>

ኢሕአዴግኣዊ ዴሞክራሲ እና ሊብራሊዝም [ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ]

መግቢያ
ኢሕአዴግ፣ የዐፄውን ሥርዐት ርዝራዥና የደርግን አስከፊ ሥርዐት አፈራርሼ አገሪቱን በተሻለ የዴሞክራሲ ጎዳና እየመራኹ ነው በማለት ያለመታከት እያበሠረና እየወተወተ ይገኛል። ካለፈው ሥርዐት አላቅቄኣችኋለኹ የሚለው የራሱ እውነታ ቢኖረውም፣ በአንጻሩ ግን ኢሕአዴግ ራሱ የሚያበጅልን ዐዲስ ቀንበር መልክ አውጥቶ ዐደባባይ ወጥቶ መታየቱ አልቀረም፡፡ ያረጀውን አገዛዝ በዐዲስ አሠራር ከሚጭንብን ከዚኽ ዐይነቱ ቀንበር መላቀቅ የኢሕአዴግ ችግር ሳይኾን፣ የእኛ የአገሪቱ ዜጎች ችግር እና የቤት ሥራ መኾኑን መረዳት ይኖርብናል።
የዚኽ መጣጥፍ ቀዳሚ ዓላማ÷ ከኹለት ዐሥርት ዓመታት በላይ የቆየው የኢሕአዴግ አገዛዝ ከዴሞክራሲ፣ ከዜጎች ነጻነትና መብት አኳያ ምን ዐይነት መንገድ ይዞ እየኼደ እንደኾነና ኢሕአዴግ በጥቂቱም ቢኾን ከጀመረው የዴሞክራሲ መንገድ ስቶ የኋላ ኋላ ራሱን ወደ ኢ-ዴሞክራሲ አገዛዝ እንደምን እንደቀለበሰ በተወሰነ መልኩ ለማሳየት ነው። መጣጥፉ በሦስት ንኡሳን ርእሶች የተከፈለ ነው፡፡ በክፍል አንድ፣ የዴሞክራሲ እና የሊብራሊዝም ፅንሰ ሐሳቦችን ከአገራችን ኹኔታ ጋራ በማያያዝ የመንደርደሪያ ሐሳብ እሰጣለኹ። በክፍል ኹለት፣ በሰው ልጆች የቅርብ ታሪክ ውስጥ ዴሞክራሲ እና ነጻነት ለመጎናጸፍ ይበጃሉ የሚባሉት ተቋማት÷ ለምሳሌ፣ እንደ ፓርላማ፣ የፍትሕና የሚዲያ፣ የመድበለ ፓርቲና የምርጫ ሥርዐት እንዲኹም ሲቪል ማኅበራትን ኢሕአዴግ እንደምን መንፈሳቸውን ቀይሮ የራሱ የፖለቲካ መገልገያ እንዳደረጋቸው፤ የምርጫ ሥርዐቱን በምሳሌነት በማንሣት ሐተታና ትችቴን አቀርባለኹ። በክፍል ሦስት፣ በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የሚገኘውን አፍራሽ የኾነ የፍትሕ አቀራረብ በማሳየትና በመጨረሻም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዐጭር ማስታወሻ በማኖር መጣጥፉን እቋጫለኹ።
፩. የዴሞክራሲ እና የሊበራሊዝም ነገር
እንደ ዕውቁ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁር ሳሙኤል ፒ. ሃንቲንግተን እይታ፣ በቅርብ የሰው ልጅ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ጊዜዎች ሦስት የዴሞክራሲ ሞገዶች ተከሥተዋል። ከፍጹማዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የተደረጉትን ሽግግሮች ምሁሩ በሞገድ አምሳል ያቀርቧቸዋል። እንደእርሳቸው ትረካ፣ የመጀመሪያው ሞገድ ከፈረንሳይና ከአሜሪካ ዐብዮት በኋላ በ19ኛው ምእት መባቻ የተነሣው ሲኾን ተከታዩ ደግሞ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በብዙ አገሮች ውስጥ የታየው ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ከ1974 እስከ 1990 (እ. አ. አ.) ሠላሳ ያኽል አገሮች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የተሸጋገሩበት ነው፤ ምሁሩ ይህን የሽግግር ወቅት “ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።
