>

በአስራ አንደኛው ሰዓት - የህዝባዊነት ክትባት [አዜብ ጌታቸው]

የአርቲስት ሜሮን ጌትነት “አትሂድ” የተሰኘው ግጥም ሌላውንም አርቲስት እያነቃቃ ነው። ግጥሙ መቼም የአመቱ ምርጥ ግጥም ነው ብል አካበድሽ! አልያም የጾታ አድልዎ ነው እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ። ብባልም ግድ የለኝም። ለለውጥ ያህል “የሴት ትምክህተኝነት” ይጀመር መሰለኝ።

የሆነው ሆኖ የአርቲስት ሜሮን ጌትነትን ግጥም ደግሜ ደጋግሜ ሰማሁት ። የህዝብን እውነተኛ ስሜት የተሸከመ ነው። በሃገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙት “የጥበብ” ባለሟል ነን ባዮች በስራቸው ውስጥ በስህተት እንኳ እውነት እንዳይቀላቀል አበጥረው፤ አንጠርጥረው፤ እያንጓለሉ በሚጥሉበት መድረክ እውነትን እንደወረደ መስማት ያስደንቃል። ብርቅም ያደርገዋል። የሜሮን ግጥም ተወዳጅነት የሚመነጨው ከዚህ ላይ ይመስለኛል።

አነሳሴ የሜሮንን ግጥም ለመገምገም አይደለም። በምን አቅሜ!። ደግሞም እኮ የሜሮንን ግጥም ሕዝብ ገምግሞታል።በልማት ሰበብ ቤቱ የፈረሰበት ድሃ ህዝብ ሁሉ “የልብ አውቃ” ብሏታል። የአርቲስትና የጥበብ ትልቁ መገለጫው ደግሞ ይህ ነው፡፤ “የልብ አውቃ” መሆን። የህዝብን ልብ ማወቅ።

ሜሮን ጌትነት ብዙ ድራማና ፊልሞችን የሰራች፤ በወጣትነት እድሜዋ በህዝብ ዘንድ ግዙፍ ሊባል የሚችል እውቅና ያካበተች አርቲስት ነች፡፡ ይህ የሚነግረን ደሞ ጥሩ ኑሮ ልትኖር እንደምትችል ነው። ጥሩ ቤት፤ ጥሩ መኪና ….ብቻ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሁሉ ማግኘት የሚከብዳት አይደለችም።

የጥበብ ሰው ነችና በግጥሟ ያገኛናት ግን ግድግዳው የተሸነቆረበት የአንድ ድሃ ቤተሰብ አባል ሆና ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ያችን ሽንቁር ግድግዳ ለመድፈን የተቦካቺው ጭቃ ተዝቃ ተጣለች! ። አስቡት የዚህን ምስኪን ቤተሰብ ስቃይ። የሜሮን የምናብ ቤተሰብ ።

አርቲስት የህዝብ፤ ህዝብም የአርቲስት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ምቾትና ድሎት ያልተለየው ኑሮ እየኖረ እንኳ በምናብ ጉዞው ልትወድቅ አንድ ሃሙስ በቀራት ጎጆ የመሸበት እንግዳ ሆኖ ያድራል። የሚላስ የሚቀመስ ካጣ ቤተሰብ ጋር በባዶ ማዕድ አንድ ላይ ይሰየማል ። ርሃብ ስንት ቀን እንደሚሰጥ ጠይቆ ሳይሆን ተርቦ መልስ ለማግኘት ይጥራል። ባጠቃላይ የህዝብን ውሎ ውሎ፤ የህዝብን አዳር አድሮ፤ ስሜቱንም አደባባይ አውጥቶ ይተነፍስለታል። ሜሮንም ያደረገቺው ይህንኑ ነው። አካበድኩ እንዴ? አይመስለኝም።

የሜሮንን በዚሁ ላብቃና ወደ ሌላዋ አርቲስት ላምራ። ውደ አርቲስት አስቴር በዳኔ። ዛሬ ሁለቱም ጀግኖቼ ሴቶች ናቸው። ግዜው የሴቶች ሆነ መሰለኝ?።

