>

የማለዳ ወግ...የመን በከባድ ሁከት ስትናጥ የእኛ ሀበሳ ! [ነብዩ ሲራክ]

* በአየር ድብደባው ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል

* በሰንአ ሶስት ሆስፒታሎች የወገን ሬሳ ተበራክቷል

* ዜጎች ከየመን በሳውዲ ድንበር እየተመለሱ ነው
* በተ.መ.ድ ስር ያሉ ስደተኞች ጭንቀት ላይ ናቸው
* ከስደተኛ መጠለያ ውጭ ያሉት ወገኖች ስጋት
* ፖለቲካው ተስፋ ያቆረጠው ዜጋ ጩኸት
* መንግስት የምህረት አዋጅ ያድረግ !

ሳውዲና የመን …
Yemen- yemaleda weg Nebiyu SirakTemen yemaleda weg Nebiyu Sirak 1ሳውዲ በየመን ላይ ጦር ከፍታ ስትናቆር በመሃል አገር ጥቃት እንዳይደርስባት ከፍተኛ ቁጥጥር ታደርጋለች። ባሳለፍነው ወራት 81 ያህል የአሸባሪው ISIS ቅጥረኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ማስታወቋ ባይዘነጋም አሸባሪዎች ሾልከው ገብተው ጉዳት ማድረሳቸው ግን አልቀረም ። ባሳለፍነው አርብ በምስራቃዊው የሳውዲ ግዛት ፣ ከባህሬን የቅርብ ርቀት ከምትገኘው የደማም ከተማ ኩታ ገጠም በሆነች ቃጢፍ በአንድ መስጊድ እኩለ ቀን የሆነው ለዚህ ማሳያ ይመስለኛል። በቃጢፍ ግዛት በተጠቀሰው መስጊፍ በአርብ የጸሎት ስነ ስርአት ላይ በተሰነዘረው ጥቃት 21 ጸሎተኞች ሲገደሉ 100 የሚሆኑ መቁሰላቸውን የሳውዲ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጀኔራል መንሱር አልቱርኪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። በዚህችው በአብዛኛው የሸአ ሙስሊም እምነት ተከታዮች በሚኖሩባት የቃጢፍ ግዛት የተሰነዘረው ጥቃት በአሸባሪው ISIS አይ ኤስ አይ ኤስ የተፈጸመ ነው ተብሎ መረጃው እያተራገበ ይገኛል። ሳውዲዎች ግን አጥፍቶ ጠፊ አሸባሪ ከማለት አልፈው ስለ አጥቂው ምንጭ አልሰጡም። አሸባሪው ደአሽ ወይም ISIS ጥቃት መፈጸሙን ማመኑን ተከትሎ የተለያዩ የአለም መገናኛ ብዙሃን ጥቃቱን የሰነዘሩት ISIS እንደሆነ ሰፊ ዘገባ እያቀረቡ ይገኛሉ !

በየመን እየሆነ ያለውም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ። ሳውዲ መራሹ ጦር በየመን ላይ የጀመረው የአየር ድብደባ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የመን በከበደ ሁከት እየተናጠች ነው ። የመን ሰማይ ስር የተኮለኮሉ የመናውያን ብቻ ሳይሆኑ የመንን ወደ ባለጸጋዋ የድፍድፍ ነዳጅ አምራች ሀገር ወደ ሳውዲ መሸጋገሪያ ያደረጉት የድሃ ሃገር ዜጎች ሳይቀር ወደ ለየለት የቀውስ አዙሪት ውስጥ ወድቀዋል ። ከአየር ድብደባ ጎን ለጎነ በሳውዲ መራሽ አረብ ሀገራት የሚረዱ ሚሊሽያዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ካሉ የሁቲ አማጽያን ጋር ግብ ግብ ገጥመው መጋደሉን ገፍተውበታል።

የሁቲ አማጽያን በበኩላቸው በሳውዲ የመን ድንበር ከተሞች አሻግረው እያስወነጨፉ የሚልኳቸው ሚሳኤሎ ች በማሸበር የሰው ህይዎት መቅጠፍ ማቁሰላቸውን ቀጥ ለዋል። ይህ እርምጃ ደግሞ ሳውዲዎችን አስቆጥቷቸ ዋል። የተቆጡት ሳውዲዎች ” ሁቴዎች ቀይ መስመር አለፉ !” በማለት ቁጣቸውን በአየር ድብደባ በቀል ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።በተወሰደው የአየር ጥቃት ያን ሰሞን በአንድ ሌሊት 150 ሮኬቶች በሰአዳ የሚገኘው የሁቲ አማጽያን ይዞታ በእሳት መአት ከሰማተ ሰማያት ታጭቆ በተወረወረ ሮኬት ተለብልቧል። ። ለባህረ ሰላጤው ሀገራት በተለይም ለሳውዲዎች የህልውና ወሳኝ ጥያቄ መልስ መስጫ በሆነው በዚህ ጦርነት የመን በቅረብ ይረጋጋል ተብሎ በማይገመት የሁከት ማጥ ውስጥ ወድቃለች !

