>

ኢሳያስ አፈወርቂን በጨረፍታ [ ክንፉ አሰፋ]

ESAT Interview with Isaias Afwerki: Part 1-2

“አንድም ቀን ስቀን አናውቅም!” አሉ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም። ይህን በሚሉ ጊዜ እፊታቸው ላይ ፈገግታ ይታይ ነበር -ምሬቱ እንዳለ ሆኖ። ኢሳያስ አፈወርቂ ሲስቁ አይተናቸው አናውቅም። ግን ኮስተር ብለው የሚናገሩት ነገር እኛኑ አያሳቀን ነው። “ካሳ ይገባናል! ካሳ ስጡን” ሲሉ አሳቁን። ቀጠል አድርገውም “ምጽዋና አሰብን ወያኔ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲጠቀምበት ፈልገው” እንደነበር ተናግረው አሳቁን። “…የሰራነው ጥፋት ስለሌለ የሚጸጥተን ነገር የለም።” አሉ እጃቸውን እንደ ጲላጦስ እያጠቡ።   ከዚህ ቀደም ለስዊድኑ ጋዜጠኛ የአስመራው የፖለቲካ ስርዓት ስዊድን ካለው ስርዓት የተሻለ እንደሆነ አስረግጠው ነገሩት። ስለ ብሄራዊ ምርጫ ለጠየቀቻቸው የአልጃዚራዋ ጋዜጠኛም “ምርጫ ምንድነው?” ብለዋት ነበር።   ከዚህ በላይ ምን የሚያስቅ ነገር አለ?

የፈለጉት ካሳ ግን ምን ይሆን? የገንዘብ ካሳ፣ የሞራል ወይንስ የሃገር? ….  ጾረና፣ ዛላምበሳ፣ ባድመ? ወይንስ ኢትዮጵያ! ?

“በዋልድባም ባመት አንዴ ይዘፈናል።” ይባላል። ኢሳያስ አፈወርቂስ ባመት አንዴ ብቅ እያሉ ስለ ኢትዮጵያ የፈለጉትን ቢናገሩ ምን ይላቸዋል? በዚያ ላይ አሁን “የኢትዮጵያ ወዳጅ” ሆነዋል።

ናሳ የተባለው የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም የአፍሪካ ቀንድን በሳተላይት ፎቶ አንስቶ ነበር። በፎቶው ላይ ሲታይ ኤርትራ ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ ነበረች። ሳይንቲስቶቹ ይህችን ቆላማ ሃገር እንደሚወራው በረሃ ሳይሆን ይልቁንም ከጠበቁት በላይ ለም ሆና ተመለከቷት።  ከሺዎች ኪሎሜትር የተነሳውን ይህንን ምስል እያቀረቡ ሲመለከቱት ግን ነገሩ ሌላ ሆኖ አገኙት።  ከሩቅ የለመለመ ቅጠል መስሎ የሚታየው ነገር አረንጓዴው የወታደር ልብስ ኖሯል። ሳዋ፤ ትልቁ የኢሳያስ አፈወርቂ ዩኒቨርሲቲ ከህጻን እስከ አዛውንት እያስገባ ውትድርና ያሰለጥናል። በኤርትራ ዛሬ ሁሉም ዜጋ ወታደር እንዲሆን ተገዷል። የወያኔን ስርዓት በሃይል ለመጣል በአስመራ ጦር ያሰፈሩ የተቃዋሚ ሃይሎች ቁጥርም ቀላል አይደለም። አረንጓዴ የለበሱ እነዚህ ሃይሎች እድሜያቸውም ሁለቱን አስር ሊነካው ነው።

የኢሳት ጋዜጠኖች ኢሳያስን ለጠየቋቸው አንደኛው ጥያቄ ምላሹ ይኸው ነው። ሁሉም አረንጓዴ ለባሽ፣ ሁሉም ነጭ ለባሽ በሆነበት ሃገር ማን ማንን ሊጠብቅ ይችላል?  “ባለስልጣናቱ ሁሉ ያለ አጃቢ የሚሄዱበት ምክንያት ምስጢሩ ምንድነው?” የሚል ነበር ጥያቄው። ጥያቄዋ አቅጣጫ ቀያሽ ጥያቄ ስለነበረች ለኢሳያስ አፈወርቂ እንደተመቻቸው ያስታውቅባቸዋል። መልስ ሲሰጡ ንፅፅር ውስጥ ገቡና እድሉን ባላንጣዎቸውን ለመምቻ ተጠቀሙበት።  ባላንጣቸው ህወሃት ብቻ አይደለም። ምእራቡም፣ ምስራቁ ዓለም የእሳቸው ጠላት ነው።

