>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9284

ክፍል ሁለት - ምክር እስከ መቃብር (ካልፎ ሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ[በእውቀቱ ሥዩም]

እንደምነሽ ሸገር
የከሰመው ወንዝሽ
የከሰመው ወዝሽ
የሚታየው ነጥፎ
እንደምነው ጣፎ
እንዴት ነው ቀበና
እስቲ ድንጋይ ላጥምድ መረብ ልጣልና፡፡
በነገራችን ላይ በኣዲስ ኣበባ የሚገኙ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች“ ኒውዮርክ”“ ዴምቨር” “ወዘተረፈ ተብለው የሚጠሩትን ያክል ባውሮፓና በኣሜሪካ ያሉ ሬስቶራንቶች ደግሞ ”ዱከም“ ፤ ኣራትኪሎ ፤ ፒያሳ በሚል ተሰይመዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድር ነው ፡፡ ኣዲስ ኣበባ ስትኖር ውጩን ይናፍቅሃል፡፡ ውጭ ስትኖር ደሞ ኣገር ቤት ይናፍቅሃል፡፡ መኖር ማለት የማይበርድ ናፍቆት ማለት ይሆን? መልመድ ይቅደም! ናፍቆት ይውደም!! ያለምንም ደም!!!
ፌንተን መንገድ ዳር ከሚገኙ ያበሻ ሬስቶራንቶች ባንዱ ተኬ ከተባለው የቀድሞው የብሄራዊ ቡድናችን በረኛ ጋር ኣመሸሁ፡፡
ሊጋብዘኝ ዝግጁ እንደሆነ ሲነግረኝ “ኣንድ ሽሮና ኣንድ ያሣ ዱለት ቢመጣልኝ ደስ ይለኛል!“ኣልሁ ራሴን እያከክሁ፡፡
“ይሄ ሁሉ ምግብ ምን ይሰራልሃል? ገና ለገና ኣገርቤት የምግብ እጥረት ስላለ ለወር የሚበቃህን ያህል በልተህ ልትሄድ ነው?“
ምግቡ ሲመጣ ተኬ ከኣሣ ዱለቴ ኣንድ ጉርሻ ጎረሰና ኣላምጦ ግንባሩን ከሰከሰ፡፡
” እንዴት ነው?“ ስል ጠየኩት፡፡
“ምምምም ያባቴን ኣውራጣት፤ ያባቴን ኣውራ ጣት ይላል” ኣለ፡፡
“ጉደኛ ነህ! ያባትህን ኣውራጣት በልተህ ታውቃለህ?”
“ምን መሰለህ!በልጅ እያለሁ ማታማታ የኣባቴን እግር ማጠብ ነበረብኝ፡፡ ትዝ ይለኛል፤ያባቴ እግር በጣም ቀጭን ተመሆኑ በላይ ሲበዛ ጸጉራም ነው፡፡ እግሬን እጠብልኝ ከሚለኝ ይልቅ እግሬን ኣበጥርልኝ ቢለኝ ይሻል ነበር፡፡ ወንድ ልጅ ሲወለድ ከነቃጭሉ ዱብ ኣለ ይባል የለ፡፡ፋዘር ደሞ ከነገምባሌው ነው ዱብ ያለው፡፡እና እግሩን ኣጥቤ ስጨርስ ኣውራጣቱን ያስመኝ ነበር፡፡ያውራ ጣቱ ጣእም እስታሁን ምላሴ ላይ ኣልጠፋም፡፡ኣውራ ጣቱ ይህን ዱለት ይህን ዱለት ይላል፡፡ኣሁን ሳስበው ኣባቴ ምናባቱ ቆርጦት እንደዛ እንደሚያረግ ኣይገባኝም፡፡እግር የሚስም ባርያ የመግዛት ኣቅም ስላልነበረው እኛን ልጆቹን እንዲህ ያስመን ነበር፡ ፡ ኣየህ ልጅ ማለት እግዜር ለወላጅ የፈነገለው ባርያ ማለት ነው፡፡”
በልተን ስንጨርስ ሊመክረኝ ተዘጋጀ፡፡
“ወደ ኢትዮጵያ የሚያስመልስህ ነገር ምንድነው?”
“ያገር ፍቅር!”