” ከሞቱ አሟሟቱ ” የእኛ ህይዎት …
በአደጋ ተከባ ባለችው ድሃ አረብ ሀገር የመን የሚገኙ በሽዎች የሚገኘቱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ም የአደጋው ተጋላጭ ሆነዋል። በዋና ከተማዋ በሰንአ አራት ሆስፒታሎች ከ60 የወገን ሬሳ እንደሚገኝ እዚያው ሰንአ ያሉ የመረጃ ምንጮች ያሰረዳሉ ። ከትናንት በስቲያ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓም ሳውዲ መራሹ ጦር ባካሔደው የአየር ላይ ድብደባም ከአምስት በላይ ኢትዮጵያውያን ሲሞቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ በትናንቱ ሳውዲ መራሽ የአየር ጥቃት አምስት ኢትዮጵያው ያንን መሞትና ሁለት ያህል መቁሰላቸውን አምኗል። የመንግስት መግለጫ በሀራድ የሚገኘው የስደተኞ ች ካንፕ መመታቱም ጠቁሞ ባስተላለፈው መረጃ መንግስት ስለደረሰው ጉዳት አዲስ አበባ ካለው የሳውዲ ኢንባሲ ማብራሪያ አንደሚጠይቅ ዛሬ ማለዳ አስታውቋል።

በሳውዲ ድንበር እየገቡ ያሉት ስደተኞች …
ምዕራባውያን ሀገራት ቻይና ፣ ህንድና አረብ ሀገራት ፣ ህንድ ፖኪስታን ፣ ቻይናና ቀድመው በባህርና በአውሮፕላን ቀድመው ፊሊፒን ፣ ሱዳን ሱማልያ ከጦርነት አደጋ ያሉ ዜጎችን አስወጥተዋል ። የኢትዮጵያ መንግስት እንደተጠቀሱት ሀገራት በየመን ያሉ ዜጎቹን ማስወጣቱ ሲጀምር በሚሰጥር ተይዞ ነበር ። ይህ ለምን እንደሆነ አሁን ድረስ ባይገባኝም ሚስጥር ተብየውን መረጃ ይፋ ካደረግኩት ወዲህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፣ የጅዳ ቆንስልና የጀዛን ኮሚኒቲ አባላት መረጃውን ይናኙት ይዘዋል!

ይህ በእንዲህ እንዳላ በእስካሁኑ የማስመለስ ሂደት አበረታች ውጤት እየታየ ነው ። በየመን ጦርነት ማጥ ውስጥ የነበሩ ወደ 3000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ጨመወሮ በሳውዲ ድንበር በጀዛን በኩል በመመለስ ላይ ናቸው ። የማስመለስ ስራው በጅዳ ቆንስል እና በጅዛን ኮሚኒቲ በኩል ተጠናክሮ ቀጥሏል ። ያም ሆኖ በየመን የኢትዮጵያ ኢንባሲ የመሚመለሱ ዜጎችን ለማስመለስ የሚያደርገውን ምዝገባ አቁሞ እንደነበር ተጠቁሟል። እንደኔ እንደኔ በቀጣይ ጦርነቱ እየከፋ እልቂቱ አለምን ከሚያስደምምበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ወንድም እህቶቻችን የማስዎጣቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የቻለውን ሊያደርግ ይገባል።