አርቲስት አስቴር በዳኔን በመጀመሪያ ያየኋት “ቀዝቃዛ ወላፈን” በተሰኝ ድራማ ነው። ከዚያ በኋላ አንድ ሁለት ድራማ ላይ ሳላያት የቀረሁ አይመስለኝም። እንደ ሜሮን ጌትነት በመሪ ተዋናይነት የሰራችባቸው ፊልሞች/ድራማዎች ብዙ አይመስሉኝም። ሳላያቸው ቀርቼ ከሆነ አላውቅም። እንደገባኝና በኢሳት ላይ ከተወልደ በየነ ጋር ካደረገቺው ቆይታ እንደተረዳሁት ፤ ከተዋናይነት በተጨማሪ የፕሮዲውሰርና ዳይሬክተርነትን ሙያ አዳብላ እንደያዘች ነው። ድንቅ ችሎታ ነው። ያም ሆነ ይህ አስቴር በዳኔ የጥበብ አምባ ሰው ነች። የጥበብ አምባ ሰዎች ደግሞ ትልቁ መለያቸው እውነትና የህሊና ነጻነት ነው ሲባል እሰማለሁ። የሁለቱ ቁርኝት “ያለ ፍርሃት እውነትን መግለጽ መቻል” ማለት ይመስለኛል። አስቴር በዳኔም ሰሞኑን ያረጋገጠቺው እውነትኛ የጥበብ አምባ ሰው መሆኗን ነው። ሃሰተኛ የጥበብ አምባ ሰው አለ ወይ? ብላችሁለምትጠይቁኝ፦ መልሴ የለም ነው። ሲጀመር እውነተኛ ካልሆኑ የጥበብም ሰው አይደሉምና ነው። (ተለጣፊ ልንላቸው እንችላለን ወይ? የሚል ጥያቄ የሰማሁ መሰለኝ ፤ በሏቸው ብቻ እኔ ልቀጥል ተውኝ)።

አስቴር በዳኔ ደደቢት በርሃ ላይ ከባለስልጣናቱና ከአርቲስት አምባ ጎረቤቶቿ ጋር ተሰይማለች። በደደቢት ባለስልጣናቱ ግብር ጥለው ምድረ ….እያበሉ ገድላቸውን በጀምስ ቦንዳዊ ስልት ይተርካሉ። እየበሉ! እየጠጡ! ዝም…” እንዳይባል የፈራው “የ”ሰራዊት ሰራዊት እጁ ቲማቲም እስኪመስል ያጨበጭባል። አስቴር በዳኔም ከጎረቤቶቿ ላለመለየት ይህንኑ አድርጋ ይሆናል። በኋላ ግን ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም ብላ ነው መሰለኝ ከአጨብጫቢው የሠራዊት “ሠራዊት” ለየት ያለ ነገር አደረገች። ለግብር ጣዮቹ ባለስልጣናት ህሊናዋ ውስጥ ሲጉላላ የነበረ ጥያቄ አቀረበች ።

ጉድ ፈላ! የአጨብጫዊ ሰራዊት “ሙድ” ነው የሚሉት ሙድ ተበጠበጠ። ብርንዶና ብላክ ሌብሉን አረከሰችባቸው። እሷ ግን ህሊናዋን አጸዳች።ተቃዋሚ የሚለው ቃል! ጠላት የሚል ስሜት ይፈጥራልና ለምን ተፎካካሪ አይባልም። 23 አመት ስልጣን ላይ ቆይታችኋል አሁንስ በምርጫ ትወርዳላችሁ ወይስ….? አይነት ይዘት ያለው ጥያቄ ጠየቀች።(የጻፍኩት ቃል በቃል ሳይሆን ፍሬ ሃሳቡን ነው) ።