በሁሉም ጉዳይ ላይ ባዕዳንን ይወቅሳሉ። እዚህ ላይ እውነት አላቸው። ታሪክ እንደሚነግረን ለሃያላን ሃገሮች አልንበረከክ ያለች ኢትዮጵያን ለማዳከም የባህር በር ማሳጣቱ ሴራ በባእዳን ነው የተጠነሰሰው። እሳቸውም ምስጢሩን በደንብ አድርገው ያውቁታል። ይህን ሴራ እውን ለማድረግ በቱርክና በግብፅ ከዚያም በጣሊያንና በእንግሊዝ ብዙ ተሞክሮ ነበር።  የጉንደት፣ የጉራ፣ የኩፊት፤ የኮቲት እና የዶጋሊ ጦርነቶች ለዚህ ዋቢ ናቸው። ሁሉም  አልተሳኩም። ይህንን የቤት ስራ በመጀመርያ ጀብሃ ከዚያ ቀጥሎ ሻእቢያ ከባእዳን ተቀብሎ መስራት ጀመረ።  የነዚህ ባእዳን ህልም በመጨረሻ በኢሳያስ አፈወርቂ እውን ሆነ። 5 ሚሊዮን ህዝብ ላይጠቀምበት የሁለት ወደብ ባለቤት ሲሆን፣ 80 ሚሊዮን ህዝብ ግን ያለ ወደብ እንዲኖር ተደረገ።

እኝህ ሰው የርስበርስ ጦርነቱን አሸንፈው ኤርትራን ባስገነጠሉ ጊዜ ጀግና ነበሩ። የግዜ እንጂ የሰው ጀግና የለምና የጀግንነታቸው ጫጉላ እንዳሰቡት ረጅም አልዘለቀም። “ነጻነቱን” በቅጡ ሳያጣጥሙት ሌሎች ጦርነቶች ውስጥ ገቡ። ትልቁ እና ዋነኛው ጦርንርት ግን ከሕዝባቸው ጋር የገጠሙት ፍልሚያ ነው። ውጤቱም ስደት ሆነ።  ዛሬ የኤርትራን ምድር ለቅቆ ለመጥፋት የማይጥር ዜጋ የለም። በኮንቬንሽናል ጦርነት ጊዜ ከሚሰደደው ህዝብ የበለጠ ቁጥር ያለው ህዝብ ይሰደዳል። ከኤርትራ ህዝብ ብዛት አንጻር ሲታይም ስደተኛው እጅግ ብዙ ነው።   የተሳካለት የኤርትራ ተወላጅ በረሃ አቋርጦ ኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ሊቢያ ይዘልቃል። ያልተሳካለት ደግሞ በየጠረፉ የሻእቢያ ራት ይሆናል። የዜጎች ኩላሊት ሽያጭም እዚያው  ይካሄዳል።  በኤርትራ እንደቀልድ የሚነገር እውነታ አለ። ኢሳያስ አፈወርቂ ለኤርትራ ካበረከቱት ነገር ሁሉ የኢቦላ ወረርሽኝ በሃገራቸው እንዳይገባ ማድረጋቸው ነው። ከዚያ የሚወጣ እንጂ የሚገባ ሰው ስለሌለ።

በዚህ ዘመን ከሚከሰቱት እልቂቶች ሁሉ የላቀ እልቂት እና ሰቆቃ የምናየው በነዚህ ወገኖቻችን ላይ ነው። ስንት ኤርትራውያን እንደበላች የሲሲሊዋ ላምባዶዛ ትመስክር።

