>
5:13 pm - Thursday April 18, 9258

የማለዳ ወግ...ስደተኞው በሀገሩ ለምን ተስፋ ቆረጠ? [ነቢዩ ሲራክ]

ክፍል 1
* በሊቢያ ሽዎች አሉ ይባላል
* እስካሁን የተመዘገቡት ግን 305 ብቻ ናቸው
* ወደ 25 የሚጠጉ ስደተኞች ከትሪፖሊ ካርቱም ገብተዋል
* በየመን ሽዎች አሉ ይባላል ፣
* እስካሁን የተመዘገቡት ግን 1000 አልደረሰም
* እስካሁን 500 የሚጠጉ ስደተኞች ከየመን ሀገር ቤት መግባታቸውን እንጃ !!!
* ብዙዎች በአደጋ ላይ ተከበው ወደ ሀገር መግባት አይፈልጉም
* ስደተኛው ሀገር ከመግባት የከፋውን የአደጋ አማራጭ ለምን ይመርጣል ?

በአደጋው ዞን ያሉ ዜጎች …

ወር በደፈነው የሳውዲ መራሽ የአየር ድብደባ ዛሬ መልኩን እየቀየረ ነው ። በአየር ድብደባው ጋብ ሳይል ቢቀጥልም በሳውዲና የመን ድንበሮች የሚሰማው የእግረኛ ጦር እንቅስቃሴ ስለመኖሩ እግር ጥሎኝ የትጥቅ ስንቁን ቅብብሎሽ መታዘቤ አልቀረም ። ይህ ሁሉ ባለንበት የአረብ አገር ከባቢ ሰማይ ስር ሲከዎን የሀገረ የመንና የመናውያን ፣ ከባለ ሃገሮች አልፎ በየመን ሰማይ ስር የሰፈሩት የተለያዩ ሀገር ዜጎች ክራሞት የከፋ እንደሆነ ቀጥሏል ።

ሌላው እውነትም በዚህው አደገኛ ክልል እየተስተስተናገደ ያለው የታሪክ ሂደት ነው ። የየመን ፖለቲከኞች ህብረት አጥተው ፣ ሀገሬው በመለያየታቸው ሀገረ የመንን ለከፋ ድቀት ዳርገዋታል ። መለያየትና መከፋፈል ብሎም ጽንፈኝነት ባመጣው ጣጣ ውድመት ድቀቱ በሰላማዊው ሀገሬ ላይ መጫኑ ሳይበቃ የመን የጦርነት አውድማ መሆኗ በገሃድ የሚታይ ነውና የሚያከራክር ነው አልልም ።

በሁከት በከረመች በባጀችው በሊቢያም የሆነው ከዚህ ያለፈ አይደለም ። አምባገነኑ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በጸደዩ የአረቡ አብዮት መባቻ አይሆኑ ሆነው ከስልጣን በተወገዱ ማግስት ሀብታሟ አፍሪካዊት አረብ ሀገር ሊቢያ ሰላሟ ስምምነት ባጡ ዜጎቿና በውጭ ጣልቃ ገቦች ከሀገርነት ተርታ ወጥታለች ። ከእድገት ተገትታ ወጥታ እንደ ዛሬዋ የመን ግርግር ጦርነቱ ለአልቃኢዳና ፣ ከአልቃኢዳ ለከፋው የአይ ኤስ አይ ኤስ ISIS ጽንፈኞች ጥቁር ባንዴራቸው ላይ የቅዱስ ቁርአኑን ጥቅስ ከጥፈው ከሀይማኖት አስተምሮቱ የማይገናኘውን እርምጃ በኩራት በአደባባይ የአዋጅ ነጋሪት መጎሸም ይዘዋል ።

