>

ኣመልህን በጉያህ ስንቅህን በሲኖትራክ [በእውቀቱ ሥዩም]

Bob-Marley-Profile-

ባንድ ወቅት የጨርቆሱ ጓደኛየ ኢልያስ ኣወቀ መኪናው ውስጥ ተቀምጦ ከዚያ በፊት ልብ ብሎት የማያውቀውን ኣንድ የቦብ ዘፈን ይሰማል፡፡ natural mysticከሚለው ዘፈኑ ነው፡፡

ቦብ ዘፍኖ ዘፍኖ የሆነ ቦታ ላይ ሲደርስ፤

Many more will have to suffer
Many more will have to die

ሲል ኢልያስ ገርሞት why? ኣለ፡፡

ቦብም Don’t ask me why ብሎ ቀጠለ፡፡

ዘፋኙና ኣድማጩ የዘመንን እና የቦታን ኣጥር ጥሰው ተገናኙና ተነጋገሩ፡፡ተዋሃዱ ማለት ይሻላል፡፡ ዮሃንስ ኣድማሱ ባንድ ግጥሙ “ዳንሱን ከዳንሰኛ መለየት ኣይቻልም” ያለው ይሄን ግጥም ኣይነቱን ኣጋጣሚ በደንብ ይገልጸዋል፡፡

ቦብ ፍልስፍናን መዝፈን እንደሚቻል ያሳየ ድምጻዊ ነው፡፡ እንደገባኝ የፍልስፍናው ዋና ጭብጥ“ ለውጥ በትግል ይመጣል” የሚል ነበር፡፡ ግን ታግሎ ታግሎ ወደ መጨረሻው የደከመው መሰለኝ፡፡ ከላይ የጠቀስኩት natural mystic የተባለ እንጉርግሮው ኣየሁት ታገልኩ ታገልኩ ተረታሁ የሚል ይመስላል፡፡ ። ግጥም ካንዱ ቋንቋ ወደ ኣንዱ መተርጎም ብዙ ኣያሰደስተኝም፡፡ከዚያ ይልቅ በወደድኩት ግጥም መንፈስ ያልወጣ የራሴን ሃሳብ መጫር እመርጣለሁ፡፡እና ቦብን በኣማርኛ ሳዳምጠው፤

“ኣይመረመሬው ከሃገረ ሰማይ
በፍጥረታቱ ላይ
መከራና ሞቱን እያፈራረቀ እንደሾላ ሲጥል
ኣሜን ብለህ ቀጥል”
የሚል ነው የሚመስለኝ፡፡

ዛሬ ትልልቅ ኣገሮች ለጥቅማቸው ሲሉ ትንንሾሽን ባንድ ሌሊት ኣፍርሰው በሚያድሩበት በዚህ ዘመን ፤ፈሪሃ እግዜር ኣለን የሚሉ ሰዎች ወንድሞቻቸውን በካሜራ ፊት ኣሰልፈው እንደ ፋሲካ በግ በሚያርዱበት በዚህ ዘመን፤ በርግጥ የሰው ልጅ ሊሸሻል የሚችል ፍጡር ነው? የሚለውን ጥያቄ ባዎንታ መመለስ ይከብዳል፡፡እና በዚህ ዘመን ማለዳ ላይ get up stand upየሚለውን ዘመን ኣዳምጣለሁ፤ ሲመሽ natural mysticየሚለውን ኣምናለሁ፡፡ከኔ የተሻለ ብሩህ ኣይን ያላቸው ወዳጆቼ ደግሞ በቦብ ዜማ ኣፍቅረዋል፡፡በቦብ ዜማ ደንሰዋል፡፡በቦብ ዜማ ኣስበዋል፡፡ በቦብ ዜማ ቀኖቻቸውን ኣስውበዋል፡፡

ቦብ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ኣምላክ ናቸው ይል ነበር ይባላል፡፡ልንታገሰው የሚገባ ጠቃሚ ተረት ነው፡፡የኣይሁድ የህንድ የፋርስ ነቢያት በመሲህነትና በኣምላክነት ደረጃ በሚመለኩበት ዓለም ውስጥ ኣንድ ኣፍሪካዊ ንጉስ እንዲህ ያለ ወግ ቢደርሰው ምን ችግር ኣለው?