“ጽድቁ ቀርቶ፣ በቅጡ በኮነነኝ” ይላሉ አበው። የካሳውን ተረት ለጊዜው እንተወውና፣ ታሪክ ኢሳያስን የሚዘክራቸው በተያያዙት የግፍ አስተዳደራቸው ይሆናል። በለስ ቀንቷቸው የኤርትራን ምድር ነጻ ቢያደርጓትም ህዝቡ ግን ነጻነትን እንደናፈቀ እነሆ 23 ዓመታት አለፉ። ህዝበ ኤርትራ ነጻ አልወጣም። ኢኮኖሚውም እንደ ቤተ-ጸሎት በአስራት ላይ ነው መሰረቱ። ነጻነትን ሳያያት፤ የነጻነትን አየር ሳይተነፍስ ሁለት አስርተ አመታት እንደዋዛ አለፉ። ለኢሳያስ፣ ሀገርን መምራት አመጽን እንደመምራት ቀላል አልሆነላቸውም። ሰላምን ማሸነፍ፣ ጦርነትን እንደማሸነፍ አልሆነላቸም።…

ኢሳያስ አፈወርቂ ዳግም ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ጋር ተቀምጠው አየን።  የቀረበላቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ሰማን። መልሶቹንም አደመጥን። አደመጥን ማለቱን የመረጥኩት ያለ ምክንያት አይደለም። በአሁን ዘመን ብዙዎች ይሰማሉ እንጂ አያዳምጡም። ለወቀሳውም፣ ለትችቱም ሆነ ለክርክሩ አመቺ ሚሆነው ከመስማት ይልቅ ማዳመጥ ሲቻል ነው። የማይደመጥ ነገር በአብዛኛው የተዛባ ትርጉም ተሰጥቶት ነው የሚቀርበው።

ታዲያ አዲሱን ቃለ-ምልልስ እንዳደረጉ በማስታውቂያ ከተነገረ በኋላ ለመስማት ትንሽ  አስጠበቁን። በመጀመርያ የትግርኛው ምላሽ ተተርጉሞ እስኪቀርብ ተጠበቀ።  ከግዜ በኋላ ደግሞ የእንግሊዝኛውን ጠብቁ ተባልን። አዲስ ነገር እንዳለ ለመስማት  እንደ ሰስፔንስ ፊልም ልብ እያንጠለጠሉ አከረሙን። ያም ሆኖ “ከጸሃይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም” ብለን አልደመደምንም። ቢያንስ አዲስ ቀልድ ይዘውልናል….  ከጸደቁ አይቀር ግን በአማርኛ ተናግረው ቢጸድቁብን መልካም ነበር። ስራውም ይቀል ነበር። ሁላችንም የምንግባባበት አማርኛ ጠፍቷቸው ነው እንዳንል፤ ደሴ ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። ከዚያም በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩንቨርስቲ የነፃ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ይማሩ ነበር።  የፈረንጅኛው ቋንቋ ሊቀልላቸው ይችላል። የሚቀርባቸው ግን አማርኛ ነው።  ሃሜተኞች እንደሚሉት ኢሳያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያውያን የቤት ስራ መስጠት ስለሚወዱ ነው በአማርኛ ለመናገር ያልፈለጉት። ከዚህ በፊት የመቶ አመት፤ አሁን ደግሞ የመቶ ሰዓት የቤት ስራ።…

በአንድ ግዛት ውስጥ ሆነን ለሺዎች ዓመታት የኖርን፤ በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በሃይማኖትና በሥነ ልቦናም አንድ የነበርን ህዝብ እንደሆንን ይሰማኝ ነበር።  እንገንጠል አሉ። ገነጠሉዋት። ኤርትራ በጂኦግራፊም ሆነ በስትራቴጂ አቀማመጥዋ  የኢትዮጵያ ራስ ነበረች ብለው የሚያምኑ ወገኖች በወቅቱ ሄዱብን ነበር ያሉት።  ይህች ክፍለ-ሃገር ራስ ሳትሆን ራስ-ምታት ነበረች የሚሉት ወገኖች ደግሞ ሄዱልን ብለው ነበር።