ከሦስተኛው ሞገድ በኋላ ግን ሒደቱ የዴሞክራሲ ልምላሜን እያጠወለገ፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ወደ ኋላ ይቀለበስ ጀምሯል፡፡ ከእኒኽ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንድዋ ናት። የአገሮቹ መንግሥታት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ገብተናል ብለው ሲያውጁ፣ ነጻነት እና የመብት ጥያቄዎች ቀዳሚ ቦታ ይይዛሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር። ኾኖም ግን፣ እነዚህ መንግሥታት የዴሞክራሲን መዋቅር ሌጣውን ተቀበሉ እንጂ በባሕርያዊነት አብሮት የሚሔደውን የሊብራሊዝም ጎዳና ስላልተከተሉ፣ በአሉበት እየረገጡ ወደፊት መራመድ ተስኗቸዋል።
በዚህ ዙሪያ ወሳኝ ጥናቶችን ያደረጉ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ የዴሞክራሲ እና የሊብራሊዝም ፖለቲካዊ መርሕ ከፍልስፍና አንጻር ሲታዩ አንድነትም ልዩነትም አላቸው። የሰው ልጅ ምሉዕ የኾነ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ፍትሐዊ ነጻነት ይኖረው ዘንድ የዴሞክራሲ እና የሊብራሊዝም መስተጋብር የግድ ይላል። ዴሞክራሲ የሚለው ቃል በዋናነት ሕዝብን ከዓምባገነናዊ ኀይል የሚከላከል ጋሻ (Demo-protection) ሲኾን፣ ሊብራሊዝም ደግሞ የሕዝብ ሉዓላዊነት (Demo-power) ነው። ዐዲሶቹ “ዴሞክራሲያዊ” መንግሥታት በተወሰነ ደረጃ የዴሞክራሲን አንዳንድ ፈለጎች ለመከተል ባይቸገሩም፣ የሊብራል ጥሪዎችን ማድመጥ ግን በእጅጉ ተስኗቸዋል።
ምናልባት፣ በዴሞክራሲ እና በሊብራሊዝም መሀል እንዴት ወይም ምን ዓይነት ልዩነት ሊኖር ይችላል ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ስለሚኖሩ በዚኽ ዙሪያ ጥቂት ብለን ማለፉ ተገቢ ነው። አንደኛ፣ ዴሞክራሲ የሚያተኩረው በሥልጣን ክፍፍል፣ በየጊዜው በሚደረጉ ምርጫዎች፣ በብዙኃን መገናኛ፣ በመድበለ ፓርቲ፣ በሲቪል ማኅበራት… ወዘተ ተቋማዊ አያያዝና አሠራር ላይ ነው። በአንጻሩ ሊብራሊዝም በሕግ የበላይነት፣ በመሠረታዊ የሰው ልጆች ነጻነትና መብት ላይ ያተኩራል።
ኹለተኛ፣ ዴሞክራሲ የመንግሥት ሥልጣን በሚያዝበት መዋቅር ላይ ሲያተኩር፣ ሊብራሊዝም ደግሞ የሥልጣን ወንዝ ከገደቡ ወጥቶ ዜጎችን እንዳያጥለቀልቅ ለመከላከል፣ በምን መንገድ እየተቀየሰና እየተገራ መሔድ እንዳለበትና እንደሚገባው ይደነግጋል። ይኸውም ዴሞክራሲ ተሳትፎ ላይ ሲያተኩር ሊብራሊዝም ደግሞ ተጠያቂነት ላይ ያተኩራል። በአንዲት አገር መልካም የነጻነትና የፍትሕ ሕይወት መንገድ ተይዟል የሚባለው፣ ዴሞክራሲ የሚጠይቀው ሕዝባዊ ተሳትፎና ሊብራሊዝም የሚሻው መንግሥታዊ ተጠያቂነት በአንድነት ተባብረው ሲገኙ ነው።
በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ የዴሞክራሲ እና የሊበራሊዝም የአጽንዖት ልዩነት እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ኹኔታ ስንመጣ፣ ሥርዐቱ የኹለቱንም መሠረታዊ ጥሪዎች ማስተናገድ የተሣነው ኾኖ እናገኘዋለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከደርግ በኋላ፣ በተወሰነ መልኩ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ቢያገኝም፣ ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግገው የሥልጣን ባለቤትነትን አልተጎናጸፈም። ይህን ለማለት የሚያስደፍረው፣ የአገራችንን ፖለቲካ ከሕዝባዊ ተሳትፎና ከመንግሥታዊ ተጠያቂነት አንጻር ስንመለከተው ትልቅ ጉድለት በመኖሩ ነው፡፡
(፩) ሕዝባዊ ተሳትፎ፦ ዜጎች በሕይወታቸው፣ በንብረታቸው፣ በማኅበረሰባዊ ኹኔታዎቻቸው ወሳኝ በኾኑ ጉዳዮች ላይ የምክክርና የውሳኔዎች አካል ባልኾኑበት ሥርዐትና አሠራር ውስጥ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ጥሪ የኾነው ሕዝባዊ ተሳትፎ አልተወለደም ማለት ነው። ለኢሕአዴግ ግን ተሳትፎ ማለት (ሀ)አስቀድሞ የወሰነውን ነገር ሥልጠና በሚል ፈሊጥ ወደ ሕዝብ ማውረድ፣ (ለ)ባለድርሻ በሚል ፈሊጥ የራሱን ወኪሎች መርጦ ውሳኔዎች በተሳትፎ የተገኙ ማስመሰል ነው። ለሐቀኛ ተሳትፎ ግን የንግግር ነጻነት እና የመሰብሰብ ነጻነት ያስፈልጋል። መንግሥት እና ዜጎች በእኩል ደረጃ መወያየታቸው ቀርቶ፣ መንግሥት አቀባይ ሕዝብ ደግሞ ተቀባይ ኾነዋል።
(፪) ተጠያቂነት፦ መረጃ ከመንግሥት ወደ ሕዝብ የማይወርድበት አገር ውስጥ የተጠያቂነትን ሥርዐት ማሟላት በእጅጉ አስቸጋሪ ይኾናል። ሥርዐቱን ለማሟላት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የኾነ ሚዲያ ይኖር ዘንድ ግድ ይላል። ዜጎች መረጃ የሚያገኙበት መንገድ እስከሌላቸው ድረስ መንግሥትን ተጠያቂ ሊያደርጉባቸው የሚችሉባቸው መንገዶች ኹሉ ይዘጋሉ።
አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን፣ ዴሞክራሲ ለማበብ ረዘም ያለ ጊዜ ይጠይቃል፤ በመኾኑም ኢሕአዴግን የበለጸገ ዴሞክራሲ አላመጣም ብሎ መተቸት አግባብነት የለውም፤ የሚል መከላከያ ያቀርባሉ። የአፍሪቃ ዴሞክራሲ ገና ለጋ በመኾኑ ለመቶዎች ዓመታት ከቆየው ምዕራባዊ ዴሞክራሲ ጋራ ሊነጻጸር አይገባም፤ ሲሉም ይሞግታሉ። ለዚኽ ዓይነቱ አስተያየት ተገቢ መልስ ሰጥተዋል ብለን የምናምነው የ20ኛው ምእት ትልቁ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጂዮቫኒ ሳርቶሪ (Giovanni Sartori) ናቸው። በእርሳቸው አመላለስ፣ ዴሞክራሲ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት መዋቅር እንጂ አንድ ወጥ ባለመኾኑ፣ አንድ መንግሥት ቢያንስ የዜጎችን የንግግር፣ የመሰብሰብና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማክበር ምን ያኽል ጊዜ ያስፈልገዋል? ጋዜጠኛን ላለማሰር፣ የፖለቲካ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን ላለመከልከል ሥርዐቱ ስንት ዘመን መቆየት ይኖርበታል?
