>
5:13 pm - Monday April 19, 5447

ኢትዮጵያ አለች ወይ? [ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ]

Dr Dagnachew Assefa facebook picአንድ የተማረ ሰው ከአዲስ አበባ ወጥቶ ወደ ሌላ ክልል ሄዶ ስራ ሲሰራ ደሞዙ ተቆርጦበት ወይም ዘግይቶበት ሰለ መብቱ ቢጠይቅ የሚሰጠው ምላሽ ”እንደውም ካለሃገራችሁ መጥታችሁ   ስራ ስላገኛቹህ ልታመሰግኑ ይገባል” ይባላሉ። አሁን ያለንበት ደረጃ አስከፊና አስቸጋሪ ነው።  እንደውም አሁን እየጠየቅን ያለነው፣ አገራችን አለች ወይ ነው? ኢትዮጵያ አለች ወይ? ልክ ከአዲስ አበባ ወጣ ስትል ከየት ነው የመጣኽው? ትባላለህ። ልክ ሌላ አገር የሄድክ እስኪመስልህ። ምንም አይነት ‘ፕሮቴከሽን’ የሌለባት አገር ሁናለች። መጀመሪያ የጠነሰሱት ብሂል አሁን እያበበ ነው። የአገሪቱ ሁኔታ ‘ኢዝ አት ስቴክ’ (is at stake)። አንተ ትቀልዳለህ ሶማሊያ፣ ጋምቤላ ተወው፥ እዚህ አምቦ እኮ የኔ ተማሪዎች ስራ ተቀጥረው ”የእኛ ተማሪዎች እስኪመጡ ብቻ ነው ስራ ሊኖራችሁ የምትችሉት” ነው የተባሉት።

አገር የለንም ነው እኮ የምልህ። ይህ ከሗላ ኪሴ አውጥቼ የምንገርህ እንዳይመስልህ ልጄ። 62  አመቴ ነው። ያለው እውነታ ይህ ነው። አገር የሚባል ነገር አብቅቷል። አዝናለሁ። ግን ያለው ሁኔታ ይህ ነው። ህገ መንግስቱ ዜጋ የሚባል ‘’ቮካቡላሪ’’ የለውም። እኛ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነው የሚለው። አንድ ሰው በግልሰብ በዜግነት ስለ መብት የሚያወራበት ሁኔታ የለም። በጣም – በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው። ወጣ ካልክማ አንተ እንዴት መጣህ? ይልሃል። ቱሪስት ነህ ወይስ ምንድን ነህ? ይልሃል። ከየት ነው የመጣህ ነው እኮ የምትባለው። የሚገርም ጉድ እኮ ነው የፈላብን።

‘አካዳሚክ ፊርደም’ የሚለውን ‘ኮምፒሊትሊ’ አውጣው። ሁሉም ፕሮፌሰር፣ ሁሉም አስተማሪ አንገቱን ደፍቶ ዛሬ ነገ ያዙኝ ብሎ የሚኖርበት አገር ነው ዩኒቨርሲቲ ማለት… ኢትዮጵያ።  የፈልጉትን ይበሉ እነግረሃለው። ይሄ ነው ያለው። ስለ ሰቆጣ የጻፈው የህግ አስተማሪ ደብዳቤ ነው የተጻፈለት እንዲባረር። ያውም እሱ የብአዴን አባል ነው ምናምን ነገር። ‘አካዳሚክ ፍሪደም’ የሚባል ‘’ቮካቡለሪወም’’ የለም። ድሮ ቀረ።

አሁን ሳምንት ምን አለኝ ‘ቸርማኑ’ እና እኛ እንመርጥና እነሱ ‘ሪኮሜንድ’ ያደርጉልናል። ‘ቼርማን’ አንመርጥም። ‘ዲን’ አንመርጥም። ካድሬወች ነው የሚመርጡልን። ምን አለፋህ። አንድ ዩኒቨርሲቲ ‘አድሚሽኑን’ (admission) ያስረከበ ዩኒቨርሲቲ ‘አካደሚክ ፍሪደም’ አለኝ ይላል እንዴ? በትዛዝ እንከሌን ተቀበሉ እነከሌን አተቀበሉ የሚባል ዩኒቨርሲቲ ‘አካዳሚክ ፊሪደሙን’ ተወው አልኩህ። እርሳው እሱን። ይገባሃል የምልህ? ‘አድሚሽኑን’ ያስረከበ ዩኒቨርሲቲ ‘’አካደሚክ ፍሪደም’’ አለ ብሎ ሊያወራ አይችልም።

መከፋፈልን እንደ ጸጋ የወሰደ ስርዓት እኮ ነው። ምን ትጠብቃለህ እስኪ ንገረኝ። “የኢትዮጵያ ህዝቦች እንኳን ደስ ያላቹህ። ብሄር ብሀረሰቦች ሆናቹህ ነው እኮ የሚለው ዘፈኑ ሁሉ።  አገር የለም። ህግ የለም። እየጠፋን ነው። ምን ትላልለህ? ስለመብት ታወራለህ እንዴ? የእኛስ፣ የተማሪወች ማህበር አለ አይደል እንዴ ካድሬወች ነው እኮ ‘ራን’ (Run) የሚያደርጉት። ሲቪል ማህበራት የሚባል ነገር የለም። ወይ ጠፈተዋል ወይ ተካተዋል።

 

Filed in: Amharic