>

የ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ማህተመወርቅ ታሰረ

በስደት ያለው ወንድሙ ኣለማየሁ ማህተመወርቅም ይናገራል

Fikadu Mahtemewerkየዕንቁ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው አቶ ፍቃዱ ማህተመወርቅ በትናንት ዕለት ‹‹ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መ/ቤት መክፈል የሚገባቸውን ግብር አልከፈሉም›› በሚል ቂርቆስ ክ/ከተማ በሚገኘው የሀገር ውስጥ ገቢ ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ ከታሰረ በኋላ በትላንትናው ዕለት ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር፡፡ ጉዳዩን የያዘው የሀገር ውስጥ ገቢ መርማሪ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመጠየቁ የተነሳ አቶ ፍቃዱ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ የሰባት ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ፍቃዱ በአሁን ወቅት በቂርቆስ ክ/ከተማ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው የሀገር ውስጥ ገቢ የእስረኞች ማቆያ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል፡፡በሚል ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ በትላንትናው ዕለት መዘገቡ የሚታወቅ ሲሆን፣ 

በኣሁኑ ሰዓት በስደት ላይ የሚገኘው የዕንቁ መጽሔት ስራ ኣስኪያጅ  ኣለማየሁ ማህተመ ወርቅ   ወንድሙ ፍቃዱ ማህተመወርቅ  ለእስር የተዳረገበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ኣስፍሮኣል።

”በረከት ይሄን ልጅ እንድታየው ብዬ ነዉ። ይገርምሀል… ይሄን ፕሬስ ከጀርባ ሆኖ የሚያሽከረክረው ይሄ ነው።” ሼም የለሽ ከማል ነበር እኒህን በማር የተለወሱ ሬት ቃላት ለአለቃው በእጅ መንሻነት የሰነዘራቸው – ስፍራው የሽመልስ ቢሮ ነው።
ወንድሜ ፍቃዱ በወቅቱ ሐምራዊ የተሰኘ መጽሄት ያሳትም ነበር። በተጨማሪ ”ሀበሻ ሪቪው” የተሰኘ ጋዜጣ ለማውጣት ፍቃድ የጠየቀው ብሮድ ካስት ባለሰልጣን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያቀረበለት የ”ሐምራዊን” ፈቃድ መልስና የጋዜጣውን ፈቃድ እንሰጥሀለን የሚል ነበር ።በዚሁ መሰረት የመጽሄቱን ፍቃድ መለሰ። እነሱም ፍቃዱ መሰረዙን አሳወቁ። የጋዜጣ ፈቃድ ጥያቄው ግን ምላሽ አላገኘም።
ከብዙ ውጣ ውረድ በዃላም ወደሼም የለሹ ቢሮ ቢቀርብም ያገኘው ምላሽ በረከት ጥርስ ውስጥ እንዲገባ የማመቻቸት አሳፋሪ ተግባር ነበር።
ቀማኛው እነሱ ዳኛዉ እነሱ በሆኑበት ሀገር እየተኖረ ምን ይደረጋል? ብለን ”እንቁ” መጽሔትን በእኔ አሳታሚነት አውጥተን ስንሰራ ብንቆይም እንቁንም ከሌሎች አራት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣ ጋር በአሸባሪነት ከሰው እኛንም ጨምሮ ከሰላሳ በላይ ጋዜጠኞች ለሰደት ተዳረግን። ከሀገር አልወጣም ያሉትንም ለእስር ዳረገ።
ያሰረውን አስሮ ያሰደደውንም አሰድዶ በዚሕም ያልረካው ቂመኛው የወያኔ ሕወሐት መንግስት ጭር ሲል አይወድምና ….ዛሬ ደግሞ እንደተራ አጭበርባሪ ሰንካላ ምክንያት አቅርቦ በመውሰድ የዛሬ ስድሰት አመት በሰረዘው ፈቃድ ”አንተስ እንደ ወንድምህ እንደ ጓደኞችህ ለምን አልተሰድክም?” በሚል ለእስር ዳርጎታል።
አይዞን ወንድሜ ይሔም ያልፋል! ታሪክ ይቀየራል።

Filed in: Amharic