የተሻለ ህይዎት ፍለጋ ወደ አውሮፖ ለመሻገር በርሃውን ቆርጠው ሊቢያ ከሚደረሱ በሽዎች የሚቆጠሩ የድሃ ሀገር ዜጎች ፣ በኑሮው ተማረው ብቻ ሳይሆን በጨቋኝ መሪዎች ተማረው ለመሆኑ ምስክር የሚሰጡ የትየለሌ ስደተኞች ናቸው ። ከከፋው የበርሃ ጉዞ አይሆኑ ሆነው ከሚያልፉት ስደተኞች መካከል ኢትዮጵያውያን ፣ ኤርትራውያንና ሶማሌያውያን ቀዳሚ ናቸው ። ያን ሰሞን ታዋቂው የቢቢሲ BBC ዜና አውታር ከአንድ የእቃ መጫኛ ላይ በተጠቀጠቀው የሳር ጭነት ውስጥ ታጭቀው ወደ ሊቢያ ሲጓዙ የተያዙትን ስደተኞች ማየት ብቻ የዚያን በርሃ ስደት አስከፊነት ብቻ ሳይሆን ለስደት የገፋቸውን ህይዎት ምሬት ያሳይ ይመስለኛል። ባሳለፍነው ወር አስከፊውን በርሃ በመቁረጥ ላይ እያሉ በአይ ኤስ አይ ኤስ ISIS በተባለው ጽንፈኛ ታጣቂዎች እጅ ወድቀው በግፍ የታረዱ አብዛኛው ኢትዮጵያዊና ኤርትራውያን 28 ክርስትያኖች ልባችን ተሰብሯል። እስላም ክርስትያን የማይለዩት ገዳዮች ክርስትያን ገደልን ብለው ባሰራጩት መረጃ በጭካኔያቸው ፕሮፖጋንዳ መስራታቸውም እውነት ነው ! እነሆ እኛም ከሀዘኑ ሳናገግም የሀገር ውስጡን ፖለቲካ ከአይ ኤስ አይ ኤስ ISIS ጽንፈኛ እያነካካን ፣ አይ ኤስ አይ ኤስ ISIS ጽንፈኛ እስልምናን አይወክልም ፣ ይወክላል ፣ ጀማል የፈጠራ ታሪክ ነው ፣ አይደለም እያልን በረቀቀው የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ተጠቂ ሆነን የቀረውን ስደተኛ ጩኸት መስማት ገዶናል … ጠልቆ የሚያም ህምም !

የመላው አረብ ሀገራት የሙስሊም ከርስትያን ጥንታዊ የታሪክ እሴት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የዚያ ዘመን አለም ስልጣኔ መሰረት ጥንታዊ የሶርያ ፣ የኢራቅ ድንቅ ከተሞችን ቅርሶች ጨምሮ ሀገረ ሊቢያ ደርሰው አረቦች ጭካኔ ጥፋታቸውን አሳይተውናል ። ዛሬም ሌላዋን የአረቦች ፈርጥ የመንን ሊያጠቁ ነጋሪት መምታት የመጀመራቸውን ነጋሩት ጉሻማ እውነት እውሸት ማረጋገጥ የሚቻለው የለም ። ይህን ሁሉ አንድቶ ለጣለው የእኔ ቢጤ በእርግጠኝነት መናገር ወደምንችልበት አሳፋሪና አሳዛኝ ምዕራፍ ላይ መድረሳችን ግን ማንም የማይክደው እውነት ነው …

የወጌ መነሻና መዳረሻ ስለ ቀደምት አረብ ሀገራቱ ቅዱሳን መጻህፍቱን ፣ ሞልቶ የተረፈውን የታሪክ ድርሳናት ያጠቀስኩ መተረክ አይደለም ! ዛሬ ያ ሁሉ ቀርቶ ታሪክና ቅርስን እያጠፉ አለምን እያሸበሩ ያሉት ጽንፈኞች ለለየለት ጥፋት ገስግሰው በጦርነት አውድማ ፣ በሽብር ጥቃት ሜዳ በሆኑት ሀገረ የመንና ሊቢያ የተነተኑ ወገኖቻችን ይዞታ ዘልቆ ቢሰማኝ የምለውን ለማለት ፈልጌ ነው ። ይህንን ዳሰሳ የማድረጌ ዋና መነሻ በአደገኛ ዞኖች በተለይም በየመንና ሉቢያ ያሉ ወገኖቻችን ጉዳይ ነው ። ሀሳብ አቤቱታ የድረሱልኝ ጥሪ ማቅረብ የቻሉ የታደሉ የምላቸው ስደተኞችን በስልክ አግኝቸ አነጋግሬያቸዋለሁ ። የመንግስት ተወካዮችን አግኝተው የመመለስ ፍላጎት ያላቸው ብዙ አይደለም የሚለውን መረጃ አግኝቸ ነበርና የተመዘገቡትንና ያልተመዘገቡትን ስደተኞችን አግኝቸ ለምን ወደ ሀገራችሁ አትመለሱም ? ነበር አልኳቸው ፣ አንዳንዶች ለመመለስ ፈልገው መመለሻው ቀዳዳ ጠፍቶባቸዋል ፣ ብዙዎች ደግሞ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው በዝርዝር አጫውተውኛል ፣ እናም እኔ ጠየቅኩ ” ስደተኞውን በሀገሩ ለምን ተስፋ ቆረጠ ? በአደጋ ላይ ተከበው የከፋውን የአደጋ አማራጭ ለምን መረጡ ? ” በማለት ጠየቅኩ …