የሚገርመው ነገር አስቴር የጠየቀቺውን ጥያቄ ለመመለስ የሞከረው የሃገሪቷ መከላከያ ሰራዊት ቁንጮ የሆነው ኤታ ማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ ነው። (የአስራ አንደኛ ክፍሉ ብቸኛ አፍሪካው ጄነራል)። ይህ ሰው የአስቴርን ጥያቄ ለመመለስ ህገ መንግስቱ እንደማይፈቅድለት እንኳ አልተረዳም። የህገ መንግስቱን አንቀጽ ፹፯ የሚያውቀውም አይመስልም።በተለይ ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀጽ ፹፯ ተራ ቁጥር ፭ ላይ የተቀመጠው ሳሞራ የአስቴርን ጥያቄ መመለስ እንደማይችል የሚያስረግጥ ነው።

ስለ ብሄራዊው መከላከያ ሰራዊት ድንጋጌዎችን የያዘው አንቀጽ 87 ተራ ቁጥር 5፦ የመከላከያ ሰራዊቱ ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወገናዊነት በሌለው መልክ ብሄራዊ ግዴታና ኃላፊነቱን ይወጣል። ይላል።
አጅሬ ግን ምን ገዶት! እውር ድንብሩን ለመመለስ ሞክረ። በተለመደው “ኢህአድጋዊ ተቃዋሚን የማጠልሸት” ዘይቤ ተቃዋሚዎች የሃገርን ጥቅም አሳልፈው ይሰጣሉ። ሰራዊት እንዲበተን፤ ሃገር እንድትጠፋ ይሰራሉ። አለና ህገ መንግስታዊ ሳይሆን ህገ – ህውአታዊ መልስ ሰጠ። በኋላ ላይ ሌሎቹ ባለስልጣናት እየዘባረቀ መሆኑን በጥቅሻ ነገሩት መሰል፤ እኔ ምድብተኛ ወታደር ስለሆንኩ ይህንን ጥያቄ ሌሎቹ ይመልሱ ብሎ ማይክ ሰጠ። ያም ሆነ ይህ አስቴር በዳኔ ህሊናዋ ያዘዛት ፈጸመች። በዛው ቅጽበት ደግሞ የሆዳቸውን ከተንበሪ ወለል አድርገው ከፍተው ምግብና መጠጡን በተሳቢ እያስጫኑ የሚያስገቡት የአጨብጫቢው ሠራዊት አባላት “በሰረገላ ቁልፍ የተከረቸመ” ህሊና ተንኳኳ። … አይከፍቱት ነገር ቁልፉን ከየት ያምጡ…? ከተሸጠ ቆየ። የህሊናቸውን ኳኳታ ለማምለጥ ምን አማራጭ ነበራቸው….? ምንም! ለዚህ የዳረገቻቸውን አስቴር

በዳኔን መርገምና መሸሽ ብቻ! ! አስቴርን ሸሹ…..! አስቴር እድፋቸውን የሚያሳይ መስተዋት ሆነችባቸው። ለምን አይሸሿት። አሁንም የአስቴርን በዚህ ላብቃና ወደ ሌላው አርቲስት ልለፍ።

አርቲስት ከምለው ገጣሚ ብለው ይሻላል። የማወራላችሁ ስለ ገጣሚ ታገል ሰይፉ ነው።

ታገል ሰይፉ ጥሩ ገጣሚ ነው። በተለይ በምስል እያቀናበረ የሚያቀርባቸው ስራዎቹ አስተማሪነታቸው የሳሳ ቢሆንም አዝናኝ ናቸው። ሌሎች በርካታ ስራዎች እንደሰራም አውቃለሁ። አሁን ላተኩር የፈለኩት ግን ሰሞኑን ለጆሮ በበቃው ቃለ ምልልሱ ላይ ነው።

ከኢትዮፕካ ሊንክ ጋር ባደረገው ረዥም ቆይታ ብዙ ነገሮችን አንስቶ ብዙ ነገሮችን ጥሏል፡፡ የኔን ትኩረት የሳቡት ግን ሁለት ነገሮች ናቸው። 1ኛው ደደቢት እንድሄድ ተጋብዤ ስለማላምንበት አልሄድም ብዬ ቀረሁ! የሚለውና 2ኛው መለስ ዜናዊ ለኪነ ጥበብ እድገት ምን አስተዋጾ አድርገዋል? ተብዬ ተጠይቄ፤ ምንም ! የሚል መልስ ሰጥቼ ነበር። ጠያቂዎቼ ግን ቆርጠው አላወጡትም። በማለት የተናገረው ነው። የመለሰው እንዳልል ጥያቄ አልቀረበለትም።

