ ወደ አስጠሊ መጠላለፍ የመሸጋገሩን እንቆቅልሽ ለመርመር ልሞክር፦

ትጥቅ ትግሉን የሚቃወሙት እናማን ናቸው? ለምን?

የተጀመረውን የትጥቅ ትግል የሚቃወሙት ወገኖች በአንድ ድምጽ የጋራ ምክንያታችን ብለው የሚጠቅሱት “ሻቢያ የሚታመን አይደለም!” የሚል ነው።ይሁንና ሁሉም በጉያቸው የያዙትና በአደባባይ የማያወጡት የተለያዩ ድብቅ ምክንያቶች(ሞቲቮች) አሏቸው። (ውድ አንባቢያን ሆይ! ወንጀልን እንጂ የሃሳብ ወይም የአመለካከት ልዩነትን በአግባቡ ለማበራየት ሞቲቭ መመርመር ተገቢ አይደለም ሲባል አውቃለሁ። ዛሬ ግን ሞቲቭ መመርመር ግድ ብሎኛልና ይህን መርህ በዚህ ጽሁፍ ላይ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ብቻዬን ባስቻልኩት ችሎት መወሰኔን ላሳውቅ እወዳለሁ፡፡ እናም እንክት አድርጌ ሞቲቭ እመረምራለሁ!)

አዎ! ትጥቅ ትግሉን የሚቃወሙት ሁሉም አደባባይ የማያወጡት የየራሳቸው የተሸፈን ምክንያት ቢኖራቸውም በጋራ መጠለል የመረጡት ግን “ሻቢያ የሚታመን አይደለም” በሚለው የወል ምክንያት ስር ነው። ምክንያቱም ወያኔን አሳድጎና አፋፍቶ ዛሬ ለምንገኝበት አዘቅት ያበቃን ሻቢያ ነው! የሚለውን የታሪክ እውነት ማስተባበል ስለማይቻል ነው። የታሪክ እውነታውን ማስተባበል እንደማይቻል ሁሉ በዚህ የታሪክ እውነታ ላይ ተመርኩዞ “ሻቢያ ዛሬም ነገም አይታመንም” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስም ጥንቆላ አልያም “የቡሄ እለት የደነቆረ ሆያሆዬ ሲል ያረጃል” እንዲሉ ይሆናልና ትክክል አይሆንም። ስለዚህ የሻቢያ መለወጥና አለመለወጥ በተጀመረው የትግል ሂደት የሚታይ ይሆናል ብለን እንቁም።

በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትግል የሚቃወሙ ወገኖች ስብስብና ሞቲቮቻቸው

1. ከግንቦት ሰባት ፤ ከአርበኞች ግንባር፤ከኢሳት አመራሮች ጋር በተለያየ ጊዜና ምክንያት ቅራኔ ውስጥ የገቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች
2. ራሳቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ኢንቨስት ያደረጉ ነገር ግን ይህን የጥቅም ንክኪ ደብቀው በተቃዋሚ ጎራ የሚገኙ
3. የትጥቅ ትግሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ ልዩ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል የሚል ከዘረኝነት የሚነሳ ስጋት ያለባቸው
4. በተቃዋሚው ውስጥ ሰርገው የገቡ ወያኔዎች
5. በጦርነት የሚመጣ ለውጥ ትክክለኛ ዲሞክራሲ አያመጣም የሚል እምነት ያላቸው
6. ሻቢያ የሚታመን አይደለም ብለው ከልብ የሚያምኑ

ቀጥለን በተናጥል እንመልከታቸው፦

1. ከግንቦት ሰባት ፤ ከአርበኞች ግንባር፤ከኢሳት አመራሮች ጋር በተለያየ ጊዜና ምክንያት ቅራኔ ውስጥ የገቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች

ከላይ በተራ ቁጥር 1 የተጠቀሱት ወገኖች እንደ ድርጅት ከግንቦት ሰባትና ከአርበኞች፤ እንደ ግለሰብ ከነዚሁ ድርጅቶች አመራሮች ጋር እንደ ሚዲያ ተቋም ከኢሳት ጋር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ባላቸው ቅራኔና አለመግባባት ምክንያት የትጥቅ ትግሉን ሲያጣጥሉ ይሰተዋላሉ።

