>
12:14 am - Wednesday January 27, 2021

ነጻነት በሌለባት ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አስተዳደር መትከል ዘበት ነው!!! [ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ]

Semayawi party press on may 29ሰማያዊ ፓርቲ በ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን በዚህች ሐገር ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማት እንደሌሉና ገዥው ቡድንም እውነተኛ ምርጫ እንደማይፈቅድ እያወቀ መሆኑን ከዚህ በፊት በሰጣቸው የአቋም መግለጫዎች ግልፅ አድርጓል፡፡ በሒደቱም እንደታየው ገና ከመጀመሪያው ምርጫ ቦርድ የሰማያዊ እጩዎችን ከምዝገባ ሰርዟል፡፡ ገዥው ቡድን ስልጣኑን ላለማጣት የአፈና መዋቅር በመዘርጋት የዜጎች በነፃነት የመምረጥ መብትን በእጅጉ አፍኗል፡፡ የገዥው ቡድን ካድሬዎችና የፀጥታ ኃይሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተዋዳዳሪዎችን፣ ታዛቢዎችንና አባላትን በማን አለብኝነት ደብድበዋል፣ አስረዋል፣ አለፍ ሲልም ገድለዋል፡፡ ዜጎች ያላቸውን አማራጮች ሊያውቁባቸው የሚችሉ የመገናኛ ብዙሃንና የሲቪክ ማሕበራት በሐገሪቱ እንዳይኖሩ ተደርገዋል፡፡ በህገ መንግስቱ በግልፅ የተከለከለውን ቅድመ ምርመራ በመተላላፍ የፓርቲያችን የቅስቀሳ መልዕክቶች ለህዝብ እንዳይደርሱ የመንግስት የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ደባ ፈፅመዋል፡፡ ሃሳባቸውን በነፃነት የገለፁ አባሎቻችን ከየቤታቸውና ከሚሰሩባቸው ቦታዎች እየታደኑ ታስረዋል፣ አሁንም በእስር እየማቀቁ ይገኛሉ፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ህገ ወጥ አሰራሮች ታጅቦ የተካሔደው ምርጫ በምንም መመዘኛ ፍትሃዊ፣ ነፃና ተአማኒ ሊሆን እንደማይችል ሒደቱ በግልፅ አመላካች ነው፡፡ በውጤቱም በሐገራችን የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖርን ወደ መቃብር የከተተና ኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ ስርዓት ሐገር መሆኗን ያረጋገጠ በውጤቱም የገዥውን ቡድን 100% አሸናፊነት አከናንቦታል፡፡ ይህ ውጤት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የጨለማ ዘመን መምጣቱን ከማሳየቱ ባሻገር ኢህአዲግ በፍርሃት ተውጦ ሁሉንም ለመቆጣጠር ባደረገው ሩጫ ለመግለፅ እስኪያፍር ድረስ የሚያሸማቅቅ ውጤት እንዲከናነብ ሆኗል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በምርጫው ሂደት ተስፋ በማጣት የመራጭነት ካርድ እንዳልወሰዱ የታወቀ ቢሆንም በአፈና ስርዓቱ ኢህአዲግን እንዲመርጡ በከፍተኛ ጫና የመራጭነት ካርድ የወሰዱ ዜጎች ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረባቸውን የፖሊሲ አማራጮችና ለሐገራችን ያለውን ቀናኢ አመለካከት በመገንዘብ ሳይገደዱ፣ በጥቅም ሳይታለሉ ወይም ሌላ ማንኛውንም ስጦታ ሳይጠብቁ ለሰማያዊ ፓርቲ የሰጡት ድምፅ እጅግ የሚያስደምም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ፓርቲያችን በዚህ አፈናና ጭቆና ውስጥ ከሕዝብ የተሰጠውን ክብርም ያከብራል፣ ያመሰግናል፡፡ በምርጫ ሂደቱ የተደበደባችሁ፣ የተሳደዳችሁ፣ የታሰራችሁ እና የተንገላታችሁ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲያችን ዛሬ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተዓማኒ፣ ተወዳጅና ተስፋ የተጣለበት እንዲሆን እናንተ ላይ የደረሰው መከራና በደል ትልቁን ድርሻ ይወስዳልና ክብርና ምስጋና ይገባችኋል፡፡

በመጨረሻም ከላይ በተዘረዘሩት ሕገወጥና የአፈና ስርዓት የተካሔደው የ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫ የሚያመላክተው ኢትዮጵያ አሁንም ነፃና ፍትኃዊ ምርጫ ልታካሂድ ቀርቶ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት ምርጫዎች ጋር እንኳ ሊወዳደር የማይችል እጅግ ኢፍትኃዊ፣ ወገንተኛና ተዓማኒነት የሌለው በመሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን አይቀበለውም፡፡ በኃይል በተቀማ ድምፅ የሚመሰረት መንግስትም በሕዝብ ተቀባይነት የለውም፡፡ የዜጎች ነፃነት ሳይከበር ነጻና ፍትኃዊ ምርጫ ሊደረግ ስለማይችል አሁንም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን እስከሚከበሩ ድረስ ሰማያዊ ፓርቲ በሚያካሂደው የነጻነት ትግል ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ እየጠየቀ ለነፃነት የሚደረገው ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳውቃል፡፡

ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Filed in: Amharic