ጥያቄው በውስጤ ሲብላላ ከቀናት በፊት በዮርድያኖስ በሚዋሰን አንድ የሳውዲ ከተማ ያገኘሁት ወንድም ስደት በቃኝ ብሎ ከተመለሰ በኃላ ሀገር ቤት ገብቶ ያስተዋለው አልዋጥልህ ብሎ ዳግም መሰደዱን እማኝነት ተቀብያለሁ ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ስደት በቃኝ ብላ እጇን ሰጥታ በአሳር በመከራ ወደ ሀገሯ የገባች እህት በፊስ ቡክ ገጿ ያሰራጨችውና በግል የላከችልኝ መልዕክት ከተቀበልኩት እማኝነት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁና መልሸ መላልሸ የዚህችን ከልታማ ጠንካራ እህት መረጃ ደጋግሜ ማንበቤን ቀጠልኩ

…” እውነት ስደትን ወዶ እና ፈቅዶ የሚጓዝ ማነው??? ” በማለት የሚጀምረው መረጃ ሲቀጥል የተሰጣቸውን የሚያነቡና የሚቀሸክቱ ጋዜጠኞችንና የመንግስትን አካሄድ በመውቀስ ከስደት ተመልሳ ያየችውን እንዲህ ታቀርበዋለች “የኢትዮጲያ ጋዜጠኞች እባካቹ እውነት መናገር ካልቻላቹ የውሸት አጫፋሪ አትሁኑ! የ3ሺ ደሞዝተኛ በባህር ይጓዛል አዎ ይጓዛል የኢትዮጲያ ኑሮ ውድነት አደለም በባህር ቢቻል እንደ አሞራስ በሰማይ አያስበርም በሦስት ሺህ ደሞዝ ቤት ኪራይ ስንት ነው? ምግብ፣ትራንስፖርት፣መሰረታዊ ነገሮችን ሁሉ ለማሟላት ሦስት ሺህ አደለም ሠላሳ ሺህ አይበቃም ሳይወድ በግድ ስደትን አማራጭ ያደርጋል ። በሀገር ሰርቶ ማደግ በየትኛው ኢኮኖሚ ነው ተሰርቶ የሚታደገው እየተኖረ ያለው እኮ በፈጣሪ ቸርነት እንጂ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ አደለም ኑሮ ማለት ኢትዮጲያ ውስጥ የካልሲ እና የኮፉያ የሆነበት ጊዜ ላይ በሀገር ሰርቶ መለወጥ አትበሉን እነ አዝግ ሚዲያዎች ።የተማረው በፓለቲካ በነፃነት እጦት ባህር አቋርጦ በብርሀ እሱን ለማሳደግ ለማስተማር ኑሮ የደቋሳትን ደካማ እናቱን ያለ ጧሪ ትቷት የሲና በርሃን ሲያቋርጥ ስንቱ ደካማ እናቱን ያለጧሪ ቀባሪ አስቀራት ቤት ይቁጠረው ። ዛሬ በሊቢያ እነዚህ ተስፈኛ ስደተኞች በጭራቆች ተበሉ ለነገስ ዋስትናችን ምንድነው? አንድ በመንግስት የምትደዳደር ሀገር ላይ እንደዚህ ለህሊና ለማመን በሚከብድ ዜጎቿ ሲቀጠፉ እንደማየት ምን የሚያም ነገር አለ? “ብድሩን የማይመልስ ወንድ ልጅ አይወለድ ” ብድራችንን መንግስት ካልመለሰ እየተነሳ ህገ ወጥ ስደተኞች የሚል ከሆነ ህገ ወጥ ስደተኛ ይሙት የሚል ህግ ካለ በፓርላማ ፀድቆ እውነቱን እየመረረን እንውጠዋለን አለበለዛ ግን እየተነሳቹ ጆሮችንን አታድሙት የቆሰለው ልባችንንን እየነካካቹ አታመርቅዙት !!! ” ይህ የሳውዲ ተመላሿ ስደተኛ ምስክርነት ነው …