ደደቢት አልሄድም ብሎ ስለመቅረቱ የተናገረው ወቅታዊ ጉዳይ ስለሆነ ነው ብዬ መቀበል አልከበደኝም። ስለ መለስ ዜናዊ ለኪነ-ጥበብ እድገት ምንም አስተዋጾ ያለማድረግ በድፍረት ተናግሮ በሳንሱር መቀስ ስለ መቆረጡ ዛሬ ላይ መናገሩ ግን ምንም መነሻ ምክንያት ላገኝለት አልቻልኩም። ለኔ እንደገባኝ ታገል ሰይፉ በዚህ ቃለ መጠይቁ ለአድማጭ ሊያሲዝ የፈለገው ፡ የማላምንበትን ነገር አላደርግም ለማለት የማልፈራ፤ ባለስልጣናቱንም ቢሆን በድፍረት የምተች ፤ ለህሊናዬ እንጂ ለማንም ለምንም የማላጎበድድ …. ነኝ የሚለውን ጭብጥ ይመለኛል።

ደደቢት እንዲሄድ ሲጋበዝ ፤ ስለማላምንበት አልሄድም! ብሎ መቅረቱ የሚደነቅ ነው። ህሊና የማይቀበለውን ነገር በይሉኝታም ሆነ በፍርሃት ያለመፈጸም ድንቅ ስብዕና ነው። ለኔ ደግሞ ከሱ ድፍረት በስተጀርባ የታየኝ ግብዣቸውን ያጣጣለባቸው የደደቢት አንበሶች (ያልተለመደ)ትዕግስት ነው። ያም ሆነ ይህ ታገል ሰይፉንም ለድፍረቱ የደደቢት አንበሶችንም ለትዕግስታቸው ብራቮ ብናላቸው ኪሳራ የለውም።
በብራቮ ላልፈው ያልቻልኩት መለስ ዜናዊ ለኪነ-ጥበብ ምንም አስተዋጾ አላደረጉም ብዬ ደፍሬ ተናግሬ ነበር። ቆርጠው አወጡት የሚለው ወቅቱ ያለፈበትን ነገር ነው።

ይህን አባባሉን መቀበል ያቃተኝ ያለምክንያት አይደለም። አዎ! ታገል ሰይፉ መለስ ዜናዊ በሞቱ ግዜ ውዳሴ- ግጥሙን በምስል አቀናብሮ የእዝን መስጠቱን ሳስታውስና ለኪነ-ጥበብ ምንም አስተዋጾ አላደረጉም ብዬ ተናገርኩ ማለቱን ሳነጻጽር ፤ አልጣጣም ብሎኝ ነው። ታገል ለጠ/ሚሩ እዝን ካቀረበው ግጥም ጥቂቶቹን ስንኞች እንመልከት

እስካሁን መድከሜ፤
ላንቺም ላከላቴ
ድንቁርናሽ ሞቴ!
እድገትሽ ህይወቴ
ብልጽግናሽ ህልሜ
ዋ! ጀግናው ወንድሜ
ሳተናው .. በርሜጎ
ህመሙን ዋጥ አርጎ .... ቀጣዩን እንሆ ስሙት

በማለት ለኢትዮጵያ እድገት ሲሉ የራሳቸውን ህይወት አሳልፈው የሰጡ ሊቅ፤ የሴት፤ የህጻን ጠበቃ….ሲል መወድስ ያቀረበላቸውን ጠ/ሚር ለኪነ ጥበብ አስተዋጾ አላደረጉም ብሎ መውቀሱ በራሱ ተገቢ አይመስለኝም። አንድ ጠ/ሚር ስንቱን መሆን ይችላል? ። እሳቸው ጥሎባቸው ከራሳቸው ሌላ ጸሃፊ አይወዱ!