በእኔ በኩል በዴሞክራሲ ፍላጎትና በገዢዎች ፍላጎት መሀል የተዘረጋው ቅራኔ እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ከዚህ ቀደም ለማሳየት እንደሞከርኹት፣ የአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ ለችግር የተጋለጠበት አንዱ ምክንያት፣ አውሮጳውያን በዘመነ አብርሆ ለመቶ ዓመታት ያኽል እንደአደረጉት፣ በሊብራሊዝም ባህል ላይ የተመሠረተ የሐሳብና አመለካከትን የመግለጽ ነጻነት፣ የኅትመት ነጻነት፣ ሃይማኖታዊ መቻቻልና በጥቅሉ በመሠረታዊ የሰው ልጆች የነጻነት ጥያቄዎች ላይ አስቀድመን ብርቱ ሥራ ባለመሥራታችን ነው።
፪. ዐዲሶቹ የኢ-ዴሞክራሲያዊ ኀይሎች ሥርዐተ ተቋማት
በዚህ ርእስ ሥር በከፊል የማቀርበው ሐሳብ በዋናነት የተመረኮዘው፣ በቅርቡ የጀርመኑ የፖለቲካ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር አንድሪያስ ሺድለር (Andreas Schedler) በ2009 (እ. አ. አ.) በዴሞክራሲ ስያሜ ስለሚንቀሳቀሱት ዐዲስ መንግሥታት በአጠኑት ጥናት ላይ ነው።
ቀደም ባለው ክፍል ለማሳየት እንደሞከርኹት፣ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ፒ. ሃንቲንግተን “ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ” ወደፊት መገስገሡን ትቶ፣ የቀኝ-ኋላ ዙር መንገድ መከተሉን መግለጻቸውን አውስቻለኹ። ሌሎች ጸሐፍትም፣ ከዚኹ የገለጻ መንፈስ ጋራ በሚሔድ መልኩ፣ ይህን ፕሮፌሰሩ ‘ቅልበሳ’ ያሉትን ፅንሰ ሐሳብ፣ አንዴ ‘ኢ-ሊብራል ዴሞክራሲ’፣ አንዳንዴ ‘ኦተሪቴሪያን ዴሞክራሲ’ የሚሉ ስያሜዎች እየሰጡ ለመግለጽ ሞክረዋል። ፅንሰ ሐሳቡ በተለያዩ ስያሜዎች ቢገለጽም፣ በዋና ጭብጣቸው፣ የሥርዐቶቹን ‘ኢ-ዴሞክራሲያዊ’ ባሕርይ የሚያሳዩ መኾኑ ላይ ግን ሙሉ ስምምነትና አንድነት አላቸው።የዴሞክራሲ ሞገድ ውስጥ የተፈጠሩት ዐዲስ ሥርዓቶች፣ በውጣኔአቸው የነጻነትና የመብት ፍንጣቂ ቢታይባቸውም፣ ከሰብአዊ ነጻነት አኳያ ሲመዘኑ ግን የተመናመነ የተሰፋ መንገድ ላይ እንዳሉ መረዳት አዳጋች አይኾንም።
“ፍጹማዊ የሥልጣን አገዛዝ” ወይም ደግሞ “የጭቆና አገዛዝ” በሚል ቀደም ብሎ የሚታወቀው ስያሜ በዐዲሶቹ ሥርዐቶች ዐውድ ውስጥ “ዴሞክራሲያዊ” የሚል ቅጽል ተለጥፎለት እናገኘዋለን። እዚኽ ላይ ማንሣት የሚገባን መሠረታዊ ጥያቄ፣ “ዴሞክራሲያዊ” የሚለው ቃል ከእኒኽ ሥርዓቶች ስያሜ ጋራ ለምን አብሮ ተያይዞ ይቀርባል? የሚል መኾን ይኖርበታል። ይህን ጥያቄ የምናነሣበት ዋነኛ ምክንያት በቀደመው ዓምባገነናዊ አገዛዝ (Dictatorship) እና በዛሬው ጠቅላይ አገዛዝ (Authoritarianism) መካከል መሠረታዊ ዝምድናና ልዩነት ይኖር እንደኾን መፈተሽ ስላለብን ነው።
ፍተሻው በቀጥታ ወደ አገራችን ተጨባጭ ኹኔታ ያመጣናል። ለመኾኑ፣ በደርግ ሥርዐትና በኢሕአዴግ ሥርዐት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ደርግን “ዲክቴተርሺፕ”፣ ኢሕአዴግን ደግሞ “ኦተሪቴርያን” የምንላቸው ለምንድን ነው? የኹለቱ ሥርዐቶች ልዩነት ሲቀርብ፦ አንዱ ገዳይ፣ ጨፍጫፊ፣ አረመኔ ተደርጎ ይተነተናል፤ ሌላው ደግሞ፣ በወዳጆቹ ዘንድ፣ እንደ ነጻ አውጪ፣ የዴሞክራሲ አራማጅ ተደርጎ ሲቀርብ፣ በተቃዋሚዎቹ በኩል ደግሞ፣ እንደ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ጎሰኛ ተደርገው እንደኾነ ዘወትር እንሰማለን። ኹለቱም አቀራረቦች ላይ ላዩን ሲታዩ በተወሰነ መልኩ እውነታ ቢኖራቸውም፣ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ግን፣ የኹለቱን ሥርዐቶች መሠረታዊ ልዩነት በበቂ አይነግሩንም። በመኾኑም የቀድሞውንና የዐዲሱን መንግሥታዊ ሥርዐቶች ልዩነት በምንመረምርበት ጊዜ፣ ፕሮፌሰር ሺድለር የሚያቀርቡት ሐሳብ የበለጠ ጠቃሚ ኾኖ እናገኘዋለን።