ሞቲቫቸው ከድርጅቶችና ከግለሰችቦች ጋር ያላቸው ቅራኔ በመሆኑ ተቃውሟቸው የሚቀጥለው ህዝብ ይሰማናል ብለው እስካመኑበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት የትጥቅ ትግሉ መጀመር ብዙሃኑን ተቃዋሚ ወገን አስደስቷል። የዶክተር ብርሃኑ ትግሉን መቀላቀል ደግሞ የበለጠ አነቃቅቷል። ይህ ተከታታይና አዎንታዊ የተግባር ምላሽ አርበኞች ግንቦት ሰባትን ከፍ ያለ የሞራል እርከን ላይ አውጥቷል። በዚህ ወቅት በአርበኞች ግንቦት7 ድርጅትም ሆነ በድርጅቱ አመራሮች ላይ ካላቸው ጥላቻና ቅራኔ በመነጨ የትጥቅ ትግሉን የሚቃወሙት እነኚህ ወገኖች እንደ ከዚህ ቀደሙ የህዝብን ጆሮ ማግኘት ስለማይችሉ የተቃውሞ ልጓማቸውን ያዝ አድርገው፤ የትግሉ ደካማ ጎን ብቅ እስኪል መጠበቅን ይመርጣሉ።

ለነዚህ ወገኖች ጥሩ መገለጫ ኤልያስ ክፍሌ (ጋዜጠኛ ጭር ሲል አልወድም) ነው። ኤልያስ “ገንዘብ ለመሰብሰብ የሌለ ጦርነት አለ እያሉ፤ ይዋሻሉ” ብሎ በተናገረ ሳምንት ሳይሞላው ዶክተር ብርሃኑ አስመራ ገቡ ሲባል ፡”መልካም እድል ለብርሃኑና ለነዓምን” በሚል ቡራኬውን ሰጥቷል።(ሞቲቩ ከአርበኞች ግንባር ጋር ያለው ቅራኔ በመሆኑ ለአርበኞች ግንባር መልካም ምኞቱን አልገለጸም) ።እናተም እንደኔው የተቃውሞ ግልቢያቸውን ልጓም ድንገት ያዝ ሲያደርጉ የታዘባችኋቸው ይኖራሉ።
እነዚህ ወገኖች የግል ጥላቻቸው ዋናውን ጠላት ወያኔን እንዲዘነጉ አድርጓቸው እንጂ፤ ወያኔ ከህዝብ ጫንቃ ላይ እንዲወርድ ይፈልጋሉ። በመሆኑም የትጥቅ ትግሉ ከተጀመረ በኋላ እንቅፋት ሆነው ለመቀጠል አልያም ትግሉን ለማክሸፍ መንቀሳቀስ የሚፈልጉ አይመስለኝም። የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸው የአብዛኛውን የለውጥ ፈላጊ ወገን ወቅታዊ ስሜት እያጠና የሚጓዝ ይሆናል።ሲሞላ ሲሞላ ጨዋታችን ሌላ! ሲጎል ሲጎል ሰው አንቀን ልንገል! እንዲል መሆኑ ነው።

ሞቲቭ መመርመር ያስፈለገውም እነኚህ የተለያየ ድብቅ ምክንያት ይዘው “ሻቢያ አይታመንም” በሚለው የወል ምክንያት ስር የተሰባሰቡት ወገኖች ተቃውሟቸውን እስከምን ድረስ ይቀጥሉበታል? የትኛው “ሞቲቭ” በየትኛው ፌርማታ ላይ ይወርዳል? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለማፈላለግ ነው። ወደ ቀጣዩ ስብስብ ልለፍ፡

2. ራሳቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ኢንቨስት ያደረጉ ነገር ግን ይህን የጥቅም ንክኪ ደብቀው በተቃዋሚ ጎራ የሚገኙ