ዛሬ ራስ ምታቱ ሲጸናባቸው እነሆ እየመጡ ነው። ዳግም ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ጋር ተቀምጠው አየን። ስለኢትዮጵያ ብቻ ይናገራሉ። ስለ ህዝቡ ይቆረቆራሉ። የኢትዮጵያ ችግር እንቅልፍ እንደነሳቸው ያወራሉ። ከዚህ ቀደምም ከኤልያስ እና ስለሺ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ። “… ያለፈውን እንርሳ። የታሪክ ባሮች አንሁን። ኑና እንወያይ።” ማለታቸውን እናስታውሳለን። መወያየት መልካም ነገር ነው። ለውይይት ግን ወቅትም ይወስነዋል። ያኔ በ99.9 በመቶ ውጤት ከተጠናቀቀው የሪፈረንደም ጫወታ በፊት “ኑና እንወያይ።” ቢሉን አሁን የገቡበት ችግር ውስጥ ላይገቡ ይችሉ ነበር።

በአንድ በኩል ከኢትዮጵያ የመለየቱ ቁጭት እንዳለ እናያለን። ደፍረው አልተናገሯትም እንጂ ስህተት እንደሰሩ ከሚሰጧቸው  ቃለ-ምልልሶች መረዳት አያዳግትም። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመቆርቆሩ ጉዳይ ግን የአዞ እንባ ይመስላል።  እዚያው እጉያቸው ላሉት ኢትዮጵያውያን ያልራሩ፣ መረብን ተሻግሮ ማሰቡ ግብዝነት ነው የሚሆነው።

በመጀመርያ አይናቸውን ጠረግ ጠረግ አድርገው የራሳቸውን ቤት ችግር ማየት ሲችሉ፣  የሌላውን ችግር አጥርተው ለመመልከት ይሳናቸዋል።

በቃለ-መጠይቁ ላይ ገጽታቸው እንደመሪ አይደለም። ሰውነታቸው ተጎሳቁሏል፣ ፈታቸውም ጠውልጓል። ከላይ ያጠለቁት ልብሳቸው የተጨማደደ ነበር። ከነበሩበት ደከም ያለ ጣራ ስር ሆነው፤ ግና ዘና ብለው በለሰለሰ አንደበት ይናገራሉ። የኢሳያስን ገጽታ የሚመለከቱ  ሰዎች በሌላ ሊተረጉሙት ይችላሉ። ራስ ወዳድ ያልሆኑ፤ ለግል ኢጎዋቸው የማይጨነቁ… ይባሉ ይሆናል። እንዲህ አይነቱ  ሁኔታቸውን ዋቢ በማድረግ ኢሳያስን እንደሞዴል የወሰዱም አሉ። ይህ ሰጥቶ ለመቀበል የሚደረግ ጨዋታና “የፖለቲካ ስህተት ላለመፈጸም” ካልሆነ በስተቀር መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው ሌላ ነው።  በኢሳያስ አፈወርቂ ውስጥ የኤርትራን ህዝብ እናያለን። ተለይቶ ያለ፣ ከሌላው አለም የራቀ፣  የተቆሳቆለና ተስፋው የጨለመበት ሰው። እሳቸው የሚመሩት ህዝብ ነጸብራቅ ናቸው።

ኤርትራ አሁን ለደረሰችበት ደረጃና ለገባችበት ቀውስ ማንም ውጫዊ አካል ሊወቀስ አይችልም። ራሱ ስርዓቱ ያመጣው መከራ ነው። ከ99.9 በመቶው ተረት-ተረት ሪፈረንደም በኋላ ነጻ አውጪው ሻዕቢያ በአለም ላይ ታይቶ ያማይታወቅ አዲስ ስርዓት አሰተዋወቀ። ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚው አንድ ነው። ህጉም አንድ ሰው ነው። የብዙሃን ፓርቲ ፓርላማ በህግ የተከለከለበት ሃገር።  ፕሬስ የሌለው መንግስት፣ ፍትህ እና ፍትሃዊ ስርዓት የሌለው ስር ዓት።… ይህ አዲስ አይነት ስርዓት የህዝቡን ህይወት የለወጠ ቢሆን ኖሮ፤  እንደተባለውም ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር ያደረገ ቢሆን ኖሮ፣ እንደ ሞዴል ሊወሰድ ይችል ነበር።  እውነቱ ሌላ ነው። ህዝበ ኤርትራ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የቢቢሲን ያለፈው ሳምንት ዘገባ መመልከቱ ብቻ ይበቃል። የዊኪሊኩ ጁልያን አሳንጅ የለቀቀው አንድ ኬብል ላይ ህጻናት እንኳን በኤርትራ መንግስት ምን ያህል እየተሰቃዩ እንደሆነ ዘርዝሮታል።