በመላ የመን ሞልተው ከተረፉት ስደተኞች መካከል እድል ቀንቷቸው የተመዘገቡትንና በመመዝገብ ላይ ያሉትን በተመሳሳይ መንገድ ማትረፍ ቢቻል ወገንን መታደግ መቻል ነውና እሰየው ነው ! ወደ መቶ ሽህ የሚገመቱ ዜጎች በአደጋ ላይ ነው ያሉት… የየመን ያሉ ወገኖች ተገፍተዋል ። አሁን የተጀመረው ከአደጋ የማውጣት በጎ ምግባር ኢህአዴግ ለፖለቲካ ፍጆታ ሆነ ለምርጫ ቅስቀሳ ፣ አለያም ላከሸፈው የመብት ጥበቃ ሽፋንና የገጽታው ግንባታ ባይጠቀምበት ደስ ይለኛል ። ይህ እንዲሆን የምመኘውን ያህል በኢህአዴግ አገዛዝ የተማረርን ማናችንም ኢህአዴግን ለማንኳሰስ ብለን የወገኖቻችን በሰላም ወደ ሀገር መግባት የጎሪጥ ልናየውና ልንቃወመው አይገባም ባይ ነኝ ። ዋናው በጦርነት ዳጥ ውስጥ የወደቁትን ወገኖቻችን ከስጋትና ከጭንቅ ብሎም ከአደጋ የመታደጉን በጎ ሂደት ማድነቅ መደገፍ መልላም ነው ። ይህን ማድረግ ባይቻለን ልንቃወመው ግን አይገባም ! …

ከስደተኛ መጠለያ ውጭ ያሉት ወገኖች ?
የስደቱ ምክንያት ፈርጀ ብዙ ነው። በዋናነት ግን ስደቱ ከሀገር ቤት የኑሮው ውድነት ጣራ መንካትና ከድህነት አረንቋ ለመውጣት የሚደረገው ግብ ግብ መውጫ መንገድ መሆኑ በቀዳሚ ምክንያትነት ይጠቀሳል። ብዙ እህት ወንድሞች ድህነቱ አንገፍግፏቸው አለያም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ይሁን የፖለቲካ ትኩሳቱ ግለት ምክንያት ክፉውን የአረብ ሀገር ስደት ሳይወዱ በግድ ተቀላቅለውታል ።

በሞት ሽረት ቀይ ባህርን አቋርጠው ፣ በደረቁ በረሃ በማጋጣ ደላሎች ግፍ ተፈጽሞባቸው በአረቧዊቷ ድሃ ሀገር የመን የደረሱ ወገኖቻች ዛሬ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ሆነው የድረሱልን ድምጽ እያሰሙ ነው ። የመለወጥ ፣ የማደግ መመንደግ ፣ በሰላም ውሎ የመግባት ህልማቸውን ለማሳካት በየመን በኩል ወደ ሳውዲ ተሻግረው ህልማቸውን ለማሳካት ሞትን ተጋፍጠውም ካሰቡት አልደረሱም። ዛሬም አነሆ በጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው። የመን ትናንትም ሆነ ዛሬ እንኳንስ ለስደተኛው ለራሷ ልጆች አልበጅ ብላለች ። እናም የእኛ ወገኖች በጦርነት ማጥ ውስጥ ወድቀው መንቀሳቀሻ ፣ መላወሻ መንገዱ ጠቧቸው በጭንቅ ላይ ናቸው። ብዙሃኑ በሰንአና ዙሪያዋ የከተሙት ወደ ቀያቸው ለመመለስ ፍላጎት እያሳዩ ቢመዘገቡም ፣ በየከተማ ገጠሩ ተበታትነው የሚገኙት ተደራሽ ያላገኙት ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለምና ልንደርስላቸው ይገባል …

በUNHCR ስር ያሉ ኢትዮ ስደተኞች እጣ ፈንታ !
UNHCR ፣ IOM ተብለው የሚጠሩት በአለም አቀፍ ስደተኞች ጉዳይ ትኩረት ሰጠው የሚሰሩ መ/ቤቶች በየመን የተመዘገቡ የኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ። እኒህ ቁጥራቸው ወደ አምስት ሽህ (5000) የሚሆኑትና ቁጥራቸው ከመቶ ሽህ የማያንሱ ስደተኞች በተለያዩ የየመን ከተሞች ተበታትነው እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም የተሰራጩ መረጃዎች እማኝ ናቸው ።

በአለም አቀፉ ስደተኞች ኮሚሽን UNHCR ተመዝጋቢ ስደተኞች የረባ ድጋፍና መብት ጥበቃ የማያደርገው በድርጅቱ መታወቂያ ለይስሙላ ቢይዙም ጥበቃ አይደረግላቸውም። አለም አቀፍ ድርጅቱ UNHC R በሁከቱ መባቻ ጓዙን ጠቅልሎ ወጥቷል። ኮሚሽኑ ያቋቋማቸው የመጠለያ ጣቢያዎች በሀገሬው ተቀጣሪ ሰራተኞች እንደነገሩ እያስዳደሩት ቢሆንም እንኳንስ ስደተኛና መጠለያውን ራሳቸውን መከላከል አልቻሉም። በስደተኝነት የተመዘገቡ ወገኖች ደግሞ ወደ ሀገር ቤት ከመመለስ ይልቅ ምርጫቸው ወደ ሶስተኛ ሀገር መሄድ ብቻ ነው ። ፍላጎታቸው ይሳካል ከሚለው አይሳካም የሚለው ማጋደሉ በማጥ ውስጥ ያሉት ዜጎቻችን ጉዳይ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል ።