ቀዳሚ የሚኾነው የኹለቱም ሥርዐቶች ተልእኮ ሥልጣንን ማካበት እና ሥልጣን ላይ መቆየት ነው። ከዚኽ አንጻር፣ ኹለቱም ሥርዐቶች ግባቸው አንድ ነው፡፡ ከግቡ ለመድረስ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ግን የተለያዩ ናቸው። እንደ ፕሮፌሰር ሺድለር አቀራረብ፣ የቀድሞዎቹ ዓምባገነኖች ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚጠቀሙባቸው ተቋማት ወትሮውንም በታሪክ ውስጥ የሰውን ልጅ ነጻነት በመፈታተን የሚታወቁትን፣ እንደ ‘የጦር ኀይል’፣ ‘ፖሊስ’፣ ‘ጸጥታ’፣ ‘ደኅንነት’፣ ‘ሲቪል ታጣቂዎች’ ናቸው። በሌላ በኩል፣ ዐዲስ የመጡት ዴሞክራሲያዊ ነን የሚሉት ሥርዐቶች ደግሞ የድሮውን የመጨቆኛ ተቋማት ትተው፣ የሰውን ነጻነትና መብት ያስከብራሉ የሚባሉትን የፍትሕ፣ የሕግ አውጪ፣ የምርጫ፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማትን ወዘተ… በጭቆና መሣሪያነት ይጠቀማሉ።
እዚህ ላይ ተገቢ የሚኾነው ጥያቄ፣ ለነጻነት የታሰቡ ተቋማት እንደምን ተቀልብሰው የመንግሥት መጠቀሚያ ለመኾን በቁ? የሚል ነው። በመኾኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ገለጻ ከሰጠን በኋላ፣ የፍትሕ ተቋማትን፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማትንና የምርጫ ተቋማትን በምሳሌነት እናነሣለን።
ከኹሉ አስቀድሞ፣ ዐዲሱ ሥርዐት ሥልጣን በሚይዝበት ጊዜ የሚረከበው “ባዶ የፖለቲካ ተቋማዊ መሬት” (institutional tabularasa) አያገኝም። እንዲያውም ካለፈው ሥርዐት የቀጠሉ ርዝራዥ ተቋማት ተፎካካሪ ሊኾኑበት ስለሚችሉ የሚጠቅመውን ተቋም ዐቅፎና አስቀጥሎ አይበጀኝም የሚለውን ያፈርሰዋል።
በኹለተኛ ደረጃ፣ ዴሞክራሲን ሊያራምዱ ይችላሉ የሚባሉትን ዐዲስ ተቋማት ይገነባል፤ ኾኖም ግን፣ ተቋማቱ በመጀመሪያ እንደ ሥርዐት የቆሙበትን መንፈስ ሽሮ ሕይወት አልባ በማድረግ ለታይታ፣ በቅርፃቸው ብቻ እውናዊ እንዲመስሉ ያደርጋቸዋል። በዚኽም ሳይገታ በራሱ ቁጥጥር ሥር ከአዋላቸው በኋላ፣ ተቋማቱን እንደ ለማዳ እንስሳ እዚያው ሥርዐቱ ግቢ ውስጥ ይለቃቅቸዋል፤ ነገር ግን እነኚኽ የተሽመደመዱና ለአገዛዙ የተገሩ ተቋማት እንዲኹ ተቀላቢ ኾነው አይቀመጡም። ሥርዐቱ እስከአለ ድረስ ትጉሃን የጭነት ፈረስ ኾነው አገልግሎታቸውን ያበረክታሉ።
በሦስተኛ ደረጃ፣ ሥርዐቱ ሲጀምር ሕገ መንግሥት ተቀርፆ በአንድ በኩል ከአሐዳዊ ወደ ፌደራላዊ ሥርዓት ሽግግር መደረጉ ተገልጧል፤ በሌላ በኩል ከአንድ ወጥ የሥልጣን ዘርፍ ወደተለያየ የሥልጣን ዘርፍ ሔዶ የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር በሕገ መንግሥቱ በሕግ ተደንግጓል፡፡ አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለን በምንመለከትበት ጊዜ ግን የምናገኘው የሚከተለውን እውነታ ነው። ሕግ አስፈጻሚው ክፍል ወደ ጎን (Horizontal) እና ወደ ላይ (vertical) የሥልጣን ሽሚያ በማድረግ በአንድ በኩል ፌደራል ተቋሙ ላይ በሌላ በኩል የሕግ አውጪው እና የሕግ ተርጓሚው ላይ ትልቅ ጫና በማሳረፍ ሥልጣናቸውን በእጅጉ ገድቦታል። በመኾኑም፣ በእኒኽ ኹለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ ሕግ አስፈጻሚው ተቋም ከሌሎቹ የመንግሥት ክፍሎች ኹሉ በበለጠ እየተጠናከረ እንዲኹም ሌሎቹን ተቋማት እያመነመነ ሔዷል።