ደግሞስ ውዳሴያቸው በግጥም፤ በዘፈን፤ በዜና፤ በእንጉርጉሮ በጎዳና ተዳዳሪዎች እንኳ ሳይቀር ከየአቅጣጫው በሚዘንብበት ወቅት ለኪነ ጥበብ እድገት አስተዋጾ አለማድረጋቸውን የሚገልጸው አስተያየቱ ያለመቅረቡ ነው የሚያስደንቅ ወይስ ይህን ተናግሮ በዝምታ መታለፉ? ግራ የሚያጋባ ስሞታ…

ጠ/ሚሩ ለኪነ ጥበብ አስተዋጾ አላደረጉም ማለቱን ተጠራጥሬ አልያም ዋሸ ማለቴ አይደለም። ብሎ ሊሆን ይችላል። የኔ ጥያቄ ማለቱን ለምን አሁን ይፋ አደረገ? የሚል ነው።ይህን የምለው(የምጠይቀው) ታገል ሰይፉ ከስርአቱ ባለስልጣናት ጋር ተሞዳሙዶና አጎብድዶ የሚኖር እንጂ እሱ እንደሚለው የህሊናው ታዛዥ አለመሆኑን በበርካታ ስራዎቹ ያሳየ መሆኑን ስለተገነዘብኩ ነው።ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ያሳተመውን “በሚመጣው ሰንበት” የተሰኘ የግጥም መድበል በመታሰቢያነት ያበረከተው ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልጆች ሲሆን በመጽሃፉ ላይ እንዲህ በሚል አስቀምጦታል፡፡

“አባታቸው ለሚወዳቸው ልጆቹ ፍቅር የሚሰጥበት ጊዜ ያጣ፡ ሙሉ እድሜውን ለህዝብ/ለሃገር/ የሰጠ ነበር መታሰቢያነቱም ለነሱ ለሰምሃል፡ ለማርዳና ለሰናይ ይሁን”ታዲያ ለስነ ጽሁፍና ኪነ ጥበብ አስተዋጾ ላላደረጉ ጠ/ሚር ቤተሰብ የጥበብ ስራን በመታሰቢያነት ማበርከት ምን ማለት ይሆን?

በዚሁ መጽሃፍ ላይ ምስጋና ካቀረበላቸው ሰዎች አንዱ ደግሞ አቶ በረከት ስምዖን ናቸው። አቶ በረከትን እንዲህ ብሏቸዋል።

(“አንተ ከሩቅ ስትታይ ከፍተኛ ባለስልጣን ነህ፡፡ እየቀረቡህ እየቀረቡህ ሲመጡ ግን ከስልጣንህ ወርደህ ወደ ሰውነት ወደ ወዳጅነትና ወደ ወንድምነት መለወጥ ትጀምራለህ…”.)

የኔ መነጽር ደግሞ አቶ በረከት የታገል ሰይፉን የሙያ አጋሮች/ጎረቤቶች (ለህሊናቸው ያደሩ ጋዜጠኞችን፤ ጦማሪያንና ……) በሃሰትና በተቀናበረ ክስ ዘብጥያ እየጣሉ፤ ከሃገር እያሰደዱ ሲያሰቃዩ የኖሩ ባለስልጣን መሆናቸው ነው የሚያሳየኝ። እናም ይህን ሳስተውልና ታገል ሰይፉ ከኝህ ሰው ጋር ያለው ቅርበት ከወዳጅነት ልቆ ወደ ወንድምነት መዝለቁን ስመለከት የዚህ ገጣሚ “ለህሊናዬ ታዛዥ ነኝ” ጩህትን ለመስማትም ያቅለሸልሸኛል።