እስካሁን በየመን ስለተመዘገቡትና ስለ ተመላሾች የሚሰጡት መረጃ ብናገለባብጠው የተመላሾች ቁጥር ተደምሮና ተደማምሮ ከ5000 ፈቀቅ አላለምና ያሳስባል። የመጣው መከራ በብልህ አስተዋይነትና ከመቻቻል ከመከወን ውጭ የሚገፈት አይመስልም ! የመን ስላሉ ወገኖቻችን በኢንባሲው በኩል መረጃ ለማግኘት ብቸገርም በየመን ጦርነት ማጥ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ስላሉበት ይዞታ ጠይቄያቸው ” የዜግነት መለያ የላችሁም !” ተብለን ተግልለናል ያሉኝ ወገኖች በየመን ኢንባሲ አሰራር የሚታየው ፍትሃዊ ያልሆነው ግድፈት ተስፋቸውን እንዳጨለመው በተጎዳ ስሜት ነግረውኛል ። የዜግነት መለያ ሰነድ ያልያዙ በባህር የመንን የደረሱት መታወቂያና ተዛማጅ ሰነድ ስለሌላቸው ለመመለስ ፍልገው ይሁንታን እንዳላገኙ በምሬት ይናገራሉ። የዜግነት መለያ የያዙት ስደተኞችን አግኝቸ ለምን ወደ ሀገር ለመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ጠይቄያቸው በፖለቲካው ንክኪ የመታሰር ፣ የመገረፍና የማሳደድ ስጋት እንዳለባቸው አጫውተውኛል !

ስደተኛው በሀገሩ ለምን ተስፋ ቆረጠ ?

ስደተኞችን በሀገሩ ለምን ተስፋ ቆረጠ ? ብየ ጠይቄ ሲመልሱልኝ … ” በዘር ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አድልኦ እየተለየን ፣ በነጻነት ሃሳባችን በመግለጻችን ፣ በሃገራችን ሰርተን በነጻነት መኖር አልቻልንምና ተሰደናል ። ኑሮው ጣራ ነክቶ በሀገራችን መስራት ገዶን በሰላም በክብር መኖር አልቻልንምና የተሻለ ፍለጋና ስደት ጥገኝነትን መርጠን ተሰደናል ። ብዙዎች ድህነት ስራ ማጣቱ ያሰደደን መመለሱን ቢፈልጉም መመለሻው እንደሚባለው የተስተካከለ አይደለም ። አድልኦ አለ ። በዘር ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አድልኦ እየተለየን ፣ በነጻነት ሃሳባችን በመግለጻችን ቂም የተያዘብን ግን ተመልሰንም የሚጠብቀን የከፋ ከመከራም የባሰ መከራ ፣ ከአደጋ ላይ አደጋ ነውና መመለሱን አንመርጥም !” በማለት በምሬት የማይመረጠውን አማራጭ ስለመረጡበት ሁኔታ በምሬት ይናገራሉ …

መንግስት ሆይ ስማን ! የምህረት አዋጅ አድረግ !
ዜጎች ስደትን የመረጡበት ወደው ሳይሆን በነባራዊው ህይወት ተገደው ነውና አሁንም አደጋ እየተሰማ ስደቱ አላቆመም ። ያልወጡት እንዳይወጡ ከማስተማር ለመደገፍ ባለፈ የወጡትና በጭንቅ ላይ ያሉት ስደተኞች ወደ ሀገራችን አንመለስም ለማለት ያሰደዳቸውን ስጋት ለማስወገድ መንግስት ግልጽ የሆነ የምህረት መመሪያ በሉት አዋጅ ሊያዋጣ ይገባል የሚለው የበርካታ ወገኖች መደመጥ ያለበት ድምጽ ነው ! መንግስት ሆይ ስማን !

ቸር ያሰማን … !

ነቢዩ ሲራክ
ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓም

Nebiyu Sirak's photo.
Nebiyu Sirak's photo.
Nebiyu Sirak's photo.
Nebiyu Sirak's photo.
Nebiyu Sirak's photo.
Filed in: Amharic