“ትያትር ቤቱን ነው ?”
“እረ ስሜቱ!”
ተኬ በመልሴ በጣም ሳቀ፡፡
“ምን ኣሳቀህ?፡፡ ኣገሬ ገብቼ ከልማቱም ከግማቱም ብሳተፍ ኣይሻልም?“ኣልኩት በቁርጠኝነት፡፡
“እንደ ወንድም ልምከርህ፡፡ እዚህ ብትቀር ይሻልሃል፡፡ ደመወዝ ይመስል ውሃ በወር ኣንዴ የሚመጣበት ኣገር ምኑ ይፈቀራል?መብራቱስ የታል? እዚህ ኣሜሪካ በየቤቱ ደጅ ላይ የሚቆመው ክሪስማስ ትሪ ከኣዲስ ኣበባ የተሻለ ያበራል፡፡ ኢትይጵያ ውስጥ ካምፖል ይልቅ ብርሌ ብዙ ስራ ይሰራል፡፡የሰለጠነው ዓለም ጨረቃ ላይ ከተማ ለመገንባት ሲራኮት እኛ በጨረቃ ብርሃን ራት እንበላለን፡፡ በዝያ ላይ የለማኝና የጎዳና ተዳዳሪው ብዛት ኣይዘገንንም?”
“እዚህም እኮ ለማኝ ኣለ” ኣልሁ፡፡
“ያገራችንን መናጢ ለማኝ ካሜሪካ ለማኝ ጋር ስታወዳድረው ሼም ኣይሰማህም? የዚህ ኣገር ለማኝ እንደምታየው ኣለቅጥ ወፍራም ሲሆን የሚለምነውም ለጂም ነው፡ ፡ ባለፈው ቬጋስ ሄጄ ያያየሁት ለማኝ ምን እያለ እንደሚለምን ታውቃለህ?”
“ምን ኣለ?”
‘ወንድሞቼ ለዛሬ ሌሊት ሸሌ የምገዛበት ፍራንክ ስለቸገረኝ ጣልጣል ኣርጉልኝ’
ስስቅለት ጊዜ ቀጠለ፡፡
”በዛ ላይ ኣገሩ ውጥረት ነግሷል፡፡ ኣዲስ ኣበባ ውስጥ የሚታየው መፈክር ይዞ የሚሮጥ ወጣትና ቆመጥ ይዞ የሚያባርር ፖሊስ ብቻ ነው፡፡ኣንተም ገና ኤርፖርት እንደደረስህ ነው መሮጥ የምትጀምረው፡፡ከምርጫ ጋር በተያያዘ ብዙ ጣጣ ይኖራል፡፡ኣደራ ገዥውን ፓርቲም ሆነ ጎምዥውን ፓርቲ እንዳትመርጥ ፡፡ዝምብለህ በኤፍ ኤም ደውለህ ለፍቅረኛህ ዘፈን ምረጥ፡፡ፌር የሆነ ምርጫ ያለው እዛ ይመስለኛል፡፡ I hope የጥላሁንን ገሰሰን ዘፈን ስትመርጥ የጥላሁን ጉግሳን የሚጋብዙ ዲጄዎች እንዳልተቀጠሩ ተስፋ ኣለኝ፡፡“
በፈገግታ ማዳመጥ ቀጠልኩ፡፡
”ያገራችን ብቸኛ ጸጋዋ ኣየሯ ነበረ ፤ ኣሁን እሱም እየተበላሸ ነው ኣሉ፡፡በኛ ጊዜ ጸሃይ ኣመለ ልስልስ ነበረች፡፡ ኣሁን ሙቀቱ ኣይጣል ነው!ጸሃይ በጣም ከማቃጠሏ የተነሳ ያዲሳባ ሴቶች እንጀራ የሚጋግሩት ጃንጥላቸው ላይ ነው ሲባል ሰምቻለሁ ፡፡ እንድያውም ኣንዳንዴ ሳስበው የሰማይ ኮርኔስ የተቀደደው በኢትዮጵያ ኣቅጣጫ ሳይሆን ኣይቀርም፡፡ድሮ ሽማግሌ ኣያትህ እንዲመርቅህ ከፈለግህ የማለዳ ጸሃይ ስር ወስደህ ታሰጣዋለህ፡፡ ዛሬ የማለዳ ጸሃይ ስር ብታሰጣው ይረግምሃል፡፡ምነው ምነው ልጄ ኣልሞት ኣልኩህ? እንዲህ እንደ እንፋሎት ዳቦ በገዛ ላቤ ከምትጥብሰኝ በግልጥ እንደ ደመራ ለምን ባደባባይ ኣታነደኝም?ኣይ ኣይይይ!ርጉም ሁን ፡፡ዘርህ ይማረክ፡፡ቤትህን ቡልዶዘር ያፍርሰው፡፡ርስትህን ህንድ ይረሰው፡፡ሎተሪን ኣንተ ቁረጠው እጣውን ግን ለጠላትህ ይድረሰው ብሎ ይረግምሃል፡፡

Filed in: Amharic