አሁንም በኔ እይታ አቶ በረከት ከቶውንም ለህሊናው የሚገዛ ወዳጅ ሊኖራቸው አይችልም። ያ ቢሆንማ ለህሊናቸው የተገዙት እነ እስክንድር ነጋ፤ ርዮት አለሙ ፤ ተመስገን ደሳለኝ ፤ አብርሃ ደስታ ፤ ሌሎችም እንደ ታገል ሁሉ ወዳጆቻቸውና ወንድሞቻቸው በሆኑ ነበር። እናም በታገል ሰይፉ የሰሞኑ ቃለ መጠይቅ ተደምማችሁ እጃችሁ ቲማቲም እስኪመስል ያጨበጨባችሁ ወገኖች ሆይ! ቆም ብላችሁ አስቡ። ይህን መሰል አጎብዳጅ ሰው ስታወድሱ እስክንድር ነጋ፤ ርዮት አለሙ ፤ ተመስገን ደሳለኝ… የታሰሩለትን አላማ እያጠለሻችሁ እንደሆነ ይታያችሁ።

የታገል ሰይፉ የሰሞኑ ቃለ መጠይቅ ። “በአስራ አንደኛው ሰዓት ህዝባዊነትን ለመከተብ” ከመፈለግ ውጭ ሌላ ምንም መገለጫ ያለው አይመስለኝም። ሰሞኑን ለሜሮንና ለአስቴር በዳኔ የተጨበጨበውን አይነት “የጀግና ሞገስ” ቢያስገኝልኝ ብሎ የወተወተው እንዳሰበው ፍሬ የያዘለት አይመስለኝም።ሊይዝለትም አይችልም…የበረከት ወዳጅ የኢትዮጵያዊውን ወገን ወዳጅነት ከሚያገኝ ዝሆን በመርፌ ቀዳዳ ….ይቀላል።
እኔም ታገል ሰይፉን በራሱ የግጥም ስልት እለዋለሁ፡

ይሄ ታገል ሰይፉ..
የገጣሚ አፋፉ
የበረከት ወዳጅ….
ለህሊናው ሰጋጅ…
ነኝ ብሎ ሲፈክር
ታዘበው እስክንድር..
በቃ በቃ ተውው …
ይቅርብህ ጭብጨባው
እንደ ሜሮን ሞገስ
እንደ አስቴር መወደስ
አልተገኝም ይቅር…
ይልቅ ከወዳጅህ ከበረከት እደር ….
በቃ ተወው ይቅር ..

ከስንኙ ጋር የሚሄደውን ምስል እሱ ይርዳኝ።

እንደ ታገል ሰይፉ ሁሉ “ሞገስን ፍለጋ” በሚል ቃለ መጠይቅ ለህሊናቸው ተገዢ መሆናቸው ለማወጅ ድፍረት ወይም አጋጣሚው ስላላገኙ እንጂ በርካታ የኪነትና የጥበብ ባለሟል ነን ባዮች ብዙ ሊሉን እንደሚችሉ እገምታለሁ። ዓለም የቲያትር መድረክ ናት ነው ያለው? ሼክስፒር፡ እውነት አለው።

መደምደሚያ፦ በኢትዮጵያ የሚገኙ አርቲስቶች አይነት

አሁንም በኔ መነጽር እይታ የኢትዮጵያ አርቲስቶች በሶስት የሚከፈሉ ይመስሉኛል።

የመጀመሪያዎቹ የህሊናቸውን በር ሙሉ ለሙሉ ያልዘጉ ባገኙት አጋጣሚ የህዝብን እውነት በስራቸው አሾልከውም ቢሆን ለማሳየትና የህሊናቸውን ውጥረት ለማስተንፈስ የሚሞክሩ ናቸው፡፡ እነኚህ አርቲስቶች የእንጀራ ነገር ሆኖ እንጂ በስራቸው ደስተኛ አይደሉም። የማይመስል ነገር(የህዝብ እውነት ያልሆነ ስራ) ከመስራት እራሳቸውን ያሸሻሉ። ባጠቃላይ ሃቅ የሚያንቃቸው አይነቶች ናቸው።እነኚህ አርቲስቶች በተለይ ከሶስተኞቹ (አጎብዳጆች) ጋር ፍጹም አይስማሙም። በስራቸውም ብዙ ተጠቃሚ አይደሉም።