ሀ) የፍትሕ ተቋማት፡-
በማንኛውም ሀገር ታሪክና በእኛም ነባራዊ ኹኔታ እንደምንረዳው፤ ያለሕግ ነጻነት የለም። እንዲኹም ሕግን ለመተግበር የፍትሕ ተቋማት ወሳኝ ድርሻ አላቸው። ኾኖም ግን የአንድን አገር ፍትሕ ለማስከበር የሕግ ተቋማት ራሳቸው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የግድ ይላል። ይኸውም የራሳቸውን ልዕልና ያላስከበሩ ተቋማት የዜጎችን ነጻነት ያስከብራሉ ማለት ዘበት ስለኾነ ነው።
አንዳንድ ጸሐፍት እንደሚነግሩን፣ የጠቅላይነት ሥርዓቶች የፍትሕ ተቋማትን ልዕልናና አቋም ለመቦርቦርና ለማዳከም ሕጉን ለመጨቆኛ በሚኾን መልኩ ደጋግመው በማመቻቸት (Judicialization of repression) ሲተገብሩ ይስተዋላሉ። ይህን ለመተግበር ከሚከተሏቸው መንገዶች የተወሰኑትን እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
I. የፍትሕ ተቋማትን ሥልጣን መገደብ (disempowerment)፤
የፍትሕ ተቋማትን መገደብ በምንልበት ጊዜ፤ የተለያየ እመቃ ደረጃ ያለው ነው። በመጀመሪያ፣ የተሠየሙትን ዳኞች ሥልጣን መገደብና ማሳነስ ነው፤ በተጨማሪም ለመመርመር የሚችሉበትን ወሰን በእጅጉ ማጣበብና በመጨረሻም ዳኞች ሊኖራቸው የሚገባውን የውሳኔ ነጻነት (ዲስግሬሽን) ማሳጠር ማለት ነው።
II. ለመንግሥት “ይበጃሉ” የሚባሉ ሰዎችን መሠየም፤
በዚህ ረድፍ የሚታየው ኢ-ፍትሐዊ ጉዞ የሚጀመረው በዳኝነት ወንበር ላይ የሚሠየሙት ዳኞች እየተመረጡ የሥርዐቱ ወዳጆች እንዲኾኑ መደረጉ ነው። የሕዝብ አስተዳደር ጥናት ያጠኑ አንዳንድ ምሁራን እንደሚነግሩን፤ አንደኛው የመንግሥት ችሎታ፣ ለጥቅማጥቅም ቀልባቸውን ሊሰጡ የሚችሉትን ነቅሶ የማውጣት ስልት ነው። እነኚኽም ለጥቅማጥቅምና ድጎማ የተመቻቹ ሹመኞች (incentive compatibility) ናቸው። በጥቅም የማይደለሉትን ደግሞ ቀጥተኛውን መንገድ ተከትለው እንዳይሔዱ በማስፈራራት ሐሳብን የማስፈጸም ጫና (dissuasive punishment) እንዲደርስባቸው ይደረጋል። ከዚኽም በተጨማሪ የፍትሕ ሒደቱን ረጅምና ውሳኔውን ለመሻር በሚያመች መልኩ ከታች ወደ ላይ እንዲሔድ፤ እልባቱ በረጅም የአቤቱታና የውሳኔ መሻርያ ሰንሰለት እንዲፈጸም ይደረጋል።
III. የተበታተነ የፍትሕ ሥርዐት፤
ሕጉን ለመጨቆኛ በሚኾን መልኩ ማመቻቸት (Judicialization of repression) በአንድ ሀገር ያለ የፍትሕ ሥርዓት አንድ ወጥ የኾነ ቅርጽ እንዳይኖረው፣ መደበኛ ከኾነው የሕግ ተቋም ተፎካካሪና በሕግ አስፈጻሚው ቁጥጥር ሥር የኾነ መንታ ተቋም በመፍጠር የመደበኛውን ፍርድ ቤት ተግባር ወደ ተቀጽላው ተቋም ማሸጋገር ነው።
ለ) የሚዲያ ቁጥጥር፤
ሚዲያን በሚመለከት ተቀዳሚው የኦተሪተርያን መንግሥታት ዓላማ፤ ፖለቲካዊ መረጃዎችን የማምረቻ ኃይልን መቆጣጠርና በአገሩ ውስጥ ብቸኛ አምራች ኾኖ መቅረብ ነው። ዜጎች በተለይ የፖለቲካ መረጃን በአማራጭ እንዳያገኙና ተፎካካሪ የኾነ የፖለቲካ ምልከታ እንዳይኖር ፍጹማዊ ሥልጣንን የተጎናጸፉ መንግሥታት ከሚያደርጓቸው ዕቀባዎች መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
