>
3:01 am - Friday January 22, 2021

ኢ–ሰብአዊነትንና ሽብርን ደግመን እናውግዝ! ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን እንታደግ! [ድምጻችን ይሰማ]

ሰኞ ሚያዝያ 12/2007
በአለማችን የተለያዩ ክፍሎች የሰው ፍጡር ክቡርነቱ ረክሶ ፍጡር በፍጡር ላይ ግፍና ጭካኔ የተመላን እኩይ ስራ ሲሰራ ማየት የእለት ተእለት ዜና እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለያዩ አካላት፣ መንግስታትም ይሁን ቡድኖች ንፁሀን እንደቅጠል እየረገፉ እናያለን፤ እንሰማለን፡፡ ሰሞኑን እየተሰሙ ያሉት ዜናዎች ደግሞ መላውን ኢትዮጵያዊ እያሳዘኑና አንገት እያስደፉ ይገኛል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ዜጎች የተሻለ ህይወት ፍለጋ ሀገራቸውን እየለቀቁ ሲሰደዱ ለከፍተኛ አደጋ ይጋለጣሉ። በመንገድ ላይ ዘራፊና ሽፍታ፣ ረሀብና ጥማት፣ እንግልትና እስር ይፈራረቁባቸዋል፡፡ ወደተሻለ ቦታ ለመሻገር ባህር ሲሻገር ሰጥሞ የሚሞተውም ተበራክቷል።
በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም አፍሪካውያን ዜጎች ላይ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል እየተፈጸመባቸው ይገኛል። ሰቅጣጩ የጭካኔ ምግባር አፍሪካዊያን ላይ በአፍሪካዊያን የሚፈፀም መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ከአስርት ዓመታት በፊት ምእራባዊያን ደቡብ አፍሪካዊያን የሚያደርጉትን የፀረ-አፓርታይድ ትግልና መሪያቸውን ኔልሰን ማንዴላን በ«ሽብርተኝነት» ፈርጀው ሳለም እንኳን ኢትዮጵያና ሌሎች አፍሪካዊያን ትግላቸውን ደግፈዋል፡፡ ይህ ታላቅ ውለታ ተዘንግቶ የተፈፀመው እና ሰሞኑን እያየነው ያለውን የጥላቻና የግፍ ግድያ ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘው ይገባል። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ይህንን ተግባር በአንድ ድምፅ እናወግዛለን፤ እንቃወማለንም፡፡
በሊቢያም በክርስትያን ወገኖቻችን ላይ አይሲስ በተባለው የሽብር ቡድን የተፈፀመው አሰቃቂ ተግባር ሌላው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ይህ ስብስብ የሚሰራውን አሰቃቂ የግፍና የሽብር ተግባር «እስላማዊ» ካባ ሊያላብስ ቢሞክርም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሙስሊሞች በአንድ ድምፅ አውግዘውታል፡፡ ጌታችን አላህ በቅዱስ ቁርአን ሱረቱል ማኢዳህ 5፡32 አንድን ነፍስ ያለአግባብ መግደል ሁሉንም ሰብአዊ ፍጡር መግደል እንደሆነ፣ በአንፃሩም አንድን ነፍስ ህያው ማድረግ (መታደግ) ሁሉንም ሰው ህያው እንደማድረግ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ገልፆዋል። ይህ የሰብአዊ ፍጡርን ሕይወት ዋጋ ትልቅነት የሚያሳይ መሆኑን በርካታ የእስልምና ዑለሞች (ሊቃውንት) ያስረዳሉ፡፡
አይሲስ የተባለው የሽብር ቡድንና «የእሱን ፈለግ እንከተላለን» የሚሉ ሌሎች ቡድኖች ሙስሊሙንም ክርስትያኑንም በግፍ ሲገድሉ ቆይተዋል፡፡ ከህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎችን በማደሪያ ቦታቸውና በትምህርት ቦታቸው ባሉበት ገድለዋል። ለአምልኮ የተሰባሰቡ ሰዎችን በመስጊድም በቤተ ክርስቲያንም ጨፍጭፈዋል፤ በስደትም ይሁን «በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ እንሰማራለን» ብለው ወደሌላ አገር የተጓዙ የሌላ አገር ዜጎችንም ሳይቀር እንደዋዛ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል፡፡ ይኸው ትናንት በተሰማ ዜና ደግሞ 28 ኢትዮጵያውያን የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ወንድሞቻችን በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ በሽብር ቡድኑ ተገድለዋል። እንደዚህ አይነቱን የሽብር ተግባር በእርግጥም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ከማውገዝም ባሻገር እንደሙስሊምነቱም እንደዜግነቱም አላህ በሰጠው ችሎታ ለመከላከል የበኩሉን ስራ መስራት አለበት፡፡ በተለያዩ ሀገራት በስደት ላይ ሆነው ህይወታቸው ከፍተኛ ችግር ላይ ለወደቁ ዜጎች በተገኘው ቀዳዳ ድጋፍ የመስጠት ስራ ላይ መሳተፍ አስፈላጊ ነው። በግለሰብ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማትም እንዲሁ የሚችሉትን ማድረግ ያስፈልጋል።
በመንግስት በኩልም አፋጣኝ ምላሽ ያሻል። መንግስትም ይሁን ሌሎች አካላት ጊዜው የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ የሚሰላበት፣ አልያም የወቀሳና ክርክር መድረክ የሚፈጠርበት አለመሆኑን ተገንዝበው ዜጎችን የማዳኑ ተግባር ላይ ትርጉም ያለውና ውጤት የሚያመጣ ስራ ላይ መጠመድ ዋነኛ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ይህንን ተግባር በይፋ ከማውገዝም ባለፈ በቻልነው ሁሉ ዜጎችን ከአደጋ የመታደግ ስራ ልንሰራ ይገባል። ቤተሰቦቻቸው ለሞቱባቸው ሁሉ መፅናናትን እንመኛለን!!!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

Filed in: Amharic