>
5:13 pm - Wednesday April 20, 1892

የማለዳ ወግ ... አድዮስ ነጻ ኮሚኒቲ ... ! [ነብዩ ሲራክ]

“ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት … የጅዳ ኮሚኒቲን ተቆጣጠረ “

Nebiyu Sirak 2እኩለ ሌሊት ሆኗል ፣ ከማህሌትና ከጎረምሶቸ ጋር ባንዱ የቀይ ባህር ዳርቻ ዘና ስል ነው ያመሸሁት ። እኩለ ሌሊተ ከመቃረቡ አስቀድሞ ልጆቸን ቦታ ቦታ አስይዠ አንድ ሃዘን ላይ የተቀመጠ ወዳጀን ውሎ አዳር ለመጠየቅና ላጽናና ጭምር ሄድኩ ። በሃዘኑ ቤት ተቀምጨ እያለሁ ስልኬ ደጋግማ ብትጮህም ፣ አልተመቸኝምና አላነሰኋትም … ወዳጀን ከቀሩት ጓደኞቹ ጋር በጫወታ አዝናንቸ ሃዘኑን አስረስቸ የሚያምር የጾም ወጤን በሚያምር እንጀራ እየበላሁም ስልኬ አላረፈችም ፣ ብቻ ድምጿን ብዘጋውም ጢዝ እያለች ሰላም ነስታኛለች …

ከወዳጀ ጋር ጫወታየን ከውኘ ከለቅሶው ቤት እንደ ወጣሁ ደጋግሞ የተደወለበትን ቁጥር ስመለከት ፣ በዚያው ቁጥር ጥሪውን እያስተጋባ ስልኬ ታጓራ ጀመር ፣ አነሳሁት ! ” ሰላም አቶ ነብዩ ” በሚል ሰላምታ ተቀበለኝ ደዋይ ወንድም ፣ ሰላምታውን መለስኩ ፣ ድምጹ ደዋዩ ማን እንደሆነ ያሳብቃል ፣ ፈገግ ብየ አስተያየቱን ልቀበል ስቁነጠነጥ ወዳጀ መናገሩን ቀጠለ ” የደወልኩት መረጃ ልሰጥህ ነው ፣ ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ዛሬ ምሽት አስመራጭ ፣ መራጭ ፣ ተመራጭን አቧድኖ ወደ ምርጫው በመግባት የጅዳን ኮሚኒቲ ምርጫ በአብዛኛው አባላቱን በመሰግሰግ በድል ተጠናቀቀ ! … ” አለኝና ስልኩን በንዴት ይመስላል ጀሮየ ላይ ዘጋው ፣ መልሸ ደወልኩለት ! ስልኩ ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቷል ! ብስጭቱ በንግግሩ ይታወቅ ነበርና ስልኩን ለምን እንደዘጋው ገብቶኛል …በአይኑ በብሌኑ ባየው በግኖ ተናዷላ … ምን ያድርግ !

ስልኩን የዘጋበት ጉዳይ ገባኝና ብዙም ሳይቆይ በጅዳ ኮሚኒቲ የምሽቱ ምርጫ መረጃ ወደ ሚሰጡኝ ወዳጆቸ ደወልኩ … አዎ የሸሸው ወላጅ ቀርቦ መምረጥ ተስኖት ምርጫው እንደተለመደው በተለመዱት አስመራጭ ፣ መራጮች ተከውኗል ! የተደራጁ ፣ የተዘጋጁት የሚመረጡት ተመርጠዋል !

አድዮስ ! ነጻ ኮሚኒቲ ፣ ሞተህ ተቀበርክ ግን አልልም ! የፈራሁት ፣ የተናገርኩ የጻፍኩት ሆኖ ሰምቸው አንጀቴ ቢያር ፣ ባዝንም “አበሻ ተስፋ አይቆርጥም !” በሚል ራስን መደለያ አባባል ራሴን ላጽናና ግድ አለኝ ! ስልኬንም ፊስ ቡኬንም አልዘጋም ! በቃ የሚመስለኝን ፣ የማውቀው ፣ የተነገረኝን መረጃ ሁሉ ከሙያ ስነ ምግባር ሳልለቅ የድርሻየን አደርጋለሁ ! የሰማኝ የለም ብየ አላዝንም ፣ ከሸፍኩ አልልም ! ዛሬም ነገም እናገራለሁ ! እጽፋለሁ ! እጦምራለሁ ! ነገም ሌላ ቀን ነውና !

እስኪ ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
መጋቢት 19 ቀን 2007 ዓም

Filed in: Amharic