የመገናኛ ምንጮች ብዝኃነት በመከልከሉ ዜጎች የመገናኛ አውታር ባለቤት የመኾን ዕድል የላቸውም። በመኾኑም በአገሪቱ የሚገኙት ሚዲያዎች በመንግሥት ሥር በመኾናቸው፤ የዝግጅቱን ይዘት ለመወሰን፣ ሕዝቡ ምን መስማት እንዳለበትና ምን መስማት እንደሌለበት በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ ይችላሉ። አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ለግለሰቦች በባለቤትነት የተሰጡ ቢኾንም የትኩረት አቅጣጫቸው ጠንከር ያሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሣት ወይም ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በትኩረት በመዘገብ እንዲሠሩ ስለማይፈቅድ ብዙ ጊዜ በመዝናኛ፣ በስፖርታዊ ዘገባዎችና ይህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የታጠሩ ፕሮግራሞችን በማስተላለፍ እንዲጠመዱ ያደርጓቸዋል። ይህ ዐይነቱ የመገናኛና ሚዲያ የትኩረት አቅጣጫ ለሥርዐቱ ብዙም አስጊ ባለመኾኑ ከጫና ለመገላገል የሚጠቅም መላ ኾኖ ሲያገለግል ይስተዋላል።
ሐ. የምርጫ ሥርዓት፡-
ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና ገብተዋል የሚባሉት አገሮች ተቀዳሚ ሥራ የሠሩት በምርጫ ተቋማት ላይ ነው። መንግሥታት በአገራቸው ሕዝብ ፊትም ኾነ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ፊት በፍትሐዊ ምርጫ ሥርዐትና ሒደት ውስጥ ማለፋቸው የቅቡልነት መሠረታዊ ጥያቄ ኾኗል። የምርጫ አስፈላጊነት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ላይ እንኳን የሕግ ዕውቅና አግኝቶ ወቅታዊ እና እውነተኛ ምርጫ ማካሔድ የአገሮች ተቀዳሚ ሓላፊነት እንደኾነ ተቀምጧል።
በኢትዮጵያም በሕገ መንግሥቱ፣ እንደ አንድ የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት ውስጥ እንዳለ አገር፣ በየአምስት ዓመቱ አገሪቱን ለማስተዳደር ተፎካካሪ ፓርቲዎች በብሔራዊ ምርጫ ለመንግሥት ሥልጣን የሚወዳደሩበት ሥርዐት ተደንግጓል። ከዚኽም በመነሣት፤ የመጪው ግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. ውድድር ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና የሕዝብ ተአማኒነት ባለው መልኩ እንዲካሔድ አቅጣጫ ተቀምጧል። የሕዝብ ተአማኒነት የሚለው እንደ መሥፈርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ ስላልሆነ ለጊዜው እንተወውና፣ “ነጻ” እና “ፍትሐዊ” በሚሉት ስያሜዎች ላይ እናተኩር። ከኹሉ አስቀድሞ፣ ቃላት በመስጠትና ቃላቱን በመደጋገም ብቻ እውንና ተጨባጭ ማድረግ ይቻላል ወይ? በአኹኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ልትጎናጸፍ ትችላለች ወይ? ስለ ነጻና ፍትሕዊ ምርጫ በመጠኑ ከአብራራኹ በኋላ፣ የጥያቄዎቹን ምላሽ ለአንባቢ እተዋለኹ።