እኝህ አንባገነን ሰው ዘንድ ሄዶ ጥያቄ የሚጠይቅና የሚጋፈጥ ጋዜጠኛ የሚደነቅ ነው። ህግ፣ፍትህ፣ ዲፕሎማሲ ምናምን የሚባሉ ነገሮች የማይገባው ሰው ዘንድ ሄዶ ለመነጋገር መወሰን ቀላል አይሆንም። ይህን ስል ያለ ምክንያት አይደለም። ትውልደ ኤርትራዊው የስዊድን ዜጋ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት ኢስኃቅ ድንገት ተይዞ ወዳልታወቀ ስፍራ ከተወረወረ 15 ዓመት ሞላው። ጋዜጠኛ ዳዊት የት እንዳለ እስካሁን አይታወቅም። በኤርትራ ዛሬ 20 ሺ የፖለቲካ እስረኞች በየእስር ቤቱ እንደታጎሩ የአምነስቲ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።  በኢሳያስ የግል እስር ቤት ውስጥ ከነበሩት 35 የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል 15ቱ በስቃይ ህይወታቸው አልፏል። በ“አደርሰር”፣ በ“አጂፕ”፣ በ“ኢራኢሮ” እና በ”ጋልዓሎ” እስር ቤቶችና በኮንቴይነሮች ታጉረው እየሞቱ ያሉት ቁጥር ጥቂት አይደለም። የምእራቡ አለም የዲሞክራሲ እሴቶች ከኤርትራ መዝገበ-ቃላት ተፍቀው እንዲወጡ ተደርጓል። በዚህ የፖለቲካ አየር እኝህ ሰው ፊት ቀርቦ የሚጎረብጡ ጥያቄዎችን ማንሳት በራስ መፍረድ ነው።…

ባየር ላይ የሚነገሩ በርካታ ጉዳዮች በቃለ-ምልልሱ ተነስተዋል። የመቶ አመት የቤት ስራው ጉዳይ ተነስቷል። ህገመንግስቱን ከሌንጮ እና ከመለስ ጋር የማርቀቁ ጉዳይ ተነስቷል። ከህብረብሄራዊ ድርጅቶች ይልቅ የዘር ድርጅቶችን ብቻ የመደገፋቸው ጉዳይም ተነስቷል።

ምላሻቸው ግን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነብን። አጠር ብለው ሲቀርቡ ይህን ይመስላሉ።

ጥያቄ፣ “ትውልድዎ እና እድገትዎን ይንገሩን?”

መልስ፣ “የትግሉ ውጤት ነኝ።”

ጥያቄ፣ “ስለጤናዎ ሁኔታ ይንገሩን ”

መልስ፣ “እድለኛ ነኝ… ጠላት እንደሚያወራብኝ አይደለሁም።”

ጥያቄ፣ “በዘር  የተደራጁ ሃይሎችን ነጥለው ለምን ይደግፋሉ?”

መልስ፣ “ሻእቢያ ድርጅት አቋቁሞ አያውቅም።”…..

እያለ ምላሻቸው ከጥያቄው ጋር አራምባና ቆቦ ሆነብን። የማይመቹ ጥያቄዎችን እንደቀልድ ያልፏቸውና ሌላ ታሪክ ሊነግሩን ይሞክራሉ። በመጨረሻ ግን ላሽ እያሉ ያለፏቸው ጥያቄዎች ላይ ጠቅለል አድርገው ምላሽ የሰጡ ይመስላል።

“..ያለፈውን እንተወው እና ወደፊት ምን ማድረግ ይገባናል የሚለው ላይ ማተኮር ነው ያለብን።” ሲሉ ምክር ሰጥተዋል። ይህች መልዕክት የቃለ-ምልልሱ ቁልፍ ትመስላለች። አስቀድመው “ባለፈው በሆነው በአንዳቸውም ነገር አንጸጸትም።” ብለውማል።