ከቀናት በፊት ከመረጃ አቀባይነት የገዥው መንግስት አቋም አንጸባራቂ የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአንድም ሶስቴ በየመን ተመለሱ ስላላቸው ወገኖች የሰጠው መረጃ ግንአት ባይከፋም የተጋነነው መረጃ ካሉት ስደተኞች ጋር የማይመጣጠን መሆኑ እውነት ነው ። በየመንና በሊቢያ በሽዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ቢኖሩም “ዜጎቸን ለመመለስ ቆርጫለሁ!” ያለው መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በየመን ስላለው ስደተኛ ቁጥር አለም አቀፍ ስደተኞች ጋር አይገናኝም። በየመን የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ከአስር ሽዎች ከፍ ማለቱ እውነት ሆኖ እያለ የተመዘገበው ተብሎ በመንግስግ የሚነገረን ቁጥር በእርግጥ ስደተኛው የት ገባ ? ያስብላል ….

ስደተኛው የት ገባ ?

ከመንግስት ኃላፊዎች መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖምና መገናኛ ብዙሃን እስካሁን በየመን ስለተመዘገቡትና ስለ ተመላሾች የሚሰጡት እንደመነሻ መውሰዱ ይቀል ይሆናልና ከዚያ ልጀምር …በየመን በሽዎች ካሉ የተመዘገበውና የተመላሾች ቁጥር ተደምሮና ተደማምሮ አንድ ሽህ 1000 እንከኳ አልደረሰም ። እናም ይህና ያ የተምታታ የመረጃ ግብአት ቢያሳስበኝ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ የመንና በሊቢያ በተመሳሳይ አደጋ የተዘፈቁ ወገኖችን ጨምሮ በየመን ወዳለው ኢንበሲና በግብጽ ሆኖ የሊቢያን ስደተኞች ጉዳይ ወደሚከታተለው በግብጽ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ስልክ ደዋወልኩ !

በትኩሱ ስጋትና የሊቢያን ስደት ካይሮ ግብጽ ላይ ሆኖ የሚከታተለውን የኢትዮጵያ አንባሲ ያገኘሁት ትኩስ መረጃ መሰረት ተመዝግበዋል የተባሉት ቁጥር 305 የደረሰው ዛሬ ላይ ነው ። ይህን መረጃ ያቀበለሉኝን የግብጽ ኢንባሲ ከፍተኛ ኃላፊዎች ዛሬ ከሊብያ ወደ ካርቱም ገብተዋል ብለው ዶር ቴዎድሮስ ስላሳወቁን ስደተኞች ጥይቄያቸው ከተመዘገቡት መካከል 25 የሚሆኑ ካርቱም ሱዳን ስለመግናታቸው ከግምት ያለፈ የተጨበጠ መረጃ የሌለ መሆኑን አስረድተውኛል ። ያም ሆኑ ሌሎች ተመዝጋቢዎች በትሪፖሊ አድርገው ወደ ሱዳን የሚወጡና በቢንጋዚ በኩል በባህር አድርገው ግብጽ እስከ ቀጣዩ አርብ እንደሚገቡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ኃላፊዎች ጠቁመውኛል ።

የግብጽ ኢንባሲ ኃላፊዎችን ከዚሁ ጋር አያይዠ በሊቢያ ስለሚገኙት ተመዝጋቢዎች ቁጥር ማነስና ስደተኞችን ለመመለስ ስለሚደረገው ጥረት ጠይቄያቸውም ነበር ። በአጭሩ የተመዘገቡትን ለመመለስ ቢንጋዚና ትሪፖሊ ኢንባሲ ካላቸው የሱዳን ኢንባሶ ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ሲገልጹልኝ ፈታኝ የሆነባቸው ከተመዘገቡት መካከል ወደ ሃገር ለመመለስ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ ስራቸውን አሳሳቢ እንዳደረገው አስረድተውኛል ። ሌላው ከዚህ ቀደም በስራ ኮንትራት ሊብያ ገብተው በስራ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ወደ ሀገር ለመግባት ፍላጎት ቢያሳዩም አሰሪዎቻቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ኃላፊዎች ይናገራሉ ።

