አልቅስ ላላው ካንጀት
ይበቃ ነበረ የ-የኔ ሰው ገበሬ በሳት አሮ መሞት !
በደል ለበቃው ሕዝብ
መናቅ ለመረረው
የባልቻ መታረድ ፣ ምን ሲል አስፈለገው ?
የስክንድር መታሰር የርዮት እንግልት
ያስነሳን ነበረ ፣ ሰው ብኖሆን ባንድነት ።
የሸዋስ ፣ ተመስገን ፣ አንዷለም ሀብታሙ
ስለምን ታሰሩ ፣
ስለምን ስለ-ማን የመከራ ገፈት ዛሬም ይቀምሳሉ?
ብለን የምንጠይቅ ሰዎች ሆነን ቢሆን
ህሊና ቢኖረን ፣ እንደሰው ብናስብ
በምኑም በምኑም ሰበብ ባንሰበስብ
ይህ አይሆንም ነበር የኛ ታሪካችን
ቀና ብለን ነበር እኛም ባገራችን ።
የሸዋስ ሲታሰር ፣ አንዷለም ሲገረፍ
መስከረም ጠብቶልን ፣ ዓመት ዓመት ስንድረስ
ቃላት ስንደረድር ፣ ስብሰባ ስንጠራ
እንደ የኪስ ሌባ ተገርፈን ስንገባ
ሰብስበው ሲያንጫጩን
እርስ በርስ ሲያጋጩን
በጎሳ ና በዘር እንደ አርማታ ድንጋይ ለማነስ ስያፋጩን
ፈልገን ነው እንጂ ፣ መረገጥ ወዶልን
ቢሻለን ነው እንጂ ፣ መዋረድ ሰምሮልን
ይበቃን ነበረ ፣ በቃን ብለን ብንል ።
ዘጠና ሚሊዮን አፉ ተለጉሞ
ነብሱ የጭንቀት ጏዳ
ደሙ “ብርክን ” ወልዳ
አያልቅም ፍርሃቱ ቢቀዳ ቢቀዳ
አይ ያበሻ ዕዳ!!!
ጏደኞቹን ቀብሮ
እናትና እህቱን ዛሬም አሳስሮ
ከአምናው ፍርሃቱ ዘንድሮም ተምሮ
በታመቀው ድምጹ ራሱን አፍኖ
ይኖራል ሀበሻ በማነሱ ገኖ !
ሳሙዔል ቢገደል ፣ ሐበሽ ቀባሪ ነው
ድንኳኑን ሰባሪ
ካርታ እየፐወዘ ፣ ተረት ተረት አውሪ !
አንድ ሳጥን ኮካ ፣ አንድ ድስት ምንቸት
የዝን ነው ጥይቱ ፣ ለሞተው ወንድሙ ወንዱ የሚቆጭበት!
ገደሉት እያለ ከንፈር መምጠጥ እንጂ
በለቅሶ መፈንዳት ፣ እሪ ማለት እንጂ
የሀበሻ መዳፎች ረስተዋል ፈንጂ !
ይልቅስ ያወራል
የአከሌ ቀብር ላይ እኔም ነበርኩ እኮ
አፈር ካለበሱት ፣ አንዱ እኔ ነኝ እኮ
” ቀበር አትሄድም ወይ !?” ይልሃል ሀበሻ
ለቅሶ አትደርስም ወይ ይልሃል ሀበሻ
ቀብር እና ለቅሶ ሆኖ የሱ ጥሻ !
ታዲያ ሳሙዔል ቢሞት ፣ ምኑ ነው እሚገርመው
ወንድሙ በደሉ ፣ ሞቱ ካላመመው ።
እስክንድር ቢታሰር ፣ አንዷለም ቢሰቃይ
የሀበሻ ወንድ ልጅ ፣ ተደፍኖበት ሰማይ
ባህር የቧጥጣል ፣ ሊወጣ ወደላይ !
ታዲያ ምኑ ይገርማል ፣ ምርጫው ቢጭበረበር
ምኑ ነው የሚገርመው ፣ ሀብታሙ ቢታሰር
ሞቶም ” መኖር ደጉ ” እያለ ለሚኖር
ለእንደዚህ አይነት ሕዝብ ፣ ምኑስ ነው የሚገርም ?
ከሳሙኤል ወዲያስ
ከሞቱ ባሻገር
ካለፈላት ሀገር
ከሞተለት ፍቅር
ከሱ ወዲያ ምንድን
ምንም ካልተሰማን ፣ ካልተነሳን በቀር
አንገት ለመቆልመም ፣ ነብስ ለመቀርቀር
ከሆነ ድንኳኑም ፣ መቀበሩም ይቅር !
ከሳሙኤል ወዲያስ
ስንት ወጥተን እንቅበር
ስንቱን እናሳስር ስንቱን እናስገድል?
ለስንቱስ እናልቅስ ስንቱንስ እንቅበር ?
ካልበቃን ፣ ዘንድሮ ባንድ ላይ ካልሞትን
ባንድ ላይ ባንድነት ፣ ሞት ጋልተጋፈጥን
የጀግና ሰው ሞቱ ፣ የዜና ማድመቂያ
የውይይት መድረክ ፣ ድንኳንን ማሞቂያ
የሚሆን ከሆነ
ከሳሙኤል ወዲያ ፣ ሞቱ የማይከፈል
ሺ ሳሙዔል አለ !
ስለዚህ ጥያቄው ከሳሙኤል ወዲያስ
ምን መሆን አለበት
አንገቶች ይቃኑ ፣ ከተመሸጉበት
ድምጾች ድምጽ ይሁኑ ከተዳፈኑበት
ጉልበቶች ይበርቱ ፣ ክንዶች ይፈርጥሙ
ሳሙዔል ይነሳ ፣ ይሁን ዲበ- ኩሉ !
ከሳሙኤል ወዲያ
ምንድን ነው ዕጣችን
የሚለው ነገር ነው ፣ የኛ ፈተናችን
ትልቁ ጥያቄ ፣ ትልቁ ጭንቃችን
ደፍረን ካልመለስነው
ዙሮ ዙሮ ያው ነው !