“ነጻ” እና “ፍትሐዊ” የሚለው ቃል በመጀመሪያ ብቅ ያለው እ.ኤ.አ. በ1927 ዓ.ም. የአሜሪካን ካልቨን ኮሌጅ ልኡክ ኒኳራጓ ለምትባለው አገር “አሜሪካ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንድታካሂድ ቃል እሰጣለኹ፤” የሚል ንግግር ሲያደርግ ቃሉ የመጀመሪያ ዕውቅናውን አግኝቷል። ቀጥሎም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ1956 ዓ.ም የቶጎ ላንድን የወደፊት ኹኔታ በሕዝበ ውሳኔ ለማረጋገጥ ባወጣው ሪፖርት ላይ ይኸው ቃል ተደግሟል። በሦስተኛ ደረጃ፤ በ1978 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔና ቁጥጥር የናሚቢያ ነጻነት፣ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ከተካሔደ በኋላ ምክር ቤቱ የሒደቱን ፍትሐዊነትና ነጻ አካሔድ ለዓለም ሲያበሥር ቃላቱ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ለማግኘት በቅተዋል።
ኹለቱ ስያሜዎች አብዛኛውን ጊዜ በአንድነት ቢጠቀሱም፤ ይዘታቸውንና ትርጉማቸውን በተናጠል ለማየት እሞክራለኹ፡፡
(ሀ) የምርጫ ነጻ ሒደት ሲባል፡-
ከኹሉ አስቀድሞ ነጻ የሚለው ቃል ዜጎች የማይሸራረፍ የመምረጥ መብት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው። የዜጎችን በነጻ የመምረጥ መብት ለመተግበር የሚከተሉት ኹኔታዎች መመቻቸት አለባቸው።
1. የመሰብሰብ እና የመመካከር ነጻነት፣
2. ማኅበራትን የማቋቋም መብት፣
3. የመንቀሳቀስ መብት፣
4. የመናገር መብት፣
5. የፖለቲካ ድባቡ ከዘለፋ፣ ከማስፈራራትና ከመዋከብ የጸዳ መኾን ይኖርበታል።
(ለ) ፍትሐዊ ምርጫ ስንል ደግሞ፡-
1. ተአማኒ በኾነ የምርጫ ቦርድ ሥር የድምፅ ቆጠራው መካሔዱ፣
2. ከምርጫው በፊትም ኾነ በኋላ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለመግባባት ሲከሠት ፍትሐዊ የግጭት መፍትሔ የሚሰጥ ተቋም መኖሩ፣
3. ኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ውድድር ውስጥ እንዲገቡ ያልተጨናነቀና እኩል ዕድል መስጠት፣
4. ኹሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያስተናግድ እኩል የሚዲያ አቅርቦት ማመቻቸት፣
5. የውድድሩ ሜዳ ለኹሉም ፓርቲዎች የተስተካከለ እንዲኾን ማድረግ ሲቻል፣
6. በዋናነት የመንግሥትና የፓርቲ የምርጫ ወጪ የሚወጣበት ቋት ሲለይ ነው።
ከላይ የጠቀስናቸው አንዳንድ ነጥቦች እንደሚያሳዩት፣ ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ የሚሟላው በአንድ ቀን የድምፅ መስጫ ኮሮጆ ውስጥ ካርድ በማስገባት ሳይኾን ሦስት የምርጫ ሒደትን ሲያካትት ነው። (ሀ)ከምርጫ በፊት ያለው የአገሪቱ የፖለቲካ ድባብና የመወዳደሪያው ሜዳ መስተካከል፤ (ለ)የምርጫው ቀን ውሎ እና ገለልተኛ አወዳዳሪ ተቋም፤ (ሐ)ከምርጫው ዕለት በኋላ በተወዳዳሪዎች መካከል ጭቅጭቅ ቢነሣ ዳኝነትን የሚሰጥ ገለልተኛ ተቋም። ከላይ ላነሣነውም ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለማግኘት፣ አንባቢ፣ የጠቀስናቸውን መስፈርቶች ከአገራችን ነባራዊው ኹኔታ ጋራ በማነጻጸር የራሱን ፍርድ መስጠት ይችላል።
(ይቀጥላል)

(አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅፅ 15 ቁጥር 789፣ የካቲት 28 ቀን 2007 ዓ.ም)

 

Filed in: Amharic