እነኚህ ወገኖች የትጥቅ ትግሉን የሚቃወሙት ለወያኔ መንግስት ልባዊ ድጋፍ ኖሯቸው ሳይሆን ጥቅማቸው የሚቀጥለው ወያኔ እንደ መንግስት ከቀጠለ ብቻ በመሆኑ ነው። እነኚህ ወገኖች ቀደም ሲል በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን እንደግፋለን በሚል ከለላ ተቃዋሚው ውስጥ ያለችግር ተቀምጠው ጥቅማቸውም ሳይጓደል እዚህ ደርሰዋል። ዛሬ የሰላማዊ ትግሉ መድረክ ሙሉ ለሙሉ ሲደረመስ የሚቆሙበት ያጡ ናቸው። በመሆኑም የትጥቅ ትግሉ እንደ ብቸኛ አማራጭ መወሰዱ በጣለባቸው ስጋት “ሻቢያ አይታመንም” የሚለውን ጎራ ተቀላቅለዋል። እነኚህ ወገኖች ጸረ-ትጥቅ ትግሉን በአጃቢነት ከማገዝ ባሻገር በግልጽ ወጥተው ጭንብላቸው እንዲገፈፍ አይፈልጉም።

3. የትጥቅ ትግሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ ልዩ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል የሚል ከዘረኝነት የሚነሳ ስጋት ያለባቸው

በተራ ቁጥር 3 የተጠቀሱት ወገኖች ደግሞ የሚቃወሙት የወያኔ አመራሮችን እንጂ ወያኔ የሚያራምደውን የአንድን ዘር የበላይነት ያነገሰ ሥርዓት ባለመሆኑ በትጥቅ ትግል የሚመጣ ሥር-ነቀል ለውጥ በትግራይ ህዝብ ላይ የተለየ ጥቃት ያስከትላል ከሚል ስጋት ትጥቅ ትግሉን አጥብቀው ይቃወማሉ።

እነኝህ ወገኖች የዘራቸው ህልውና በቀጥታ ከትጥቅ ትግሉ መሳካት አለመሳካት ጋር የተቆራኘ ነው ብለው ስለሚያምኑ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፤ ትግሉን ለማክሸፍ ይሰራሉ። ይሁንና እነኚህ ወገኖች በተራ ቁጥር አንድ፤ አምስትና ስድስት የተጠቀሱትን ወገኖች አጀብና ከለላ ካላገኙ በስተቀር በፊት ለፊት ራሳቸውን ችለው በተቃውሞ ሊንቀሳቀሱ ስለማይችሉ ተቃውሞቸውም ሆነ ሴራቸው ዘላቂ ሊሆን አይችልም።

4. በተቃዋሚው ውስጥ ሰርገው የገቡ ወያኔዎች

በተራ ቁጥር 4 የተጠቀሱት ሰርጎ ገቦች ከመሽሩፍ ቆራጮቻቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ማሳካት አለባቸውና እስኪጋለጡ ድረስ የቻሉትን ያደርጋሉ። በተለያዩ ቀዳዳዎች እየገቡ ቅራኔውን የሚያባብሱትም እነኚህ ወገኖች ናቸው። እነኚህ ወገኖች በተራ ቁጥር አንድ አምስትና ስድስት፤ እንደተጠቀሱት ወገኖች የትጥቅ ትግሉ መጀመርም ሆነ የዶክተር ብርሃኑ አስመራ መግባት የመሳሰሉት አበረታች እርምጃዎች ልጓም አያሲዛቸውም፡፡ እንዲያውም ሜዳውን ካገኙ የበለጠ ይጋልባሉ።ችግሩ ሜዳው በተራ ቁጥር አንድ አምስትና ስድስት በተጠቀሱት ወገኖች ክልል በመሆኑ እነሱ ልጓም ሲይዙ መጋለቢያ ሜዳ ማግኘት አለመቻላቸው ነው።

