>

ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ የታላቁ ማንቼስተር ሩጫን አሸነፉ (Fisseha Tegegn)

 Fisseha Tegegn

የአምና ድሏን ለማስከበር ወደ ብሪታኒያዋ ማንቼስተር ያቀናችው ጥሩነሽ ዲባባ እሁድ ጠዋት (May 18, 2014) ላይ የተካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር እንደተጀመረ ከሁለተኛው ኪሎ ሜትር አንስታ ከፊት በመውጣት ብቻዋን ከሮጠች በኋላ የሩጫውን ፍጥነት እና አጠቃላይ ሂደት በቁጥጥሯ ስር በማድረግ በፍጹም የበላይነት አሸናፊ ሆናለች።

የተደጋጋሚ የኦሎምፒክ እና አለም ሻምፒዮና ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤቷ ጥሩነሽ ዲባባ 10 ኪሎ ሜትሩን ሮጣ ለመጨረስ 31 ደቂቃ ከ 09 ሰከንዶች ወስዶባታል።

በቅርቡ በታሪኳ የመጀመሪያዋ የሆነው የማራቶን ውድድርን አድርጋ ለንደን ላይ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታ ያጠናቀቅችው ጥሩነሽ በግማሽ ማራቶን ከዚህ በፊት ያስመዘገበችው እና ለተከታታይ ሁለት አመታት ያሸነፈችው የማንቼስተሩ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳ ላይ ውድድር በትራክ ላይ ያሳየችውን የበላይነት በጎዳና ላይ ውድድሮችም ለመድገም ጥሩ ብቃት ላይ እንደምትገኝ ያረጋገጡ ናቸው።

ቀነኒሳ በቀለ እና ዊልሰን ኪፕሳንግ 10 ኪሎ ሜትሩ ሊጠናቀቅ 500 ሜትሮች ያህል እስከሚቀሩት ድረስ ከፊት በመውጣት አብረው ቢሮጡም ቀነኒሳ መጨረሻ ላይ በሚታወቅበት ፈጣን የአጨራረስ ብቃት በመታገዝ ርቀቱን 28:23 በሆነ ጊዜ በመጠናቀቅ የመጀመሪያው የሆነው የታላቁ ማንቼስተር ሩጫ ድልን ተጎናጽፏል።በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያዊው ታላቅ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና የአለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ኬኒያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ ፉክክር በቀነኒሳ በቀለ የበላይነት ተጠናቋል።

በቅርቡ በታሪኩ የመጀመሪያው የሆነው የማራቶን ውድድርን አድርጎ የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈው የተደጋጋሚ የኦሎምፒክ፣ አለም ሻምፒዮና እና የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ቀነኒሳ በቀለ በጎዳና ላይ ውድድሮች ድል አድራጊነቱን ተያይዞታል።

ስውዲን ጎተንበርግ ከተማ ውስጥ በሚካሄደው አመታዊው የጎተቦርግስ ቫርቬት ግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች በፍጹም የበላይነት አሸናፊ በመሆን አጠናቀዋል።

ወርቅነሽ ደገፋ ግማሽ ማራቶኑን 1 ሰአት ከ10 ደቂቃ 12 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ስታሸንፍ፣ የሀገሯ ልጅ ታደለች በቀለ በ12 ሰከንዶች ያህል ከወርቅነሽ ዘግይታ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን አግኝታ ጨርሳለች። ሆላንዳዊቷ ሂልዳ ኪቤት ሶስተኛ በመሆን ውድድሯን ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያዊያኖቹ ሂሩት አለማየሁ፣ አሰለፈች መርጊያ እና ኢንደያ መሀመድ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በመያዝ አጠናቀዋል።

በወንዶቹ የጎተንበርግ ግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ውጤት ያልቀናቸው ሲሆን ብርሀኑ ሹሜ እና አዱኛ በቀለ እንደ ቅደም ተከተላቸው ስድስተኛ እና ስምንተኛ ደረጃዎችን በመያዝ አጠናቀዋል። የወንዶቹን ውድድር ኤርትራዊው ግርማይ ገብረስላሴ ሲያሸንፍ፣ ኬኒያዊው ሪቻርድ ሜንጊች ሁለተኛ፣ ዩጋንዳዊው አብርሀም ኪፕሊሞ ሶስተኛ ህነዋል። http://www.total433.com

Filed in: Amharic