ቦብ ማርሊ ቀንደኛ ኣጫሽ ስለሆነ መታሰቢያ ኣይገባውም እያሉ የሚከራከሩ ወዳጆች ገጥመውኛል ፡፡ ወይ የወንቃው ጊዮርጊስ! እንደዚህ ክርክር ከሆነ የቸርቺል ጎዳና መፍረሰ ኣለበት ማለት ነው፡፡ቸርቺል በዘመነ መንግስቱ ታታሪ ኣጫሽ ስለነበረ ዛሬ በስሙ ሲጃራ ተሰይሞለታል፡፡

ቦብ ከመወለዱ መቶ ኣመታት በፊት ጸጉርን መገማመድም ሆነ እጸ ፋርስ መጠቀም ለኢትዮጵያ እንግዳ ኣልነበረም፡፡ ኣለቃ ኣጽሜ የተባሉ የኣገራችን ታሪክ ጸሃፊ እጸ ፋርስ ማጨስ የተጀመረው በልብነድንግል ዘመን እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ለኣእምሮ ብሩህነት ፍቱን ነው እየተባለ ብላቴናው ሁሉ በቂጣና በማር እየደባለቀ የሚበላው ኣብሾም የሃሽሽ ዝርያ ነው፡፡“ጠላ ያለ ጌሾ፤ ቅኔ ያለ ኣብሾ እየተባለ ኣዳሜ ያንን እየበላ ሲቀባዥር ኖሯል፡፡ ብዙ እጾች በስማቸው ሳይሆን በብእር ስማቸው ተሸፍነው ስለኖሩ የሌሉ ይመስላሉ፡፡እንኳን ተራው ሰው ኣንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ቴዎድሮስን ያነገሱት የግብጹ ኣቡነ ሰላማ የኦፒየም ተጠቃሚ እንደነበሩ በመቅደላ ኣብሯቸው የተሳረው ሃኪም ሄነሪ ብላንክ ነግሮናል፡፡

ዛሬ ቦብ ማርሊ ሰው ይሁን ኣሞራ ለይተው የማያውቁ የጠረፍ ኣገር ባለኣገሮች ያለ ያእቆብ መሰላል ወደ ሰባተኛው ሰማይ ኣድርሶ የሚመልስ እጽ ያጨሳሉ፡፡ መቸስ ኣንዳንዱ ሰው በእንጀራ ብቻ ኣይኖርም፡፡ኣንዳንድ ነገሮችንም ይጨምራል፡፡

የላቀ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሌላው ልዩ ባደረጋቸው ችሎታ እንጂ ከሌላው ሰው ጋራ በሚጋሩት ድክመት መመዘን ኣሪፍ ኣደለም፡፡ ኣሁን ኣሁን በትልልቅ ሰዎች የግል ምርጫቸው ጥልቅ ብሎ መፈትፈትና ስማቸውን ማዋረድ የፊስቡክ ኣመል ሆኗል፡፡ ጥሩነሽ ውጭ ኣገር ወለደች ብሎ ርር ድብን የሚል ሰው በሃገር ፍቅር ስም ንፍገቱንና ድድብናውን እየገለጸ ነው፡፡ ኣስቡት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ኢትዮጵያን የመውደድና የመጥላት ምልክት እንዴት ሊሆን ይችላል? በክፉ ቀን የደረሱልን ኣለም ኣቀፍ ኣርቲስቶች የኢትዮጵያ ዜጋ ኣይደሉም፡ ፡በሌላ ገጽ፤ የምጽዋት እህል ሽጦ ታንክ የሚሸምት ኢትዮጵያዊ ባለበት ኣገር ውስጥ ዜግነትን እንደ ትልቅ የቅድስና መለኪያ ማድረግ ኣያሳምንም፡፡ የሰውን ኣገር ሰው በጭፍን መጥላትxenophobiaን ከሃገር ፍቅር ስሜት ጋር የሚያምታቱ በርክተዋል፡፡

ባገራችን ከስርኣት ኣልበኞች በላይ ግፍ ሲሠሩ የኖሩ ህዝብን ስርኣት እናስይዛለን የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡በኣጼ ዮሀንስ ኣራተኛ ዘመን ትምባሆ ሲያጨስ የተገኘ ሰው ኣፍንጫውንና ከንፈሩን ይፎነን (ይቆረጥ)ነበር፡፡ለዝርዝሩ Gerald h portal ፤ My mission to Abyssinia ገጽ 149፡፡
በሚያጨሰው እጽ ተገፋፍሮ ይህን መሰል ጭካኔ የሰራ ሰው መኖሩን ኣላውቅም፡፡

ወለላወቼ፤ ነገርን ነገር እየገፋ እዚህ ኣደረሰኝ እንጂ ስለ ማጨስን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ኣላማ የለኝም፡፡ ኣንድ የባነነ የጥንት ኣበሻ ተናገራት ኣባባል ኣለች፡፡“ኣመልህን በጉያህ ስንቅህን በኣህያህ ”ትላለች፡፡ኣንድ ግለሰብ የዜግነት ግዴታውን እስከተወጣ ድረስ፤ የግል ኣመሉ ሁላችንም የምንጋራውን ኣደባባይ የማይጋፋ እስከሆነ ድረስ፤ ስራው ያውጣው ብለን ልንተወው ይገባል ማለት ነው፡፡

Filed in: Amharic