5. በጦርነት የሚመጣ ለውጥ ትክክለኛ ዲሞክራሲ አያመጣም የሚል ልባዊ እምነት ያላቸው

በተራ ቁጥር 5 የተጠቀሱት ደግሞ ከግል አመለካከታቸውና እምነታቸው በመነሳት ትጥቅ ትግሉን ይቃወማሉ። ይህ አመለካከታቸው ወይም አቋማቸው ሃይማኖታቸውን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይችላል። አልያም የተለያዩ ሃገራትን የትጥቅ ትግል ውጤት ከማገናዘብ የያዙት አቋም ሊሆን ይችላል። እነኚህ ወገኖች ጦርነት እስከሆነ ድረስ በአስመራም ተደረገ በሶማሌ ለነሱ ለውጥ የለውም። ሁሉንም አይደግፉም። ትጥቅ ትግሉን ካለመደገፍ በዘለለ ግን በተቃውሞም ሆነ በማክሸፍ ረገድ ግድ ብሏቸው አይንቀሳቀሱም።

6. ሻቢያ የሚታመን አይደለም ብለው ከልብ የሚያምኑ

በተራ ቁጥር 6 የተገለጹት ወገኖች ትግሉን የሚቃወሙት በርግጥም ሻቢያን ካለማመን በሚመነጭ እውነተኛ ስጋት በመሆኑ ትግሉ ውጤት እያገኘ ከሄደ፤ የተሳሳተ አመለካከት እንደነበራቸው አምነው ለመቀበል የሚቸገሩ አይደሉም። ትግሉን ለማደናቀፍ የጠለቀ ሴራ ውስጥ የሚገቡም አይደሉም።ይሁንና በቁጥር አንድና አምስት ከተጠቀሱት ጋር ሆነው ጸረ-ትጥቅ ትግሉን በዋናነት እያንቀሳቀሱ የሚገኙ በመሆናቸው በተራ ቁጥር ሁለት ሶስትና አራት ለተጠቀሱት ወገኖች ከለላ እየሰጡ መገኘታቸውን በራሳቸው ጊዜ እስኪረዱ ድረስ ችግር መፍጠራቸው አይቀርም።

ከላይ ልገልጽ እንደሞከርኩት ትጥቅ ትግሉን የሚቃወመው እያንዳንዱ ስብስብ አደባባይ የማያወጣው የየራሱ የተሸፈን ምክንያት ቢኖረውም በጋራ መጠለል የመረጡት “ሻቢያ የሚታመን አይደለም” በሚለው የወል ምክንያት ስር ነው። ይህን እንደ ጋራ ምክንያት የመረጡት “ወያኔን አሳድጎና አፋፍቶ ዛሬ ለምንገኝበት አዘቅት ያበቃን ሻቢያ ነው!” የሚለውን የታሪክ እውነት ማስተባበል ስለማይቻል ነው ብለናል።

ይሁንና ትግሉ ውጤት እያገኘ ከሄደ ሁሉም እንደ ሞቲቩ አይነት ከተቃውሞው ባቡር ላይ በየኬላው ይንጠባጠባል። ትግሉ ውጤት ካጣም የተቃውሞው ባቡር ከአንድ እስከ ስድስት የተዘረዘሩትን ወገኖች በየፉርጎው ጠቅጥቆ “ቀድመን መክረን ነበር” የሚለውን ….እያዜመ ወደ ማይመለስበት …ይነጉዳል።ከዚህ ያውጣን ።

እንደ ማጠቃለያ

የሃሳብና የአመለካከት ልዩነቶች ሁሌም ይኖራሉ ቢቻል ልዩነትን ማጥበብና ወደ አንድ መሰባሰብ ካልተቻለም ላለመስማማት ተስማምቶ ሁሉም ባመነበት መጓዝ ስልጡንነት ነው ።

አሳማኝ በሆነ ምክንያት አመለካከትን መለወጥና ሰልፍን ማስተካከልም ብልህነት እንጂ ወላዋይ አያስብልም። ወላዋይ የሚያስብለው እንደ አባ መላ በሰመር ወያኔ በዊንተር ተቃዋሚ ደግሞ ሰመር ሲመጣ ወያኔ….መሆን ነው።( በነገራችን ላይ አባ መላ ስንቴ አቋም እንደ ለዋወጠ ልብ ብላችኋል? አራቴ አቋም ለውጧል።