ከዚህ ቀደም ከኤልያስ እና ስለሺ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ያሉትንም እናስታውስ። “የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚለው አንቀጽ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ መጨመር ስህተት ነው።” ብለዋል። ራሳቸው ከቀድሞ ወዳጆቻቸው ጋር ሆነው ያረቀቁትን ሰነድ ነው ስተት መሆኑን የነገሩን።  ይህ ነገር ስህተት ከሆነ ታዲያ የሰራነው ስህተት የለም ብለው ለምን ይዋሻሉ? እንደሚባለው የአልዛይመር ችግር ይኖርባቸው ይሆን?

እርግጥ ነው። ስለ ኢሳያስም ሆነ ስለ ኤርትራ ጉዳይ እኛ አያገባንም።  አምባገነንነታቸው የኛ ጉዳይ ላይሆን ይችላል። የዚያች ሃገር ጉዳይ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” ብሎ 99.9 በመቶ ድምጽ የሰጠው ህዝብ ጉዳይ ነው። ግና ባሰኛቸው ጊዜ እየተነሱ ቁስላችንን ሲነካኩብን ዝም የማለት ሞራል አይኖረንም። ከአሰብ በግፍ እና በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈናቅለው ሲያበቁ መስቀል አደባባይ ለወራት የፈሰሱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ከቶውንም ከአእምሯችን አይጠፋም።  ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ በሰራነው አንጸጸትም፣ እንዲያውም ካሳ ይገባኛል ሲሉ በድፍረት ተናገሩ። ምን እንላለን? በወገኖቻችን ላይ እየሰሩ ላሉት ግፍ ፈጣሪ ይከፍላቸዋል። ካሳቸውንም ከታሪክ መዝገብ ያገኙታል።

በፖለቲካ ቋሚ ጠላት ወይንም ቋሚ ወዳጅ የለም። የጋራ ጥቅም ግን አለ። ሰጥቶ መቀበል የሚሉት ነገር። ኢሳያስ አፈወርቂ ግን ለጋራ ጥቅም ሳይሆን ለጽድቅ እንደሚሰሩ አይነት ነው እየነገሩን ያሉት።  በኢትዮጵያ ችግሮች አሉ። አማራጭ የፖለቲካ በሮች በሙሉ ተዘግተዋል። አገዛዙ ፍጹም አንባገነን ሆኗል። ኤርትራን መጠጋት እንደ መፍትሄ የወሰዱ ወገኖች ሌላ የትግል አማራጭ ስላጡ ሊሆን ይችላል። የቸገረው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው። ያለፉት ተመክሮዎች ግን ሻእቢያን በጥርጣሬ እንድናይ ያደርገናል።  ከአስር አመት በፊት አስመራ የመሸጉ ሃይሎች አሁንም አስመራ ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ እዚያው ሲያረጁ ሌሎቹ  ደግሞ አእምሯቸውን ስተው ሲለቅቁ  እያየን ነው። የእነ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ  ደብዛ መጥፋት፣ 18 የአርበኞች ግንባር አባላት በድንገት መሰወር፣ አስመራን እንዳይለቅቁ እገዳ የተጣለባቸው የተቃዋሚ ሃይል አባላት… ወዘተ እጣ ፈንታ በኢሳያስ እጅ ላይ ነው ያለው።   ስለ ኢትዮጵያ መቆርቆር ከዚህ ይጀምራል። እነዚህ ወገኖቻችንን ነጻ ካደረጓቸው በኋላ ኢትዮጵያውያንን ለውይይት ቢጠሩ አንድ ነገር ነው። በትንሹ ያልታመነ፣ በትልቁ አይታመንምና።

ቀድሞ “ከኤርትራ ውጭ ነጻነት ላሳር!” ብለው የነበሩ ሃይሎች አሁን ላይ ሆነው “ተሳስተናል!” እያሉን ነው። ለዚያውም በምሬትና በጥላቻ። ታዲያ ችግሩ የት ነው ያለው? ከተቃዋሚዎቹ  ወይንስ ከሻዕቢያ?  መልስ የሚሻው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

 

Filed in: Amharic