ትርፖሊና ቢናጋዚ ብሎም ሚስራታ አካባቢ ከሁከቱ ስጋት ሸሽተው እየራዱ ተሰብስበው በሚገኙበት ቦታ በስልክ አህኝቸ አነጋግሬያቸዋለሁ ። እኒህ በጭንቅ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች መካከል ወደ ወንድሞቻችን በተቀሉ ማግስት አድራሻቸውን አግኝቸ በግብጽ የኢትዮጵያ ኢንባሶን ኃላፊዎች ያገኘኋቸው ወደ 18 የሚቆጠሩ ከሁለት አመት በፊት በኮንትራት ስራ በአንድ ሆስፒታል እየሰሩ የሚገኙ እህቶች ከተመዘገቡት መካከል የተወሰኑት ለመመለስ ፍላጎት አለማሳየታቸውን አጫውተውኛል ። የቀሩት ደግሞ ምዝገባ አንጅ ውጤት አላየን ብለው ተስፋ ወደ መቁረጡ ተገፍተዋል …

ከሊብያ ስደተኞች በተጓዳኝ የመን ስላሉ ወገኖቻችን በኢንባሲው በኩል መረጃ ለማግኘት ብቸገርም በየመን ጦርነት ማጥ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ስላሉበት ይዞታ ጠይቄያቸው ” የዜግነት መለያ የላችሁም !” ተብለን ተግልለናል ያሉኝ ወገኖች በየመን ኢንባሲ አሰራር የሚታየው ፍትሃዊ ያልሆነው ግድፈት ተስፋቸውን እንዳጨለመው በተጎዳ ስሜት ነግረውኛል ። ከዚሁ ጎን ለጎን የዜግነት መለያ የያዙት ስደተኞችን አግኝቸ ለምን ወደ ሀገር ለመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው አጫውተውኛል ። ከምን ወደ ሃገራቸው ለመመልስ አላሳያችሁም ብየ ጠይቄያቸው ” በዘር ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አድልኦ እየተለየን ፣ በነጻነት ሃሳባችን በመግለጻችን ፣ በሃገራችን ሰርተን በነጻነት መኖር አልቻልንምና ተሰደናል ። ኑሮው ጣራ ነክቶ በሀገራችን መስራት ገዶን በሰላም በክብር መኖር አልቻልንምና የተሻለ ፍለጋና ስደት ጥገኝነትን መርጠን ተሰደናል ። ብዙዎች ድህነት ስራ ማጣቱ ያሰደደን መመለሱን ቢፈልጉም መመለሻው እንደሚባለው የተስተካከለ አይደለም ። አድልኦ አለ ። በዘር ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አድልኦ እየተለየን ፣ በነጻነት ሃሳባችን በመግለጻችን ቂም የተያዘብን ግን ተመልሰንም የሚጠብቀን የከፋ መከራ ነውን ከመከራ መከራ ፣ ለአደጋ አደጋ አንመርጥም !” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛልና አዝኛለሁ! የእኒህ ግፉአን ተስፋው የጨለመለመባቸው ስደተኞች የሰጡኝ ምላሽ ቢያንስ ስደቱን ለመቀነስ ከልብ ለሚፈልግ ስለ ስደቱን ነባራዊ እውነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየው ይመስለኛል። መልዕክቱ በውስጤ ዘልቆ ግብቷልና ጠልቆ ቢያም ፣ ቢሰማኝ ስደተኞውን በሀገሩ ለምን ተስፋ ቆረጠ ? በአደጋ ላይ ተከበው የከፋውን የአደጋ አማራጭ ለምን መረጡ ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ከተጠቂው በላይ እማኝነት የሚሰጥ የለምና በዚሁ ዙሪያ ቅኝቴን ቀጥየበታለሁ !

በክፍል ሁለት ዳሰሳየ እስክመለስበት…ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓም

Filed in: Amharic