ወያኔ፤ተቃዋሚ፤ወያኔ፤ተቃዋሚ (በምህጻረ ቃል ወ.ተ.ወ.ተ መሆኑ ነው።እውነትም ወተወተ አትሉም? በጣም የሚገርመው ደግሞ ይኽው ሰው ዛሬም ጉምቱና ጠንካራ ተቃዋሚ የሚባሉ ወገኖችን በጸረ-ትጥቅ ትግሉ ዙሪያ እያወያየ መሆኑ ነው! በጸረ-ትጥቅ ትግሉ ዙሪያ የተሰባሰቡት ወገኖችን ዋናው ጠላታቸውን ወያኔን ዘንግተዋል ያልኩትም ለዚህ ነው። ባይሆንማ ኖሮማ ለአበበ በለው መሰል ትንታግና ሳተና ተቃዋሚ ከአባ መላ ይልቅ ግንቦት ሰባትና አርበኞች በቀረቡት ነበር።)

ወደ መደምደሚያዬ ልለፍ፦አዎ! ሻቢያን ያለማመን መብት ነው።ትግሉን አለመደገፍም መብት ነው። መብት ያልሆነው ትግሉን ለማደናቀፍ ማሴርና መንቀሳቀስ ነው። ትግሉን ለማደናቀፍ መስራት መብት ሊሆን የሚችለው ለጠላት (ለወያኔ) ብቻ ነው። ምክንያቱም “ጠላት” የሚለው ፍርጃ በራሱ በተቃራኒ ወገን ላይ ጥቃት መሰንዘርን ወይም እራስን ከጥቃት መከላከልን በመብትነት ስለሚይዝ ነው። እኛ ደግሞ እርስ በእርስ ጠላት አይደለንምና አንዳችን አንዳችንን የማደናቀፍ መብት ሊኖረን አይችልም።(ቢያንስ ቢያንስ ከሞራል አኳያ) የለም ማደናቀፍም መብታችን ነው ባልንበት ቅጽበት ጠላት መሆናችንን አወጅን ማለትነውና የጨዋታው ሜዳም፤ ህጉም ይለወጣል።

በሌላ ወገን ሻቢያን ማመንና በሻቢያ እገዛ ለነጻነት መታገልም መብት ነው። መብት የማይሆነው እንደኛ ሻቢያን አምኖ የማይታገል ጠላት ነው! ብሎ መፈረጅ ነው።

እንደ ምክር፦ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 6 ለተዘረዘሩት የትጥቅ ትግሉ ተቃዋሚዎች

ለተራ ቁጥር አንድ ተጠቃሾሽ ፡ አደብ ግዙ! ዋናው ጠላት ወያኔ መሆኑን አትዘንጉ!
ለተራ ቁጥር ሁለት ተጠቃሾሽ፡ ተረቱ ሆድ ካገር ይሰፋል እንጂ ሆድ ካገር ይበልጣል እንዳልሆነ አስተውሉ!
ለተራ ቁጥር ሶስት ተጠቃሾሽ፡ የዘረኝነት መነጽራችሁን አውልቁ! የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ወያኔ እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም! የትጥቅ ትግሉ የትግራይን ህዝብ ከወያኔ አፈና ነጻ የሚያወጣ እንጅ የሚቀጣ አይደለም። ይህንን የሚሰብከው ወያኔ ብቻ ነው።
ለተራ ቁጥር አራት ተጠቃሾሽ፡ እስክትጋለጡ እድላችሁን ሞክሩ!
ለተራ ቁጥር አምስት ተጠቃሾሽ፡ ትጥቅ ትግሉ አማራጭ ስለጠፋ ብቻ የተመረጠ መሆኑን አስቡ።
ለተራ ቁጥር ስድስት ተጠቃሾሽ፡ ግዜ ሰጥታችሁ መጪውን ለመመልከት ትዕግስት ይኑራችሁ።

ድል ለነጻነት ናፋቂው ኢትዮጵያዊ!

ቸር ወሬ ያሰማን!

አዜብ ጌታቸው
azebgeta@gmail.com

Filed in: Amharic