ሁለተኞቹ አይነቶች ልኑርበት አይነት ናቸው። ለገበያ ፍጆታ የሚሆን የፍቅር ዲስኩርና የወንጀል ስንክሳር እያመረቱ ከግራውም ከቀኙም ሳይጣሉ መኖር የሚሹ ናቸው። እነኚህ አይነቶቹ ሙያቸው እንደማንኛውም ስራ የእለት ጉርስ ከማሰገኘት ባለፈ የህዝብን እውነት የመግለጽ ልዩ ሃላፊነት ያለበት ሙያ መሆኑን ሊቀበሉ አይሹም። የህሊናቸውን ወቀሳ የሚሞግቱትም በዚህ እምነታቸው ነው። ገንዘብ እሳካገኙ የትኛውንም ስራ አይመርጡም።እነኚህ አይነቶቹ ከአንደኞቹም ከሶስተኞቹም ጋር ሰላም ለመፍጠር ይጥራሉ። ከየትኛውም ጋር እውነተኛ ወዳጅነትም አይኖራቸውም።ሦሦተኞቹ የሰራዊት ፍቅሬ፤ አይነቶች ባለስልጣናቱን ለማስደሰት ጠብ እርግፍ የሚሉ ናችው። ህሊና አልፈጠረባቸው። (ፈጥሮባቸው ከነበረም ቦታው ለልማት ተፈልጎ ተነስቷል) ብቻ ራሳቸውንም ሙያቸውንም በውዴታ ለባለስልጣናቱ ያስገዙ ናቸው።

ወንዝን ወደ ሰማይ አትንነው በርሃ ላይ ዝናብ ለማዝነብ ቀና ደፋ የሚሉ ለህዝብና ለሃገር አሳቢ ባለስልጣናት እንዳሉን ለማሳየት ሆድ-ወለድ ድራማ የሚደርሱ አጎብዳጆች ናቸው።(የሰራዊት ፍቅሬን ሰማያዊ ፈረስ ልብ ይሏል) እነዚህ አርቲስት ነን ባዮች ፤ በተለይ በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሱት ጋር አይስማሙም። ለመንግስት ባላቸው ቀርቤታና አመኔታ ከፍተኛ ጥቅም የሚያጋብሱ ቱጃሮች ናቸው።በዚህ የመከፋፈያ መስፈርት ያልተጠቃለሉ የእውነተኛ አርቲስት መገለጫ የሆኑ እንዳሉም ሳንዘነጋ ነው። (ታማኝና ሻምበልን መጥቀስ በቂ ይመስለኛል)በነገራችን ላይ ይህ የግሌ አመለካከት ነው። ሌላውም የራሱ የመከፋፈያ መስፈርት ይኖረው ይሆናል።

አሳፋሪ አርቲስቶች እንዳሉ ሁሉ የሚያኮሩ አርቲስቶም አሉ። ነገር ግን የልማታዊውን መንግስት መልካም ገጽታ የሚያጠለሽ እኔን መሰል ጸሃፊ እግሌን እገሌን አከብራለሁ ብሎ ቢጽፍ ለአርቲስቶቹ ጥሩ ስለማይሆን እንጂ ስራቸውን እየዘረዘርኩ ባመስግናቸው ደስ ባለኝ ነበር።ለግዜው ግን አልፌዋለሁ።

በሜሮንና በአስቴር ወቅታዊ ስራዎች ላይ እየተንደረደርኩ የጀመርኩትን የዛሬን ጽሁፌን ልቋጭ እንደገና እየተንደረደርኩ ነው።

ከዚያ በፊት ግን አንድ ነገር ማለት እሻለሁ! የለውጥ አየር እየነፈሰ ነው። በሰላማዊም ይሁን በጸባዊ ትግል ብቻ! በምንም ይሁን በምን መንገድ፤ ይሄ መንግስት በመጨረሻው ሰዓት ላይ እንደሚገኝ እላችኋለሁ። ብዙ አመላካች ነገሮች አሉ….። አመላካች ነገሮቹንና ሌሎችም ትዝብቶቼን ይዤ ወደፊት ልመለስ። ለዛሬው ግን በዚህ ላብቃ።
የነገ ሰው ይበለን….
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
አዜብ ጌታቸው!
azebgeta@gmail.com

Filed in: Amharic